Friday, May 24, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

‹‹በቅርብ ቀን›› ለሕገወጦችና ለሙሰኞች የወጣች ፀሐይ እንዳትሆን

በቻላቸው ደስ

ቀናት ቀናትን እየወለዱ ወራት በዓመታት እየተተኩ ስድስት የተባሉት ወራት ሁለት ዓመት ከስድስት ወራት አስቆጠሩ፡፡ በእነዚህ ጊዜያት በርካታ ኢትዮጵያውያን ደንበር ተሻግረው ደኅንነታቸው፣ ክብራቸውና ጥቅማቸው ሳይከበርላቸው በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ዜጎች ከድጡ ወደ ማጡ ወደሚባል የስደት፣ የባርነትና የስቃይ ሕይወት መሻገራቸውን መስማት የዕለት ተዕለት ዜናችን ሆኗል፡፡

የውጭ ሥራ ሥምሪት ሕጋዊ ዕውቅና ከማግኘቱ በፊት ተገቢው ቁጥጥር ሳይደረግበት ለረዥም ጊዜ በዘፈቀደ ሲሠራበት የቆየ ነው፡፡ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ፀድቆ የዜጎች የመንቀሳቀስና ሌሎች ሰብዓዊ መብቶች ሕጋዊ ዕውቅና ካገኙ በኋላ፣ መንግሥት ሕገ መንግሥቱን ለማስፈጸም የሚረዱ ዝርዝር ሕጎችን ለማውጣት በሚንቀሳቀስበት ወቅት፣ የውጭ ሥራ ሥምሪቱ ተገቢውን ትኩረት አግኝቶ ለመጀመርያ ጊዜ ዘርፉን የሚቆጣጠር አዋጅ በ1990 ዓ.ም. ታውጆ ተግባራዊ ሆኗል፡፡ ይህ አዋጅ በሥራ ላይ በቆየበት ጊዜ የታዩትን ክፍተቶች ለመሙላትና ዘርፉን በተጠናከረ ሁኔታ መምራት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣ አዋጁ ሥራና ሠራተኛ የማገናኘት አገልግሎት አዋጅ ቁጥር 632/2001 ተተክቶ ሲያገለግል ከቆየ በኃላ ዘርፉ ለሁለት ዓመት ከአራት ወራት ታግዶ ቆይቷል፡፡ በቅርቡም በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተሻሽሎ ፀድቋል፡፡

ምንም እንኳ ለስድስት ወራት ብቻ በሚል መግለጫ የታገደው ይህ የሥራ ዘርፍ በርካቶችን ለከፋ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ሥነ ልቦናዊ ችግሮች አጋልጦ በመጨረሻ ከሁለት ዓመታት በኋላ ቢፀድቅም፣ የዜጎችንና የመንግሥትን የመተማመን፣ ቃል የማክበርና የአፈጻጸም ችግሮች በተግባርም በዘርፉ ላይ ያለውን የዕውቀት ማነስና የመልካም አስተዳደር ዕጦት አጉልቶ ያሳየ እንደሆነ አምናለሁ፡፡

አዋጅ ቁጥር 632/2001 መንግሥታዊና የግል የሥራና አሠሪ ኤጀንሲ በሥራ ሥምሪት አገልግሎት አሰጣጥ የሚኖራቸውን ሚና በሕግ መወሰን አስፈልጓል፡፡ በተለይም ወደ ውጭ አገር ለሥራ የሚሄዱ ኢትዮጵያውያን መብታቸው፣ ደኅንነታቸውና ክብራቸው ተጠብቆ ባላቸው ችሎታና አቅም በይበልጥ የሚሠሩበትን ሁኔታ ማመቻቸትም አስፈልጓል፡፡ በዚህም ሥራና ሠራተኛ በማገናኘት ሥራ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሥራ ሥምሪት ላይ የሚደረገውን ክትትልና ቁጥጥር አሠራር ሥርዓት ለማጠናከር በማሰብ መውጣቱ ቢገለጽም፣ አዲሱ አዋጅ በራሱ ያለበት ክፍተት የትናንቱን፣ የዛሬውንና የነገውን ፍላጎት አላገናዘበም፡፡ በክፍተቶች ታጅቦ በሥራ ላይ እንዲውል ውሳኔ አግኝቶ በሥራ ላይ ለመዋል በቅርብ ቀን የሚል የመመርያ ጥበቃ ሽር ጉድ ተያይዟል፡፡

ይህንን ያህል ጊዜ እንኳ ፈጅቶ ለውይይት የቀረበ ቢሆንም፣ በውስጡ አደረጋቸው የተባሉት ማሻሻያዎች እንደተባለው  የግል ሥራና ሠራተኞች ኤጀንሲዎችን ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ የሕግ ክፍተት የመድፈን፣ የዜጎችን ክብር፣ ደኅንነትና መብት የማስጠበቅ፣ ኤጀንሲዎችም  ከሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር የተፈራረሙትን ውል ተግባራዊ የማድረግ፣ ዜጎች ለሥራ ከሚሄዱባቸው አገሮች ጋር የተጠናከረ ግንኙነት ለመመሥረትና ነባሩን የዲፕሎማሲ ግንኙትን ለመፈተሽ፣ የኢትዮጵያ ኤምባሲና ቆንስላ ጽሕፈት ቤቶች ለሥራ ወደ ውጭ አገር የሄዱ ዜጎችን ከመጠበቅ አኳያ እያደረጉ ያሉትን እንቅስቃሴ ለማሻሻል፣ እንዲሁም በሕጋዊ መንገድ ፈቃድ ወስደው የሚሠሩ ኤጀንሲዎች ከሕገወጥ ደላሎች ጋር በመቀናጀት እየሠሩ መሆኑ ስለተደረሰበት  በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ማሻሻያ ለማድረግ ይሁን እንጂ፣  አሁንም ምላሽ ያላገኙ በርካታ ጉዳዮች ከመኖራቸውም በላይ አሁንም ለሕገወጦች የሚከፍተው በር የሰፋ መሆኑን እየተመለከትን ነው፡፡

በቅርብ ቀን እየተባለ ከሁለት ዓመት ከስድስት ወራት በላይ አስመዝግቦ ወደ ሕግነት የተለወጠው አዋጅ አሁንም በቅርብ ቀን ጠብቁ የተባለውን መመርያ ለማውጣት ፋሽን በሚመስል ‹በቅርብ ቀን እንመጣለን› የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫዎች ተሰላችተን፣ በየቀኑ የስደት ስቃይና ዋይታ መስማትን ልምድ አድርገነዋል፡፡ እህቶቻችን በየቀኑ እየደረሰባቸው የሚገኘውን ችግር ቤተሰብ በችግርና በድህነቱ ላይ ተጨማሪ መራራ እንዲጋት ማድረግ ለዘርፉ መሪዎች፣ ደላሎች፣ አስፈጻሚ አካላትና አንዳንድ ኤጀንሲዎች ምንም የመሰላቸው አይመስልም፡፡   እስከ ዛሬ ድህነትን እናሸንፋለን ብለው ወጥተው ወደ ቤታቸው ሳይመለሱ የቀሩ እህቶቻችንንና የእናቶቻቸውን እንባ በአላየንም አልሰማንም ዓይነት ምላሽ ማለፍን ምርጫቸው አድርገዋል፡፡  

በዘርፉ ውስብስብነት ምክንያት ምን ያህል ሕገወጦችና ኪራይ ሰብሳቢዎች ተደራጅተውና ተቀናጅተው እንደሚንቀሳቀሱ ለመመልከት ሩቅ መሄድ አያስፈልግም፡፡ ምንም እንኳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ መሠረት ከጥቅምት 15 ቀን 2006 ዓ.ም. ጀምሮ   ለሥራ ወደ ውጭ በተለይም መካከለኛው ምሥራቅ መጓዝ የተከለከለ ቢሆንም፣ በየቀኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዕድሜአቸው ለአቅመ ሔዋን ያልደረሱ ሴቶችን ጨምሮ ጉዟቸውን የሚያደርጉት በቦሌ ኢንተርናሽናል ኤርፖርት መሆኑ ብቻ በቂ ይመስለኛል፡፡

በዚህ ሒደት ውስጥም የመንግሥት ሹማምንት ሳይቀሩ በገንዘብ እየተመሳጠሩ የሕገወጥ ኤጀንሲዎችና የደላላዎችን የተቀናጀ ተሳትፎ መመልከት ይቻላል፡፡ ከዚህም እልፍ ሲል የወገንን ለቅሶ ወደጎን በማለት ገንዘብ ብቻ ለማግኘት አፀያፊ በሆነው የሰው ልጅ  ንግድ ላይ  በጎረቤት አገሮች ቢሮ በመክፈት ተሰማርተው የሚገኙ አንዳንድ ሕገወጥ ኤጀንሲዎችንም መመልከት የችግሩን ግዙፍነት ያሳየናል፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቆ ‹መመርያውን በቅርብ ቀን› የሚል ነጋሪት እየጠበቀ በሚገኘው አዲሱ አዋጅም እነዚህን ሕገወጦችና በጥቅም የተሳሰሩ ኪራይ ሰብሳቢዎችን ሳስብ፣ በተለይም ደግሞ አዋጁ ለማንኛውም ሥራ የሠለጠነና ክህሎት ያለው ሠራተኛ መኖር ዘርፉን ከማሳደጉ በላይ የተሻለ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማስገኘት ዓይነተኛ መንገድ  መሆኑ እሙን ነው፡፡ በቤት ሠራተኝነት ለመሥራት ፍላጎት ያላት (ከአሁን በፊት ልምድ ይኑራት አይኑራትም) ግለሰብ ቢያንስ የስምንተኛ ክፍል ትምህርት ማጠናቀቅና የሙያ ምዘና ፈተና ማለፍ እንዳለባት ማስቀመጡ፣ የዜጎችን ተንቀሳቅሶ የመሥራት ሕገ መንግሥታዊ የሥራ ዋስትና የሚጋራ ነው፡፡ የትምህርት ደረጃን ግዴታ አድርጎ ማስቀመጥ ውጤቱ ዜጎችን ለሕገወጥ አዘዋዋሪዎችና ለቀን በላተኞች ሲሳይ ጀባ የሚደርግ መንገድ እንደከፈተ ዕምነቴ ነው፡፡

ከሁሉም በላይ ግን አሁንም በመመርያ ማውጣት ሰበብ የሚባክነው ጊዜና አደረጃጀትን በተመለከተ እየተሠራ ያለው ነገር ግልጽ አለመሆኑ ያሳስባል፡፡ በሕጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱት ኤጀንሲዎች ለከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውስ ከማጋለጥ ጋር ተያይዞ ትኩረት ተሰጥቶበት፣ በተጠናከረና በተደራጀ መንገድ በፍጥነት መፍትሔ መስጠት ካልተቻለ ውጤቱ መልካም አይሆንም፡፡ ዘርፉ የታገደበትን ዓላማ ማለትም የዜጎችን ክብር፣ ደኅንነትና ጥቅም የማስከበር ጉዳይ ወደ ጎን ተብሎ ‹‹በቅርብ ቀን›› የምትለው ነጋሪት ለሕገወጦችና ለኪራይ ሰብሳቢዎች የወጣች ፀሐይ መሆኗ አይቀርም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው   [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles