Thursday, July 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከትናንት እስከ ዛሬ

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከትናንት እስከ ዛሬ

ቀን:

(ክፍል አንድ)

በበኃይሉ በላይ

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትራችን የአገራችንን ፖለቲካ እንደ አዲስ ቀደው ከመስፋታቸው በተጨማሪ፣ አንዳንድ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ለውጦችን በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ መንግሥት ስላቀዳቸው የፖሊሲ ለውጦችና ምከንያቶቹ ለማስገንዘብ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ስለአገራችን ኢኮኖሚ፣ ወቅታዊ ተግዳሮቶችና ስለታቀዱ መፍትሔዎች የተለያዩ ንግግሮችን አድርገዋል፡፡ አንዳንድ ተቃዋሚዎች ቢኖሩም እነዚህ የፖሊሲ ለውጦች በብዙ የዘርፉ ምሁራን ተቀባይነትን አትርፈዋል፡፡ በተለይ ታዋቂው የቢዝነስ ሰውና የኢኮኖሚ ባለሙያ አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ቀደም ብሎ በሚያዚያ ወር 2010 ዓ.ም. ስለጉዳዩ ‹‹The Ethiopian Economy at Across Road April-2018›› በሚል ርዕስ አጭር ጥናት አቅርበው ነበር፡፡ የባለሙያው ምልከታና የወቅቱ የመንግሥት የለውጥ አቅጣጫዎች የሚደጋገፉና ተመሳሳይ ሊሆኑ ችለዋል፡፡

ጸሐፊው በዚህ ጽሑፍ ስለአገራችን ኢኮኖሚ፣ ወቅታዊ ተግዳሮቶች፣ መንስዔዎቻቸውና መፍትሔዎቻቸው በመንግሥት አዲስ አቅጣጫዎችና በግለሰቡ ጥናት ላይ አንዳንድ ነገሮችን ለመጨመርና ያለውን የተለየ አመለካከት ለአንባቢያን ለመግለጽ ይሞክራል፡፡ በክፍል አንድ እንደ መግቢያ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በማንሳት ትናንትና ዛሬ በማለት ይመለከታል፡፡ ላለፉት 27 ዓመታት በልማታዊው አጠቃላይ ኢኮኖሚ፣ የግብርና መር ፖሊሲና በዘርፉ የነበረውን አፈጻጸም ይዳስሳል፡፡ በክፍል ሁለት በማምረቻ ኢንዱስትሪውና አገልግሎቱ የነበረውን፣ ያለውንና ምናልባት የሚቀጥለውን የመንግሥት ፖሊሲና አፈጻጸም በማስቃኘት እውነት የሚባለው ልማታዊ መንግሥትና ፖሊሲ ነበረን ሲል ይጠይቃል፡፡ ወደ ኢንዱስትሪ (ያውም አምርቶ ለውጭ ገበያ የሚያቀርብና የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኝ) ዘርፍ ሊደረግ የሚታሰበው ሽግግርን ውጤታማነት ይቃኛል፡፡ በመጨረሻ ለኢኮኖሚ ፖሊሲያችን ተገቢ ነው ስለሚለው የለውጥ ዕርምጃ ሐሳብ ያቀርባል፡፡

ትናንትም ይሁን ዛሬ በግብርና፣ በሰብል ልማትና በእንስሳት እርባታ ላይ የተመሠረተው የአገራችን ኢኮኖሚ ዛሬም ድረስ የመሠረታዊ ለውጥ ባለቤት አይደለም፡፡ ትናንት በፊውዳሏ ኢትዮጵያ በዚህ ዘርፍ የተመረተው የብዙኃኑ አርሶ አደርና አርብቶ አደር ምርት የየአካባቢው መኳንትና መሳፍንት፣ ከዚያም የማዕከላዊው መንግሥት ሲሳይ ነበር፡፡ በቀጥታና በዓይነት እየቀረበ፡፡ ገባሩ ያመረተው ትርፍ ምርት የበላተኞች ብቻ ስለነበር ቀጣይነት የነበረው ዕድገት ማስመዝገብ ሳይቻል ቀርቷል፡፡ የደከመበትን ምርትና ዋጋውን አግኝቶ ካልተጠቀመበት፣ መልሶ ሥራውን ካላጎለበተበትና የሰው ልጅ በድካሙ ለውጥን ማሽተት ካልቻለ ምርታማነትና ዘላቂ ዕድገት አይታሰቡም፡፡

አገራችን ዘመናዊ ጉዞዋን ከጀመረች በኋላም ቢሆን በወታደራዊው መንግሥት መሬት ላራሹ ታውጆ ብዙኃኑ የመሬት ባለቤት ቢሆንም፣ የእያንዳንዱ አምራች ምርትና ዋጋው የአምራቾች ማኅበራት የመንግሥት የገበያ ፖሊሲ ሰለባዎች ነበሩ፡፡ ስለዚህ ተመሳሳይ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ላለፉት 27 ዓመታት ድህነት ለተንሰራፋበት ኢኮኖሚ ይበጃል ብሎ መንግሥት አዛዥና ናዛዥ የሚሆንበትን የኢኮኖሚ መስመር የተከተለው አብዮታዊውና ልማታዊ መንግሥታችንም ቢሆን፣ ፖሊሲውን የተጠቀመበት የቆየውን የፊውዳሎችና የጭሰኞች ግንኙነትና ባህሪውን በሚያስቀጥል መንገድ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ አስገባሪዎች ቢቀየሩ ወይም አዲስ ስም መያዛቸው ለውጥ የለውም፡፡

የመጀመርያውን የፊውዳሉንና የመጨረሻውን የልማታዊ መንግሥት ኢኮኖሚ ለማወዳደር የሚከተሉትን ሁለት ቁም ነገሮች ማስተዋል ተገቢ ነው፡፡ ግብርና የንግድ ትርፍ (Tax and Business Profit) በፊውዳል ኢኮኖሚ በጥቂት ፊውዳሎችና በብዙኃኑ አምራች መካከል መጀመርያ የነበረው ግንኙነት የገባሮችና የአስገባሪዎች ብቻ ነበር፡፡ ምርጫ አልነበረም፡፡ አስገባሪዎች ጌቶች ወይም የጌታ ልጆች፣ ባለ ርስት ነን ብለው ስለነበሩ ብቻ ከአምራቹ ግብር ይጠይቁ ነበር፡፡ አምራቹም ይህን ተቀብሎ እንደ ግዴታ ሲፈጽመው ዘመናት አልፈዋል፡፡ በዓለም ላይም ሆነ በአገራችንም ግብር ግዴታ ብቻ ነበር በውስጡ አማራጭና ስምምነት አልነበረውም፡፡ አስገባሪዎች በአንድ አገር ውስጥ የተወሰነ ሚና እንደነበራቸው ግልጽ ቢሆንም፣ የሚበልጠው ግን ሸክምነታቸው ነበር፡፡

በዓለም ላይ ከኋላ ቀሩ ፊውዳሊዝም ከድክመቶቻቸው ጋር የተሻሉ ወደ ሆኑት ዘመናዊው ሥርዓቶች ካፒታሊዝም፣ ሶሻሊዝምና የሁለቱ ቅልቅል ወደ ሆነው ልማታዊ ኢኮኖሚ የተደረገው ሽግግር በተለያዩ ዘዴዎች ከላይ የተገለጸውን የገባሮችና አስገባሪዎች ግንኙነት በባህሪው በመቀየር ነው፡፡ የመጀመርያው የፊውዳል አስገባሪዎች ስለነበሩ ብቻ የሚገባቸውን ሳይሆን፣ በሀራራቸው ላይ ተመሥርተው የሚፈልጉትን ግብር ወደ ዜጎች የጋራ አስተዳደራዊና ልማታዊ ወጭ መቀየርና መመጠን ለዜጎች ሁሉ በፍትሐዊነት በማከፋፈል ገቢውን ለታለመለት ዓላማ በተገቢው ሥርዓት በመጠቀም ነበር፣ ወደ ታክስ ማለት ነው፡፡ (ግብር፣ ገባር የሚሉት ቃላት የተያያዙ ናቸው፡፡ ዛሬም በአገራችን ዜጎች አምነውበትና በፍላጎታቸው ለመንግሥት የሚፈጽሙት መዋጮ ከስምምነት በሕግ ኃይል የተጫነ፣ እንደ ጥንቱ በሙስና የሚባክን፣ ለአምራቾችና ለባለቤቶች ቅድሚያ ጥቅም ላይ ያልዋለ በመሆኑ የጥንቱን ስም መያዙ ግን ትክክል ይመስላል)፡፡

ሌሎች ለውጦች ደግሞ በፊውዳሉ ሥርዓት አቆጥቁጠው የነበሩ ተጨማሪ የኢኮኖሚ ዘርፎችን ማዘመንና ማስፋፋት ናቸው፡፡ በሁለት ልንከፍላቸው እንችላለን፡፡ የመጀመርያውን የግብርና ዘርፍ የተለያዩ ምርቶችን ወደ ገበያ የሚያደርሱ ለዚህ ዘርፍ ግብዓት ለአምራቹ አርሶ አደርና አርብቶ አደር መሠረታዊ ሸቀጦችን የሚያቀርቡ፣ ለዚህ ዓብይ ተግባር ወሳኝ የሆኑ የሚዳሰሱ ወይም የማይዳሰሱ መሠረተ ልማቶችን የሚያቀርቡ፣ ከቀበሌና ከወረዳ ጀምሮ እስከ ዓለም አቀፍ ገበያ የሚያደርስ የኢኮኖሚውን የተለያዩና በአገልግሎት ዘርፍ የሚጠቃለሉ ሥራዎችን በማዘመንና በማጎልበት ሁሉንም ተጠቃሚ ማድረግ ነው፡፡

ለዘለቄታው ሁሉም ተጠቃሚ የሚሆነው አንዱን በአንዱ ላይ በመጫን ሳይሆን ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ከመቶ ዓመታት በፊት መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር በተሰኘው መጽሐፋቸው እንደገለጹት አምራቾች፣ የምርቱ ባለቤቶች ሌላ አማራጭ ሲጠቀሙ ወይም ለምሳሌ በተበታተነ መልኩ ምርቶቻቸውን ራሳቸው ወደ ገበያ ቢያቀርቡ ወይም ግብዓቶችን በቀጥታ ሲገዙ የሚያገኙት ተጨማሪ ዋጋና የሚጠበቅባቸው ወጭ (ወይም የነጋዴው ትርፍ ማለት ነው) የግዴታ ምርቶቻቸውን ወደ ገበያ ራሳቸው ሲያደርሱና ሲገዙ ከሚባክነው ጊዜ፣ ዋጋና በዚህ ምክንያት ሳያመርቱ ከሚቀሩት የምርት ዋጋ ድምር ማነስ አለበት፡፡ በዚህ ሁኔታ አምራቾች የነጋዴዎችን አገልግሎት መጠቀም ይመርጣሉ፡፡ የጋራ ስምምነቱ መሠረት የሚቆመው በዚህ መሠረት ላይ ብቻ ሲሆን፣ ከዚህ ካፈነገጠ ለሁሉም የችግር መጀመርያ ይሆናል፡፡

ሁለተኛው የማምረቻ ኢንዱስትሪ ዘርፍን ማዘመንና ማስፋፋት ነው፡፡ የማምረቻ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ከኢኮኖሚ ሀብቶች መካከል ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይና ዕውቀትን ይፈልጋል፡፡ በተለይ ከግብርና ጋር ሲነፃፀር ደግሞ የሚፈልገው የሰው ጉልበት አነስተኛ ነው፡፡ ዘርፉን ቀጣይነት ባለው ዕድገት በፅኑ መሠረት ላይ ለመትከልና ዕድገቱን ለማስቀጠል የግብርና ዘርፉን በመጠቀም ቢያንስ የተወሰነ የአገር ውስጥ ትርፍ ካፒታል ባለቤት መሆን፣ ለማምረቻ ኢንዱስትሪው ግብዓት የሚሆኑ ምርቶችን ማምረትና በኢንዱስትሪው ለሚመረቱ ምርቶች ሰፊና አስተማማኝ የአገር ውስጥ ገበያ (እንደ ሁኔታው ለተወሰነ ጊዜ ከተመሳሳይ የውጭ ምርቶች የተጠበቀ ወይም የተከለለለ ሊሆን ይችላል) መቅደም ይኖርባቸዋል፡፡ በዚህ ሒደት ተጨማሪ የሥራ ዕድል መፍጠር፣ ምርታማነትና ተወዳዳሪነት በሒደት፣ በልምድና በገፍ (በብዛት) በማምረት (Mass Production) ሲያድግ ከአገር ውጭ መጀመርያ በአካባቢ ገበያ ከዚያ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪና ውጤታማ መሆን ይቻላል፡፡ ከላይ እንደተገለጸው ሒደቱ ሁሉንም በሚጠቅም ቢያንስ በጊዜያዊ መደጋገፍ ላይ እንጂ፣ አንዱን በአንዱ ላይ በመጫን ወይም በፍላጎት ብቻ ኢንዱስትሪን ማስፋፋት አይቻልም፡፡

ለዚህ ደግሞ ከግብርናው ጀምሮ የአገልግሎት ዘርፉና የማምረቻ ኢንዱስትሪው ተዋናዮችና ባለቤቶቻቸው ግለሰብም ይሁን ማኅበራት፣ የፓርቲ ድርጅትም ይሁን የመንግሥት የልማት ድርጅት በአገር ኢኮኖሚ ውስጥ በሚሠሩት  ሥራ (Business) ልክ የአደጋ ተጋላጭ (Business Risk) መሆን አለባቸው፡፡ በዚህ ተጋላጭነት መሠረት በትክክል ሲሠሩና ሲሳካላቸው በድካማቸው ልክ ተገቢውን ትርፍ (Business Profit) ማግኘት ሳይሆን፣ ደግሞ መክሰር (Business Loss) ይኖርባቸዋል፡፡ ሲሳካላቸው የሚያገኙት ገቢ ከልፋታቸው፣ ከድካማቸውና ተጋልጠውበት ከነበረው አደጋ መጠን ጋር ከፍና ዝቅ ማለት ይኖርበታል፡፡ በሁሉም ዘርፍ፡፡ ሳይሳካላቸውም ኪሳራቸው ተመሳሳይ መሆን ይኖርበታል፡፡ ይህ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ሁኔታ በእያንዳንዱ ዘርፍ፣ በግብርናው፣ በአገልግሎቱና በኢንዱስትሪው የሚፈለገውን ፍትሐዊ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት የሚገፋና በሒደት የሚያስተካክል ዓብይና የመጀመርያው ሁኔታ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የመጀመርያ ኢንቨስትመንቶችም ይሁኑ ከዚያ በኋላ በዘርፎች መካከል የሚኖረው የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት የበለጠ የተሳለጠ እንዲሆን ተጨማሪ ፖሊሲዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ከላይ የተጠቀሱትን ተግባራት በየትኛውም መንገድ (ፖሊሲ) መፈጸም የሚቻል ቢሆንም፣ የአንድ አገር ኢኮኖሚ ባለው የሀብት ዓይነት (Types of Resources) አጠቃላይ ኢኮኖሚው ባለበት ደረጃና በባህሪው ላይ ተመሥርቶ ተገቢውን መንገድና ፖሊሲ በመከተልና በመፈጸም፣ ከጅምሩ የነበረውን የፊውዳል ሥርዓት፣ የብዙኃኑን ገባሮችና የጥቂት አስገባሪዎችን (የፊውዳሉና የጭሰኛው) ግንኙነት በመሠረታዊ ባህሪው መቀየር አስፈላጊ ይሆናል፣ ለተሻለ ዘላቂ ዕድገትና ለውጥ፡፡

ከላይ የተገለጹት ዓብይ ተግባራት መንግሥት በትክክል በሚቆጣጠረው ኢኮኖሚ (ከተቻለ)፣ በከፊል ጣልቃ በሚገባበት የልማታዊ መንግሥት ወይም በሒደት ብዙኃኑ ገዥና ሻጭ ሁነው በሚሳተፉበትና ጥቂቶች ተፅዕኖ የማይፈጥሩበትን የገበያ ሥርዓት ዕውን በማድረግ መፈጸም ይቻላል፡፡ መጨረሻው ተመሳሳይ ከሆነ ችግር የለውም፡፡ በፊውዳሉ ሥርዓተ ማኅበር ስለነበሩ ብቻ ተጠቃሚ ነበሩ የምንላቸው አስገባሪዎችን ነበር፡፡ በመረጃ ላይ ባልተመሠረተ ገበያ፣ በአምራቹና በአገሪቱ መሠረተ ልማት ኋላ ቀርነትና በግዴለሽ የመንግሥት ፖሊሲ ምክንያት የብዙኃኑን ምርት ወደ ገበያ ስላቀረቡ ብቻ ጥቂቶች ምንም የሥራ አደጋ ተጋላጭ ሳይሆኑ፣ በቀላሉ  ሰማይ መድረስ ከቻሉ ንግድ ፈቃድ መንግሥት ቢሰጣቸውም ግብር ቢከፍሉም አስገባሪዎች መሆናቸውን መረዳት ተገቢ ነው፡፡ ከቀበሌና ወረዳ ጀምሮ እስከ ውጭ ንግድ ድረስ፡፡ በተመሳሳይ በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ተወዳዳሪ የሌላቸው አስመጪዎች፣ በብዙኃኑ ጥረት በተገኘ የውጭ ምንዛሪ ተጠቅመው ከውጭ አገር ባስገቡት ሸቀጥ በብዙኃኑ ላይ ዋጋ ጭነው የልባቸውን ካደረሱና ከተንቀባረሩ አዲሶች፣ የበለጠ አቅምና ጉልበት ያላቸው ፊውዳሎች ናቸው ማለት ነው፡፡

በመካከል ያሉ አገልግሎት ሰጭዎች፣ የትራንስፖርትና የፋይናንስ ተቋማት ስላሉ ስለጀመሩ ብቻ ትርፋማ ሁነው ከቀጠሉ አምራቹን ካላገለገሉ፣ የአምራቹን ከፍተኛ አደጋ ካልተጋሩ ተመሳሳይ ነው፡፡ ግለሰብ፣ ማኅበር፣ አክሲዮን ማኅበር፣ ፓርቲና መንግሥት ቢሆኑም ለውጥ የለውም፡፡ ላቡን የሚያንጠፈጥፈው አርብቶ አደርና አርሶ አደር፣ በባህሪው የከፍተኛ አደጋ ተጋላጭ የሆነው የግብርና ዘርፍ፣  ባመረተው ምርትና በሚጠቀምበት ሸቀጥ የሚተረፍበት ዘመናዊ ጭሰኛ ነው፡፡ ጭሰኛና ዘርፉ በሒደት ቢቆረቁዝ ደግሞ አይገርምም፡፡ በዚህ ሒደት የሚመዘገብ ዕድገት ጥቂት ሲሆን፣ ባለቤቱም ብዙኃኑ አምራቹ አይሆንም፡፡ ስለዚህ ተመልሶ ለዘላቂ ዕድገት አይውልም፡፡ በአገራችን የከተማ ኢኮኖሚ ሳያድግ ከተሞቻችን ከወረዳ ጀምሮ ያበጡት በዚህ ምክንያት ነው፡፡ የአገራችን ወቅታዊ የኢኮኖሚ ችግሮች መንስዔ ዕድገት ብቻ ሳይሆን፣ ዕድገቱ እብጠት በመሆኑ ነው፡፡ እብጠት ደግሞ ሁልጊዜም ገደብ አለው፡፡ እብጠቱ ሁሉን አቀፍ ሲሆን፣ ሁሉንም መብት ግዴታ ነው፡፡ በዚህ ዓውድ ከግብርናው ዘርፍ ጋር ለሚቀራረብ የሥራ አደጋ ተጋላጭ የሆነውን ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ፣ የቴክኖሎጂና የአስተዳደር ዕውቀት የሚጠይቀውን የማምረቻ ኢንዱስትሪውን ዕድገት መጠበቅ ሞኝነት ነው፡፡

ከውጭ አገር የገባ ጥሬ ዕቃን ተጠቅሞ፣ ምርቱን በረዥም የየብስና የባህር ትራንስፖርት አጓጉዞና የወደብ ኪራይ ከፍሎ ከዓለም ገበያ የውጭ ምንዛሪ የሚያፍስ ዘርፍ መመኘት ህልም ብቻ ነው፡፡ ልማታዊ፣ አብዮታዊና ወዛደራዊ ቢሆንም ይህን ሁኔታ ያስቻለ አብሮ የነገደ ፓርቲና መንግሥትም የአፄዎች መሆኑን መረዳት ተገቢ ነው፡፡ በብዙኃኑ ምርት ላይ የሰበሰበውን ገቢ በሙስና የላቀ ፋይዳና ውጤት በሌላቸው በቅንጦት መሠረተ ልማቶች ያባከነ መንግሥት እንደ ጥንቱ አስገባሪ ፊውዳል እንጂ፣ ዘመናዊ መንግሥት ሊባል አይችልም፡፡ የወቅቱ የኢኮኖሚያችን ችግሮች የተከተልነው ፖሊሲ በትክክል ስላልተፈጸመና የነበረውን የፊውዳሎች ባህሪ በዋናነት በማስቀጠሉ ምክንያት የተከሰቱ ናቸው፡፡ ከዚህ ውስጥ መንግሥት፣ አቶ ኤርሚያስና ሌሎችም የሚጠቅሷቸው ጥቂቶችን ብቻ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ባለፉት 27 ዓመታት የተከተልነውን የልማታዊ መንግሥት ፖሊሲ፣ አፈጻጸሙንና ውጤቱን በኢኮኖሚው ዘርፎች ከፋፍለን ስንመለከተው የበለጠ ግልጽ ይሆናል፣ ከግብርናው እንጀምር፡፡

የግብርናው ዘርፍ የልማታዊ መንግሥት አቅጣጫ፣ ግብርና መሩ የኢኮኖሚ ፖሊሲና አፈጻጸሙ

አብዮታዊው የኢሕአዴግ መንግሥት ለሰፊው አርሶ አደርና አርብቶ አደር የቆመ መሆኑን፣ ድህነት የተንሰራፋበት ኢኮኖሚ ነው በማለት ልማታዊ መንግሥት ነኝ ብሎ ቢነሳ ትክክል ነበር፡፡ ከኢኮኖሚ ሀብቶች መካከል በአፃራዊነት ብዙ የሰው ጉልበት፣ ሰፊ ለእርሻ ሥራና ለእንስሳት ግጦሽ የሚሆን መሬትና እጅግ አነስተኛ መዋዕለ ንዋይና ዕውቀት ባሉት የአንድ አገር ኢኮኖሚ፣ ግብርና መር ፖሊሲን ቢያስቀድም ተገቢ ነበር፡፡ ነገር ግን በተበጣጠሰ መሬትና በዝናብ ላይ ጥገኛ የነበረውን የሰብል ልማትም ይሁን የእንስሳት እርባታ ከየት ጀምሮ የት አደረሰው? የሚለው ጥያቄ ግን መልሱ በነበረበት ነው፡፡ ለዘርፉ የተደረጉ ድጋፎችንና የግብዓት አቅርቦቶችን፣ የተመረቱ ምርቶች የገበያ ሒደት፣ ዋጋቸውና የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን መመልከት እንችላለን፡፡ መንግሥታችን ለሰብል ልማቱ ዘመናዊ ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘርና ኬሚካሎች አቅርቧል፡፡ ነገር ግን ላለፉት 25 ዓመታት ገደማ በፓርቲ ድርጅቶቹ ከአቅርቦቱ ረብጣ ገንዘብ በማትረፍ ነበር፡፡ እስከ 2010/2011 ዓ.ም. ድረስ፡፡ የሁለት ዓመታቱ ትርፍ ደግሞ የማዳበሪያ ፋብሪካን አገር ውስጥ የሚያስገነባ ነበር፡፡

ለዝርዝሩ ሪፖርተር ጋዜጣ ባለፈው ዓመት ‹‹ለቀጣዩ ምርት ዘመን 1.5 ሚሊዮን ቶን ማዳበሪያ ያስፈልጋል በተያዘው ሳምንት የማዳበሪያ ግዥ ጨረታ ይወጣል፤›› በሚል ርዕስ በድረ ገጹ ይዞት የወጣው ዘገባ ‹‹. . .ከዚህ ቀደም የማዳበሪያ ግዥ የሚፈጸመው ከገዥው ፓርቲ ጋር ግንኙነት ባላቸው ኢንዶውመንት ትሬዲንግ ኩባንያዎች አማካይነት በመሆኑ፣ የንግድ ሰንሰለቱ ረዥምና መንግሥትን ከፍተኛ ወጪ ሲያስወጣ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ ኮርፖሬሽኑ ይህንን አሠራር በማስቀረት (ቀጥታ ከማዳበሪያ አምራቾች ግዥ በመፈጸም ማለት ነው) 2009 በጀት ዓመት 882 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ኩንታል ማዳበሪያ በዘጠኝ ቢሊዮን ብር ግዥ ፈጽሞ አጠቃላይ የማዳበሪያ ወጪ በ2.6 ቢሊዮን ብር፣ ይህም በአንድ ኩንታል የማዳበሪያ ዋጋ በ500 ብር እንዲቀንስ አድርጓል፤›› ይላል፡፡ ከላይ የንግድ ሰንሰለቱ ረዥምና መንግሥትን ከፍተኛ ወጪ ሲያስወጣ መቆየቱ ይታወሳል ማለት፣ በመንግሥት ፍላጎትና ውሳኔ በተፈጠረ ተጨማሪ የገበያ ሰንሰለት የገዥው ፓርቲ ድርጅቶች ሀብት ሲያካብቱበት የነበረ መሆኑ ይታወሳል ማለት ነው፡፡

በሪፖርተር ባይሽሞነሞን ኖሮ ዘገባው ሲቀጥል በማዳበሪያ ዋጋ ላይ በታየው የዋጋ ቅናሽ (ለገጠሩና ለአርሶ አደሩ የቆመው ልማታዊ መንግሥት ከ25 ዓመታት በኋላ የማዳበሪያ ግዥን ቀጥታ ከአምራቾች ለመግዛት በወሰደው ታሪካዊና ቁርጠኛ አቋም ምክንያት ቢባል ነገሩን ይገልጸዋል)፣ አርሶ አደሮች ደስተኛ መሆናቸውንና የሚጠቀሙትን የማዳበሪያ መጠንም መጨመር እንዳስቻላቸው ገልጸዋል ይላል፡፡ ያላግባብ የበላተኞች ሰለባ ሆኖ አነስተኛ መጠን ማዳበሪያ ለመጠቀም፣ ለዝቅተኛ ምርታማነትና ተጠቃሚነት ታዳርጎ የኖረውን አርሶ አደር ችግር ለማየት የምንችለው እንዲህ እንደ አጋጣሚ ከ25 ዓመታት በኋላ በተደረገ በትክክል በማይገለጽና በሚሽሞነሞን ለውጥ ነው፡፡

ለሰፊው አርሶ አደር ኬሚካሎችና ምርጥ ዘር የሚቀርቡት በተመሳሳይ መንገድ ነበር፡፡ የማይፈልገው ዓይነትና ወቅተ ካለፈ በኋላ መቅረባቸው የሁልጊዜ ዜና ነው፡፡ እስካሁን የማዳበሪያ ፋብሪካ አገር ውስጥ የለም፡፡ አርሶ አደሩ ለማዳበሪያ አቅርቦቱ በየክልሎች የፋይናንስ ተቋማት የብድር አገልግሎት ያገኛል፡፡ ወለዱና አመላለሱ ግን ከአራጣ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ጥናት አያስፈልግም፡፡ አብቁተን፣ አምባሰልንና ባህር ዳር የክልሉን አርሶ አደርና የማዳበሪያን ዕዳ መመልከት በቂ ነው፡፡ ደደቢት፣ ጉና እያሉ መቀጠልም ይቻላል፡፡ መንግሥት በአሥር ሚሊዮኖች ሔክታር የሚቆጠር ለእርሻ የሚውል መሬት አለኝ ብሎ ለውጭ ባለሀብቶች በአሥር ሺዎች ሔክታር የሚቆጠር መሬት ቢሰፍርም ጠብ ያለ ነገር የለም፡፡ የእርሻ መሬቱ የሚገኘው የሕዝብ ቁጥራቸው አነስተኛ በሆኑት በጋምቤላና በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች ሲሆን፣ በእርሻ ሥራ ጥርሱን ከነቀለው የኦሮሚያ፣ የደቡብና የአማራ አርሶ አደር በጥንቃቄ እየተጠበቁ ዘመናት ሊያልፉ ችለዋል፡፡

ጸሐፊው በከተማ የኖረ ከመሆኑ በሻገር በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በእርሻ ኢንቨስትመንት ሥራ ተሰማርቶ ከታዘበ በኋላ አጠቃላይ የግብርናውን ዘርፍ በመከታተል ሲሆን፣ ይህን ጽሑፍ መጻፍ የቻለው ለውጭ አገር ገበያ (ሰሊጥ) እና ለአገር ውስጥ የማምረቻ ኢንዱስትሪ ግብዓት (ጥጥ) የሚሆኑ ምርቶችን በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል አምርቶ የመሬት ፍለጋውን ቢሮክራሲ፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክን የፋይናንስ አቅርቦት፣ የእርሻ ሥራውን፣ እስከ ገበያው ድረስ በተጨባጭ መሬት ላይ በመታዘብ ነው፡፡ ከሰፊው አርሶ አደርም በላይ ለዚህ ዘርፍ የሚቀርብ ምርጥ ዘር የሚደረግ የቴክኒክ ድጋፍ የለም፡፡ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በበጋ ተሰፍሮ በተረከቡት ማሳ ሌላ መሠረተ ልማት ሳይሆን መንገድ ስለሌለው በክረምት ወጥተው መግባት አይችሉም፡፡ ስለዚህ ለአጭር ጊዜም ቢሆን ብዙ የሰው ጉልበት በሚፈልገው ሥራ ከአገሪቱ ሕግ ውጪ በሆነ ልማዳዊ አሠራር ከፍተኛ ሳይሆን ጉድ የሚባል ወጪ ያወጣሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ ምርት ቢያመርቱ በወቅቱ ለገበያ ለማቅረብ በጋውን መጠበቅና ከተመረተው ምርት ዋጋ 25 በመቶ የሚሆን ከፍተኛ የትራንስፖርት ወጪ ይጠበቅበታል፡፡ መንገድ ስለሌለ ብቻ፡፡

የእንስሳት ሀብት ልማታችንም ተመሳሳይ ነው፡፡ አርብቶ አደሩ እንደ ጥንቱ ለከብቶቹ ውኃና መኖን ለመፈለግ የእንስሳቱን ጭራ እየተከተለ ነው፡፡ የከርሰ ምድር ውኃ በልፅጎ ወይም አነስተኛ መስኖዎች ተገንብተው በየአካባቢው ለራሱና ለእንስሳቱ የመጠጥ ውኃ ማግኘት ተፈጥሮ ከምትለግሰው ውጪ፣ ለእንስሳቱ መኖ ማግኘት አልቻለም፡፡ በቋሚ ሥፍራ ላይ ባለመርጋቱ ምክንያት ሌሎች የዘርፉ ግብዓቶችን ውጤታማነት የማይቻል ያደርገዋል፡፡ በዚህ መንገድ የተመረተው ምርት ወደ ገበያ ሲወጣ በላተኛ ነጋዴ ወረዳ ላይ፣ ጅምላ ነጋዴ አዲስ አበባ ከዚያም የግብርና ምርት ላኪዎች ሊደርስ ይችላል፡፡ በዚያው በነበረው መንገድ፡፡ ለውጭ ገበያ የሚቀርበው ሰሊጥና ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚሆነውን ጥጥ ዋጋ የሚወስነው ገበያ ወይም አቅርቦትና ፍላጎት አይደሉም፡፡ አምራቹ ምንም ድርሻ የለውም፡፡ በዶላር ሀራራ መርህ በአምራቹ ላይ ዋጋውን የሚጭኑት ፊታውራሪ ምርት ገበያና ጅንአድ ናቸው፡፡ የየራሳቸውን ካተረፉ በኋላ ሁለቱም ቀጣዮች የላኪዎችና የማምረቻ  ፋብሪካዎች ብቻ ጠበቃ ናቸው፡፡

አገሪቱ ከፍተኛ የእንስሳት ሀብት ቢኖራትም የውጭ ምንዛሪ ገቢው ተጠቃሚ አይደለችም፡፡ ምክንያቱም ከሌሎች በተጨማሪ ብዙው ሀብት የሚገኘው በአገሪቱ ጠረፍ አካባቢዎች ስለሆነና እነዚህ የአገራችን ቁም እንስሳት ለዓለም ገበያ የሚቀርቡት በሱዳንና በሶማሊያ በኩል እንደሆኑ ጥናቶች ስለሚያረጋግጡ፣ የተራዘመው ሕጋዊው የአገራችን የገበያ ሰንሰለትና የመንግሥት አሠራር፣ ግብርና ቀረጥ ጋር ተባብረው እንስሳቱን ወደ ኮንትሮባንድ ሽያጭ ስለሚገፋቸው መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ ሕገወጡ የኮንትሮባንድ ንግድ አደጋና ወጪ አለው፡፡ የኮንትሮባንድ ገበያው አማራጭ የአገር ውስጡን ገበያ የሚያስከነዳ ባይሆን ሕጋዊ መሆንና አገሩን የሚጠላ ሰው አይኖርም፡፡ ይህ ደግሞ ከመንግሥት ቀረጥ እስከ አቀባባይ ነጋዴዎች ትርፍ ድረስ መሆኑን በመረዳት ማስተካከል፣ ከኬላና ከፌዴራል ፖሊስ የድንበር ጥበቃ የተሻለ ዘዴ ነው፡፡

እነዚህ ጥቂት የግብርናው ዘርፍ ምርት ነጋዴዎች ምን እንደሆኑ አንባቢያን ዙሪያውንና ከተሞችን ከአዲስ አበባ ጀምሮ ከተመለከቱ በቂ ሲሆን፣ የአገልግሎት ዘርፉ የአንዱ ተዋናይ ናቸው፡፡ ከሌሎች ጋር ወደፊት በዘርፍ ምሳሌዎችን እናነሳለን፡፡ እንደ ብዙ ባለሙያዎች አቶ ኤርሚያስ በተለይ በደረቅ መሠረተ ልማቶች ግንባታ  (Hard Infrastructure) ምሳሌ ሊሆን የሚችል ሥራ ተሠርቷል ይላሉ፡፡ ትክክል አይመስልም፡፡ ዶ/ር ዓብይ ባደረጓቸው ንግግሮች ላለፉት 27 ዓመታት በአገሪቱ ለግብርናው ዘርፍ የፈሰሰ መዋዕለ ንዋይ፣ የተገነባ መሠረተ ልማት እንደሌለና ዘርፉ በሚገባው መንገድ ዘምኖ ከዝናብ ጥገኝነት እንዳልተላቀቀ አስገንዝበዋል፡፡ ትክክል ናቸው፡፡ ከሁሉም መሠረተ ልማቶች በፊት ለዚህ ዘርፍ ትኩረት ቢደረግና ዛሬ ይህ ዘርፍ በሁለትና ሦስት እጥፍ ቢያድግ ኖሮ፣ ለአገራችን ኢኮኖሚ ዛሬ ሌላ ቀን ነበር፡፡ የአስፋልት መንገድም ይሁን የህዳሴውን ግድብ ጨምሮ ቀድመው የተጀመሩትንና የተገነቡትን፣ ብዙም ውጤታማ መሆን ያልቻሉትን መሠረተ ልማቶች መገንባት ጭንቅ ሳይሆን ቀላል በሆነ ነበር፡፡ ከ85 በመቶ በላይ በግብርና ላይ በተመሠረተና በከፍተኛ ደረጃ ለዘመናዊ ማደበሪያ ጥገኛ ሆኖ ለ27 ዓመታት ለዘለቀ ዘርፍ በውጭ ምንዛሪ ከባህር ማዶ እየገዛ፣ የወደብ ኪራይ እየከፈለ፣ በከፍተኛ የአገር ውስጥ የየብስ ትራንስፖርት ወጪና ረብጣ ገንዘብ እያተረፈ ማዳበሪያ ያቀረበ መንግሥት (የማዳበሪያ አምራቹ ኩባንያ ያለ ለውለታችን የሸለመን ይመስለኛል)፣ የአገሪቱን ሀብት በአስፋልት መንገድ፣ በኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችና የቅንጦት መሠረተ ልማቶች ላይ ቀድሞ ያባከነ መንግሥት፣ በመዲናዋና በከተሞች ለሰማይ ጠቀስ ግንባታ ቅድሚያ የሰጠ መንግሥትና ኢኮኖሚ፣ ልማታዊ መንግሥትና ኢኮኖሚ ነበርኩ፣ ግብርና መር የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነበረኝ ካለ ሸፍጥ ብቻ ነው፡፡

የአገሪቱ የመንግሥትም ይሁን የግል የፋይናንስ ተቋማት፣ ሌሎች የአገልግሎት ዘርፉ ተዋናይዎች ለግብርናው ዘርፍ ባዕድ ሆነው መዝለቃቸውን ዘርፉን እንደ ኮረንቲ በሩቁ ብለው ግን የምርቱና የውጤቱ ጥገኛ ሆነው ስላሉ ብቻ እንደፈለጉ እያተረፉ እስከ ዛሬ መቀጠላቸው ግልጽ ነው፡፡ ይህንን ለማረም ቅድሚያ ሰጥቶ መሥራት ሲገባ፣ ብዙ ሕዝብና ሰፊ መሬት ይዞ የምግብ እህል ከውጭ ገበያ የሚሸምት ኢኮኖሚ ከፍተኛ፣ መዋዕለ ንዋይ በሚፈልግና አነስተኛ የሰው ጉልበት በሚጠቀም የኢንዱስትሪ ዘርፍ የሥራ ዕድል እፈጥራለሁ፣ በዓለም ገበያ ላይ ተወዳድሬ የውጭ ምንዛሪ አስገኛለሁ፣ የኢንዱስትሪ ፓርክ እገነባለሁ ማለት ደግሞ ቀጣይ ሸፍጥ ይሆናል፡፡ ሁሉም መሠረቱ ግን የፊውዳሎች ባህሪ በአዲስ ገጽታ በመቀጠሉ ምክንያት ነው፡፡ የዓለም ቁጥር አንዷ ባለ ሀብትና ቴክኖሎጂ አገር አሜሪካ በውጭ ንግድና ሸፍጡ ከስሬያለሁ እያለች ባለችበት ሁኔታ፣ የእኛን ውጤታማነት ማሰብ ድንቅና ተዓምር ነው፡፡ (ቀሪው ክፍል በሚቀጥለው ሳምንት ይቀጥላል)

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው     [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...