Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ሞቆ የቀዘቀዘባቸው ስንት ይሆኑ?

ሰላም! ሰላም! የተወደደባት እንዲያው ለአፍ የሚሞቅ ሰላምታ ብቻ የረከሰባት ዓለም ዳግም ሞታ ዳግም ልትወለድ ትንሳዔዋ ደረሰ። ከሰላሙ በላይ ኪሱ ለሞላ ስቅለት ድነቱ፤ ለጎደለ ደግሞ ትንሳዔ ፍርዱ ሆነ ማለት አይደል? “ይገርማል እኮ ባሻዬ ጊዜው እንዴት ይሮጣል?” ብላቸው በቀደም ከስግደት ሲመለሱ፣ “ከስቅለት እስከ ትንሳዔ ያለውን ነው? ወይስ ከፋሲካ ወደ ፋሲካ የሚሮጠውን ማለትህ ነው?” ብለው አዞሩብኝ። “የሦስት ቀናት ዕድሜና  የዓውደ ዓመት ቆጠራ ምንና ምን ሆኖ?” ብላቸው፣ በጣር ሦስት ቀናት ሦስት ዓመታት፡፡ በትፍስህት ደግሞ ዓመት ማለት ቅፅበት እንደሆነ አብራሩልኝ። ወይ ጣርና ጊዜ አያ! ታዲያ ባሻዬ ጣርና ትፍስህት ተሰባጥረው በተሰፉባት ዓለም ጊዜ እንደ ቆጣሪው ይወሰናል ማለታቸው ነው። “ከአሁን አሁን ከባድ ዝናብ ጥሎ ጎርፍ ጠራረገን ብለን ስናንጋጥጥ ለካ አምሮት እያንሳፈፈ ቀልብ ካስከዳን ከራርሟል፤” ብዬ ደግሞ የባሻዬን ልጅ ፋሲካን በባዶ ስለሚያሳልፉ ወገኖቼ ሳጫውተው፣ “ሚቲዎሮሎጂ የማይተነብየውን እየተነበይክ አገር አታሸብር፤” ብሎ አስጠነቀቀኝ። አንዳንዴ በትንቢትና በታሪክ መሀል ያለውን ሰፊ ልዩነት ይስትዋል ልበል? እውነቴን እኮ ነው።

‹ሁሌም ፋሲካ የለም› የሚባለው አባባል እኮ አሁን አሁን ለአንዳንዶቻችን ‘መቼም ፋሲካ የለም’ ወደሚለው የተሸጋገረ መሰለኝ። መቼም ጊዜው የሽግግር ነው። ግን አባባሎቻችን ብቻ እየተሻገሩ የሀብት ሽግግር ሳናይ ማለፋችን ነው በቃ? ለነገሩ ሙሉ ለሙሉ እንዲያ ብሎ መደምደም አይገባም። ምክንያቱም የሀብት ሽግግር ላይ ባንሆንም ገዝተን ቤታችን ውስጥ በሸምቀቆ ገመድ የኋላ አግሩን አስረን ባናስጮህም፣ በየፌስቡክ ይዞታችን ላይ ያለ ቀረጥ፣ ያለ ካሽና ያለ ክሬዲት ፎቶ እየለጠፍን ጎረቤት መጥራት የጀመርን ብዙ ነን። ምኑን? በጉን ነዋ! በሬ ይሁንላችሁ? ግድ የለም ይቻላል። በነፃ የማይሸመት ፎቶግራፍ ኢንተርኔት ተራ የለም። ይኼ ታዲያ ከማኅበረሰባዊ መስተጋብር ወደ ማኅበረሰባዊ ድረ ገጾች ያደረግነው ሽግግር የቴክኖሎጂ ሽግግር ላይባል ነው? ምን አለበት የሀብት አምሮትን በቴክኖሎጂ ብንበቀልበት!

ይገርማችኋል ሰሞኑን ፋሲካን በማስመልከት አንድ የተሠራ ጥናት በሬዲዮ ሳዳምጥ ነበር። እሱም የዜጋው በዓል አከባበር ከጊዜ ወደ ጊዜ ምን ዓይነት መልክ እየያዘ ይተነትናል፡፡ በእውነቱ በጣም አስደንጋጭና ግራ አጋቢ ነገር ሰማሁ። አብዛኛው ሰው በሰጠው አስተያየት በዓል የሚያከብረው ቤቱ ከጠዋት እስከ ማታ ተጠቅልሎ ተኝቶ በመዋል ነው አሉ። ምን ግራ አጋባህ አትሉኝም? በዓውደ ዓመት ቀኑን ሙሉ ተኝተን ከዋልን በአዘቦት ቀን 24 ሰዓት ነው የምንተኛው ማለት እኮ ነው። መቼም ጨዋታ ነው አትቀየሙኝም። ይኼውላችሁ ሐበሻ የሚታማው ውስጡ አምቆ በያዘው ገመናው ብቻ ነው ይባላል። ካላመናችሁ በየግላችሁ ለሀሜት የምትፈጁዋቸውን ማገዶዎች ይዘት ፈትሹና መልሱን ድረሱበት። ‘የለም ሐበሻ የሚታማው በስንፍናው ነው’ የምትሉ ወደ እናንተ ሐሳብ ስለምመጣ ተረጋጉ። አሁን ልብ ብላችሁ ብታስቡት የበዓል ቀንና የአዘቦት ቀን አዋዋላችን ሲታይ በሥራ የተጠመድን የምንመስለው በየትኛው ነው?

 ታዲያ እኔ ምን አልኩ? አንዱ በቀደም በባሻዬ ሬዲዮ ሳደምጠው፣ በቀጥታ የሬዲዮ ውይይት ላይ ሊሳተፍ ደውሎ፣ “እኔ” አለ። “ከወዲሁ ያስጨነቀኝ የሥጋ ዋጋ እንዳይጨምር ነው፤” ሲል አልሰማም?! ባሻዬን ትክ ብዬ ሳያቸው፣ “ልክ እንደ ሥጋው  ዋጋ ለሰው ስሜትና ሐሳብ ዋጋ እያደር መርከስ አብዝተን ብንጨነቅ የት እንደርስ ነበር?” ብለው  አቀረቀሩ። ባሻዬ ደግሞ በትንሽ በትልቁ ማቀርቀር ይወዳሉ። ምናልባት እኔ በዕድሜ ስለማንሳቸው ይሆናል ጉድ ሰምቼና ሁለነገራችንን ታዝቤ ቀና የምለው? እንዲያውም አንዳንዴ ራሳቸው ባሻዬ፣ “ሆድህን ሰፋ አድርገው፤” ይሉኛል። እኔ ደግሞ ቀጥታ ተርጉሜ፣ “ከዚህ በላይ?” እላለሁ። ከዚህ በላይ ካሰፋነውማ ሌላ ሦስት ሺሕ ዘመን ሆድና ሆድ ተኮር እሳቤዎች እንደ ነገሡ፣ እንዳስጨነቁንና እንዳሳሰቡን ቀረን በቃ። በአዕምሮ የምንሰፋበት ቀን ስለሚናፍቀኝ እኮ ነው በፋሲካ ምድር ሆድን የምኮንነው። የምናገረውን አላውቅምና ይቅር በሉኝ አደራ!

እናላችሁ እንዲህ የባጥ የቆጡን ስሰማና ሳይ በመሀል በመሀል አንድ ገጽየፈጀው የማንጠግቦሽ አስቤዛ ዝርዝር ትዝ እያለኝ ልቤ ድንግጥ ድንግጥ እያለ ተቸገርኩ። ገበያው እንደምታዩት ነው። ሁሉም ‘ታላቅ ቅናሽ’ እያለ ለጥፏል። ከስንት ወደ ስንት እንደቀነሱ አናውቅ፣ እንደጨመረ አናውቅ። “ሰውን ማመን ገዝቶ ነው? ሸጦ ነው?” ስለው፣ “አንተ ደላላ ሆነህ ያላወቅከውን እኔ እንዴት አውቃለሁ?” የሚለኝ ወዳጄ የባሻዬ ልጅ ነው። አንድ ያልገባው ነገር ምን መሰላችሁ? ምናልባት መንግሥት ራሱ ተናግሮት ሲያበቃ ለራሱ ያልገባው . . .  ደላላ ያልሆነ በከተማው ላይ ቢፈለግ አለመኖሩን ነው። እዚህ ጋ አባባሌን አዛብታችሁ እንዳትረዱብኝ ደላላ ሁለት ትርጉም አለው። አንድ ፈላጊና ተፈላጊን ከመሀል ሆኖ ማገናኘት። ሁለት አባብሎና አዘናግቶ ገደል መክተት። ስም በመለጠፍ መቼም አንታማም፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ያስቀመጥናቸውን ሕገወጥ ደላላ ብለን አውግዘናል። “እኛ አላልንም መንግሥት ነው፤” ትሉ ይሆናል እኮ በልባችሁ። አቤት ሰው! የመንግሥትና የግል እዚህ ድረስ ይከፋፍለን በቃ?!

  የጀመርኩትን ልጨርስላችሁና የመንግሥትና የግሉን በሌላ ጨዋታ  ልመለስበት። “ታላቅ ቅናሽ” ብሎ ነገር ሮኬት ሳይንስ ሆኖብኛል እያልኳችሁ ነበር። አዎ። በግ ተራ ወርጄ ላቱን መትሬ አንድ ተለቅ ያለ በግ መረጥኩና (ማንጠግቦሽ ትልቅ በግ ሲታረድ ትወዳለች) ”ስንት ነው?” ስለው ሻጩን “ተጽፎበታል እኮ፤” ብሎ ወደ ሆዱ ጠቆመኝ። አዙሬ ሳየው የ15 በመቶ ቅናሽ ይላል። “ምን ማለት ነው?” ብዬ ስጠይቀው ሻጩ ምን ቢለኝ ጥሩ ነው? “ከአምናው የፋሲካ የበግ ዋጋ ሲነፃፀር 15 በመቶ ቀንሷል ማለት ነው፤” አለኛ። ከዚህ በላይ ሕገወጥ ደላላነት አለ እስኪ አሁን። ‘ሲወልዱ አይታ ምን አለች’ አሉ። እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ ሁሌ ፋሲካ ቢሆን ድለላውን ትቼ በግ ነጋዴ እሆን ነበር። ኋላማ ትቼው ስሄድ ባለበጉ፣ “ነጋዴ ለዘለዓለም ይኑር” አይልም በእኔ እየሳቀ?! “ምን?” ብዬ ዞሬ አየሁት። “በኸኸኸኸኸ!” ብሎ ግን የደገመው መሰለኝ በበግኛ። ምን አስዋሸኘኝ እንዴ?! ቂቂቂ!

የማንጠግቦሽን መጠይቅ ለማሟላት አንድ ሁለት ቪላ ጆሮውን ብዬ ሳበቃ ኮሚሽኔን ለመቀበል ቀለበት መንገድ ዳር ተቀጣጠርኩ። አሁን እስኪ ካልጠፋ ቦታ ሰው ቀለበት መንገድ ዳር ይቀጣጠራል? አንዳንድ ሰዎች ቀለበታቸው ውስጥ አልገባ ስንላቸው ቀለበት መንገድ ዳር ይቀጥሩናል። ግርግሩ ደርቷል። ክንፍ ላይ የመደብነው መንገድ የአማካይነቱን ሥፍራ ወስዶ ከተማ መሀል ለመሀል ተዘርግቶ ፀሐይ የሚሞቅ ዘንዶ መስሏል። ‹ቀለበት መንገድ መዝለል ክልክል ነው› ብሎ መለጠፍ ከተከለከለ ቆየ መሰለኝ። ኮሚሽኔን የሚያቀብለኝ ሰው ሲቆይብኝ መንገድ መንገዱን እያሁ አንድ ነገር ማሰብ ጀመርኩ።

ይኼኔ አንዱ አልፎ ሂያጅ አጠገቤ መጥቶ ቆመና አላፊ አግዳሚውን እየቃኘ፣ “እየው ያንን” ብሎ ጠቆመኝ። አንድ ልጅ እግር በግ ተሸክሞ ቀለበት መንገድ ያቋርጣል። “እስኪ አሁን ያ ሲኖትራክ ቢዳምጠው ለማንኛቸው ልናዝን ነው?” እያለ አንገቱን ያወዛውዛል። ይኼን ጊዜ በጣም አጭር ቁምጣ የታጠቀ ስስ ካኔቲራ የለበሰ ፈረንጅ እየሮጠ በአጠገባችን አለፈ። መንገደኛው ሸክሙን አውርዶ የገበያ መንገዱን ረስቶ እንደ ትንግርት ያየዋል። “ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ቀለበት መንገድ ዳር ተለማምዶ መስሎታል ኮከብ የሆነው? አይ ፈረንጅ?” እያለ አላስቀምጥ ሲለኝ እኔ ማዶ አያለሁ። አምጠው ወልደው አንድ ጥሩ ጎልማሳ የሚያደርሱ እናት ቦርሳቸውን እንዳነገቱ ከዘርፋፋው ቀሚሳቸው ጋር እየታገሉ መንገዱን ያጠሩትን አጥሮች ይዘላሉ። ይኼን ይኼን ግን አናይም። በዚህ በዚህ አናፍርም። ምክንያቱስ አትሉኝም? ለጤናው አስቦ ጥጉን ይዞ የሚሮጥ ፈረንጅ ለሕይወታችን ከማንሳሳው ከእኛ ቀድሞ ዓይን ይገባላ። ከዓይን ያውጣችሁ እንጂ ሌላ ምን እላለሁ!

በሉ እንሰነባበት። ኮሚሽኔን ተቀባብዬ ዶሮና በጉን ገዛዝቼ ቤት ላደርስ አሸክሜ ተጣደፍኩ። ቤት ስንደርስ ተሸካሚው ግራ ገባው። “እዚህ ነው ሠፈርዎ?” አለኝ። “አዎ” አልኩት። “ይኼ ነው ቤትዎ?” አለኝ ደግሞ። “ምነው?” አልኩት። አንዳች ነገር የተጠራጠረ መሰለ። መንደሬም ኑሮዬ እንደ ማንኛውም ነዋሪ መሆኑን ሲያይ፣ ዶሮና በግ የመግዛት አቅሜን ሲገምተው ለካ ግራ ገብቶት ኖሯል። “በል እንካ፤” ብዬ 20 ብር ስሰጠው፣ “ከመቶ ብር በታችማ አያዋጣም፤” አለኝና አረፈው። “ትቀበላለህ አትቀበልም?” ስለው፣ “ዋጋዬን ተናግሬያለሁ። ካልከፈሉ እጠቁማለሁ፤” አይለኝ መሰላችሁ? መጣቻ የእኔዋ ማንጠግቦሽ እሳት ለብሳ እሳት ጎርሳ። “ምን ብለህ ነው የምትጠቁመው አንተ?! በዓመት አንዴ በሉ ብለህ እኛን ላይ ነው መንደርተኛው ላይ የምትጠቁመው? የእኔ አንበርብር ምንተስኖት ለፍቶ ሠርቶ፣ ቆጥቦና አብቃቅቶ ኑሮውን በጥበብ የሚኖር አርዓያ ባል ነው። ከጠቆምክ ሰርቆና አምታቶ ከአገር ከሕዝብ ቀምቶ አውሮፓና አሜሪካ ገንዘቡን የሚያሸሸውን ጠቁም። የእኛ በግና ዶሮ መግዛት ገረመህ? አሉልህ እኮ ተነግሮ የማያልቅ የሕዝብ እንባ ያፈሰሱልህ፤” ስትለው ላብ አጠመቀው።

በእሱ ቤት እንግዲህ ‘መኒ ላውንድሪ’ ሊያጋልጥ ጫፍ ደርሶ ነበር። ሀሜትና ትችቱን ባለምደውና ልብ ባልገዛ ኖሮ በዓውደ ዓመት ምድር ጣቢያ አድሬ ነበር። መቼስ የማይለመድ የለም ለመድነው። ክፉንም ደጉን ማለቴ ነው ታዲያ። እንዲያው ስታስቡት ስንቱ ነው አሁን በባዶ ቤት ገንዘቡንና ንብረቱን በጉቦ አሟጦ፣ በፍትሕ ዕጦት ለፈሪሳውያን ባደላ ችሎት ፊት ቆሞ ተረትቶ ፋሲካን በቆሎ የሚያሳልፈው? ስንቱ ያለ ቤትና ያለ ትዳር ቀረ? ስንቱ ተበላ? ስንቱ አበደ? ስንቱ ወደቀ? ስንቱ ከሰረ? “ለሰላሳ ዲናር ሊያጣ ነፍስ ይማር. . .” ያለው እኮ ዘፋኙ ሀቅ ነው። ታዲያ ይሁዳ ዋጋውን እስኪያገኝ እስኪ እኛ አጠገባችን ያሉትን አግኝተው ያጡትን፣ ስቀው ያዘኑትን እያሰብን በዓሉን እናሳልፍ። አይመስላችሁም? በእርግጥም ሞቆ የቀዘቀዘባቸው ስንት ይሆኑ? መልካም ፋሲካ! መልካም ሰንበት!

 

     

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት