Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየሕፃናት ሁለተኛ ቤቶች

የሕፃናት ሁለተኛ ቤቶች

ቀን:

መገናኛ አካባቢ ረጂና በሚሰኝ ደይ ኬር ውስጥ ነው፡፡ ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ተኩል ቢሆንም ሕፃናቱ ገና አልተሟሉም፡፡ የወትሮው ፕሮግራምም ገና አልተጀመረም፡፡ የነበሩት ሕፃናት ግን በተለያዩ ጨዋታዎች ተጠምደዋል፡፡ ግማሾቹ ይሯሯጣሉ፡፡ አንደኛው ሕፃን እናቱን ጓደኛው ላይ ያየውን የስፓይደር ማን ምሥል ያለበትን ካኒቴራ ካልገዛሽልኝ ብሎ ማልቀስ ይዟል፡፡ እሷም እሺታዋን እየገለጸች እንደምትገዛለት ቃል እየገባች ታባብለዋለች፡፡ ቀሚሷን እየጎተተ ማልቀሱን ቀጠለ፡፡ ተመሳሳይ ገጠመኞች ረጂና ደይ ኬር የተለመዱ ናቸው፡፡ ደይ ኬሩ ከአንድ ዓመት እስከ አራት ዓመት ድረስ ያሉ ሕፃናትን ይቀበላል፡፡ 25 ኢትዮጵያውያንና የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው ሕፃናትም አሉ፡፡

መገናኛ ከአምቼ ጀርባ የሚገኘው ደይ ኬሩ ሰፋ ያለ ቦታ ላይ ያረፈ ቪላ ነው፡፡ ግቢውም እንደዚሁ ሰፋ ያለ ሲሆን ፊት ለፊት የሚገኘው ቦታ በኮንክሪት ተሠርቷል፡፡ ሕፃናቱ ዥዋዥዌና ሸርተቴ የሚጫወቱበት ሰፋ ያለ አረንጓዴ ቦታም አለው፡፡ ከአንደኛው ጥግ ካለው በአሸዋ የተሞላ ቦታ ላይም የተወሰኑት ሕፃናት በአሸዋው መጫወት ይዘዋል፡፡ የሚሯሯጡ የሚነጫነጩና የመሰልቸት ስሜት የሚታይባቸውም አሉ፡፡

  ተቋሙ ሥራውን ከጀመረ ጥቂት ወራት ማስቆጠሩን የምትናገረው የተቋሙ ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሔራን ታደሰ አገልግሎቱ ብዙም አለመታወቁን ታመለክታለች፡፡ ይህም ትርፋማ እንዳይሆን አድርጐታል፡፡ በወር ለአንድ ልጅ እስከ 3,200 ብር ድረስ ቢያስከፍሉም የቤት ኪራይና የተለያዩ ወጪዎችን ሸፍኖ የሚቀረው ብዙም አይደለም፡፡ ‹‹የሕፃናቱ ቁጥር 30 ቢደርስ እንኳ የተወሰነ ማትረፍ ይቻላል፤›› የምትለው ወ/ሮ ሔራን የደንበኞች ቁጥር አነስተኛ መሆኑ በትርፋማነታቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ እንደሚገኝ ትናገራለች፡፡

ልጅ ማሳደግ ከባድ ኃላፊነት መሆኑን ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ይህ በተለይም ቀን ሙሉ ሥራ በሚውሉ ወላጆች ዘንድ የበለጠ ትርጉም ይኖረዋል፡፡ ለዚህም የሕፃናት ማቆያ ተቋማት (ደይ ኬሮች) ዓይነተኛ መፍትሔ ይሆናሉ፡፡ ይሁን እንጂ ደይ ኬሮችን የሚጠቀሙ ጥቂቶች ናቸው፡፡ ለዚህም የተለያዩ ምክንያቶች ይነሳሉ፡፡

በአንድ የመንግሥት ድርጅት ውስጥ ተቀጥራ ትሠራለች፡፡ ትዳር መሥርታ ጐጆ ከወጣች ደግሞ ሁለት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ወንድ ልጅም አላት፡፡ ቤታቸውም ሞቅ ሞቅ ያለ ነው፡፡ በዚህ ደስተኛ ብትሆንም ችግር የሆነባት ነገር ግን ነበር፡፡ ሕፃኑ የቤተሰብ እንክብካቤ ቢያስፈልገውም ይህ ለእነሱ የሚቻል አልሆነም፡፡  

‹‹ሁለታችንም ጠዋት የወጣን ማታ ነው የምንመለሰው፡፡ ሠራተኛም ሆነ ሞግዚት መቅጠር አልፈለግንም፡፡ ስለዚህ ሌላ አማራጮችን ለመፈለግ ተገደድን፤›› የምትለው ትዕግስት ወርቁ (ስሟ ተቀይሯል) ቀን ቀን ልጇ ሊቆይባቸው የሚችልባቸውን የተለያዩ ደይ ኬሮችን ማፈላለጋቸውን ትናገራለች፡፡

የተዘዋወረችባቸው የሕፃናት ማቆያዎች ቅዳሜና እሑድ እንደማይሠሩ፣ አገልግሎታቸውም ከጠዋት ሁለት ሰዓት እስከ 11 ሰዓት ድረስ ብቻ መሆኑን፣ ከ400 ብር ጀምሮ እስከ 1,200 ድረስ የአገልግሎት ክፍያ እንደሚጠይቁ ተገንዝባለች፡፡ የሕፃኑን ወተት አፍልተው የሚያጠጡ፣ ልብስም የሚያጥቡ፣ የተለያዩ መጫወቻዎችን የሚያቀርቡም አጋጥመዋታል፡፡ ከወላጆች የሚጠበቀውም ፖፖና ብርድ ልብስ እንዲሁም ተጨማሪ ምግቦች ማቅረብም ከባድ ሆኖ አልተሰማትም፡፡

በዚህ ደስተኛ ብትሆንም ልጇን ግን አምና ለመስጠት አልደፈረችም፡፡ ልጆቻቸውን ደይ ኬር አስገብተው የሚያውቁ ሰዎች የነገሯት ነገር አስፈራት፡፡ በደይ ኬቶች ውስጥ የንፅህና ችግር እንዳለ፣ በዚህም ሕፃናት በቀላሉ ተላላፊ በሽታዎች እንደሚጋለጡ እንዲሁም አንዱን ካንዱ በመለየት እኩል እንደማይንከባከቡ የታዘቡትን ነግረዋታል፡፡ ከዚህ ባሻገርም ልጃችሁ ታሟል በሚል በየጊዜው ደውለው እንደሚጠሯቸው ‹‹ደይ ኬር ማስገባትሽን እስከትዘነጊ ድረስ ትጠሪያለሽ፡፡ ታሟል ነይ ውሰጂ ትባያለሽ፡፡ ዴይኬር ውስጥ የሚሠሩት ሞግዚቶች አስፈላጊው ክህሎት ሳይኖራቸው ስለሚቀጠሩ ሁኔታው በሕፃናቱ ዕድገት ተፅዕኖ አለው፤›› ሲሉ በራሳቸው የደረሰውን በመንገር ሌላ አማራጭ እንድትፈልግም መከሯት፡፡

ከሰማቻቸው ተነስታ ልጇን ደይ ኬር ላለማስገባት ወሰነች፡፡ ቤተሰቦቿ እንዲያግዟት የአራት ወር ሕፃን ልጇን ይዛ ትኖርበት ከነበረው አራት ኪሎ ወደ ወላጆቿ ሠፈር ጀሞ አካባቢ ገባች፡፡ አዲስ የተከራየችው ቤትም ለወላጆቿ ቤት ቅርብ ነው፡፡ ጡረተኛ ወላጆቿም ሕፃኑን ለመንከባከብ ወደ ኋላ አላሉም፡፡ ጠዋት ለሥራ ስትወጣ ሕፃኑን አቀብላቸው ትሄዳለች፡፡ ከሥራ ስትመለስ ደግሞ ይዛው ትገባለች፡፡ ሥራ አይስተጓጐልባትም፡፡ ‹‹ወላጆቼ ባይኖሩ የግድ ሥራዬን አቆም ነበር፤›› ስትል ከሥራ ጋር ልጅ ማሳደግ ያለውን ፈተና ትገልጻለች፡፡

ቀደም ባሉት ጊዜያት ብዙ ሴቶች ከቤት ይውሉ በነበረበት ልጆችን ተንከባክቦ የማሳደግ፣ ኃላፊነት የእናትየው ብቻ ነበር፡፡ ሕፃናቱን የሚጠብቅ ሞግዚት መፈለግ ከቅብጠት ይቆጠር ነበር፡፡ በተመሳሳይ እንደዛሬው ደይኬሮችም አልነበሩም፡፡ ኃላፊነቱ ሙሉ በሙሉ እናቶች ላይ የወደቀ ነበር፡፡ ይህ በተወሰነ መልኩ መሻሻል ቢያሳይም አሁንም  በርካታ እናቶች ልጅ የማሳደግ ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ብዙ ሴቶች ሴቶች ተምረው፣ ሥራ ይዘው ገቢያቸውን ይደግፉ፣ ቤተሰባቸውን ያስተዳድሩ ጀምረዋል፡፡ ይህም ልጆቻቸውን የሚንከባከቡ ሞግዚቶች እንዲፈልጉ፣ ደይኬሮችን እንዲጎበኙ እያስገደዳቸው ይገኛል፡፡ የደይ ኬር አገልግሎት እንደ ፈረንሣይና ጣሊያን ባሉ አገሮች ከመደበኛ ትምህርት እኩል ቦታ አላቸው፡፡ ሕፃናት በደይ ኬር እንዲያልፉ ይጠበቃል፡፡

እዚህ እኛ ጋርም ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ሕፃናት ማቆያዎች እየተስፋፉ ነው፡፡ ይህ ልጆቻቸውን የሚያቆዩበት ሌላ አማራጭ ለሌላቸው ወላጆች ዕፎይታ ሆኗል፡፡ ይሁንና የተለያዩ ችግሮች ሲያጋጥሙ፣ በዚህም ጥቂት የማይባሉ ወላጆች አገልግሎቱን አቋርጠው ሌላ አማራጭ ሲፈልጉ አልያም ከሥራ ትተው ልጆቻቸውን ለማሳደግ ሲገደዱ ይስተዋላል፡፡

‹‹ደይ ኬር የሚቆዩ ሕፃናት ከአመጋገብ ጀምሮ የተለያዩ ችግሮች ያጋጥሟቸዋል፡፡ እኛ ወላጆች ሦስት አራት ዓይነት ምግብ እንቋጥራለን፡፡ ነገር ግን ሳይመግቧቸው ይቀራሉ፤›› የሚሉት አቶ ታምራት ኃይለሚካኤል ናቸው፡፡

የሚኖሩት ጀሞ ኮንዶሚኒየም አካባቢ ነው፡፡ እሳቸውና ባለቤታቸው የመንግሥት ሠራተኞች ናቸው፡፡ የመጀመሪያ ልጃቸውን ሲያሳድጉ ብዙም አልተቸገሩም ነበር፡፡ ሁለተኛና ሦስተኛ ልጃቸውን ለማሳደግ ግን እየተፈተኑ ይገኛሉ፡፡ የሦስት ልጆች አባት የሆኑት አቶ ታምራት የተለያዩ ደይኬሮችን በር አንኳኩተዋል፡፡ የአንድ ዓመትና የሁለት ዓመት ከአራት ወራት ዕድሜ ያላቸውን ልጆቻቸውን የሚቆዩበት ተስማሚ ደይ ኬር በቀላሉ ማግኘት አልቻሉም፡፡ እስካሁን ስድስት ደይኬሮችን ሞክረዋል፡፡ ማቆያዎቹ ካለባቸው የአያያዝ ችግሮች አንፃር በወራት ቆይታ ሌላ ለመፈለግ ይገደዳሉ፡፡

‹‹ወላጅ የቋጠረላቸውን ምግብ በሚገባ አይመግቧቸውም፡፡ ምግብ ሳያንስ የአንዱን ምግብ ተሰብስበው እንዲበሉ ያደርጓቸዋል፡፡ የማይፈልጉትን ምግብ ብሉ ይሏቸዋል፤›› ሲሉ ልጆቻቸው በተደጋጋሚ ጊዜ የማይፈልጉትን ምግብ እንዲበሉ መገደዳቸውን ይናገራሉ፡፡ በፅዳት ረገድም ችግሮች እንደሚያጋጥሙ፣ ብዙ ጊዜም ወላጅ በቂ ዳይፐር እያቀረበ ነገር ግን ሕፃናቱ ቀኑን ሙሉ በአንድ ዳይፐር እንዲቆዩ የሚደረግበት፤ ለልጆች መተኛ ፍራሽ የሌላቸው ደይኬሮችም እንዳሉ ይገልጻሉ፡፡ ይህም ሕፃናቱ ወለል ላይ እንዲተኙና ለቅዝቃዜው ያጋልጣል፡፡ በሌላ በኩልም በአንድ ጠባብ ክፍል ውስጥ እንዲውሉ በመደረጉም ለጉንፋንና ለሌሎች ተላላፊ በሽታዎች በቀላሉ የሚጋለጡበት ሁኔታዎች አሉ፡፡

‹‹አያያዛቸው ሕፃናትን ለተለያዩ የጤና ችግሮች ተጋላጭ ያደርጋቸዋል፡፡ ብዙ ጊዜ ደይ ኬር አድርሻቸው ከመመለሴ ድንገት ተደውሎ ልጅህ ታሟልና ውሰደው ይሉኛል፡፡ ስሄድ ከቤት ሰላም የወጣ ልጅ ታሞ አገኘዋለሁ፤›› በማለት አቶ ታምራት በተደጋጋሚ ልጆቻቸው የገጠማቸውን የጤና ችግር ይገልጻሉ፡፡

የአቶ ታምራት ልጆች የሚቆዩበት ደይ ኬር አገልግሎት ጠዋት ሁለት ሰዓት ይጀምርና 11 ሰዓት ላይ ያበቃል፡፡ ለአንድ ልጅ በወር 400 ብር ያስከፍላሉ፡፡ ዋጋው ተመጣጣኝ ቢሆንም ያለው ዘርፈ ብዙ ችግር አገልግሎቱ ዕፎይታን ብቻ ሳይሆን ችግርንም ሠጥቷቸዋል፡፡ ልጄን የሚጠብቅልኝ አለ ብለው መረጋጋት አልቻሉም፡፡ በመሆኑም ልጆቻቸውን ከደይ ኬር አስወጥተው አራት ኪሎ ለሚኖሩት እናታቸው በአደራ መስጠትን መርጠዋል፡፡ ይህም በመጠኑም ቢሆን እፎይ ማለት ችለዋል፡፡ በዚህ መዝለቅ ካልተቻለ ግን ባለቤታቸው ሥራዋን ትታ ልጆቹን ለማሳደግ ትገደዳለች፡፡ በዚህ አቶ ታምራትና ባለቤታቸው ተስማምተዋል፡፡

ሥራው የተለየ ጥንቃቄ ቢያስልገውም ተቋማቱ የተረዱት አይመስሉም፡፡ ሕጋዊ ተቀባይነት ያላቸውን ሕፃናት ማቆያ ማግኘት ከባድ ነው፡፡ ጥቂት የማይባሉት ደይኬሮች ሕጋዊ ፈቃድ የላቸውም፡፡ ወደ ሥራው የሚገቡትም ስለሥራው ተረድተው ሳይሆን የራሳቸውን ልጅ ለመጠበቅና በዚያውም ገቢ ለማግኘት እንደሆነ መታዘብ ይቻላል፡፡ ይህ ሕፃናቱን እንዴት መያዝ እንዳለባቸው፣ በሙያው የሠለጠኑ ሞግዚቶችን እንዳይቀጥሩ ከወላጅ ጋርም እንዲጋጩ እያደረገ ይገኛል፡፡

ደይ ኬር የመክፈት ፍላጐት ያደረባት ልጇን በቅርበት ሆና ለመንከባከብ እንዲሁም ከቤት ሳትወጣ የምትሠራው ሥራ ስለምትፈልግ ነው፡፡ መሪየም እድሪስ ትባላለች (ስሟ ተቀይሯል) ቤተል አካባቢ ደይ ኬር ከፍታ መሥራት ከጀመረች አራት ዓመታት አስቆጥራለች፡፡

ሥራውን ስትጀምር ሕጋዊ ፈቃድ አልነበራትም፡፡ አሥር የሚሆኑ የዘመዶቿንና በቅርበት የሚያውቋት ወዳጆቿን ልጆችና የራሷን ልጅ ይዛ ነበር የጀመረችው፡፡ አሁን ላይ የደንበኞቿ ቁጥር 25 ደርሷል፡፡ አራት ሞግዚቶችም ቀጥራለች፡፡ ይሁንና የተለያዩ ችግሮች እየተጋረጡበት ነው፡፡

ሕፃናት በልዩ ጥንቃቄ መያዝ እንዳለባቸው ታምናለች፡፡ የቀጠረቻቸው ሞግዚቶች ግን ይህንን ማድረግ አልቻሉም፡፡ ሕፃናቱን ይበድላሉ፡፡ ከደንበኞቿም እያጋጯት ይገኛሉ፡፡ ‹‹ሞግዚቶቹ በጣም ያስቸግራሉ፡፡ ብዙ ጊዜ ሕፃናቱ ዳይፐር አይቀይሩላቸውም፡፡ ምግብም ሳይመግቧቸው እንደበሉ አድርገው ይናገራሉ፡፡ ሌላ ነገር ቢበላሽ ምንም አይደለም፡፡ ሕፃናትን መበደል ግን ኃጢአት ነው፤›› በማለት የሞግዚቶቹ አለመታመን ከምንም በላይ እያማረራት መሆኑን ትናገራለች፡፡

የቤት ኪራይም ሌላ ራስ ምታት ነው፡፡ ከአራት ዓመታት በፊት ሥራውን ስትጀምር ለቤት ኪራይ ትከፍል የነበረው 3,000 ብር ነበር፡፡ አሁን ላይ ዋጋው በማይታመን መጠን አሻቅቧል፡፡ 3,000 ብር ትከፍልበት የነበረውን ቤት 14,000 ብር እንድትከፍል ሆኗል፡፡ ይህንን ለማካካስም ለአንድ ልጅ 400 ብር ታስከፍል የነበረውን በእጥፍ አሳድጋ 800 ብር አድርጋለች፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ከምንም የሚያተርፋት አልሆነም፡፡ ለሞግዚቶች ከ800 እስከ 1,000 ብር ከፍላና ሌሎች ወጪዎችን ሸፍና እጇ ላይ የሚቀረው እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡

ከወላጆች በኩል ያለው ችግርም ቀላል አይደለም፡፡ ‹‹አብዛኞቹ ወላጆች ልጃቸውን ደይ ኬር በማስገባታቸው ከተለያዩ ጣጣዎች እንደተገላገሉ ይሰማቸዋል፡፡ ብዙዎች ልጃቸውን በእኛ ላይ የመጣል ስሜት ይታይባቸዋል፡፡ ልጃቸውን በሰዓቱ የማይወስዱም ብዙ ናቸው፡፡ በቂ ምግብ የማያመጡም አሉ፤›› ስትል ጥቂት የማይባሉት ልጁ የማይፈልገውን አልያም በጥንቃቄ ያልተሠራ ምግብ እንደሚልኩ ሁሉ፣ በአንድ ወቅትም ከአንደኛው ልጅ የምሳ ዕቃ ውስጥ የዕቃ ማጠቢያ ሽቦ ማግኘቷን ትገልጻለች፡፡

ወርኃዊ ክፍያ ለመስጠት የሚያስቸግሩ ወላጆችም አሉ፡፡ ልጄን ምግብ አላበላችሁትም በሚል መጨቃጨቅም የደይኬሮች የየዕለት ገጠመኝ ይመስላል፡፡  ፊትሽን አጠቆርሽብኝ ብለው ሰጣገባ የሚጀምሩም ያጋጥማሉ፡፡ ሁኔታዎች ተደራርበው በሥራው እንዳትገፋ ተስፋ ያስቆረጧት መሪየም አገልግሎቱን ሰኔ ላይ ለማቋረጥ ወስናለች፡፡

ልጆቻቸው በቂ ትኩረት እንዲያገኙ የሚፈልጉ ወላጆች ለምን አንድ ሞግዚት ለአንድ ሕፃን አይሆንም ሲሉ ይጨቃጨቃሉ፡፡ ይህ ከቦታውና ከወጪው አንፃር የማይታሰብ ነው፡፡ ‹‹የልጆቹ ቁጥር ባነሰ ቁጥር የበለጠ ትኩረት እንደሚያገኙ የሚሰማቸው ወላጆች ይመጣሉ፡፡ በተቃራኒው ደግሞ በርካታ ልጆችን ሲያዩ የተሻለ እንክብካቤ ቢኖር ነው በሚል ግምት ልጆቻቸውን ብዙ ልጆች ባላቸው ደይኬሮች ማስገባት የሚመርጡም አሉ፤›› የሚሉት መካኒሳ አቦ ማዞሪያ አካባቢ ስሙ እንዲገለጽ የማይፈልጉት ደይ ኬር ያላቸው ወ/ሮ ሰአዳ አህመድ ናቸው፡፡

የሁለት ልጆች እናት የሆኑት ወ/ሮ ሰአዳ ከድሮም ጀምሮ ደይ ኬር የመክፈት ምኞት ነበራቸው፡፡ ይሁን እንጂ ለረጅም ጊዜ በቤተሰብ የንግድ ሥራ ውስጥ ይሠሩ ነበር፡፡ ነገር  ግን ከሥራው ጋር ልጆቻቸውን ለመንከባከብ ይቸገሩ ነበር፡፡ በመሆኑም በአቅራቢያቸው የሚገኙ የተለያዩ ደይኬሮችን ጐብኝተዋል፡፡ ምቹ ዴይኬር ግን አላጋጠማቸውም፡፡ ይህም ምኞታቸው የነበረውን ደይ ኬር እንዲከፍቱ ዕድል ፈጠረላቸው፡፡ ወዲያውም የራሳቸውን ሁለት ልጆችና የዘመዳቸውን ልጆች ይዘው ሥራ ጀመሩ፡፡

ከጀመሩ ሁለት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ የሚጠብቋቸው ሕፃናት ቁጥርም 40 ደርሷል፡፡ ከስምንት ወራት ጀምሮ እስከ ሦስት ዓመት ድረስ ያሉ ሕፃናትን ይቀበላሉ፡፡ ንጽህና መጠበቂያ፣ ፍራሽ፣ ብርድ ልብስ የሚያዘጋጁ ሲሆን ለአንድ ልጅ 1,000 ብር ያስከፍላሉ፡፡ በአስፈላጊው ሙያ የሠለጠኑ እስከ 1,500 ብር የሚከፍሏቸው አሥር የሚሆኑ ሞግዚቶች አሏቸው፡፡ የቤት ኪራይ በወር 20,000 ብር ይከፍላሉ፡፡

አገልግሎቱን የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ ቢጨመርም የቤት ኪራይና የተለያዩ ወጪዎች መኖር ትርፋማነታቸውን እምብዛም እንዳደረገው ወ/ሮ ሰአዳ ይናገራሉ፡፡

በወላጆች በኩል የሚስተዋሉት ችግሮችም ለሥራቸው እንቅፋት እየሆነ ይገኛል፡፡ በውላቸው መሠረት የታመመ ልጅ ወደ ደይ ኬሩ መውሰድ አይፈቀድም፡፡ ይሁን እንጂ የታመሙ ሕፃናትን በግዴለሽነት ወደ ደይ ኬሩ የሚልኩ ወላጆች ብዙ ናቸው፡፡ በተለይም የሕፃኑ ህመም ተላላፊ በሚሆንበት ወቅት ሁሉም ሕፃናት የሚታመሙበትና ከወላጆች የሚጋጩበት ሁኔታ ያጋጥማል፡፡

ለብዙ አደጋዎች ተጋላጭ የሆኑት ሕፃናት ልጆች ጥብቅ የሆነ ክትትል ያስፈልጋቸዋል፡፡ ለዚህም አስፈላጊውን እንክብካቤና ክትትል ማድረግ የግድ ይላል፡፡ ይሁን እንጂ ሁለቱም ወላጆች ሠራተኛ በሚሆኑበትና ቤት ሌላ የሚረዳቸው ሰው ከሌለ ይህንን ለማድረግ ከባድ ይሆናል፡፡

በመሆኑም ሕፃኑን ቤት ውስጥ ሆኖ የሚንከባከበው ሞግዚት መቅጠር አልያም በአቅራቢያ የሚገኝ ደይ ኬር መጠቀም የግድ ይላል፡፡ አቅሙ የሌላቸው ግን ከሥራ ገበታ ቀርተው ሕፃኑን ለማሳደግ ይገደዳሉ፡፡ ጥቂት የማይባሉት በዚህ መልኩ ችግራቸውን ቢቀርፉም ይህንንም ለማድረግ አቅሙ የሌላቸው ላጤ እናቶች የበለጠ ተጐጂ ይሆናሉ፡፡

ተመሳሳይ ችግር ያለባቸውን እናቶች ለመርዳት የተቋቋመው ስትሮንግ ኸርት የተባለው ግብረ ሰናይ ድርጅት ጥቂት የማይባሉ ላጤ እናቶችን ችግር ለመቅረፍ ችሏል፡፡

ድርጅቱ ከተቋቋመ አራት ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ከአንድ ሳምንት እስከ ሦስት ዓመት ድረስ ያሉ ሕፃናትን ተቀብሎ ያቆያል፡፡ ይህንን የሚያደርገውም እናትየው ልጇን ስትንከባከብ ከሥራ ቀርታ ለከፋ ችግር እንዳይጋለጡ ለማድረግ ነው፡፡ በዚህ መልኩ 44 ሕፃናትን ተቀብሎ ነፃ የደይ ኬር አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ ቢሆንም ግን ችግሮች አልጠፉም፡፡

የተቋሙ መሥራችና ዳይሬክተር አቶ ጌትነት ተፈሪ እንደሚሉት፣ ተቋሙ ከንጋቱ አንድ ሰዓት ጀምሮ እስከ 11 ሰዓት ድረስ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ በተቋሙ የሚቆዩ ሕፃናት አራት ዓመት እስኪሞላቸው ድረስ  ንጽህና፣ ምግብ፣ ጤናና ሌሎችም አገልግሎቶችን ያገኛሉ፡፡ ይህንን የተማመኑት ወላጆች ሙሉ ለሙሉ ልጆቻቸውን ይዘነጋሉ፡፡ ከኃላፊነት ይሸሻሉ፡፡ አንዳንድ ወላጆች አገልግሎቱ ቤት ድረስ እንዲሆላቸው ይፈልጋሉ፡፡ ‹‹ቤት ድረስ ሄደን ልጆቹን እንድንወስድ ይፈልጋሉ፤›› የሚሉት ዳይሬክተሩ ልጆች ጠዋት ወደ ተቋሙ ሲመለሱ ቆሽሸውና ተርበው እንደሚያገኟቸው ይናገራሉ፡፡ ሕፃናቱ አጥፍተዋል በሚል ያለአግባብ የሚቀጡ፣ በእሳት የሚያቃጥሉ ወላጆች ሁሉ እንደሚያጋጥሙ ይህም ተቋሙን እየፈተነ እንደሚገኝ አቶ ጌትነት ተናግረዋል፡፡

በሁለቱም ወገኖች በኩል የሚስተዋሉት ችግሮች ደረጃውን ባልጠበቀ አሠራር የሚፈጠሩ ናቸው፡፡ ለተቋማቱ ፈቃድ የመስጠትና የመቆጣጠር ኃላፊነት ያለበት የአዲስ አበባ ምግብ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ነው፡፡ የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የሕፃናት ማቆያ ማዕከላት ሊያሟሉ የሚገባቸውን ልዩ ልዩ መሥፈርት አዘጋጅቶ በሥራ ላይ ካዋለ ቆይቷል፡፡

በመሥፈርቱ ከተካተቱት መካከል አንድ ማዕከል ራሱን የቻለ ግቢ ግቢው ለሌላ አገልግሎት የማይውል፣ ከነፍሳት መራቢያ፣ ከቆሻሻ መጣያ፣ ከመጥፎ ሽታ፣ ከኬሚካልና አደጋ ከሚያስከተሉ እንደ ድንጋይ፣ ጠጠር፣ ጉድጓድና ስለታማ ነገሮች የፀዳ መሆን ይገባዋል የሚሉት ይገኙበታል፡፡ እንዲሁም ማዕከሉ ፎቅ ላይ መሆን የለበትም፣ ደረጃውን በጠበቀ ቁሳቁስ ሊገነባና ፕላስቲክ የተሠራ ወፍራም ሰው ሠራሽ ሣር ሊኖረው ይገባል፡፡ ደረጃውን የጠበቀ የሕፃናት የተለየ ማረፊያና መፀዳጃ ክፍልም ያስፈልገዋል፡፡

በተጨማሪም ሞግዚቶች ቢያንስ በሕፃናት አያያዝ፣ እንክብካቤና ሥነ ልቦና አግባብ ካለው ተቋም ሥልጠና የወሰዱ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሌሎች የማዕከሉ ሠራተኞችም እንደየሥራ ባህሪያቸው ሥልጠና የወሰዱ እንዲሆኑ ይጠበቃል፡፡ የሞግዚቶቹና የሕፃናቱን ቁጥር ንጽጽር በተመለከተም ዝርዝር ሁኔታዎች ተቀምጠዋል፡፡ ከዜሮ እስከ 29 ወር ለሚገኙ አራት ሕፃናት አንድ ሞግዚት፣ ከ30 እስከ 35 ወር ለሆኑ ስምንት ሕፃናት አንድ ሞግዚት፣ ሦስት ዓመት ለሞላቸው አሥር ሕፃናት አንድ ሞግዚት እንዲኖር ግድ ይላል፡፡

በአዲስ አበባ ምግብ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን የአካባቢ ጤና አጠባበቅ ባለሙያና የምግብ ነክ ኢንዱስትሪዎችና ጤና ነክ ተቋማት ብቃት ማረጋገጥ ኦፊሰር ወ/ሮ ቤዛዊት ግርማ እንደሚሉት፣ በከተማው የሚገኙ ከ40 የሚበልጡ ደይ ኬሮች መሥፈርቱን አሟልተው ፈቃድ ተሰጥቷቸው እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ፈቃድ ሳይኖራቸው የሚሠሩ ተቋማትም ጥቂት አይደሉም፡፡ ነገር ግን ቢሮው ድንገተኛ ፍተሻ ያደርጋል፡፡ በዚህም መሥፈርቱን አሟልተው ፈቃድ በተሰጣቸው ነገር ግን አሠራራቸው ችግር ያለበት ማዕከላት ላይ እርምጃ ይወስዳል፡፡ እርምጃውም ፈቃድ እስከ መንጠቅ ይደርሳል፡፡  

የተቋማቱ አስፈላጊነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል፡፡ አገልግሎት አሰጣጣቸውን እንዲያስተካክሉ፣ የተፈላጊነታቸውን ያህል ሰው እንዲገለገልባቸው ማድረግ ግድ ይላል፡፡

በሌላ በኩል ልጅ ከማሳደግ ጋር ተያይዘው የሚታዩ ችግሮችን በተለይም የእናቶችን ከሥራ ገበታ ላይ መቅረት ለመግታት እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ በቅርቡ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ከሦስት ዓመት ያልበለጠ ዕድሜ ያላቸውን ሕፃናት ማቆያ እንዲያስገነቡ የሚያስገድድ ረቂቅ አዋጅ በፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴር ተዘጋጅቷል፡፡ ይህም ሴት ሠራተኞች በተረጋጋ መንፈስ መሥራት እንዲችሉ፣ ለልጆቻቸው ሲሉ በተደጋጋሚ ጊዜ ከሥራቸው የሚቀሩ ሴቶችን ቁጥር በመቀነስ ለተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ጥራት እንዲኖረው እንደሚያስችል ተገልጿል፡፡ ረቂቁ በተያዘው ዓመት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እንደሚቀርብ ታውቋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...