Monday, June 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ሠራተኞች በዕርከን ምደባና በአስተዳደራዊ ጉዳዮች እንደተበደሉ ገለጹ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኮርፖሬሽኑ በትምህርት ዝግጅት ማነስ በሚፈልጉበት ቦታ ያልተመደቡ ሠራተኞች እንዳሉ ይገልጻል

አራት የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን በማዋሃድ ከሦስት ዓመታት በፊት እንደ አዲስ የተመሠረተው የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ሠራተኞች፣ በተቋሙ የተካሄው የሥራ ምደባን ጨምሮ በበርካታ የአስተዳደራዊ ችግሮች በደል እንደደረሰባቸው እንደሚገኙ አስታወቁ፡፡ ኮርፖሬሽኑ የቀረበበትን ቅሬታ አስተባብሏል፡፡

በጽሑፍ ባቀረቡት ቅሬታም ሆነ ስማቸው እንዳይገለጽባቸው በጠየቁ የኮርፖሬሽኑ ሠራተኞች የቀረበው አቤቱታ እንደሚያስረዳው፣ በተቋሙ አዲስ መዋቅር ተግባራዊ መደረጉን ተከትሎ አዳዲስ የሥራ ምደባዎች ተካሂደዋል፡፡ ይሁንና፣ ‹‹በአዲሱ መዋቅር መሠረት ተገቢው ሠራተኛም ሆነ የሥራ መሪ በተገቢው የሥራ መደብ ላይ መመደብ ሲገባው፣ ለአስተዳደሩ ታማኝ በሆኑ፣ በትውውቅ፣ ቅርበት ባላቸውና የጥቅም ተጋሪ በሆኑ ሠራተኞች የሥራ መደቡ ከሚጠይቀው መሥፈርት በታች በአድሏዊነት ምድባው ተካሂዷል፤›› ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡

ሠራተኞቹ ከደመወዝ ባሻገር ተገቢው የሥራ መደብ ለተገቢው ሠራተኛ መሰጠት ሲገባው፣ ይህ አልሆነም ያሉ ሲሆን፣ ‹‹ቀደም ሲል ይህን ያህል ታገኝ ነበር፡፡ አሁን ግን ይህን ያህል ደመወዝ ስለጨመርንልህ አርፈህ ሥራህን ሥራ፤›› የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸውና እንዲህ ያሉ ማሸማቀቂያዎች እየተሰነዘሩባቸው እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ እንዲህ ያሉ ጫናዎች እንደበረቱባቸው የሚናገሩት ሠራተኞቹ፣ ለኮርፖሬሽኑ አስተዳደር ያቀረቧቸው ጥያቄዎች ምላሽ ባለማግኘታቸው ‹‹መብት ይጠየቃል እንጂ አይለመንም፤›› በሚል መነሻ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት፣ አንዳንዶቹም ሥራቸውን እስከመልቀቀል እንዳደረሳቸው ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ባለን የትምህርት ዝግጅትና የሥራ ልምድ መሠረት ፍትሐዊ የሥራ ምደባ ይሰጠን የሚሉት የኮርፖሬሽኑ ሠራተኞች፣ ከዚህ ቀደም የተካሄደው ምደባ ዳግም በፍትሐዊነትና ግልጽነት በሰፈነበት መንገድ እንዲካሄድ መጠየቃቸውም ተሰምቷል፡፡

ከዚህ ባሻገር የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን የ2010 በጀት ዓመት ዕቅድን በሚመለከት ሠራተኛውም ስለዕቅዱ አተገባበር ገለጻ ሳይደረግለትና ሳይወያይበት በማኔጅመንቱ ውሳኔ ፀድቆ ሲተገበር መቆየቱን የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፣ ኮርፖሬሽኑ የስድስት ወራትም ሆነ የዘጠኝ ወራት የአፈጻጸም ሪፖርቶችን በማዘጋጀት ከሠራተኛው ጋር አለማወያየቱም የግልጽነትና የአሳታፊነት ችግሮች የሚታዩበት ተቋም እንደሆነ በመግለጽ ተችተዋል፡፡

 ከሠራተኞቹ የተወጣጡ ተወካዮችም እንዲህ ያሉትን ቅሬታዎች የተካተቱበትን ደብዳቤ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላትና ኮርፖሬሽኑን ለሚከታተለው የንግድ ሚኒስቴር ማሳወቃቸውን ለመረዳት ተችሏል፡፡

በሠራተኞቹ የቀረበበትን አቤቱታዎች በሚመለከት ምላሽ እንዲሰጥባቸው ከሪፖርተር ጥያቄ የቀረበለት ኮርፖሬሽኑ በኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት በኩል አስተባብሏል፡፡ የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ እቴነሽ ገብረ ሚካኤል ለሪፖርተር በሰጡት ምላሽ፣ የቀበረው አቤቱታ በአብዛኛው መነሻው በልማት ድርጅቱ ከተካሄደው የሥራ ምደባ ጋር የሚያያዝ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ ኮርፖሬሽኑን በሚመጥን መሥፈርት መሠረት በወጣው የሥራ መደብ ተገቢው የትምህርት ደረጃ ያላቸው ሠራተኞች መመደባቸውን የገለጹት ኃላፊዋ፣ ምንም እንኳ አንዳንድ ነባር ሠራተኞች በተቀመጠው የትምህርት ደረጃ መሠረት ማሟላት ያልቻሉት ምደባ ቢኖርም በዚህ ሰበብ ከሥራ ገበታው የተቀነሰ ሠራተኛ እንደሌለ አክለዋል፡፡ ይልቁንም አዲሱ የሥራ ምደባ ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት ሠራተኛው ለምደባ ምን ማሟላት እንደሚጠበቅበት፣ ፎርም እንዴት እንደሚሞላ፣ የትምህርት ደረጃውና የሥራ ልምዱ በሚፈቅድለት የሥራ መደብ ላይ ለመመደብ ማሟላት የሚጠበቅበት መሥፈርት ምን እንደሆነ ገለጻም፣ ሥልጠናም እንደተሰጠ አብራርተዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ አትራፊ መንግሥታዊ ድርጅት እንደመሆኑ መጠን፣ ተወዳድሮና ገበያውን መስሎ ለመገኘት ብቃቱ ያላቸው ሠራተኞች ያስፈልጉታል ያሉት ወ/ሮ እቴነሽ፣ ሠራተኞች በሚያቀርቡት መጠን አስተዳደራዊ ችግሮች እንደሌሉበት አስተባብለዋል፡፡ ኮርፖሬሽኑ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ካሉት ነባር ሠራተኞች በቀር ከውጭ ቅጥር አለመፈጸሙን፣ ይሁንና በአዲሱ የሥራ ድልድል መሠረት ነባር ሠራተኞቹ ማሟላት ያልቻሏቸውን የሥራ መደቦች በውጭ ቅጥር ለማሟላት የሥራ ማስታወቂያ ማውጣቱን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በ2010 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ላይ ውይይት ሳይደረግ መታለፉን በሚመለከት ለተነሳው ቅሬታ፣ ምንም እንኳ ሠራተኛው በጅምላ ተሰብስቦ የሥራ አፈጻጸሙን እንዲገመግም አይደረግ እንጂ፣ በየሥራ ዘርፉ እንዲወያይበት መደረጉን፣ የሥራ አፈጻጸም ብቻም ሳይሆን፣ ዕቅድ ዝግጅት ሲደረግ ጀምሮም አስቀድሞ ከሠራተኛው ጋር ውይይት ተደርጓል ያሉት ወ/ሮ እቴነሽ፣ ዕቅዱና አፈጻጸሙ ምን እንደሚመስል ውይይት ተደርጎና ኮርፖሬሽኑ ተጠሪ ለሆነበት ንግድ ሚኒስቴርም ቀርቦ ውይይት እንደተደረገበት ተጠቅሷል፡፡

እንዲህ ያሉ ቅሬታዎች እየቀረቡበት የሚገኘው የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን፣ በዚህ ዓመት ስላገኘው ገቢም ሆነ ስላስመዘገባቸው የንግድ እንቅስቃሴዎች የሚገልጹ መረጃዎች በቅርቡ ተጠናቅረው ይፋ እንደሚደረጉ አስታውቆ፣ በሠራተኞች የሚቀርበው ቅሬታ ግን ሙሉ በሙሉ ትክክለኛውን እውነታ እንዳልሆነ ሞግቷል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በሚቋቋሙበት አዋጅ ቁጥር 25/1984፣ በሚኒስትሮች ደንብ ቁጥር 369/2008 በታኅሳስ 2008 ዓ.ም. መመሥረቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ኮርፖሬሽኑ ሲቋቋም አለ በጅምላ የተሰኘውን የንግድ ድርጅት፣ አንጋፋውን የእህል ንግድ ድርጅት፣ የኢትዮጵያ ፍራፍሬና አትክልት አክሲዮን ማኅበር (ኢትፍሩት)፣ እንዲሁም የግዥ አገልግሎት ድርጅት የተሰኙ አራት የልማት ድርጅቶችን አካቶ የተቋቋመ ነው፡፡

ኮርፖሬሽኑ 11 የንግድ ማዕከላት፣ 64 የእህልና የቡና ንግድ ማዕከላት፣ 19 የመሠረታዊ ሸቀጦች፣ የፍራፍሬና አትክልት የጅምላ መሸጫ መደብሮች፣ 105 የኢትፍሩት ችርቻሮ መሸጫዎች፣ እንዲሁም ሰባት የእጅ በእጅ ሽያጭ ማካሄጃ የአለ በጅምላ መደብሮችን የሚያስተዳድር ነው፡፡ ኮርፖሬሽኑ አራት ቢሊዮን ብር በሚጠጋ የተከፈለ ካፒታል የተመሠረተ ሲሆን፣ 2000 ያህል ሠራተኞችን በቋሚነት፣ እንዲሁም 500 ገደማ ጊዜያዊ ሠራተኞችን እንደሚያስተዳድር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች