Sunday, June 23, 2024

አገሪቱን የማይመጥኑ ድርጊቶች ይወገዱ!

የአንድን አገር የሰላም፣ የዴሞክራሲ፣ የብልፅግናና የዘለቄታ ጉዞ አመልካች ከሆኑ መሥፈርቶች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱት የመንግሥት አገርን በብቃት የመምራት አቅምና የሕዝብ እርካታ ናቸው፡፡ እነዚህ ሁለቱ ባልተጣጣሙበት ኩርፊያ፣ ግጭት፣ ሕገወጥነትና ሥጋቶች ይነግሣሉ፡፡ የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ሲቃኝ ደግሞ የተለያዩ ማንነቶች፣ ባህሎች፣ ቋንቋዎች፣ እምነቶች፣ የፖለቲካ አመለካከቶችና የመሳሰሉት ቢኖሩም፣ እነዚህን ልዩነቶች አቻችሎና አስታርቆ አገርን መምራትና እርካታ መፍጠር የግድ የሚባልበት ጊዜ ውስጥ ነን፡፡ ለዘመናት ሕዝቡ በልዩነቶቹ ውስጥ ሆኖ ያኖራትን አገር በአግባቡ መምራት ሲያቅት፣ ችግሮች ሲፈጠሩ አፋጣኝ መፍትሔዎችን አለመፈለግና ችላ ማለት ለአገር ህልውና አይበጅም፡፡ ለዘመናት በልዩነቶቹ አጊጦ የኖረ ሕዝብ የሚፈልገው ሰላም፣ ዴሞክራሲና ብልፅግና ነው፡፡ ይህ ይሆን ዘንድ ደግሞ አገሪቱን የማይመጥኑ ድርጉቶችን ማስወገድ ተገቢ ነው፡፡ ዋና ዋና ጉዳዮችን እናነሳለን፡፡

  1. የፓርቲና የአስተዳደር ሥራዎች አይደባለቁ

በማናቸውም የዴሞክራሲ ሥርዓት በሚከተሉ አገሮች ፓርቲዎች በምርጫ ሥልጣን ይይዛሉ፡፡ ለፖለቲካ ተሿሚዎችና ለባለሙያዎች ኃላፊነቶች ተለያይተው ይሰጣሉ፡፡ በሁሉም ሥፍራ የፖለቲካ ተሿሚዎችን ብቻ በመመደብ አገርን በካድሬ ለማስተዳደር ስለማይቻል፣ ለባለሙያዎች ትልቅ ትኩረት ይሰጣል፡፡ ከፌዴራል ተቋማት እስከ ወረዳ መዋቅር፣ ከመንግሥታዊ የፋይናንስ ተቋማት እስከ አነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች ማደራጃ፣ ከጤና ድርጅቶች እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ሁሉም ቦታዎች ውስጥ የፓርቲ አባላት ብቻ ሹመት ምን የሚሉት ነው? በመላ አገሪቱ የሚገኙ ከተሞች ሥራ አስኪያጆች፣ የከተማ ፕላነሮችና የመሳሰሉት ሳይቀሩ በባለሙያዎች የማይሞሉት ለምንድነው? አገሪቱ ያስተማረቻቸው ልሂቃን ካላገለገሉዋት ምን ይሠሩላታል? ሁሉም የሥራ አመራር በካድሬ ተይዞ ውጤት ይገኛል ማለት ዘበት ነው፡፡ ውጤቱም በተግባር እየታየ ነው፡፡ በአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ዜጎች እንደ ችሎታቸውና ዝንባሌያቸው አገራቸውን እንዲያገለግሉ ዕድሉ ይሰጣቸው፡፡ በዚህ በሠለጠነ ዘመን እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት ለአገሪቱ አይመጥንም፡፡

  1. ኃላፊነትን በአግባቡ አለመወጣት

በአሁኑ ጊዜ በበርካታ ቦታዎች ቸልተኝነት ከመቼውም ጊዜ በላይ አብቧል፡፡ የሚቆጣጠር አካል የለም ወይ እስኪባል ድረስ ኃላፊነትን በአግባቡ አለመወጣት ባለመቻሉ ምክንያት ብቻ፣ በየቦታው በጣም የሚያሳፍሩ ድርጊቶች ተንሰራፍተዋል፡፡ ግብር ከፋዩ ሕዝብ አገልግሎት ሲስተጓጎልበት ቅሬታ ቢያቀርብም አዳማጭ የለውም፡፡ በየቦታው ራሳቸውን ያነገሡ ሹማምንት ማንንም ሳያፍሩ በአደባባይ ጉቦ ይጠይቃሉ፡፡ አልሰጥም ያለውን ያንገላታሉ፡፡ ብልሹ አሠራሮችን በማስፈን የመንግሥት አገልግሎት መስጫ ተቋማትን የደላሎች መፈንጫ አድርገዋል፡፡ ፍትሕ ፍለጋ የሚባዝኑ ዜጎች እንባቸውን የሚያብስላቸው በመጥፋቱ ይብሰለሰላሉ፡፡ በወረዳና በክፍላተ ከተሞች፣ በማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች፣ በሕክምና ተቋማት፣ በግብይት ሥፍራዎች፣ በመንገድና ትራንስፖርት መሥሪያ ቤቶች፣ ወዘተ ኃላፊነትን በአግባቡ መወጣት ቅንጦት ሆኗል፡፡ በአንድ ሰሞን የዘመቻ ግርግር ደንገጥ ብለው የነበሩ ሹመኞች ነገሮች ሲረጋጉ ለበቀል ይነሳሉ፡፡ በዚህ ሥልጡን ዘመን ለሕዝብም ለአገርም የማይመጥኑ በየቦታው ተኮልኩለው አገር ሲያተራምሱ ያስቆጫል፡፡

  1. በየቦታው ግጭት መቀስቀስ

አስተዳደራዊ በደሎች በበዙ ቁጥር ሕዝብ ይከፋል፡፡ መጠኑ ሲያልፍ ደግሞ አመፅ ይቀሰቀሳል፡፡ እንዲህ ዓይነቱን አጋጣሚ ከተጠያቂነት ለመዳን የሚፈልጉ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ለግጭት መቀስቀሻነት ይጠቀሙበታል፡፡ በትምህርት፣ በልምድና በክህሎት ያልበሰሉ ራስ ወዳዶች የራሳቸውን ኔትወርክ በመመሥረት ሕዝብን መቆሚያ መቀመጫ ካሳጡ በኋላ፣ ያገኙትን ዘርፈው ሹልክ ማለት ሲፈልጉ ነውጥ እንዲነሳ ያደርጋሉ፡፡ ብሔርን በብሔር ላይ የሚያነሳሱ፣ የአንዱን ዕምነት ተከታዮች በሌላው ላይ የሚቀሰቅሱና ፀብ የሚያጭሩ አሉ፡፡ ከራሳቸው ጥቅም በላይ አገራዊው ዘለቄታ ራዕይ የማይታያቸው ወገኖች ከልካይ የሌለባቸው እስኪመስሉ ድረስ ትርምስ ይፈጥራሉ፡፡ ለሕግ የበላይነት ደንታ ስለሌላቸው ሕገወጥነትን እንደ መደበኛ ሥራ ያዩታል፡፡ ሕዝብን ከሕዝብ ለማናቆር የጠባብ ብሔርተኝነት አጀንዳዎችን ያራግባሉ፡፡ በአንድነትና በሰላም ተከባብሮ ይኖር የነበረን ሕዝብ ይበጠብጣሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ ከመጠን በላይ እየተለጠጡ የዜጎችን ሕገ መንግሥታዊ መብት በመጣስ ሲያፈናቅሉና ንብረት ሲዘርፉ፣ የአገርን ክብር ጭምር እያዋረዱ ነው፡፡ ለአገር የማይመጥኑ ድርጊቶችን እየፈጸሙ ነው፡፡  

  1. ስህተትን በስህተት ማረም

ካለፉት ጥፋቶች ባለመማር ተደጋጋሚ ስህተቶች ሲሠሩ ይታያሉ፡፡ በአገር ጉዳይ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትን ማግለል፣ ሽማግሌዎችን ማራቅ፣ ምሁራንን አትድረሱብኝ ማለትና ወጣቶችን ተስፋ ማስቆረጥ ለዓመታት የዘለቀ የአገር በሽታ ነው፡፡ አገርን ለመምራት ከብቃትና ከቁርጠኝነት ባሻገር የተለያዩ አስተያየቶችን ማድመጥም የአመራር ችሎታ ማሳያ ነው፡፡ እየታየ ያለው ግን በአንድ አቅጣጫ በተቃኘ አስተሳሰብ የእውነትና የብርሃን መንገድ መሪ ለመሆን መንደፋደፍ ነው፡፡ የጀመሩትን ጉዞ ሳያቋርጡ በየመሀሉ የሌሎች ወገኖችን ምክርና የዕውቀት ተሞክሮ ማዳመጥ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ ይህንን ዓይነቱን መልካም አጋጣሚ ወደ ጎን እየገፉ ከስህተት ወደ ስህተት መረማመድ ማንንም አያዋጣም፡፡ በተለያዩ ጊዜያት የታየው ግን ስህተትን በስህተት ለማረም እየተሞከረ ነው፡፡ ከዚህ የሚገኘው ውጤት ደግሞ አንገት ከማስደፋት የዘለለ ፋይዳ የለውም፡፡ ሕዝብ እርካታ እንዲሰማውና በአገሩ ተስፋ እንዲኖረው ካልተደረገ በስተቀር ሕዝብን እያስከፉ በግትርነት መቀጠል ውጤቱ አያምርም፡፡ ይህም ለአገሪቱ አይመጥንም፡፡

በአጠቃላይ እንደ አገር ሲታይ የተጀመሩት የለውጥ መልካም ዕርምጃዎች ግባቸውን የሚመቱት፣ ለዘመኑ የሚመጥን የአመራር ጥበብ መጎናፀፍ ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ትናንት የነበረው የአመራር ጥበብ ለዛሬ አይሠራም፡፡ የዛሬውም ለነገ ፋይዳ የለውም፡፡ በትናንት ታሪክ እየተኩራሩ የዛሬውን ዘመን በዚያው መንገድ ለመግራት መሞከር ፋይዳ ቢስ ነው፡፡ ይህች አገር ምንም እንኳ ለዘመናት በድህነትና በኋላቀርነት ውስጥ ብትዳክርም፣ በአንድ ወቅት ገናና ታሪክ የነበራት ናት፡፡ ለዓለም ካበረከተቻቸው ቅርሶች፣ ሥልጣኔዎችና በልዩነቶች ውስጥ ተቻችሎ የመኖር ተምሳሌታዊነቷ ጋር የተገመደው ታሪኳ፣ በጥቁር ዓለም ሕዝቦች ዘንድ አንፀባራቂ ያደረጋትን ፀረ ኮሎኒያሊስት ተጋድሎዋን ጭምር ይተነትናል፡፡ ለአገሩ ቀናዒ የሆነው ሕዝቧ ደግሞ ሕግ አክባሪ፣ ሰላም ወዳድና በአግባቡ የሚመራው ካገኘ አንፀባራቂ ድል ማስመዝገብ የሚችል ነው፡፡ ይህንን ኩሩ ሕዝብ በአግባቡ መምራት ካልተቻለ የታሪክ ተጠያቂ ያደርጋል፡፡ በዚህ በሠለጠነ ዘመን ይህቺ ታሪካዊት አገር ልትመነደግ ስትፍጨረጨር የማይመጥኗት ድርጊቶች ሊወገዱ ይገባል!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሕግ የማጥቂያ መሣሪያ እንዳይሆን ጥንቃቄ ይደረግ!

የሕግ መሠረታዊ ዓላማ ዜጎችን ከማናቸውም ዓይነት ጥቃቶች መጠበቅ፣ ለሕይወታቸውና ለንብረታቸው ከለላ መስጠትና በሥርዓት እንዲኖሩ ማድረግ ማስቻል ነው፡፡ በዚህ መሠረት ሁሉም ዜጎች በሕግ ፊት እኩል...

መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ የተንሰራፋው ሌብነት ልዩ ትኩረት ይሻል!

በየዓመቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከበጀት ረቂቅ በፊት መቅረብ የነበረበት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ግኝት ሪፖርት ማክሰኞ ሰኔ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ዘግይቶ ሲቀርብ፣ እንደተለመደው...

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ምን ታስቧል የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በጀት ለተለያዩ መንግሥታዊ ወጪዎች ሲደለደል...