Monday, October 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትአትሌቲክሱ በአኅጉራዊ ተሳትፎው የሜዳሊያ ሰንጠረዡን አሻሻለ

አትሌቲክሱ በአኅጉራዊ ተሳትፎው የሜዳሊያ ሰንጠረዡን አሻሻለ

ቀን:

በአኅጉር ደረጃ በየሁለት ዓመቱ የሚካሄደው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና፣ ከሐምሌ 25 እስከ 29 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ በምዕራብ አፍሪካዊቷ ናይጀሪያ ሲካሄድ ሰንብቶ እሑድ ሐምሌ 29 ቀን 2010 ዓ.ም. መጠናቀቁ ይታወሳል፡፡ በሻምፒዮናው የተካፈለችው ኢትዮጵያ በሁለት ወርቅ፣ በሦስት የብርና በአምስት የነሐስ በድምሩ በአሥር ሜዳሊያዎች አምስተኛ ደረጃ ይዛ ውድድሮቿን አጠናቃለች፡፡ ብሔራዊ ቡድኑ ረቡዕ ነሐሴ 2 ቀን 2010 ዓ.ም. ማለዳ አዲስ አበባ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በናይጀሪያ አላባ ከተማ በተካሄደው በዘንድሮው ሻምፒዮና ሁለቱ የወርቅ ሜዳሊያዎች የተመዘገቡት በ10,000 ሜትር ወንዶችና በ20 ኪሎ ሜትር ዕርምጃ ሴቶች ነው፡፡ አትሌት ጀማል ይመር ርቀቱን ለማጠናቀቅ 29፡08.01 ጊዜ ሲፈጅበት፣ በሴቶች 20 ኪሎ ሜትሩን ለማጠናቀቅ አትሌት የኃልየ በለጠው 01፡31.46 በሆነ ጊዜ አጠናቃ ማሸነፉ ታውቋል፡፡

የብር ሜዳሊያዎቹን በ10,000 ሜትር አትሌት አንዳአምላክ ይመር 29፡11.09 ሰዓት፣ በ5,000 ሜትር ጌታነህ ሞላ 13፡49.68 እና በሴቶች 5,000 ሜትር ርቀቱን 15፡54.48 ሰዓት ለሰንበሬ ተፈሪ አማካይነት የተገኙ ሲሆን፣ የነሐስ ሜዳሊያዎቹ በሴቶች 5,000 ሜትር  መስከረም ማሞ፣ በ10,000 ሜትር አስናቀች አወቀ፣ በ800 ሜትር በሀብታም አለሙ፣ በወንዶች 3,000 ሜትር መሰናክል በጌትነት ዋለና በሴቶች ከፍታ ዝላይ በአርዓያት ዲቦ አማካይነት መገኘታቸው ታውቋል፡፡

ሻምፒዮናው በኬንያ የበላይነት ሲጠናቀቅ፣ ኬንያ በ11 የወርቅ፣ በስድስት የብርና በሁለት የነሐስ በድምሩ 19 ሜዳሊያዎችን ማስመዝገብ መቻሏ ታውቋል፡፡

ኢትዮጵያ ካልተካፈለችባቸው ሁለት ሻምፒዮናዎች ውጪ በሌሎቹ ሻምፒዮናዎች 42 የወርቅ፣ 50 የብርና 59 የነሐስ በአጠቃላይ 151 ሜዳሊያዎች ማስመዝገቧን ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡ በሩጫው ዘርፍ በተለይም በአኅጉራዊው መድረክ በምሥራቅ አፍሪካውያኑ ኢትዮጵያና ኬንያ መካከል ለዓመታት የዘለቀ የተፎካካሪነት መንፈስ ፀንቶ ቢቆይም፣ አሁን ላይ ግን ልዩነቱ እየሰፋ መምጣቱ ከናይጀሪያው ሻምፒዮና መረዳት ይቻላል፡፡

ለፌዴሬሽኑ ቅርበት ያላቸው ሙያተኞች እንደሚሰጡት አስተያዬት ከሆነ፣ ተቋሙ ከአጭር ርቀት እስከ ማራቶን ባለው የውድድር ዘርፍ ጠንካራ ሥራ የመሥራት ካልሆነ በቀር የክህሎትና የብቃት ችግር እንደሌለበት ይናገራሉ፡፡ ለዚህም በፌዴሬሽኑ አሁን ያለው አመራር ከወራት በፊት በአገር አቀፍ ደረጃ ባደረገው የዳሰሳ ጥናት መሠረት፣ በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የልቀት ማዕከላትን በመለየት እንቅስቃሴ መጀመሩ የለውጥ  ተስፋ ብቻ ሳይሆን የመነቃቃት ምልክት እንዳሳየ ይናገራሉ፡፡

በአፍሪካ ደረጃ እ.ኤ.አ. በ1979 በሴኔጋል ዳካር አስተናጋጅነት የተጀመረው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና፣ የዘንድሮውን ጨምሮ ለ21ኛ ጊዜ ቢካሄድም፣ አኅጉራዊው ይህ ውድድር ግን የዕድሜውን ያህል በጥንካሬው ሲጠቀስ አይስተዋልም፡፡  ከመዋቅራዊ ይዘት እስከ ውድድር ዝግጅት ከፍተኛ ክፍተት የሚስተዋልበት መሆኑ ትኩረት ለማጣቱ አንዱ መንስዔ እንደሆነ ይነገራል፡፡ በ16 የአትሌቲክስ ውድድሮች አሃዱ ያለው ይህ ሻምፒዮና በሁለት አሥርታት ዕድሜው ከፍ ማለት የቻለው ወደ 22 የውድድር መስኮች ብቻ መሆኑ ለድክመቱ ማሳያ እንደሚሆን የሚገልጹም አሉ፡፡

በአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን አስተናጋጅነት በየሁለት ዓመቱ የሚካሄደው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ የተሳተፈው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን በናይጀሪያ አላባ ከተማ በነበረው ቆይታ የትራንስፖርትና የሎጂስቲክ ችግሮች ገጥሞት መቆየቱ ተነግሯል፡፡ ሆኖም ቡድኑ ከእንዲህ ያሉት መሰናክሎች ተላቆ የተፎካካሪነት አቅሙን ማጎልበቱ ላይ መበርታት፣ ጽናቱንም ማሳየት እንደሚጠበቅበት የሚገልጹ አልታጡም፡፡

እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ ከሆነ፣ ኢትዮጵያ በራሷ የውስጥ ችግሮች ሳቢያ በሦስተኛውና በአሥረኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ባትሳተፍም፣ በሌሎቹ ሻምፒዮናዎች ግን በሁሉም ተካፍላለች፡፡ በደቡብ አፍሪካ ደርባን ከተማ  ተዘጋጅቶ በነበረው 20ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተሳተፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በወቅቱ በአንድ የወርቅ፣ በሁለት የብርና በሦስት የነሐስ በድምሩ በስምንት ሜዳሊያዎች ስምንተኛ ደረጃን ይዞ መመለሱ አይዘነጋም፡፡ ብቸኛውን የወርቅ ሜዳሊያ ያስመዘገበው አትሌት ጫላ ባዩ በ3,000 ሜትር ውድድር እንደነበር ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...