Sunday, June 16, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ማምኮ መንግሥት ካልደረሰለት ሊዘጋ ጫፍ መድረሱን አስታወቀ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ችግር ደርሶበት ሳይሆን ችግር አድርሷል ተብሎ ተከሷል››

የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን

ከተመሠረተ 22 ዓመታት ያስቆጠረው ማምኮ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ መንግሥት ወይም የሚመለከተው አካል በፍጥነት ደርሶ ካልታደገው በቅርብ ቀናት ውስጥ ሊዘጋ እንደሚችል አስታወቀ፡፡

ለመዘጋት ጫፍ ላይ መሆኑን ያስታወቀው ኩባንያው ምክንያቱን እንደገለጸው፣ ከሦስት ዓመታት ወዲህ በሕገወጥ መንገድ የተሰማሩ ማንነታቸው ያልታወቁ አካላት በተመሳሳይ የንግድ ምልክት የጥራት ደረጃው የወረደ ተመሳሳይ ምርት ገበያውን በማጥለቅለቃቸው ምርቱን መሸጥ አልቻለም፡፡

በስፋትና በጥራት የሚታወቅባቸውን ‹‹ማምኮ ሶፍት›› የፊት ማበሻ ሶፍት፣ የገበታ ወይም አፍ ማበሻ ሶፍት፣ የወጥ ቤት ንፅህና መጠበቂያ ሶፍትና ጥራቱን የጠበቀ ደብተር ላለፉት 22 ዓመታት በተመጣጣኝ ዋጋ ለኅብረተሰቡ ሲያቀርብ እንደነበር ያስታወሱት የኩባንያው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መርዱፍ ሳሊም፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት ግን በሕገወጥ መንገድ የተሰማሩና እስካሁን ድረስ ማንነታቸው ያልታወቁ አካላት እንቅፋት እንደሆኑባቸው ተናግረዋል፡፡

ኩባንያው ባለ 130 ግራምና ባለ መቶ ግራም ደረጃውን የጠበቀ ሶፍት እያቀረበ ቢሆንም፣ በተመሳሳይ የንግድ ምልክትና አድራሻ ባለ 80 እና 70 ግራም ሶፍት ገበያውን ማጥለቅለቁን አክለዋል፡፡

የአገሪቱ ሕግ በሚፈቅደው መሠረት ተቋቁሞ ያለን ኩባንያ፣ የሚመለከተው የመንግሥት አካል ክትትል አድርጎ መታደግ ሲገባው፣ ሕገወጦቹን ማበረታታት መምረጡን አስረድተዋል፡፡ ለሚመለከታቸው ለንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን፣ ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንና ለፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ተደጋጋሚ አቤቱታ ቢያቀርቡም ምላሽ መነፈጋቸውን ተናግረዋል፡፡

ላለፉት ሦስት ዓመታት ኩባንያው በራሱ በኩል ክትትል አድርጎ ሊደርስበት ባለመቻሉ ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ሪፖርት ሲያደርጉ፣ ሕገወጦቹን ተከታትሎ ከመያዝ ይልቅ የማምኮ ዋና አከፋፋዮችን በማሰርና በማስፈራራት፣ ሕገወጦቹ የበለጠ እንዲስፋፉ መደረጉን ገልጸዋል፡፡ ለ22 ዓመታት በኅብረተሰቡ ውስጥ ያተረፈውን መልካም ስምና ተወዳጅነት፣ ሕገወጥ ግለሰቦች ያላግባብ በመጠቀም ለመበልፀግ ባላቸው ፍላጎት ‹‹ማምኮ›› የሚለውን የመፀዳጃ ሶፍት አስመስለው በመሥራት ገበያውን ሲያጥለቀልቁት፣ መንግሥት ዝም ብሎ ተመልካች መሆኑ እንዳሳዘናቸው ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡

ኩባንያቸው ባደረገው ክትትል ሕገወጦቹ አምራቾች ባለ 70 ግራምና 80 ግራም ሶፍት ለማቅረብ የወጣን ጨረታ ለመጫረት፣ ያቀረቡትን ሰነድ አግኝቶ ለሚመለከተው የመንግሥት አካል ቢያቀርብም ምላሽ እንደሌለ አስታውቀዋል፡፡ ከ22 ዓመታት በፊት በሼክ መሐመድ አል አሙዲ፣ በአቶ አህመድ ካራማና በአቶ መርዱፍ ሳሊም በ3.5 ሚሊዮን ብር ሥራውን በ50 ሠራተኞች የጀመረው ማምኮ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ፣ አሁን ከ200 በላይ ሠራተኞች እንዳሉት ገልጸዋል፡፡ ዘመናዊ ማሽኖችን አስገብተው እየሠሩ መሆናቸውንና ማሽኖቹ እንኳን ለኢትዮጵያ ለምሥራቅ አፍሪካ የሚበቃ ምርት ማምረት የሚችሉ መሆናቸውን ጠቁመው፣ አሁን በተፈጠረባቸው ችግር ሙሉ በሙሉ ሥራ ማቆማቸውንና ያመረቱት ምርትም በመጋዘን ታሽጎ መቀመጡን ገልጸዋል፡፡ የኩባንያው ጥቅም የአገር ጥቅም መሆኑንና የሕዝብ ሀብት መሆኑን በማስተዋል፣ መንግሥትና የሚመለከታቸው አካላት ኩባንያው እያደረሰበት ያለውን ሕገወጥ ድርጊት ተከታትለው ዕርምጃ እንዲወስዱ ጠይቀዋል፡፡

ማምኮ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ደረሰብኝ የሚለውን ጉዳትና የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት ምላሽ መንፈጋቸውን በሚመለከት የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን አቤቱታ፣ ምርመራና ክስ አቀራረብ ዳይሬክቶሬት ክፍል ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ ማምኮ ያቀረበው አቤቱታም ሆነ ቅሬታ የለም፡፡ እንዲያውም ያመረተውን ምርት በቀጥታ ለተጠቃሚዎች ባለማሠራጨቱና ሲጠየቅም በአከፋፋዮች በኩል እንዲያገኙ ምርቱን በመከልከሉ ክስ እንደቀረበበት እንደሚታወቅ አስታውቋል፡፡ ከዚህ ውጪ የተለየ ነገር እንደማያውቅ አክሏል፡፡ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንና ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽንን ለማነጋገር የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡       

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች