ከሰሞኑ በኬንያ በሚካሄደው የመካከለኛውና የደቡባዊ አፍሪካ አገሮች የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) የምርምር ፎረም ላይ የቀረቡ ጥናቶች ኢትዮጵያን ጨምሮ አምስት አገሮች የ17.5 ቢሊዮን ዶላር የወጪ ንግድ ዕምቅ አቅም እንዳላቸው አመላክቷል፡፡
የኮሜሳ ሴክሬታሪያት ለሪፖርተር በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ኬንያ በምታስተናግደው አምስተኛው የኮሜሳ የምርምር ፎረም ላይ ይፋ የተደረጉ የምርምር ውጤቶች ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ሱዳን፣ ሊቢያና ግብፅ በኮሜሳ አባል አገሮች መካከል በሚደረግ የእርስ በርስ የንግድ ልውውጥ ከፍተኛ ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉ አገሮች ተብለዋል፡፡
ጥናቱን ያከናወኑት በዚምባብዌ የንግድ፣ የኢንዱስትሪና የኢተርፕራይዝ ልማት ሚኒስቴር ውስጥ ዋና የኢኮኖሚ ባለሙያና ተመራማሪው ሚስተር አዳም ዊሊን የጠቀሰው መግለጫው፣ በዝቅተኛው ግምት መሠረት በተወሰደው የትንበያ ጥናት መሠረት የዲጂታል ንግድ ፋሲሊቴሽን ዕርምጃዎች በእነዚህ አገሮች ውስጥ በአግባቡ ቢተገበሩ ከ17.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ የወጪ ንግድ ገቢ በቀጣናው ለማስመዝገብ ያስችላቸዋል፡፡
የዲጂታል ንግድ ፋሲሊቴሽን በሰነድ መመዝገብና መካሄድ የሚጠበቅባቸውን የንግድ አሠራሮች በዲጂታል ሥርዓት በማገዝ ውጤታማ የንግድ ልውውጥ እንዲካሄድ በማድረግ የንግዱ ማኅበረሰብ ብቻም ሳይሆን መንግሥታትም ከፍተኛውን ጠቀሜታ እንደሚያርፉበት የኢኮኖሚ ባለሙያው ገልጸዋል፡፡
ምንም እንኳ በዲጂታል የንግድ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ቢሠሩ ውጤታማነታቸው ከፍተኛ እንደሚሆን የተነገረላቸው እነ ኢትዮጵያ፣ በተግባር እንዲህ ያለውን የንግድ ሥርዓት እየተገበሩ በሚገኙት እነ ኬንያ፣ ማዳጋስካር፣ ሞውሪሺስና ሩዋንዳ ብልጫው ተወስዶባቸዋል፡፡ እነዚህ አገሮች ከፍተኛ የተቀላጠፈ የዲጂታል የንግድ አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ ውጤት ያገኙ ተብለዋል፡፡ የኤሌክትሮኒክ የንግድ እንቅስቃሴን በመተግበር እንደ እነኢትዮጵያ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ ይችላሉ ተብለው ከተለዩት የኮሜሳ አገሮች ውስጥ ኮሞሮስ፣ ዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ ጂቡቲ፣ ማላዊ፣ ስዋዚላንድ፣ ሲሼልስ፣ ኡጋንዳ፣ ዛምቢያ፣ እንዲሁም ዚምባብዌ ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ አገሮች በመካከለኛ ደረጃ ሊመዘን የሚችል የኤሌክትሮኒክ ንግድ አገልግሎትን መተግበር የጀመሩ ተብለዋል፡፡
እንዲህ ያለውን የተቀላጠፈ የንግድ ልውውጥ በአባል አገሮች መካከል እንዲስፋፋ የሚወተውተው ኮሜሳ፣ ከአካዴሚው፣ ከፖሊሲ አማካሪዎች፣ ከመንግሥትና ከግሉ ዘርፍ፣ እንዲሁም ከዓለም አቀፍ ተቋማት የተውጣጡ ከ60 በላይ ባለሙያዎች በሚሳተፉበት የአምስት ቀናት የፎረሙ ቆይታ ወቅት በርካታ ንግድ ነክ የምርምር ጽሑፎች እንደሚቀርቡበት አስታውቋል፡፡ ከ88 የምርምር ጽሑፎች ውስጥ ምርጥ የተባሉትን 11 ጽሑፎች እንደሚገምግም ይጠበቃል፡፡
እ.ኤ.አ. በ1994 የምሥራቅና የደቡባዊ አገሮች የጋራ ገበያን ለመፍጠር የተመሠረተው ኮሜሳ፣ በአሁኑ ወቅት ከ20 በላይ አገሮችን በአባልነት ያካተተ የቀጣናው የንግድና የኢኮኖሚ ተቋም ነው፡፡ እነዚህ አገሮች ከ660 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት ኢኮኖሚ መጠን ያላቸው (ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አንፃር)፣ ከ490 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የሚገኝባቸው፣ የወጪና ገቢ ንግድ መጠናቸው እስከ 300 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት አገሮች የተሰባሰቡት ይህ ተቋም፣ ዋና መሥሪያ ቤቱን በዛምቢያ በማድረግ እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ አንጋፋ የጋራ የንግድና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመፍጠር የሚንቀሳቀስ ነው፡፡