Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየአዲስ ቪው ሆቴል ባለቤት በአምስት ሚሊዮን ብር ዋስትና ከእስር ተለቀቁ

የአዲስ ቪው ሆቴል ባለቤት በአምስት ሚሊዮን ብር ዋስትና ከእስር ተለቀቁ

ቀን:

ከሰው መግደል ሙከራ ወንጀል ነፃ ሆነዋል

ከተመሠረቱባቸው 29 ክሶች 22 በብይን ውድቅ ተደርገዋል

የተለያዩ የወንጀል ድርጊቶችን በመጥቀስና በመዘርዘር የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በግላቸው 29 ክሶችንና ሌሎች 11 ክሶች በድርጅታቸውና ሌሎች ተጠርጣሪዎች ላይ፣ ጳጉሜን 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ከተመሠረተባቸው በኋላ ዋስትና ተከልክለው በማረሚያ ቤት የቆዩት፣ የአዲስ ቪው ሆቴል ባለቤት በአምስት ሚሊዮን ብር ዋስትና ሰሞኑን ከእስር ተለቀቁ፡፡

በከፍተኛ የዋስትና ብር ከእስር የተለቀቁት የአዲስ ቪው ጄኔራል ሰርቪስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር (አዲስ ቪው ሆቴል) ባለቤት አቶ ዓብይ አበራ የተከለከሉት የዋስትና መብት ተፈቅዶላቸው ከእስር የተለቀቁት፣ በግላቸው ተመሥርተውባቸው ከነበሩት 29 ክሶች ውስጥ 22 በብይን ውድቅ በመደረጋቸውና እሳቸውም በድጋሚ የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው በመጠየቃቸው ነው፡፡ ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ተደራራቢ ክስ እንዳለባቸው በመጥቀስ ዋስትናቸው እንዳይከበር በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት መዝገብ ቁጥር 59304 አስገዳጅ ትርጉም መስጠቱን ጭምር በመግለጽ የተቃወመ ቢሆንም፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ስምንተኛ ወንጀል ችሎት የዓቃቤ ሕግንና የተከሳሹን ክርክር በመተንተን የዋስትና መብታቸውን አክብሮላቸዋል፡፡ አቶ ዓብይ ከአገር እንዳይወጡም ለዜግነትና ኢሚግሬሽን ጉዳይ ዋና መምርያ ዕግድ እንዲጻፍ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡   

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በተጠርጣሪው ላይ ክስ የመሠረተባቸው በወንጀል ተግባር የተገናኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ፣ አራጣ ማበደር፣ ፈቃድ ሳይኖራቸው የባንክን ሥራ ተክቶ መሥራት፣ ከባድ የማታለል ወንጀል መፈጸም፣ በሕገወጥ መንገድ ኢትዮጵያውያንን ለሥራ ወደ ውጭ አገር መላክ፣ ግብር በወቅቱ አለመክፈል፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ ደረሰኝ ሳይቆርጡ ግብይት መፈጸም፣ በሐሰተኛ ሰነድ መገልገል፣ የመከላከያ ሚኒስቴር የጦር መሣሪያዎችን ለመግዛት በሚያወጣው ዓለም አቀፍ ውስን ጨረታ በመሳተፍና ሚስጥር አሳልፎ መስጠት ወንጀሎችንና ሌሎች በክሱ ላይ የጠቀሳቸውን ፈጽመዋል በማለት መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ መሠረት ዓቃቤ ሕግ በአቶ ዓብይ ላይ መሥርቷቸው የነበሩ በሕገወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ፣ አራጣ ማበደር፣ ማታለል፣ የቫት ደረሰኝ ሳይቆርጡ ሽያጭ መፈጸም፣ ግብር አለመክፈልና ሐሰተኛ ሰነድ ማቅረብ ወንጀሎችን አሻሽሎና በማስረጃ አስደግፎ እንዲያቀርብ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 119(1) መሠረት ትዕዛዝ ሰጥቶት ነበር፡፡ የተሰጠውን ትዕዛዝ ባለመፈጸሙ በአንቀጽ 122(3) ክሶቹ ተገቢነት የሌላቸው ክሶች መሆናቸውን ፍርድ ቤቱ ስላመነባቸው፣ በብይን ውድቅ አድርጓቸዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ በመሠረተው ‹‹አራጣ ማበደር ወንጀል›› ክስ ላይ ተከሳሽ ገንዘቡን መቼ እንዳበደሩና ተበዳሪም መቼ ገንዘቡን እንደተቀበለ የማያሳይ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ ዓቃቤ ሕግ በጠቀሳቸው ቀናት ክፍያው ተፈጸመበት ያለው ቀን ብድሩ ከተሰጠበት ቀን እንደሚቀድም ጠቁሟል፡፡ ብድሩም እስከ መቼ እንደቀጠለ የሚገልጸው እንደሌለም አክሏል፡፡ በክሶቹ መብዛት (40 ክሶች ናቸው) ምክንያት ዓቃቤ ሕግ አሻሽል የተባለውን ክስ ‹‹አሻሽያለሁ›› ብሎ ያቀረበው ከፍ ብሎ ያቀረበውን ክስ ቀይሮ በማቅረብ እንጂ፣ ፍርድ ቤት እንዲያሻሽል ትዕዛዝ የሰጠበትን እንዳልሆነም በመዝገቡ ላይ ጠቅሶ አሳይቷል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በመከራከሪያው ‹‹የጦር መሣሪያ ምሥሎችን ማሳየት ሚስጥር ነው፤›› ቢልም፣ ሚስጥር ስለመሆኑ በየትኛው ሕግ፣ ደንብ ወይም መመርያ እንደተደነገገና የትኞቹን የመሣሪያ ዓይነቶች እንዳሳየ ሕግ ጠቅሶና አሻሽሎ እንዲያቀርብ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ቢሰጠውም፣ ያንኑ መልሶ ከማቅረብ ባለፈ ሊያሻሽል እንዳልቻለ ገልጿል፡፡ ተከሳሹ ዓቃቤ ሕግ ክሱን እንዳላሻሻለ ጠቅሰው ያቀረቡትን ተቃውሞ ፍርድ ቤቱም በማረጋገጡ፣ በሕጉ መሠረት ክሶቹ እንዲቋረጡ ማድረጉን በትዕዛዙ ገልጿል፡፡

የክሶቹን መቋረጥና በብይን ውድቅ የተደረጉላቸውን ክሶች በመጥቀስ፣ ከ100 በላይ ሠራተኞችን እንደሚያስተዳድሩ፣ የቤተሰብ ኃላፊ መሆናቸውን፣ በሚሊዮን የሚቆጠር ሀብት ያላቸው ድርጅቶችን የሚያስተዳድሩ መሆናቸውን፣ ዓቃቤ ሕግ ዋስትና እንዳይፈቀድላቸው ያደረገው ‹‹የዓቃቤ ሕግ ምስክሮችን የመግደል ሙከራ አድርጓል›› በማለት ቢሆንም፣ ምስክሮቹ ከተሰሙ በኋላ ‹‹መከላከል ሳያስፈልገው በነፃ ተሰናብቷል›› መባላቸውን በመጥቀስ፣ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 74 መሠረት፣ በድጋሚ የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው መጠየቃቸውን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በድጋሚ የቀረበውን የዋስትና ጥያቄ ተቃውሟል፡፡ ተደራራቢ ክሶች እንደቀረበባቸውና ሰበር ችሎት በመዝገብ ቁጥር 59304 አስገዳጅ ትርጉም መስጠቱን፣ ዋስትናውን ለመቃወሚያ ምክንያት ማቅረቡንም ፍርድ ቤቱ ጠቁሟል፡፡

ዓቃቤ ሕግ ከላይ የጠቀሳቸውን ምክንያቶች በማቅረብ አቶ ዓብይ ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ ቢቃወምም፣ አንድ ተከሳሽ የወንጀል ክስ ቀርቦበት ዋስትና ሊከለከል የሚገባው በልዩ ሁኔታ ሊከለከል የሚገባ ሆኖ ሲገኝ ብቻ መሆኑን በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 19(6) ድንጋጌ መንፈስ መገንዘብ እንደሚቻል ፍርድ ቤቱ ጠቁሟል፡፡ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 74 የዋስትና መብት የተፈቀደለትም ሆነ የተከለከለ ተከሳሽ፣ አዲስ ነገር በተገኘ ጊዜ ሌላ ትዕዛዝ ሊሰጥ እንደሚችል መደንገጉንም ፍርድ ቤቱ ጠቁሟል፡፡ በመሆኑም አቶ ዓብይ በዓቃቤ ሕግ ምስክሮች ላይ የመግደል ሙከራ ፈጽመዋል ተብሎ በመዝገብ ቁጥር 207296 ከቀረበባቸው ክስ በነፃ መሰናበታቸው መረጋገጡንና ተደራራቢ ክሶች ከተባሉትም 29 ክሶች ውስጥ 22 ውድቅ የተደረጉላቸው መሆኑን በትዕዛዙ አስፍሯል፡፡

የሰበር ችሎት ውሳኔም ‹‹የግድ ዋስትና መከልከል አለበት›› የሚል ሳይሆን፣ ዋስትናን ለመከላከል ከግንዛቤ ውስጥ ሊገባ የሚቻልበትን ሁኔታ የሚመለክት መሆኑንም ፍርድ ቤቱ አክሏል፡፡ በአቶ ዓብይ ላይ ቀደም ሲል ዓቃቤ ሕግ የመሠረታቸውና ለዋስትና መከልከል ምክንያት የሆኑት በእጅጉ የቀነሱ በመሆናቸው፣ የዋስትና ክልከላቸውን ትዕዛዝ ለማንሳት በሕጉ ድንጋጌ መሠረት ማንሳት የሚያስችል አዲስ ነገር መገኘቱን አስረድቷል፡፡ በመሆኑም የአዲስ ቪው ሆቴል ባለቤት አቶ ዓብይ አበራ በአምስት ሚሊዮን ብር ዋስትና ከእስር እንዲለቀቁ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...