Saturday, May 18, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ወባን ከኢትዮጵያ የማጥፋት ሥራው ተጀምሯል ግን አልተጠናቀቀም

በአምባሳደር ፓትሪሺያ ሃስላክ     

ባለፉት 15 ዓመታት ከሰሐራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገሮች የወባን ማዕበል ከመግታት አኳያ ታሪካዊ ስኬቶችን አስመዝግበዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃም ወባን ከመቆጣጠር አኳያ የተገኘው ውጤት የማያሻማ ነው፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት በወባ ሊጠፋ ይችል የነበረ 6.2 ሚሊዮን ሕይወት መትረፉን አመልክቷል፡፡

ከ1997 ዓ.ም. ወዲህ የኢትዮጵያ መንግሥት ከተለያዩ ማኅበረሰቦች፣ ለጋሾችና ከሌሎች አጋሮች ጋር በመሆን ባደረገው ጥረት ወባን ጨምሮ በተለያዩ በሽታዎች የሚመጣን ሞት መቀነስ ችሏል፡፡ በዚህም ዕድሜአቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆነ ሕፃናት የመሞት ዕድል በ28 በመቶ ዝቅ ሊል ችሏል፡፡

ሚያዝያ 17 ቀን ዓለም አቀፉን የወባ ቀን ስናስብ፣ ይህንን ስኬት እናወሳለን፡፡ አሜሪካ በዓለማችን ዙሪያ በጤና ላይ የሚሠሩ ሥራዎችን በመደገፍ ግንባር ቀደም ለጋሽ አገር እንደመሆኗ፣ ከአጋሮቿ ጋር ተቀራርባ በመሥራት ሰዎችን እጅግ ከባድ ከሆነው የወባ በሽታ ጫና ለማላቀቅ ከፍተኛ ቁርጠኝነት አላት፡፡

ሁላችንም የገባነውን ቃል ማደስ ይኖርብናል፡፡ አሁንም በዓለም ዙሪያ በየዓመቱ በዚህ በሕክምና ሊድን በሚችለውና ልንከላከለው በምንችለው በሽታ ከ430,000 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ሕይወታቸውን ያጣሉ፡፡ ከእነዚህም 90 በመቶ የሚሆኑት ከሰሐራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገሮች የሚገኙ ሲሆን፣ አብዛኛዎቹ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆነ ሕፃናት ናቸው፡፡ በየሁለት ደቂቃው አንድ ሕፃን ለሞት ይዳረጋል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ አንድን ሰው በተደጋጋሚ ለሕመም በሚዳርገው በወባ በሽታም ሚሊዮኖች በመሰቃየት ላይ ይገኛሉ፡፡ በአፍሪካ ከግማሽ በላይ ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሰ ሕፃናት በወባ በሽታ ምክንያት ትምህርታቸውን መከታተል አይችሉም፡፡ በጤና ወጪ ረገድም እነዚህ አገሮች በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ያወጣሉ፡፡ ምርታማነታቸውም ይቀንሳል፡፡

 የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ወባን የመከላከል ውጥን ይህንን በሽታ ለመዋጋት ቁልፍ አጋር መሆኑን ቀጥሏል፡፡ ውጥኑ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰሐራ በታች ለሚገኙ 19 አገሮች ድጋፍ በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ የፕሬዚዳንቱ ወባን የመከላከል ውጥን ለረጅም ጊዜ አገልግሎት ላይ የሚውሉ በፀረ-ትንኝ ኬሚካል የተነከሩ አጎበሮችን፣ ፀረ-ተባይ ኬሚካሎችን የመርጨት ዘመቻን፣ አርቲሚሲኒን-ተኮር የሆነ ጥምር መድኃኒቶችን ያካተተ ሕክምናን፣ በእርግዝና ወቅት ወባን በመከላከል ላይ ያተኮረ ሕክምናን፣ እንዲሁም ማኅበረሰቡን በማስተማር የተለያዩ ሥልቶችን አቀናጅቶ ይጠቀማል፡፡

በኢትዮጵያ የፕሬዚዳንቱ ወባን የመከላከል ውጥን ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ ከብሔራዊ የወባ መቆጣጠሪያ መርሐ ግብር፣ እንዲሁም እንደ ኤቢቲ አሶሼትስና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሕፃናት መርጃ ድርጅት ጋር በመቀናጀት ለረጅም ጊዜ አገልግሎት ላይ የሚውሉ በፀረ-ትንኝ ኬሚካል የተነከሩ አጎበሮች በስፋት እንዲዳረሱና ወረርሽኙ በተስፋፋባቸው አካባቢዎች በሚገኙ ሁሉም አባወራዎች የኬሚካል መርጨት ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ በኬሚካል የተነከረው አጎበርና የኬሚካሉ ርጭት ሰዎች በወባ እንዳይያዙም ሆነ በሽታው ከሰው ወደ ሰው እንዳይተላለፍ ከማድረግ አኳያ ከፍተኛ ጠቀሜታ አላቸው፡፡

የበሽታው ጫና በሚበረታባቸው አካባቢዎች በሚገኙ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውና የጤና አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ተደራሽነታቸው ውስን በሆኑባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ አባወራዎች ላይ በማተኮር፣ ፍትሐዊ አገልግሎት የሚሰጥበትን ሁኔታ እናመቻቻለን፡፡

ከዚህም ሌላ የፕሬዚዳንቱ ወባን የመከላከል ውጥን የሕክምና ባለሙያዎችና የማኅበረሰብ ጤና ባለሙያዎች ለወባ ታካሚዎች እንዴት ሕክምና መስጠትና እንክብካቤ ማድረግ እንዳለባቸው ሥልጠና ይሰጣል፡፡ መንግሥታት በየአገራቸው የሚደረጉ ወባን የመግታት እንቅስቃሴዎችን ይመሩ ዘንድም ያግዛል፡፡

ባሳለፍነው የአውሮፓውያን ዓመት ብቻ የፕሬዚዳንቱ ወባን የመከላከል ውጥን ቤት ለቤት በተደረገ የኬሚካልና የፀረ-ተባይ ርጭት የ1.6 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንን ሕይወት መታደግ ችሏል፡፡ 17.9 ሚሊዮን ለረጅም ጊዜ አገልግሎት ላይ የሚውሉ በፀረ-ትንኝ ኬሚካል የተነከሩ አጎበሮችን፣ 12.3 ሚሊዮን የወባ መድኃኒቶችን፣ እንዲሁም ከ3.2 ሚሊዮን በላይ ፈጣን ምርመራ ለማካሄድ የሚያገለግሉ መሣሪያዎችን አቅርበናል፡፡ በዚሁ ዓመትም የፕሬዚዳንቱ ወባን የመከላከል ውጥን 2,300 የጤና ባለሙያዎች የወባ ታማሚዎች አያያዝን የሚመለከት ሥልጠና እንዲወስዱ ድጋፍ ሰጥቷል፡፡

ይኼ ሁሉ ተዳምሮ ውጤት ያመጣል፡፡ ይሁንና አሁንም ብዙ ሥራ ይጠብቀናል፡፡ በተለይም ጨቅላ ሕፃናትና ነፍሰጡር እናቶች በወባ እንዳይጠቁ የመከላከል ሥራውን ይበልጥ ማጠናከር ይኖርብናል፡፡ በእርግዝና ወቅት ወባ በእናትና በልጇ ላይ ለሕይወት አሥጊ የሆኑ ጉዳቶችን ሊያደርስ ይችላል፡፡ ከእነዚህም መካከል በነፍሰጡር እናቶች ላይ የሚከሰት የደም ማነስ ችግር፣ ውርጃ፣ ከመደበኛው ጊዜ ቀድሞ መውለድ፣ ሞቶ የሚወለድ ሕፃንና ከተለመደው የክብደት መጠን በታች ሆኖ መወለድ ይገኙባቸዋል፡፡

ለነፍሰጡር እናቶች በቅድመ-ወሊድ ክትትል ወቅት የሚሰጥ ጉዳት የሌለውና ውጤታማ የሆነ ሕክምና ያለ ሲሆን፣ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት ላይ የሚውሉ በፀረ-ትንኝ ኬሚካል የተነከሩ አጎበሮችን መጠቀምም በጣም አስፈላጊ ነው፡፡

በተለይም በድህነት ውስጥ ላሉ ዜጎች የጤና አገልግሎቶችን ተደራሽነት መጨመር በርካታ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች አለው፡፡ በበርካታ አገሮች የጤና ባለሙያዎች በወባና ሌሎች ሕፃናትን በሚያጠቁ በሽታዎች ዙሪያ ሥልጠና እንዲወስዱ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶች ተተግብረው፣ በተለይም ዝቅተኛ የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ያለባቸው ማኅበረሰቦች የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኙ ሁኔታዎች እንዲሻሻሉ ተደርጓል፡፡

የወደፊቱ የአገሪቱ የማኅበረሰብ ጤና አደጋ ተጋርጦበታል፡፡ የወባ በሽታ የሚፈጥረውን ጫና መቀነስ አልያም ሙሉ በሙሉ ማስወገድ የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማረጋገጥም ሆነ ከትምህርት ገበታ መቅረትን፣ ድህነትን ከመዋጋት፣ የፆታ እኩልነትን ከማረጋገጥና የእናቶችንና የሕፃናትን ጤና ከማረጋገጥ አንፃር የሚኖረው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡

በዓለማችን ላይ ያሉ ያደጉ አገሮች በታዳጊ አገሮች ያለውን የወባ ችግር ለማስወገድ የሚደረገው የገንዘብ ዕርዳታ ሊተኮርበት የሚገባ መሆኑን ተገንዝበዋል፡፡ በዚህም መሠረት የወባ ክስተትን በ50 በመቶ ለመቀነስ  የሚወጣው አንድ ዶላር የ36 ዶላር ኢኮኖሚያዊ ትርፍ እንደሚያስገኝ ተመልክቷል፡፡ ሌላኛው ጥናት እንዳመለከተው ደግሞ ወባን ከምድረ-ገጽ ማጥፋት የሁለት ትሪሊዮን ዶላር ኢኮሚያዊ ጠቀሜታና የ11 ሚሊዮን ሰዎችን ሕይወት ይታደጋል፡፡

በሚቀጥሉት ከሦስት እስከ አምስት ዓመታት በዚህ ረገድ በኢትዮጵያና በሌሎች ወባ በተንሰራፋባቸው አገሮች የሚመዘገበው ስኬት ወባን ከምድረ-ገጽ ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ የተያዘውን የረጅም ጊዜ ግብ ለመምታት ወሳኝ ድርሻ ይኖረዋል፡፡ ይህንን ክፉ ወረርሽኝ ከዓለማችን ላይ ማስወገድ ስንችል በሚሊዮን የሚቆጠር ሕይወትን እንታደጋለን፡፡ በትሪሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ትርፍ ማግኘትም እንችላለን፡፡

በዚህ አጋጣሚ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ የአገሪቱ ክልሎች ያሉ ማኅበረሰቦችን በመርዳት ረገድ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኙ አቻዎቼንና ባልደረቦቼን ለማመስገን እወዳለሁ፡፡ ወባን ከምድረ-ገጽ ለማጥፋት የሚደረገው ትግል ግቡን እንዲመታ የእናንተ ጥረት በእጅጉ ወሳኝ ነው፡፡ ይህ ለብቻችን ልናሳካው የምንችለው አይደለም፡፡ እንደ ለጋሽ የምንሰጠው ገንዘብም ግቦቻችንን ለማሳካት በቂ አይደለም፡፡ ይህንን ክፍተት ለመሙላት ከግሉ ዘርፍ ጋር በመቀናጀት አዳዲስ የገንዘብ ድጋፍ የምናቀርብባቸውን መንገዶች ማሰብ ይኖርብናል፡፡ ወባን ለአንዴና ለመጨረሻ ከኢትዮጵያና ከመላው ዓለም ለማጥፋት እንችል ዘንድ አጋሮቻችን፣ የንግዱ ማኅበረሰብ፣ እንዲሁም መላው ኅብረተሰብ በጋራ ጥረት እንዲያደርጉ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡ እንደ ወባ ያለን ክፉ በሽታ ማስወገድ ትክክለኛና ወቅታዊ ዕርምጃ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊዋ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡ 

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles