Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናነባር የኢዴፓ አመራሮች ፓርቲው መፍረሱን አስታወቁ

ነባር የኢዴፓ አመራሮች ፓርቲው መፍረሱን አስታወቁ

ቀን:

‹‹ፓርቲው በግለሰቦች ፍላጎት አይፈርስም››

አዲሱ አመራር

‹‹የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአዋጅ ከተሰጠው ሥልጣንና መብት ውጪ በፓርቲው የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ፍፁም ሕገወጥ የሆነ ድርጊት በመፈጸሙ፣ ከሐምሌ 29 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ከፍላጎታችን ውጪ በቦርዱ ሕገወጥ ድርጊት ህልውናችንን ያጣን መሆናችንን እንገልጻለን፤›› ሲሉ የኢትዮጵያውን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ነባር አመራሮች ውሳኔያቸውን ለሕዝብ ይፋ አደረጉ፡፡ ኢዴፓ መፍረሱንም አስታወቁ፡፡  

የፓርቲው መሥራችና የቀድሞ ሊቀመንበር አቶ ልደቱ አያሌውን ጨምሮ ሌሎች ነባር አመራሮች ይህን ያስታወቁት እሑድ ሐምሌ 29 ቀን 2010 ዓ.ም.፣ ‹‹የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ኢዴፓን በሕገወጥ መንገድ ያፈረሰው ስለመሆኑ›› በሚል ርዕስ በቅሎ ቤት አካባቢ በሚገኘው የፓርቲው ዋና ጽሕፈት ቤት ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት ነው፡፡

‹‹ቦርዱ የኢዴፓ ከፍተኛ የሥልጣን አካል የሆነውን ብሔራዊ ምክር ቤት ውሳኔዎች ያለበቂ ምክንያት አልቀበልም ከማለት ጀምሮ፣ በፓርቲያችን ውስጥ ለፈጸሙት ከፍተኛ የዲሲፕሊን ግድፈት የኢዴፓን ሕገ ደንብ በጠበቀ አሠራር ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ ለተደረጉትና ፓርቲውን ጥለው ለወጡት ለጫኔ ከበደ (ዶ/ር) ያልተገባ ዕውቅና በመስጠት፣ ኢዴፓን ወደ ግለሰብ የሳምሶናይት ፓርቲነት ለመቀየር ያለውን ግልጽ ፍላጎት በተደጋጋሚ አሳይቷል፤›› በማለት ምርጫ ቦርድን ወቅሰዋል፡፡

‹‹የምርጫ ቦርድን ሕገወጥ ድርጊት መንግሥት ማጣራት አድርጎ እንዲያስቆም ቀደም ሲል ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ ከእሳቸው ሥልጣን መልቀቅ በኋላ ደግሞ ለአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አቤቱታ ያቀረብን ቢሆንም፣ እስካሁን ምንም ዓይነት መፍትሔ ሳናገኝ ቀርተናል፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡

ምንም እንኳን ነባር አመራሮች ይህን ቢሉም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ወንድሙ ጎላ፣ እንዲህ ያለው ወቀሳና ክስ ዴሞክራሲያዊ ስላልሆነ ፓርቲው ለገጠመው ችግር መፍትሔም አይሆንም ሲሉ ለሪፖርተር ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

‹‹በአሁኑ ጊዜ በርካታ ፓርቲዎች ዕርቅ አድርገው በአንድነት ለመሥራት እየተንሳቀሱ ናቸው፡፡ እነሱም በዚህ መሠረት ቢሄዱ መልካም ነው፡፡ እኛም የምንመክረው ይህንኑ ነው፡፡ ነገር ግን ፓርቲው ፈርሷል ለማለት ሒደት አለው፡፡ አንዱና ዋነኛውም መንገድ ጠቅላላ ጉባዔ ማካሄድ ያስፈልጋል፤›› በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ችግራቸውን ተቀራርበው ቢፈቱ መልካም ነው ያሉት አቶ ወንድሙ፣ ‹‹በቀጣይ ተገናኝተው እንዲነጋገሩ የበኩላችንን አስተዋጽኦ ለማበርከት እንፈልጋለን፤›› ሲሉ ሐሳባቸውን አጠቃለዋል፡፡

በተመሳሳይ የኢዴፓ የጥናትና ምርምር ክፍል ኃላፊ አቶ ዋስይሁን ተስፋዬ፣ ‹‹አንድ ፓርቲ ሕጋዊነቱን የሚያጣው በግለሰብ ፍላጎት ነው እንዴ?›› በማለት በመጠየቅ፣ በነባር አመራሮቹ ፓርቲው ፈርሷል የሚለው አባባል ሕገወጥ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

‹‹ፓርቲ እንዴት እንደሚቋቋምና እንዴት እንደሚፈርስ ሕጋዊ አሠራር አለው፡፡ ስለዚህ አንድ ሰው ከፓርቲው ስለወጣ ፓርቲው ፈረሰ ማለት፣ ግለሰቡ ራሱን ከፓርቲው በላይ የማየት አባዜ ውጤት ነው፤›› ሲሉም ተቃውሞአቸውን አሰምተዋል፡፡

‹‹ከዚህ በኋላ ድርጅቱ ውስጥ ያሉ አቋሞች እኔን አይወክሉኝም ማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ፓርቲው ፈርሷል ማለት ወንጀልም ጭምር ነው፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ