ብሔራዊ የግብርና ባዮቴክኖሎጂ ምርምር ማዕከል በሥነ ሕይወት ዘርፍ ዓለም ለደረሰባቸው የምርምር ሥራዎች አጋዥ የሆኑ የቴክኖሎጂ መሣሪያዎች ባለቤት መሆኑ ቢነገርለትም፣ በኃይል መቆራረጥ ምክንያት የምርምር ሥራዎች መስተጓጎላቸውንና በከፍተኛ ወጪ የተገዙ መሣሪያዎቹ ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑን የማዕከሉ ኃላፊዎች አስታወቁ፡፡
ማዕከሉ በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ሥር ከሚገኙ 17 ብሔራዊ የምርምር ማዕከላት አንዱ በሆነው የሆለታ ግብርና ምርምር ማዕከል ንዑስ ማዕከል በመሆን በ2002 ዓ.ም. ነበር የተቋቋመው፡፡ ነገር ግን ባለፈው ዓመት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አወዛጋቢው የባዮሴፍቲ አዋጅ ተሻሽሎ በመቅረቡ ሳቢያ፣ የብሔራዊ ባዮቴክኖሎጂ ማዕከሉ የልውጥ ሕይወት ምርምርን በአገር ውስጥ እንዲያካሂድ፣ ከውጭ አገር በዘረመል ምህንድስና የተመረቱ ምርቶችንም እንዲመረምርና እንዲተነትን የሕግ ድጋፍ ተሰጥቶት ወደ አገር አቀፍ ማዕከልነት ከፍ እንዲል ተደርጓል፡፡
አዋጁ ከወጣ በኋላ ከኅዳር 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ቀድሞ የጀመራቸውን የምርምር ዘርፎች በማጠናከር፣ የግብርናውን ዘርፍ ምርታማነት ሊያሳድጉ የሚያስችሉ የምርምር ውጤቶችን ማፍለቅ እንዲችል ከፍተኛ ኢንቨስትመንት እየፈሰሰበት ነው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ በተለይ በዕፅዋት ሳይንስ የዝርያ ተለያይነት፣ የማብዛት፣ የማዳቀል፣ የማስፋፋትና የምርምር ሒደቱ እስከ ሃያ ዓመታት ይፈጅ የነበረውን የዝርያ ተለያይነት፣ የዲኤንኤ የመለየትና የመተንተን ሥራ በቀላሉ በአገር ውስጥ ማጥናት የሚያስችሉ ዘመኑ የደረሰበት የቴክኖሎጂ መሣሪያዎችን በመግዛት እያስፋፋ ይገኛል፡፡
በአሁኑ ጊዜም በማዕከሉ ውስጥ አራት ቤተ ሙከራዎች ሲኖሩ፣ ምርምር ለሚከናወንባቸው የጥናት ዓይነቶች አጋዥ የሆኑ ዘመናዊ መሣሪያዎች እንደተሟሉላቸው ይነገራል፡፡ ‹‹በዓለም ላይ አሉ የሚባሉ መሣሪያዎች አስገብተን እየተጠቀምን ነው፡፡ እነዚህም መሣሪያዎች በዲኤንኤን ትንተናም ሆነ ማንኛውንም ሕዋስ የመለየትና የትንተና ብቃታቸው ትክክለኛነት ተወዳዳሪ የሌላቸው ናቸው፤›› ሲሉ፣ በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የባዮቴክኖሎጂ ጥናት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር እንዳለ ገብሬ ገልጸዋል፡፡
መሣሪያዎቹ በውድ ዋጋ ተገዝተው ወደ አገር ውስጥ ቢገቡም፣ የባዮቴክኖሎጂ ጥናት ዘርፍ ለአገሪቱ ትልቅ አቅም እየፈጠረ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪም ለጥናት የተሰጠው ትኩረት የጊዜም ሆነ የሀብት ብክነት መቀነስ እንዳስቻለም ዳይሬክተሩ አክለዋል፡፡ ‹‹ከዚህ በፊት ይህን አቅም ባለመገንባት ከጤፍ፣ ከቡናና ከመሳሰሉት ሀብቶቻችን መጠቀም የሚገባንን ብዙም አልተጠቀምንም ነበር፡፡ አሁን ግን የኢትዮጵያ ብቻ የሆኑ ዝርያዎችን አሻራ ማውጣት የሚያስችሉ መሣሪያዎች ባለቤት መሆናችን ትልቅ ፋይዳ አለው፤›› በማለትም ዶ/ር እንዳለ ይገልጻሉ፡፡
የማዕከሉ የዕፅዋት ባዮቴክኖሎጂ ቡድን መሪ አቶ ቴዎድሮስ ታደሰ በበኩላቸው፣ ‹‹እነዚህ መሣሪያዎች በአንድ ጊዜ 15 ሺሕ የሚደርሱ የዝርያ ዓይነቶችን በአንድ ቅፅበት መለየት ይችላሉ፤›› ብለዋል፡፡
ነገር ግን እነዚህ የዘመኑ ቴክኖሎጂ ያፈራቸውና ከፍተኛ ወጪ ወጥቶባቸው የተገዙ መሣሪያዎች በተደጋጋሚ በሚከሰት የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑን፣ ዶ/ር እንዳለም ሆኑ በማዕከሉ ምርምር የሚያደርጉ ባለሙያዎች ገልጸዋል፡፡
‹‹መሣሪያዎቹ በአብዛኛው ከ250 ሺሕ እስከ 500 ሺሕ ዶላር ወጥቶባቸው ነው የተገዙት፡፡ ሆለታ አካባቢ የኃይል ችግር በመኖሩ ብዙ ጉዳት እያደረሰብን ነው፡፡ በተደጋጋሚ ኃይል በሚቆራረጥበት አጋጣሚ ብልሽት እያጋጠመን ነው፤›› ብለዋል ዳይሬክተሩ፡፡
የኃይል መቆራረጡ በመሣሪያዎች ላይ ከሚያደርሰው ጉዳት በተጨማሪ በማዕከሉ የሚከናወኑት የምርምር ሥራቸው በባህሪያቸው ለብልሽት የሚዳረጉ በመሆናቸው፣ ኃይል ባለመኖሩ ምክንያት ተመራማሪዎች ከአንድ ዓመት በላይ የደከሙባቸው የጥናት ውጤቶች ሙሉ በሙሉ የሚጠፉበት አጋጣሚም እንዳለ ዶ/ር እንዳለ ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም እነዚህን ብልሽት ያጋጠማቸውን መሣሪያዎች ለመጠገን የሚያስችል ክፍል አለመኖሩ ሌላው የማዕከሉ ችግር መሆኑንም ኃላፊዎች ይገልጻሉ፡፡ በአገሪቱ ውስጥ እንዲህ ዓይነት መሣሪያዎችን መጠገን የሚችሉ ኢንጂነሮች እጥረት በመኖሩ፣ ማዕከሉ ያሉትን ለመቅጠርም ሆነ በኮንትራት ለማሠራት ከመንግሥት የክፍያ ሥርዓት አንፃር ውድ በመሆኑ መቸገሩ ተገልጿል፡፡
ለጊዜው የተጎዱ መሣሪያዎች በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽንን ትብብር ማዕከሉ ለማስጠገን ቢሞክርም፣ ከባለሙያ በላይ የሆኑ ችግሮች በማጋጠሙ መሣሪያዎቹ ከተሠሩባቸው አገሮች ባለሙያዎችን በከፍተኛ ወጪ ለማስወጣት እየተገደደ መሆኑን ዶ/ር እንዳለ ጨምረው አስረድተዋል፡፡
ማዕከሉ ለጊዜው በኃይል መቆራረጥ ሳቢያ የሚፈጠረውን ጫና ለመቀነስ በጄኔሬተር ለመጠቀም እየሞከረ ቢሆንም፣ የሚደርሰውን ጉዳት ብዙ ሊቀንስ ስላልቻለ መንግሥት በቋሚነት ችግሩን እንዲፈታለት እየጠየቀ ይገኛል፡፡