Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርነገረ ኢትዮ ኤርትራ

ነገረ ኢትዮ ኤርትራ

ቀን:

በንጉሥ ወዳጅነው

አሁን በምሥራቅ አፍሪካ በተለይም በኢትዮጵያና በኤርትራ አዲስ ብርሃን ፈንጥቋል፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ አዲስ የተሃድሶና የለውጥ አመራር ከመጣ ያለፉት አራት ወራት ወዲህ፣ በኢትዮ ኤርትራም ሆነ በቀጣናው መቀራረብና መተባበርን ለማምጣት በተጀመረው ዕርምጃ ምክንያት እነሆ ዓለምን ያስገረመ ዕርቅና ይቅር መባባል በይፋ ከመታየቱ ባሻገር፣ ማንም ሦስተኛ ወገን በሌለበት ተፈጽሟል፡፡ በእዚህ ረገድ ዶ/ር ዓብይና የኤርትራ አዛውንት መሪ ኢሳያስ ከሕዝቡም በላይ በተለይ ከነባሩ ግርምት የሞላበት አካሄድ አንፃር ሲመዘን በታሪክ የሚመዘገብ ድንቅ አሻራ አሳርፈዋል (የሌሎች አገሮች መንግሥታት ምሥጋናና ሽልማት እስከመቸር የደረሱትም ለእነሱ መሆኑን ልብ ይሏል)፡፡

ኤርትራ ከተራዘመ የትጥቅ ትግልና እልህ አስጨራሽ የእርስ በርስ ውጊያ በኋላ ከኢትዮጵያ ተነጥላ እንደ አገር ራሷን ያወጣችው ከ27 ዓመታት በፊት ነበር፡፡ ይሁንና ‹‹ሕግደፍ›› (ሕዝባዊ ግንባር ለፍትሕና ዴሞክራሲ) በሚል ምሕፃረ ቃል በሚጠራው ገዥና መሪ ፓርቲ የትጥቅ ትግሉንም የተሳተፈው፣ አሁንም በዚሁ ኃይል እየተመራ የሚገኘው የኤርትራ ሕዝብ በልማት በመልካም አስተዳደርም ሆነ በፍትሕ ወይም ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በመገንባት የተሳካ ጊዜ አሳልፏል ሊባል አይችልም፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ከጎረቤት አገሮች ጋር ጠንካራ ወዳጅነትና ትብብር አለመፍጠሩ ያስከፈለው ዋጋ ቀላል አልነበረም፡፡

በተለይ እንደ አገር ከሁለት አሥርት ዓመታት በፊት ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት ውስጥ ያስገባቸው የድንበር ውዝግብ የሺዎችን ሕይወት ከመቅጠፍ ባሻገር፣ ከሁለት ደሃ አገሮች በቢሊዮን ዶላር የሚገመት ሀብት ነጥቋቸዋል፡፡ ከሁሉ በላይ በዘርና በደም፣ በታሪክና በእምነት ጭምር ዘመናትን ላለፈ ጊዜ የተሳሰረውን የሁለቱን አገሮች ሕዝብ ወንድምና እህታዊ መስተጋብር ክፉኛ አላልቶት ቆይቷል፡፡ አንድ ትውልድ ለሚባል ዘመን ጥላቻና ቂም በቀል ሲቀሰቀስ መክረሙ፣ የፈጠረብን ክፍተትንና መራራቅን በቀላሉ የሚገመት አይደለም። ለእዚህ ሁሉ ክፍተት በዋናነት የኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት ያለፉት 20 ዓመታት ፖሊሲና አካሄድ እንቅፋት የነበረ ሲሆን፣ የኤርትራ መንግሥትም ግትርነት የተሞላበትን ዕርምጃ ለመልቀቅ ተቸግሮ መክረሙ ይታወቃል፡፡

በእዚህ ሒደት ግን ኢትዮጵያዊያንንና ኤርትራዊያንን እንደ መጽሐፍ ቅዱሱ ሙሴ የኤርትራን ባህር በበትር ከፍሎ አርነት የሚያወጣቸው መሪ አልነበራቸውም። እነሆ አሁን ግን ዕድሜ ለአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ብሎም፣ የሰላም ሐሳቡን ለመቀበል ተነሳሽነት ያሳየውና ከረዥሙ ፈተና የተሞላበት ውጣ ውረድ በኋላ የሰላምና የዕርቅ መንፈስ መሻሉን የተገነዘበው የኤርትራ መንግሥት፣ ለሁለቱ አገሮች ሕዝቦች ተስፋ የሚባል ብርሃን ፈንጥቀዋል፡፡

አዲስ የዕርቅና የፍቅር ችቦም በአስመራና አዲስ አበባ በጋራ ለኩሰዋል፡፡ ይህ ዕውን እንዲሆን ጅምሩን ማጠናከርም የሁላችንም ድርሻ መሆን ይኖርበታል፡፡ በተለይ በአገሮቹ ሕዝቦች መካከል አብሮነትን፣ ፍቅርንና ሰላምን የሚያስተምሩና ትብብርን የሚያሳድጉ ማኅበራዊ፣ ባህላዊና ኪነ ጥበባዊ ሥራዎችን ማስቀደም ያስፈልጋል፡፡ በምጣኔ ሀብት ትብብር ረገድም የወጪና የገቢ ምርት አቅርቦትና ፍላጎትን ሕጋዊና ተወዳዳሪ መሠረት በማስያዝ ማቀላጠፍ፣ በቱሪዝምና በድንበር ላይ ግብይት ረገድ ያሉንን ተስፋዎች የመጠቀም ብሎም እንደ ወደብና ትራንስፖርት ባሉት መስኮች ከአገሮቹ ባለፈ የዜጎቹ የሥራ ዕድል እንዲሰፋ መሥራት ለነገ የማይባል ተግባር ሆኖ ይገኛል፡፡ አገሮቹንም በረዥም ጊዜ ወደ ጠንካራ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ውህደት ለማድረስ መሠረት እየጣሉ ለመሄድ አስቸጋሪ አይሆንም፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሁለቱ አገሮች ሰላም ማጣት ምክንያት ተነጣጥለው የቆዩ ቤተሰቦችና ሕዝቦች መገናኘት ችለዋል፡፡ በሚያሳዝን የለቅሶና የደስታ ሲቃ ድብልቅልቅ ስሜት ውስጥ ሆነው በየአገሪቱ ሲተቃቀፉና ሲሳሳሙ ያየነው፣ የፍቅርና የአብሮነት  ተስፋም ብዙዎችን ያስደመመ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ እንኳንስ ለኤርትራዊያን ይቅርና ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በአሜሪካ ባደረጉት ጉብኝት ወቅት፣ ኤርትራዊያን ከኢትዮጵያዊያን ወገኖቻቸው ጎን ቆመው በፍቅርና በአንድነት መንፈስ ውስጥ ሲዋኙ መመልከት የመሪዎች መጥፎም ሆነ በጎ ተግባር በሕዝቦች መነጣጠልና ትብብር ውስጥ ያለውን ስሜት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡ በእርግጥ እስካሁንም ቢሆን የሁለቱ አገሮች አንዳንድ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎችና ወዳጅ አገሮች ይኼን በደም፣ በታሪክ፣ በባህልና አብሮ በመኖር ሊፋቁ የማይችል ትስስር ያለው ሕዝብ ለማቀራረብ ብዙ ጥረት አድርገዋል፡፡ በመንግሥት ደረጃም በተለይ የኢትዮጵያ መንግሥት በስደተኝነት መልክ ወደ አገራችን የሚመጡትን ኤርትራዊያን መጠለያ በመስጠት፣ በየትኛውም የአገራችን ክፍል ተንቀሳቅሰው እንዲኖሩ በመፍቀድና እንደ አገራችን ዜጎች እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ድረስ በነፃ እንዲማሩ በማድረግ በኩል ወገናዊነቱን ማሳየቱ፣ በበጎ ጅምር የሚጠቀስ እንደነበር አይካድም። ያም ሆኖ በመንግሥታት ደረጃ መቀራረብ ባለመፈጠሩ ምሉዕነት ያለው የዕርቅ መንፈስ ሳይታይ ቆይቷል፡፡ መወነጃጀሉም እንደ ቀላል የሚታይ አልነበረም፡፡  

አሁን ካለው የአገራችን ተሃድሶ አዲስ አመራር ባሻገር የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ወንድምና እህት የሆነው የኤርትራ ሕዝብ የውስጥ ስቃይም፣ የሰላም መታወክ እንዲፈታ አንዳንድ ምሁራንንና ወጣቶች (አንዳንዶቹ የዕርቅ አፈላላጊ ነን ብለው ተፍተፍ ሲሉ የነበሩ ባለሀብቶችና ምሁራን አሁን ላይ ድምፃቸው የተሰማ ባይሆንም)፣ አሁን ለተጀመረው ይፋዊ መቀራረብ ቀዳሚ ጥረት አሳይተው ነበር ማለት ስህተት አይመስለንም። ለነገሩ የፖለቲካ ውሳኔ ሰጪነት መዳከም ሆኖ እንጂ፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ  ወደ ሥልጣን በመጡ ጊዜ እስከ አስመራ ሔደው በመደራደር በሁለቱ አገሮች መካከል ዕርቅና መቀራረብ ለመፍጠር እንደሚሠሩ ተናግረው አልነበረም፡፡ ያ ጅምር ቀደም ብሎም በኢትዮጵያ በኩል የነበረውን ፍላጎት አመላካች ቢሆንም ዞሮ ዞሮ በፖለቲካዊ ዲፕሎማሲም ይሁን፣ በፍቅርና ይቅር መባባል የመደመር ፍልስፍና ዕርቁን ለስኬት ያበቃው ይኼው አዲሱ አመራር ነው፡፡ በእዚህ በኩል ታሪክ የማይዘናጋው ተግባር መፈጸሙንም ዕውቅና መስጠት ግድ ይለናል፡፡

ከዓመታት በፊት እውነት የማይመስለው የሁለቱ ሕጎች ዕርቅና ሰላም ዛሬ በሁለቱም አገሮች መሪዎችና ሕዝቦች ሙሉ ፍላጎት ማድረግ ይቻላል፣ ዕውን ሆኗል፡፡  ከእዚያም አልፎ ወደ ሁለንተናዊ ትብብርና መደጋገፍ የሚወሰዱ ዕርምጃዎችም እየተወሰዱ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ያኔ ግን ወንድምና እህት ኤርትራዊያን ወደ አገራችን መምጣታቸውና ከኢትዮጵያዊያን ባልተናነሰ ሁኔታ ለእነርሱ እየተደረገ ያለውን ዕገዛና ድጋፍ ሊተቹና ሊቃወሙ የሞከሩ አንዳንድ ኃይሎችም ነበሩ፡፡ ያም ሆኖ በሁለቱ አገሮች መንግሥታት መካከል አለመግባባቱ ቢኖርም፣ እንኳን በሕዝብ ለሕዝብ መካከል የነበረው የአብሮነት መንፈስ ግን ዛሬ ላይ ለተንቦገቦገው የፍቅርና የሰላም ችቦ መለኮስ ሙቀት የሰጠ ተግባር ነበር፡፡

 የማይካደው እውነት ማንንም ጣመም አስደሰተም፣ አሁን ላይ በይቅር መባባልና ትብብር መንፈስ ቂምና በቀልን በማስቀረት ብሎም የድንበሩን ጉዳይ ወደ ስምምነት በማድረስ የፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ በጎ ግንኙነት ለመፍጠር በሁለቱ አገሮች መካከል የተደረሰበት ትልቅ ዕርምጃ ከፍ ባለ ዋጋ መታየት ያለበት ነው፡፡ ለአገሪቱ ሕዝቦች ብቻ ሳይሆን፣ ለመላው የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና አገሮችም አዲስ የሰላም  ብርሃን የፈነጠቀ ዕርምጃ ተደርጎም መወሰድ አለበት፡፡ (በነገራችን ላይ ከሰሞኑ ኤርትራ ከሶማሊያ መንግሥት ጋር ያደረገችው ድርድርና ኢትዮጵያን ጨምሮ በኤርትራ ላይ የተጣለው ዓለም አቀፍ ማዕቀብ እንዲነሳ መጠየቃቸው የቀጣናዊ ለውጡ ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡)

መንግሥት ለረዥም ጊዜ ኤርትራን በሚመለከት የተከተለው የፖሊሲ አቅጣጫ በአብዛኛው ጠቃሚ የሚባል እንዳልነበር አሁን ግልጽ ሆኗል፡፡ ገና ከወደብ ባለቤትነትና የድንበር ጉዳይ አንስቶ የተወሰዱ ዕርምጃዎችም በርካታ የችግር የዞረ ድምር የተሸከሙ እንደሆነ በብዙ ተነግሯል፡፡ በእዚያ ላይ የተፈጠሩ ችግሮችን እንዲህ እንደ አሁን በሆደ ሰፊነት ከመፍታት ይልቅ፣ አንዱ አገር የሌላውን መንግሥት ተገዳዳሪ በመደገፍ የመጠፋፋት አዙሪት ውስጥ የቆየንበት ጊዜ ክፉኛ የሚያስቆጭ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ አገሮች ያሏቸውን የኢኮኖሚ አማራጮች ጥቅም ላይ አለማዋላቸው አጉል ድንቁርናና ጀብደኝነት የቀፈደደው ድርጊት ነበር፡፡

ያም ሆኖ ሕዝብ ለሕዝብ ያለውን ነገር ባለመሟጠጡና የተበጠሰ ክር ባለመሆኑ፣ ዛሬ መሪዎቹ ወደ ቀልባቸው መምጣት ሲጀምሩ የሰላሙ አየር ከባቢን በብዙ ሲሞላው ታይቷል፡፡ መጪው ትውልድ ሊያስተካክለው በሚችልበት አግባብ የተቃኘ የአንድነት መሠረት ለመጣልም ዕድል ያለ እየመሰለ ነው፡፡ ሒደቱ ግን አሁንም  የሁለቱን አገሮች ወንድምና እህት ሕዝቦች የጋራና ዘላቂ ጥቅምን ሊያስከብር በሚችል ቅኝትና መርህ እንዲመራ ማድረግ የመንግሥታቱና የምሁራን ሚና ሊሆን ይገባል። ላለፉት ሳምንታት እንዳየነው፣ ዛሬ በየአገሮቹ የተገኙ መሪዎችን ለመቀበልና ለማስተናገድ ሕዝቡ በእንባ እየተራጨ በአደባባይ ያሳየው ስሜት ግን ሁለቱን አገሮች ከማለያየት ይልቅ ማቀራረብና ማስታረቅ በእጅጉ የቀለለ ተግባር እንደሆነ ነው፡፡

የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግሥት ችግራቸውን በመነጋገር መፍታትና ለሰላም እጅ መዘርጋት ከሁለቱ አገሮች ሕዝቦች በላይ ለቀጣናውም ትልቅ ዕፎይታን የሚሰጥ መሆኑን ግን ዓለምም መስክሮታል (የአሜሪካ፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት፣ የአፍሪካ ኅብረትና የአንዳንድ የተናጠል አገሮችን መልዕክትና መግለጫ ያስታውሳል)፡፡ ጦረኝነትና ግጭትም ለማንም የማይበጅና የዜሮ ድምር ፖለቲካን የሚያከናንብ መሆኑን መገንዘባቸው ብቻ ሳይሆን፣ ይኼንን በድህነት ተርታ ጠርዝ ላይ የሚገኝ አንድ የነበረ ሕዝብ መታደጋቸውም ይበል የሚያሰኝ ዕርምጃ  ተደርጎ ታይቷል። ስለሆነም ቀጣዩን ጊዜ የበለጠ መተማመንና መደጋገፍ ብሎም የጋራ ተጠቃሚነት በማስፈን መራመድ ግድ የሚል መሆኑን በጥልቀት ማስተዋል ብልህነት ነው፡፡

ከዚህ ባሻገር የኤርትራ መንግሥት የሚነሱበትን አንዳንድ የውስጥና የውጭ ችግሮች መፍታትና ዓለም ይበልጥ እንዲያምነውና አጋር እንዲሆነው ተግቶ መሥራት ይኖርበታል፡፡ ላለፉት 20 ዓመታት የሁለቱ አገሮች የግትርነትና አለመግባባት መጠኑ ቢለያይም፣ ሁለቱም አገሮች በሰብዓዊ መብት አያያዝና በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሲወቀሱ የኖሩ ናቸው፡፡ በተለይ የኤርትራ መንግሥት የሰብዓዊ መብት አያያዝ አስመልክቶ በተለያዩ ወቅቶች በተለያዩ አካላት ጠንከር ያሉ ወቀሳዎች ደርሰውበታል፡፡ ለማዕቀብም ተዳርጎ ቆይቷል፡፡ አሁን ይኼን ገጽታ ለመቀየር የተግባርና የፖሊሲ ለውጥ እንደሚያስፈልገው ጥርጥር ባይኖረውም፣ የጎረቤታሞቹ አገሮች መደጋገፍም የሚያግዘው ነገር እንዳለ ዕሙን ነው፡፡

በእርግጥ የኤርትራ መንግሥት ‹‹የሕዝብህን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በሚዘገንን ሁኔታ ትጥሳለህ፡፡ ተቃዋሚ ዜጎችህን ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በየጎጡ በሠራሃቸው ኮንቴይነሮች ውስጥ አፍነህ ትገድላለህ፡፡ በግርፋት ታሰቃያለህ፡፡ አካል ታጎድላለህ፡፡ ዓይን ታጠፋለህ. . . ወዘተ፤›› መባሉን አጢኖ ለወደፊቱ ከጎረቤት አገሮች ጋር ወዳጅነትና ትብብርን ከመፍጠር ባሻገር ለአገሩ ሕዝቦችም የሚመች ምድር በአዲስ መንፈስ ለመገንባት መነሳሳት አለበት የሚሉ ወገኖቸ ብቅ ብቅ እያሉ ያሉትም ለዚሁ  ነው፡፡ ይኼም ከውስጥ አልፎ ብሎም ለጎረቤት አገሮች ሰላምና ደኅንነት ብሎም ለቀጣናው መለወጥ የጎላ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡

በአጠቃላይ ነገረ ኢትዮ ኤርትራ በፍቅርና በሰላም ብርሃን እየታደሰ መምጣቱ ሰላም ወዳዶችን ሁሉ የሚያስደስት ተግባር ነው፡፡ ያም ሆኖ በሁለቱ አገሮች መንግሥታት መጋጨት የሚጠቀሙ የሚመስላቸው ወገኖች ያልታደሱ የአሮጌው ዘመን ቁማርተኞችና አንዳንድ የወደብና መሰል ጥቅሞችን በብቸኝነት መጠቀም የሚሹ ጥገኛ ኃይሎች ሒደቱን ለማሰናከልም ሆነ ለማጣጣል ደፋ ቀና ማለታቸው አይቀሬ ነው፡፡ እርግጥ በአገራችን ያለው ፖለቲካዊ ለውጥና አዲሱ አመራር ፋታ የለሽ እንቅስቃሴ ውስጥ በመሆኑ፣ እስካሁን የሰላም ሒደቱን የሚያስተጓጉል የጎላ ክፍተት ባይታይም ነገሩን በጥሞና እያጤኑ ለሁለንተናዊ ተጠቃሚነት መገስገስ የሚያስፈልግ ይሆናል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው  [email protected]  ማግኘት ይቻላል፡፡       

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...