‹‹ፋሲካ መጣ ገበታው ቀና አለ!›› የሚሉት ሸካዎች ናቸው፡፡ በየዓመቱ የሚከበረው የፋሲካ በዓል ሲመጣላቸው በቋንቋቸው ‹‹ማዲካም›› ይሉታል፡፡
ማዲካም በቀጥተኛ ትርጉሙ ቀና ያለ ገበቴ ማለት ሲሆን በጾሙ ወቅት ተከድነውና ተሰቅለው የቆዩ የምግብ ዕቃዎች ታጥበውና ፀድተው ለምግብ የሚዘጋጁበት፣ ፋሲካ መጣ ገበታው ቀና አለ ማለት እንደሆነ ድርሳናት ያመለክታሉ፡፡
የዘንድሮ ፋሲካ ሚያዝያ 23 ቀን 2008 ዓ.ም. ላይ ውሏል፡፡ በዓሉ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ የተለያዩ አገሮች የሚገኙ ኦርቶዶክሳውያን ኤርትራና ግብፅን ጨምሮ፣ እንዲሁም በምሥራቅ አውሮፓና በአሜሪካ ባሉት ኦርቶዶክሳውያን እየተከበረ ነው፡፡
ምዕራባውያኑና ተከታዮቻቸው በሚከተሉት ጎርጎርዮሳዊ የዘመን አቆጣጠር መሠረት ከአንድ ወር በፊት ፋሲካቸውን ማክበራቸው ይታወሳል፡፡
- በዓሉ ሲገለጥ
በዓሉ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች መሠረተ እምነቱን ይዘው እንደየባህላቸው ያከብሩታል፡፡ ከነዚህ አንዱ የሆኑት በደቡብ ክልል ሸካ ዞን የሚገኙት ሸከቾዎች ፋሲካን በራሳቸው ባህላዊ መለያ ያከብሩታል፡፡ በዓሉ ሐሙስ የሚጀምር ሲሆን ዕለቱ ‹‹ዳጲ ማዮ ማዮ›› ይባላል፡፡ ይህም የንፍሮ ቀን ማለት ሲሆን፣ ቀኑን በጾም በማሳለፍ ወደማታ የሚበላው ምግብ ንፍሮ ብቻ ነው፡፡ የስቅለት ቀን የሚባለው ዓርብ ‹‹አኪላቶስ›› ሲባል በዚህ ቀን በተለይ እናቶች ቀኑን በልዩ ሁኔታ ያከብሩታል፡፡ እናቶች ጠንካራ የፈትል ገመድ አዘጋጅተው የሁለቱን እጃቸውን ክንድ ባንድ ላይ የኋሊት በማሰር ይውላሉ፡፡ ወደማታ ሲሆን እጃቸውን ከፈቱ በኋላ በሠፈሩ ያሉ ሴቶች በኅብረት ‹‹ዮዲ›› በሚባል በደንና በዕፅዋት በተከበበና በተከበረ ቦታ በመሰባሰብ ቅጠል አንጥፈው ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ዘለግ ባለ ድምፀትና ተመስጦ ‹‹እቶማራማራ እቶስ›› ‹‹ዮሻ ዮሻ ኢቶስ›› እያሉ ለረዥም ሰዓታት ይሰግዳሉ፡፡ ‹‹መሐሪ የሆነው ክርስቶስ ተይዞ ለሞት ተሰጠ›› የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን፣ በየሁሉም ሠፈር የሚከናወነው ስግደት በድምቀት ከሠፈር ሠፈር የሚሰማ ነው፡፡ ስለሸካቾ ብሔረሰብ የሚያወሳ አንድ ድርሳን እንደሚያመለክተው፣ ‹‹በስቅለት ዕለት (ዓርብ) ምዕመናኑ ሙሉ ቀን ጹመው ‹የሺ-ቅቶሶች›ን ይለምናሉ፡፡ ‹የሺ-ቅቶሶች› ማለት ከሥረ መሠረቱ ከእኛ ጋር ያለን ጌታ፤ ተይዞ ለእኛ የተሰቀለው፤ ለእኛ ብሎ የሞተ፤…›› የሚለውን ቃል ያመለክታል፡፡ በተጨማሪም የጸሎት አዝማቹ ‹‹እቶ ማራማራ እቶስ!›› የሚለውም የክርስቶስ ተከታዮችን ያመለክታል፡፡
እሑድ ፋሲካ ወይም የዋናው ማዲካም ዕለት በመሆኑ ከብት ይታረዳል፤ እናቶች ገሪግዮ በሚባል ጎምዛዛ ቅጠል አፋቸውን አራት ጊዜ ‹‹ጮሚበቾ›› በማለት ካበሱ በኋላ መመገብ ይጀምራሉ፡፡
ሸከቾች በዓመት ውስጥ ካሉት ወራት የሦስቱን ስያሜ በተለይ ከሁዳዴና ፋሲካ ጋር ያያይዙታል፡፡ የካቲት፡- ‹‹መዴጉፓ›› የሁዳዴ ጾም በየካቲት ወር ስለሚጀምር፣ እስካሁን በቅበላ ቆይተሃልና ገበታህን አጥበህ ድፋው ወይም ጾም ጀምር የሚል አንድምታ ያለው ነው፡፡ መጋቢት፡- ‹‹ገኤውቆ›› የጾም እኩሌታ የሚደርስበት ወር በመሆኑ በርታ እንደማለት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር የደብረዘይት በዓል የሚከበርበት መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ሚያዝያ፡- ‹‹መካሞ›› ጾም ልትፈታ ነው፡፡ ስለዚህ ተደፍቶ (ተቀምጦ) የከረመውን ገጽታህን ቀና አድርገህ ጾምህን ፍታ፣ የፋሲካ በዓልን አክብር ማለት ነው፡፡ በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎችም አከባበሩ ጉልህ ይሆናል፡፡
ከትንሣኤ በፊት ያሉት ሰሙነ ሕማማትና ዓርብ ስቅለት በተለይ በጾምና በስግደት የሚከበሩ ናቸው፡፡ በወይራ ቅጠል ጥብጠባ በማሳረጊያው ይደረጋል፡፡ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትውፊትና ሥርዓት መሠረት ከሆሳዕና ሰኞ (እሑድ ሌሊት) እስከ ጸሎተ ሐሙስ ያሉት ቀናት ከክርስቶስ ልደት በፊት የነበሩትን 5500 ዓመታት (አምስት ተኩል ቀናት) “የዓመተ ፍዳ” መታሰቢያ ሆነው ተሠርተዋል፡፡
- ምግብ
በእሑድ ፋሲካ ዋዜማ ቀዳም ሥዑር (ቅዳሜ ሹር) ቄጠማ እየታደለ “ገብረ ሰላመ በመስቀሉ ወአግሀደ ትንሣኤሁ” (በመስቀሉ ሰላምን አደረገ፤ ትንሣኤውም ግልጽ ሆነ) ተብሎ ይከበራል፡፡ ምሽት ላይ ምእመናን ወደየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያናቸው ጧፍና ሻማ በመያዝ በምሥራቹና በሥርዓተ ቅዳሴው ለመካፈል የሚጓዙበት ነው፡፡ እስከ መንፈቀ ሌሊት ይቆያሉ፤ በፋሲካ ሌሊት የምሥራቹን ጧፍና ሻማ በመለኮስ በቤተ መቅደሱ ዙሪያ የሚደረገው ዑደት “ትንሣኤከ ለእለ አመነ ብርሃነከ ፈኑ ዲቤነ” (ትንሣኤህን ላመንን ለእኛ ብርሃንህን ላክልን) በሚለው ዝማሬ የታጀበ ነው፡፡ ዶሮ ሲጮህ ይፈስካሉ፤ ለምእመናኑ በመንፈሳዊ እርሻ የተመሰለው ሁዳዴው ሲጀመር
“ጀግናው ዐቢይ ጾም ቢታይ ብቅ ብሎ፣
ቅቤ ፈረጠጠ አገር ርስቱን ጥሎ”
ተብሎ በቃል ግጥም የታጀበው ጾም ሲፈታ፣ በተለይ ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት ላይ ከቅባት የተለየው አካል እንዳይጎዳ ልዩ ምግብ ይዘጋጅለታል፡፡ ማለስለሻ እንዲሆን ተልባ ይቀርባል፡፡ በጸሎተ ሐሙስም ለየት ያለ የምግብ ባህል አለ፡፡ ጸዋሚዎቹ ጉልባንና ንፍሮ ቀምሰው እስከ ትንሣኤ ሌሊት ሳይመገቡ ያከፍላሉ፡፡ ጉልባን ባቄላ፣ ስንዴና ጥራጥሬ ተቀላቅሎበት የሚዘጋጅ የምግብ አይነት ነው፡፡ ዓርብ ስቅለት ከስግደት መልስም ጉልባን ይበላል፡፡ የሐዘን መግለጫ ሆኖ ተወክሏል፡፡
እንደየኅብረተሰቡ ባህል የፋሲካ ድፎ ዳቦ፣ ዶሮ ዳቦ፣ ኅብስት፣ የዶሮ ወጥ እንቁላል፣ የዕርድ ከብቶችን ማዘጋጀት ጠጅና ጠላ መጠጥ ማዘጋጀት የክብረ በዓሉ አንዱ ገጽታ ነው፡፡ ከመልካም ምኞቱ እንኳን አደረሳችሁ፣ ጾመ ልጓሙን እንኳን ፈታልዎ በአነጋገር ደረጃ የሚጠቀስ ነው፡፡ ከርቀትም ሆነ ከቅርበት ያሉ ቤተሰቦች የሚሰባሰቡበት ስጦታ ሙክት፣ ድፎ ዳቦና መጠጦች የሚለዋወጡበትም ነው፡፡
- ብሒሎቹ
ፋሲካ ላይ ትኩረት የሚያደርጉ ብሒሎችም አሉ፡፡
ፋሲካን ሊያገኙ ሁዳዴን ይመኙ፤
ሳይጾሙ ፋሲካ፣ ሳያዝኑ ደስታ የለም፤
ፋሲካ የሌለው ጦም፣ ደስታ የሌለው ዓለም፤
ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ዓመታዊው ግን ተዘዋዋሪው የፋሲካ (ትንሣኤ) በዓል በመጣ ቁጥር እየተፈጠሩ ካለፉት ሥነቃሎች አንዱና በቆሎ ተማሪዎች ዘንድ በኅብረ ዝማሬ ይቀርብ የነበረው እዚህ ላይ ይታወሳል፡፡
‹‹ሰኞ መከሩ፣ ማክሰኞ ዘከሩ
ሮብ ዶለቱ፣ ሐሙስ አገቱ
ዓርብሳ ሰቀሉታ፣
እሑድሳ
እንጣጥ ብሎ ተነሣ
ጌታዬ አንበሳ፡፡››
- የፋሲካ ቀመር
የፋሲካ (ትንሣኤ) በዓል አከባበር በአቆጣጠር ልዩነት የተነሣ ከ16ኛው ምእት በኋላ ምሥራቆችና ምዕራቦች ከመለያየታቸው በፊት ከ326 እስከ 1582 ድረስ በ325 በተካሄደው ኒቅያ ጉባኤ ውሳኔ መሠረት ክብረ በዓሉ በተመሳሳይ ቀን ይውል ነበር፡፡
በዓሉ ምንግዜም ቀኑና ሌሊቱ እኩል 12፣ 12 ሰዓት ከሚሆንበት መጋቢት 25 (በጁሊያን ማርች 21) በኋላ፣ ከአይሁድ ፍሥሕ (ፋሲካ) በኋላ፣ ባለው እሑድ ሁልጊዜ እንዲውል ይደነግጋል፡፡ ከጥቅምት 1575 ዓ.ም. (1582) በኋላ የጁሊያን አቆጣጠርን ያሻሻለው የጎርጎርዮስ ቀመር በአብዛኛው የአውሮፓ ካቶሊኮች ተቀባይነት በማግኘቱና በተፈጠረው የቀናት መሳሳብ ሌላ የትንሣኤ በዓል ሊፈጠር ችሏል፡፡
የኦርቶዶክስ ፋሲካ የጁሊያንን ቀመር፣ ኢትዮጵያና ኮፕት ደግሞ በራሳቸው ቀመር የኒቅያውን ድንጋጌ ይዘው በመዝለቃቸው ክብረ በዓሉን በአንድ ቀን ያከብራሉ፡፡ በኢትዮጵያና በኮፕት ባሕረ ሐሳብ መሠረት የኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት ዓርብ መጋቢት 27 ቀን፣ ትንሣኤው እሑድ መጋቢት 29 ቀን 34 ዓ.ም. የዋለ ሲሆን፣ በየዓመቱ እነዚህ ዕለታት የስቅለት መነሻ፣ የትንሣኤ መነሻ ተብለው ይታሰባሉ፡፡
ትንሣኤን ተከትለው ቀናቸው በየዓመቱ የሚዘዋወሩት ጾሞችና በዓሎች የአወጣጥ ሥርዓት መደበኛውን ፀሐያዊ አቆጣጠር ሳይሆን የፀሐይና ጨረቃን ጥምር አቆጣጠር (ሉኒ-ሶላር) ይከተላል፡፡ ይህም በመሆኑ ትንሣኤ በመጋቢት 26 እና በሚያዝያ 30 መካከል ባሉት 35 ቀናት ውስጥ ይመላለሳል፡፡
ጥንታዊ መጽሐፍ ፍትሐ ነገሥት በፍትሕ መንፈሳዊ ክፍሉ ስለ ትንሣኤ በዓል አከባበር እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹… የትንሣኤውን በዓል በዕለተ እሑድ እንጂ በሌላ ቀን አታድርጉ፤ በመንፈቀ ሌሊት ብሉ፤ ያም ባይሆን በነግህ ብሉ. . . ከዚህም በኋላ ፈጽሞ ደስ እያላቸሁ ጾማችሁን በመብል በመጠጥ አሰናብቱ፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ተነሥቷልና፡፡››
- የፋሲካ ቀን ቋሚ ለማድረግ ?
በባሕር ማዶ ከ1920ዎቹ ጀምሮ በየዐረፍተ ዘመኑ የፋሲካ በዓል ቋሚ ቀን ተቆርጦለት እንዲከበር ሐሳብ እየቀረበ ነው፡፡ የሩቁን ትተን ከሃቻምና (2006 ዓ.ም.) ወዲህ በአማራጭነት የቀረበው፣ ባለፈው ጥር ወር በካንተርበሪው ሊቀ ጳጳስ ጁስቲን ወልቢ እንደተስተጋባው፣ ‹‹የኤፕሪል ሁለተኛ ወይም ሦስተኛ እሑድ›› ላይ እንዲውል ነው፡፡ ይባል እንጂ የቀረበው ሐሳብ በሌሎች ወገኖች ተቀባይነት እያገኘ አይደለም፡፡ የ325 ዓ.ም. ኒቅያ ጉባኤ ድንጋጌ፣ ምሳሌው በጨረቃ የሚወጣው የአይሁድ ፋሲካ (ፍሥሕ) የሆነለት የክርስቶስ ፋሲካ፣ ስሌቱ በጨረቃ ጭምር የሚገኝ መሆኑ አስረግጦ በደነገገበት ተዘዋዋሪነቱን ትቶ እንዴት ቋሚ ይሆናል ብለው ይጠይቃሉ፡፡
የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፋሲካን የምታከብረው በኒቅያ ድንጋጌ ቀንና ሌሊቱ እኩል 12፣12 ሰዓት ከሚሆንበትና መጋቢት 25 ቀን ላይ ከሚውለው የፀደይ ዕሪና/ እኩሌ (Spring Equinox) ቀጥሎ፣ ከምትታየው ሙሉ ጨረቃ (የአይሁድ ፋሲካ/ፍሥሕ የሚውልበት) በኋላ በሚመጣው የመጀመሪያ እሑድ ስለሚሆን በዓሉ ቋሚ ፈጽሞ አይሆንም ሲሉ ይሞግታሉ፡፡ ይልቅስ ምዕራቦች ከ16ኛው ምእት ዓመት በፊት ከምሥራቆች ጋር በአንድነት ያከብሩት እንደነበረው ወደዚያው እንዲመለሱ ይመክራሉ፡፡ ሃቻምና በሚያዝያ 2006 ዓ.ም. የተገናኙት ፖፕ ፍራንሲስና የኮፕቲክ ፖፕ ቴዎድሮስ ዳግማዊ በጉዳዩ ላይ ተነጋግረው ነበር፡፡
- መልዕክቶች
የዘንድሮውን በዓል አስመልክቶ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ፣ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ባስተላለፉት መልእክት፣ ‹‹የክርስቶስ ትንሣኤ ለሰው ሁሉ ትንሣኤ በኩር ሆኖ ተፈጽሞአል፤ በመሆኑም የትንሣኤን በዓል ስናከብር ‹ክርስቶስ ተነሣ› ብለን የምሥራች በመናገር ብቻ ሳይሆን እኛም እርሱ በተነሣው አኳኋን እንነሣለን እያልን ተስፋ ትንሣኤያችንን በማብሠርና በማስተጋባት ጭምር ሊሆን ይገባል፤›› ብለዋል፡፡
እንዲሁም ‹‹እኛ ክርስቲያኖች በሱባኤው ወቅት በጾም፣ በጸሎት፣ በምፅዋት፣ በንሥሐ፣ በቅዱስ ቁርባን፣ ፍቅርንና ሰላምን ገንዘብ በማድረግ ዲያብሎስንና ኃጢአትን ስንታገላቸው እንደቆየን ሁሉ፣ አሁንም በበዓለ ፋሲካው ቀን ጧሪ የሌላቸውን አረጋውያን፣ አሳዳጊ የሌላቸው ሕፃናት፣ በድርቅ የተጎዱትን ወገኖች በተለይም በአሁኑ ወቅት የግድያና የአፈና ሰቆቃ ደርሶባቸው ሰኃዘንና በችግር ላይ የሚገኙት የጋምቤላ ብሔረሰብ ልጆቻችንና ወገኖቻችን በሁሉም ነገር ከጎናቸው ሆነን በማገዝ፣ በመመገብ፣ በማጠጣትና በማልበስ፣ በሽተኞችን በመጠየቅና በመርዳት ፍጹም የደስታና የድል ቀን አድርገን ማክበር ይገባናል፤ በዚህ መልካም ሥራችንም የትንሣኤ ልጆች መሆናችንን ማስመስከር ይኖርብናል፤›› በማለት ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳሳት ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስም ባስተላለፉት መልእክት፣ ኢየሱስ ክርስቶስን መውደዳችንና ማፍቀራችን የሚገለጠው፣ እርሱን በመምሰልና እርሱ የሠራውን ሥራ በመሥራት ስለሆነ ችግረኞችንና አቅመ ደካሞችን፣ እንዲሁም ሕሙማንን እንድንወዳቸው፣ እንድንደግፋቸውና እንድንራራላቸው ያስፈልጋል። የዕለት ምግብ ያጡ ወገኖችን፣ የምንችለውን ያህል በመርዳትና በመመገብ፣ የክርስቶስን ብርሃን በማሳየት፣ ክብረ በዓሉ የደስታና የፍሥሐ እንዲሆንላቸው፣ በእምነታችን ምስክርነትን እንድንሰጥ አደራ ማለትን እወዳለሁ ብለዋል።
አያይዘውም በቅርቡ በጋምቤላ መሣሪያ በታጠቁ ክፍሎች በንጹሐን ላይ የደረሰው ኢሰባዊ ድርጊት ቤተክርስቲያኒቱን በጣም ያሳዘነ ተግባር መሆኑን አውስተው፣ ይህ ዓይነቱም ተግባር ወደፊት እንዳይደገም መንግሥት አስፈላጊውን ሁሉ እንዲያደርግና ከቦታቸው ሳይወዱ በግድ ተይዘው የተወሰዱት ወገኖች ወደ አገራቸው በሰላም ይመለሱ ዘንድ ቤተ ክርስቲያኒቱ ትጠይቃለች ብለዋል፡፡