Sunday, June 16, 2024

የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ጉዳይ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ባለፉት ሦስት ዓመታት በኢትዮጵያ ያጋጠመው ከፍተኛ አመፅና የፖለቲካ አለመረጋጋት የሰዎችን ሕይወት ከመቅጠፍና ንብረት ከማውደም ባለፈ፣ በኢኮኖሚው ላይ ያደረሰው ጉዳት ባይለካም እጅግ ከፍተኛ እንደነበረ መገመት አይከብድም፡፡ በተለይ በየዓመቱ እየተዳከመ የመጣው የወጪ ንግድ ግኝት ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት ከፍተኛ መቀዛቀዝ ማሳየቱ የሚታወስ ሲሆን፣ ከሬሚታንስም (ሐዋላ) ሆነ ከወጪ ንግድ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ግኝቱ እጅግ ተዳክሟል፡፡ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ በገጠመው ችግር ሳቢያ ሕይወት አድን መድኃኒቶች ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት እስከማይቻልበት ደረጃ ደርሶ ከፍተኛ መሰናክል ፈጥሯል፡፡

የወጪ ንግድን በማበረታታት የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ያሳድጋል በሚል እሳቤም መንግሥት የብርን የመግዛት አቅም በ15 በመቶ እንዲዳከም ማድረጉ የሚታወስ ነው፡፡ ይሁንና ይህ አከራካሪ መፍትሕ እምብዛም ለውጥ አምጥቷል ለማለት የሚያስደፍር ክስተት እንደሌለ የሚከራከሩ ጥቂት አይደሉም፡፡

በአገሪቱ የተንሰራፋውን አመፅና ብጥብጥ ተከትሎም ዳያስፖራው ወገናችን እየተገደለ ወደ ኢትዮጵያ ገንዘብ አንልክም የሚል ዘመቻ በማድረግና መንግሥትን ለማዳከም በማለም፣ በቀጥተኛ መንገድ ገንዘብ እንዳይላክ ሲቀሰቅስ ቆይቷል፡፡ በዚህም ምክንያት በባንክና በጥቁር ገበያ መካከል ከዚህ ቀደም ታይቶ የማያውቅ ከፍተኛ የሆነ ልዩነት ሊፈጠር ችሏል፡፡

ይሁንና ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከተሰየሙ በኋላ በወሰዷቸው የውጭ ምንዛሪ ማግኛ ዕርምጃዎች፣ የውጭ ምንዛሪ በእጃቸው የሚገኙ ሰዎች ገንዘባቸውን ወደ ባንክ እንዲወስዱ የሰጡትን ማሳሰቢያ ተከትሎ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦቱ በመጠኑም ቢሆን መሻሻል አሳይቷል፡፡ በባንክና በጥቁር ገበያ መካከል የነበረው የሰፋ ልዩነት ሣንቲም ቤት ድረስ ወረዶ ነበር፡፡ ይሁንና ይህ ብዙም ሳይቆይ በጥቁር ገበያ ለውጥ መታየት ጀምሯል፡፡

የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ችግር ያገናዘበና ፈጠራ የታከለበት የተባለለት የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ እንዲቋቋም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባቀረቡት ጥሪና በወሰዱት ተነሳሽነት፣ ፈንዱን የማቋቋም እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ ዳያስፖራው ለትረስት ፈንዱ የሚያደርገውን አስተዋፅኦ በገንዘብ እንዲደግፍ ‹‹የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ›› በሚባል ስያሜ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተከፍቶ ገንዘብ እየተጠራቀመ ይገኛል፡፡

የዚህ ትረስት ፈንድ ጠንሳሽ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ዳያስፖራው በአገሩ የሚኖረው ኢኮኖሚያዊም ሆነ ፖለቲካዊ ተሳትፎ እንዲያድግ በተደጋጋሚ ጥሪ ሲያቀርቡ የነበረ ሲሆን፣ በተለይ ዳያስፖራው ለአገሩ ከማኪያቶ ላይ አንድ ዶላር በቀን ቀንሶ እንዲሰጥ የሚል ሐሳብ ለመጀመርያ ጊዜ የተነሳው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን በያዙ በሁለተኛው ሳምንት ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር ባደረጉት ስብሰባ ላይ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር በውጭ በተለይም በዱባይና በቻይና ገንዘባቸውን ያጠራቀሙ ሰዎች ዶላራቸውን እንዲያመጡ አሳስበው፣ ‹‹ኮንትሮባንድ ሌላው ወሳኝ ችግር ነው፡፡ ኮንትሮባንድ ማለት የዕቃ ብቻ አይደለም፡፡ የዶላር ኮንትሮባንድ አለ፡፡ እነዚህ ሁሉ ተደምረው ነው የውጭ ምንዛሪ የሚባለው እንጂ፣ እናንተ እንደምትሉት የብሔራዊ ባንክ መመርያ ብቻ አይደለም፤›› ሲሉም የዶላር ግኝት ችግር ምንጭን አስረድተዋል፡፡

በወቅቱ ባደረጉት ንግግርም ዳያስፖራው መንግሥትን በሠልፍና በጽሑፍ እንዲቆነጥጥና በሬሚታንስ እንዳይጎዳ በማለት ጥሪ አቅርበው ነበር፡፡

ይኼንን ሐሳብ ይበልጥ ለመግፋት ከዳያስፖራው ጋር በቀጥታ ተገናኝተው ለመወያየት ከሐምሌ 21 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ለስድስት ቀናት በአሜሪካ ሦስት ከተሞች ጉብኝት አድርገው ነበር፡፡ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ፣ ሎስ አንጀለስና ሚኒሶታ መድረኮች የተዘጋጁ ሲሆን፣ በመድረኮቹ ጎልተው ከተነሱ ነጥቦች አንዲ ይህ የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ነው፡፡ በአሜሪካ የሚኖሩና በሥፍራው መገኘት የቻሉ የአውሮፓና የካናዳ ነዋሪዎች የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ለማድረግ ቃል ገብተዋል፡፡

በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ በነበረው መድረክ ላይ የተገኘውና አጭር ንግግር ያደረገው ታማኝ በየነ፣ አንድ ዶላር ቢጠየቅም ሌሎችንም በማስተባበር አሥር ዶላር በቀን በማሰባሰብ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ ለመላክ ቃል ገብቷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበድር ዓለም አቀፍ ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር የፈንዱን ጠቀሜት በእጅጉ ያጎሉ ሲሆን፣ ‹‹በቀን አንድ ዶላር ለምኛችኋለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ዓይነ ሥውራን እስካሁን ማስተማር የቻልነው አራት ፐርሰንት ብቻ ነው፡፡ ለእኔ አትርዱኝ፡፡ ረዳት ያጡ ዓይነ ሥውራንን አስተምሩ፤›› ብለዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ መሠረት በርካታ ዳያስፖራ ኢትዮጵያውያን አስተዋፅኦ ለማድረግ ከፍተኛ ተነሳሽነት በማሳየታቸውም፣ በንግድ ባንክ በተከፈተውና የሒሳብ ቁጥሩም 1000255726725 በሆነ የፈንዱ ማጠራቀሚያ ገንዘብ ማጠራቀም ተጀምሯል፡፡ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአካውንት ዳይሬክቶሬት የተገኘ መረጃ እንደሚያመላክተው፣ ሐምሌ 11 ቀን 2010 ዓ.ም. በባንኩ የቀድሞ ፕሬዚዳንትና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥና ዋና ኢኮኖሚስት አቶ በቃሉ ዘለቀ በተፈረመ ደብዳቤ አካውንቱ መከፈቱ ታውቋል፡፡ አካውንቱም በውጭ ምንዛሪ ገንዘብ የሚጠራቀምበት ሲሆን፣ ለጊዜው ገንዘቡ የማይንቀሳቀስ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ይሁንና ብሔራዊ ባንክ በቀጣይ በሚሰጠው ውክልና መሠረት ፈንዱን የሚያቀሳቅሰውን አካል ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲያስታውቅ፣ ፈንዱ የሚንቀሳቀስ እንደሆነም ታውቋል፡፡

በዚህ የሒሳብ ቁጥር ገንዘብ ማጠራቀም የሚፈልጉ የዳያስፖራው አባላት ከባንኩ ጋር በትብብር ከሚሠሩ 762 በላይ ባንኮች በተሳሰሩበት የባንኩ የስዊፍት አድራሻ “CBETETAA”፣ አልያም ከባንኩ ጋር በውል የሚሠሩ 20 የሐዋላ አስተላላፊ ድርጅቶችን በመጠቀም ገንዘብ ማጠራቀም እንደሚችም ተነግሯል፡፡

‹‹የእኛ ሚና ሒሳብ መክፈትና ገቢ የሚሰበሰብበትን መንገድ ማመቻቸት ብቻ ነው፣›› ሲሉ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ በልሁ ታከለ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

የዚህ የዳያስፖራ ፈንድ መቋቋሙን የሚቃወሙ ባይኖሩም፣ አስተዳደራዊ የሆኑ ጥያቄዎች መልስ ሳያገኙና ሕጋዊ ሰውነት ያለው ተቋም ሳይመሠረት ገንዘብ መሰብሰብ መጀመሩን የሚያጠይቁ በርካታ ባለሙያዎችና የዳያስፖራው አባላት አሉ፡፡

የሕግ ባለሙያ የሆኑትና በተለይ በሲቪል ማኅበረሰብ ሕግ ላይ ትኩረት የሚደርጉት አቶ ቁምላቸው ዳኜ እንደሚሉት፣ ይኼንን ዓይነት ተቋም ለመመሥረት የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ በአገሪቱ እስካሁን የለም፡፡ ‹‹ነገር ግን የአደራ በጎ አድራጎት ድርጅት›› ማቋቋምን የሚደግፍ ድንጋጌ በበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት አዋጅ ላይ እንዳለ ይጠቅሳሉ፡፡ ይሁንና ትረስት ፈንዱ በዚህኛው የሕግ ድንጋጌ ሊሸፈን የሚችል እንዳልሆነም ያስረዳሉ፡፡

‹‹የዚህኛው ባህርይ ይለያል፣ እንደ ሕዝባዊ መዋጮ ዓይነት ባህርይም ይታይበታል፤›› ሲሉም ይገልጻሉ፡፡ ስለዚህም የዳያስፖራ አካውንቱ ተከፍቶ ገንዘብ መጠራቀሙ የሕግ ማዕቀፉ ሳይበጅና ተቋማዊ ሳይደረግ መሆኑ አግባብነቱ ላይ እንደሚያጠያይቅም ይናገራሉ፡፡

‹‹ቀደም ብሎ የሕግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ ቢሆን መልካም ነበር፡፡ አካውንቱ የተከፈተው በመንግሥት ነውና ያላግባብ ጥቅም ላይ የመዋል ዕድሉ ጠባብ ነው ሊባል ቢችልም፣ ሥርዓት ሊበጅለት ግን ይገባል፤›› ይላሉ፡፡

ነገር ግን የዳያስፖራ ፈንዱ የመንግሥት ተነሳሽነት ስላለበት፣ ካሁን በኋላም ሕግ ማውጣትና መተግበር እንደሚቻልም ያስረዳሉ፡፡

የትረስት ፈንዱ በቦርድ እንደሚመራ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢናገሩም፣ አካውንቱ ተከፍቶ ተቋማዊ አደረጃጀቱ ግን የተጓተተ የመሆኑን ምክንያታዊነት የሚጠይቁ አሉ፡፡

ነዋሪነታቸውን በለንደን ያደረጉት የፋይናንስ ባለሙያውና የፋይናንስ ዘርፍ ተንታኙ አቶ አብዱልመናን መሐመድ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መጠይቅ፣ ትረስት ፈንዱ መቼ ነው የተቋቋመው? አባላቱ እነማን ናቸው? በማንስ ተመረጡ? የቦርድ አባላቱ እነማን ናቸው? የሥራ አስፈጻሚዎቹስ? የውጭ ኦዲተርስ ተሹሞለታል ወይ? የመተዳደሪያ ደንቡንስ ከየት አግኝተን ማየት እንችላለን? ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡

በሌላ ወገን ደግሞ ለዚህ ትረስት ፈንድ ገንዘብ የሚያዋጡት ግለሰቦች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ካላቸው ፍቅር እንጂ፣ በጉዳዩ አምነው ስላልሆነ ቀጣይነት ላይኖረው ይችላል የሚሉም አሉ፡፡ ስለዚህ ለዳያስፖራ ፈንዱ ግልጽነትና ተጠያቂነት የታከለበት አሠራር እስካልተዋቀረ ድረስ ሊቋቋም አይገባውም በማለት ይከራከራሉ፡፡ ለዚህም ከመንግሥት ዋስትና ይሻሉ፡፡

በትረስት ፈንዱ አካውንት ገንዘብ ያስገቡ ማርቆስ ፈለቀ (ዶ/ር) የሚባሉ ሐኪም በትዊተር ገጻቸው ላይ እ.ኤ.አ. የ2018 ግዴታቸውን 365 ዶላር ማስገባታቸውን ይፋ ሲያደርጉ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ልዩ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍፁም አረጋ በትዊተር ገጻቸው በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹በርካታ አጋሮች የትረስት ፈንዱ አካውንት ይፋ ከተደረገ ጊዜ አንስቶ በደስታ ምላሻቸውን ሲያሳዩ ተስተውሏል፡፡ በድጋሚ ማሳወቅ የምንፈልገው ነፃ በሆነ፣ በግልጽነትና አጋሮቻችንን በማያስቀይም መንገድ ጥቅም ላይ እንደሚውል ነው፡፡ ይኼንንም በሚመለከት ተከታታይ ማብራሪያ እንሰጣለን፤›› ብለዋል፡፡

ዳያስፖራው በአገሩ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ሁኔታ ላይ ብቁ መረጃ እንደሌለው በመግለጽ፣ የተሻለ ቅርበት ያላቸው አካላት የማሳወቅ ግዴታቸውንም እንዲወጡ ጥሪ የሚያቀርቡ አሉ፡፡ የተሻለ እውቀት እንዲኖርም የትረስት ፈንዱ ማቋቋሚያ የሕግ ማዕቀፎች ሲዘጋጁ ለትችት እንዲረዱ ይፋ መሆን እንዳለባቸውም ይጠይቃሉ፡፡

የሲነርጎስ አማካሪዎች ቀጣናዊ ዳይሬክተር አቶ አበራ ቶላ የትረስት ፈንዱ መቋቋም በአገሪቱ ፖሊሲና በተግባር መካከል ያለውን ክፍተት ለመሙላት የሚያግዝ ነው ይላሉ፡፡

‹‹መንግሥት ሀብት ያልመደበባቸው ሥፍራዎች በተለይም የፖሊሲ አካል ያልሆኑትና ብዙ ርቀት መጓዝ የሚጠይቁ የአካል ጉዳተኝነት ጉዳዮች ምላሽ እንዲያገኙ ያግዛል፤›› ይላሉ፡፡ ‹‹የተዘነጉ ናቸውና እነዚህን አካል ጉዳተኞች ከቴክኖሎጂ ጋር ለማዋሀድም ይረዳል፤›› ሲሉም ያክላሉ፡፡

እንደ አቶ አበራ ምልከታ፣ ዋናው ጉዳይ በትኩረት እየታቀደና ዲዛይን እየተደረገ ነው ወይ የሚሄደው የሚለው መታየት አለበት፡፡ ‹‹አንድ ጊዜ የመጣ ገንዘብ በርካታ ሥራ ሊሠራ ስለሚችል የዘላቂነት ጥያቄ ግን አይኖርበትም፤›› ብለዋል፡፡

ከዳያስፖራ ፈንዱ ጋር በተገናኘ ጥያቄ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ በውጭ አገሮች የገንዘብ ማሰባሰብ ሥራዎችን ለማከናወን፣ የሕግና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን ማጤን ነው፡፡

ይህም በተለይ ሥጋት የሆነባቸው ግለሰቦች የሚጠቅሱት፣ ኢትዮጵያ ለህዳሴ ግድቡ ቦንድ በአሜሪካ በመሸጧ መቀጣቷን በማስታወስ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የመሸጫ ፈቃድ ሳታገኝ የሸጠችው ቦንድ ተመላሽ እንዲደረግና የስድስት ሚሊዮን ዶላር ቅጣት እንዲጣልባት ተደርጎ ነበር፡፡

‹‹ትረስት ፈንዱን ለማቋቋም የሚወጣው ሕግ ይኼንን ጉዳይ በግልጽ ማስቀመጥ ይጠበቅበታል፡፡ በውጭ አገሮች እንደዚህ ዓይነት ድርጊቶችን ሪፖርት የማድረግ ግዴታና ገደብ ስለሚኖር መጤን አለበት፡፡ ፈንድ መቋቋሙን በተመለከተ ሪፖርት ማድረግ ሊያስፈልግም ይችላል፤›› ሲሉ የሕግ ባለሙያው አቶ ቁምላቸው ያሳስባሉ፡፡

ካሁን ቀደም በኢትዮጵያ የዳያስፖራ ፈንድ ባይሆንም፣ የተለያዩ የትረስት ፈንዶችን የማቋቋም እንቅስቃሴዎች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል ተጠቃሽ የሆነው የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣንን ለማቋቋም ቅድመ ዝግጅቶችን እያደረገ የሚገኘው የቅርስ መንከባከቢያ ትረስት ፈንድ ነው፡፡

ይህ ፈንድ በተቋሙ የቅርስ እንክብካቤና ጥበቃ መምርያ ኃላፊነት እየተጠና የሚገኘው ትረስት ፈንድ ኮሚቴ ተዋቅሮ፣ የውጭ አገርና የአገር ውስጥ ፈንድ የማሰባሰብ ተሞክሮዎችን በመቀመር የሕግ ማዕቀፍ ለማዘጋጀት እየሠራ እንደሚገኝ፣ የመምርያው ኃላፊ አቶ ኃይሉ ዘለቀ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

የዚህ ትረስት ፈንድ ማቋቋሚያ አዋጅ በ2011 በጀት ዓመት የመጀመርያው ሩብ ዓመት ተጠናቅቆ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና በተለያዩ የሚመለከታቸው አካላት ከተገመገመ በኋላ፣ ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ተልኮ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ይሁንታን አግኝቶ በፓርላማ አዋጁ እንደሚፀድቅ አቶ ኃይሉ ተናግረዋል፡፡

በአገሪቱ የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ጨምሮ ሌሎች ትረስት ፈንዶችን የማቋቋም እንቅስቃሴዎች ስላሉ፣ በተለይ ልምዶችን ከአፍሪካ በመቀመር ሕጉን እንዲያዘጋጅ ኮሚቴ መዋቀሩንም አቶ ኃይሉ ገልጸዋል፡፡

የዳያስፖራ ትረስት ፈንድን በተመለከተ የዳያስፖራው መነቃቃት ሳይቀዛቀዝ፣ በፍጥነት ወደ ተግባር መገባት እንዳለበት አቶ አበራ ያሳስባሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -