ባለፈው ዓመት ለፀደቀው የኢንዱስትሪ ፓርኮች አዋጅ ቁጥር 886/2007 ማስፈጸሚያ የሚሆን ረቂቅ ደንብ በቅርቡ በሚኒስትሮች ምክር ቤት እንደሚፀድቅ ተገለጸ፡፡ ደንቡን በሚመለከት መንግሥታዊ ተቋማትና የግሉ ዘርፍ በረቂቅ ሰነዱ ላይ ውይይት እያካሄዱ ነው፡፡ ረቂቅ ደንቡ የግንቦት ወር ከማለቁ በፊት እንደሚፀድቅ ይጠበቃል፡፡
በሁለት ዙር ከተካሄዱት ውይይቶች አንዱ የሆነውና ማክሰኞ ሚያዝያ 18 ቀን 2008 ዓ.ም. በተካሄደው ውይይት ሚኒስቴሮችና ሌሎች መንግሥታዊ ተቋማት ተነጋግረውበታል፡፡
ረቂቅ ደንቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን አዋጅ ከኢንቨስትመንት አዋጁ ጋር በማዛመድ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ ተፈጻሚ የማድረግ ዓላማ ይዞ መዘጋጀቱን የገለጹት፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሲሳይ ገመቹ ናቸው፡፡ አቶ ሲሳይ በሰጡት ማብራሪያ መንግሥት በአገሪቱ ትልልቅ የኢንዱስትሪ ፓርኮች መሠረተ ልማት አሟልቶ ከመገንባት በተጨማሪ፣ የአገር ውስጥ ባለሀብቶችም በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማትና በኢንቨስትመንት እንዲሳተፉ ለማድረግ እንደሚፈልግ አስታውቀዋል፡፡
በረቂቅ ደንቡ ከተካተቱት 12 ክፍሎች ውስጥ በተለይ ክፍል ስድስት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው መሆኑን ያብራሩት በረቂቁ ላይ አስተያየት ከሰጡ ምሁራን አንዱ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰሩ ዶ/ር ሙራዱ አብዶ ናቸው፡፡ በክፍል ስድስት ረቂቅ ደንቡ ያሠፈራቸው አንቀጾች ስለማኅበራዊና አካባቢያዊ ጉዳዮች የሚደነግጉ ናቸው፡፡ በረቂቅ ደንቡ መሠረት ፈቃድ የተሰጣቸው አልሚዎች ሥራ ከመጀመራቸው በፊት የማኅበራዊና የአካባቢያዊ ተፅዕኖ ግምገማ ሪፖርት፣ የማኅበራዊና አካባቢያዊ ተፅዕኖ አስተዳደር ፕሮግራምና መሰል ይዘቶች ይጠቀሳሉ፡፡
ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ለኢንዱስትሪ ፓርኮች ካለው ተጠሪነት በሚመነጭ ሥልጣን፣ በኮሚሽኑ በሚተዳደሩ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ፣ የውኃ ጥራት፣ የቆሻሻ ውኃ ማጣራት፣ የውኃ አቅርቦትና የፍሳሽ አወጋገድ ሥርዓቶች በአግባቡ መከናወናቸውን መቆጣጠር በረቂቅ ደንቡ ከሚጠበቁበት ሥራዎች ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ሁሉንም መንግሥታዊ አገልግሎቶችን በአንድ ማዕከል በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ እንዲቀርቡ ከማድረግ ጀምሮ፣ በፓርኩ ለሚሰማሩ የውጭ አገር ዜጎች የቪዛ አገልግሎትና የሥራ ፈቃድ የሚሰጥባቸውን ሒደቶች የማቀላጠፍ፣ አመልካቾች ቪዛም ሆነ የሥራ ፈቃድ ለማግኘት ማሟላት የሚጠበቅባቸውን መሥፈርቶች ረቂቅ ደንቡ ይደነግጋል፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርክ ቪዛም ሆነ የሥራ ፈቃድ የሚሰጥባቸው መስኮች፣ ከሥልጠና እስከ ዓውደ ጥናት ለመሳተፍ የሚመጡትን ጨምሮ ኢንቨስት ለማድረግና ሥራ ለመቀጠር የሚመጡ የውጭ አገር ዜጎችና ቤተሰቦቻቸው የሚስተናገዱባቸውን አሠራሮች ረቂቅ ደንቡ ይዘረዝራል፡፡
በሌላ በኩል ግንቦት 20 ቀን ተመርቆ ሥራ የሚጀምረው የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክን ጨምሮ መንግሥት ሰባት ተጨማሪ ፓርኮችን በዋና ዋና የክልል ከተሞች ለመመሥረት ከ750 ሚሊዮን ዶላር በላይ በጀት መመደቡን አስታውቋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ አማካሪና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ ሰሞኑን ከአገር ውስጥ ባለሀብቶች ጋር ባደረጉት ስብሰባ፣ መንግሥት በሐዋሳ ብቻም ሳይሆን በሌሎች ወደፊት ከስድስት እስከ ዘጠኝ ወራት ባለው ጊዜ ውስጥ በሚገነቡ ፓርኮች ውስጥ የማምረቻ ቦታ በሊዝ በመግዛት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በአምስት ዓመት ውስጥ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚቀጠረው ሰው ብዛት ከሁለት ሚሊዮን በላይ እንደሚሆን ያስታወቀው ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ በ130 ሔክታር ላይ 38 ትልልቅ የማምረቻ ሼዶች የተገነቡለት የሐዋሳው ኢንዱስትሪ ፓርክን ጨምሮ የድሬዳዋና የመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ እንደሚጀመር አስታውቋል፡፡ ከሁለቱ በተጨማሪም በቦሌ ለሚ የምዕራፍ ሁለት ግንባታና በቅሊንጦም አዲስ የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡
ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲሆን ተደርጎ እንደ አዲስ የተደራጀው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽንን በሥሩ እየመራ የኢንቨስትመንት ማበረታቻና የውጭ ኢንቨስተሮችን ወደ አገር ውስጥ የማምጣት ተግባራት ከተሰጡት ኃላፊነቶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በአሥር ቢሊዮን ብር ካፒታል በመንግሥት ከተቋቋመ አንድ ዓመት ያስቆጠረ ሲሆን፣ በመንግሥት የተገነባውን የቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክን ጨምሮ ወደፊት የሚመጡትንና በአሁኑ ወቅት እየተንቀሳቀሱ ያሉትን የግል ኢንዱስትሪ ፓርኮችንም ይቆጣጠራል፡፡