Wednesday, October 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊመልካም ምኞት መግለጫዎች

መልካም ምኞት መግለጫዎች

ቀን:

ዓውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ መልካም ምኞት መግለጽ የበርካቶች የረዥም ጊዜ ልምድ ነው፡፡ በበዓላት ዋዜማና በበዓላት ሰዎች በተለያየ መንገድ በጎ ምኞታቸውን ይገላለጻሉ፡፡ ከከተሜነት መስፋፋት ጋር በተያያዘ እንደ ሌሎች ነገሮች ሁሉ ምኞት መግለጫ መንገዶቹ መለወጣቸው አልቀረም፡፡ ዛሬ ዛሬ መልካም ምኞትን በኤሌክትሮኒክስ መገናኛዎች በቀላሉ ማስተላለፍን ብዙዎች ይመርጡታል፡፡ ስልክ መደወል ወይም ቴክስት ማድረግን ቀላል ሆኖ ያገኙታል፡፡ በሌላ በኩል ለበዓል በአካል የሚገናኙ፣ ፖስት ካርድና ሌሎችም ስጦታዎች የሚለዋወጡም ጥቂት አይደሉም፡፡

ቴክስት በማድረግ ረገድ ለቤተሰብ፣ ለዘመድ፣ ለጓደኛ፣ ለሥራ ባልደረባና በተለያየ አጋጣሚ ያወቋቸውን ሰዎች ሁሉ እንኳን አደረሳችሁ የሚሉ እንዳሉ ሁሉ የመልካም ምኞት መግለጫቸውን የቅርብ ለሚሏቸው ሰዎች ብቻ የሚልኩም አሉ፡፡ ቴክስት በአንድ ወቅት የሚቀራረቡ ከጊዜ በኋላ ግን የተራራቁ የሚገናኙበት አንዳንዴ ደግሞ የተጣሉ ሰዎች እርቀ ሰላም የሚያወርዱበት መንገድ ሲሆን ይስተዋላል፡፡ በበዓል ቴክስት በመላላክ ወዳጅነታቸውን ያጠናከሩ አለመረሳሳታቸውን ያሳወቁም ያጋጥማሉ፡፡ በአቅራቢያቸው ለሚኖሩ በአካል ምኞት የሚገልጹም ብዙ ናቸው፡፡

አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች የተለያዩ ሃይማኖታዊ አገላለጾችን በመልካም ምኞት መግለጫቸው እንደሚያካትቱ ገልጸውልናል፡፡ ሃይማኖታዊ ገለጻ ሳያጣቅሱ መልካም በዓል የሚሉም ብዙዎች ናቸው፡፡ በየትኛውም መንገድ ተጠቅሞ ማንኛውም ዓይነት ይዘት ያለው መልዕክት መላላክ ከዓውደ ዓመት ሥርዓቶች ትልቁ እንደሆነ በርካቶች ገልጸውልናል፡፡ እነዚህ ሰዎች ስልካቸው ላይ ቁጥራቸው ላለ ሰዎች በቴክስት፣ ያስተላልፋሉ፡፡ ለቴክስታቸውም ምላሽ ይጠብቃሉ፡፡ የላኩለት ሰው ካልመለሰላቸውም እስከ ማኩረፍ ሊደርሱ ይችላሉ፡፡

አቶ መንገሻ ታደሰ በበዓላት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት የሚልኩላቸው በአማካይ 40 የሚሆኑ ሰዎች አሉ፡፡ መልሰው ቴክስት የማያደርጉላቸው ቢኖሩም ቅር አይሰኙም፡፡ አንድ በዓል አልፎ ለሚመጣው በዓልም መልሰው ይልኩላቸዋል፡፡ ‹‹እንኳን አደረሳችሁ፤ ከነመላው ቤተሰባችሁ መልካም በዓል ይሁንላችሁ፤ በትምህርትና በሥራ አጋጣሚ ለተዋወቅኳቸው ጓደኞቼ እልካለሁ፡፡ አሜሪካ፣ ካናዳና ጄኔቫ ለሚኖሩ ጓደኞቼ ሳይቀር እልካለሁ፤›› ይላሉ አቶ መንገሻ፡፡ ለባለቤታቸውና ለልጆቻቸው ደግሞ ስጦታ ይሰጣሉ፡፡

አብሮ አደጎቻቸውንና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሥራ የተዋወቋቸው ሰዎችን መልካም በዓል ማለትን ትልቅ ቦታ ይሰጡታል፡፡ ‹‹በሐሳብ ዘወትር ከእናንተ ጋር ነኝ የሚል መልዕክት አስተላልፋለሁ፡፡ እነሱም ለካ አልረሳንም ብለው ደስ ይላቸዋል፤››  ይላሉ፡፡ ቴክስት ሲልኩላቸው ከሚመልሱላቸው መካከል አንዳንዶቹ መመለስ ቢያቆሙም እሳቸው ግን አንዴ መላክ የጀመሩለት ሰው መቼም ቴክስቱ እንደማይቀርበት ይናገራሉ፡፡ ሰዎች በተለያየ አጋጣሚ ሲራራቁ ተረሳስተው እንዳይቀሩ በዓላት በጎ ምኞት መለዋወጥ ጥሩ እንደሆነ ያምናሉ፡፡

የዩኒቨርሲቲ ተማሪዋ ሊንዳ ጥላሁን የእንኳን አደረሳችሁ ቴክስት መላክ የምትጀምረው በበዓላት ዋዜማ ነው፡፡ የሞባይል ካርድ ትሞላለች፡፡ ረዘም ያለ ቴክስት ጽፋ ስልኳ ላይ ቁጥራቸው ላላት ሰዎች በአጠቃላይ የግሩፕ ቴክስት ትልካለች፡፡ ስልካቸው የጠፋባት ሰዎች ካሉ ቁጥራቸውን አፈላልጋ ትልክላቸዋለች፡፡ ለበዓል የማታውቀው ሰው እንኳን ቴክስት ቢልክላት መልስ ትልካለች፡፡ ከምትልክላቸው ሰዎች መካከል ያልመለሱላትን እንደምትቀየም ትገልጻለች፡፡ በዓል ካለፈ በኋላ ቢሆንም በምታገኛቸው አጋጣሚ ቅሬታዋን ትነግራቸዋለች፡፡ ከበዓል በኋላ ሊንዳና ጓደኞቿ መካከል ማን ቀድሞ ቴክስት ላከ? ማን አልመለሰም? የሚለው ጉዳይ መነጋገሪያም ይሆናል፡፡ ‹‹ለበዓል ከማንም ጋር አልደዋወልም፡፡ ስጦታ የመቀያየር ልማድም የለኝም፡፡ ቴክስት ግን በጣም ያስደስተኛል፡፡ ስልኬ በየደቂቃው ቫይብሬት ሲያደርግ በዓል በዓል ይለኛል፤›› ትላለች፡፡ ባለፈው ዓመት ለእንቁጣጣሽ ለተጣላቻት ጓደኛዋ ቴክስት ላከች፡፡ መልሳ ልካላት በዛው አጋጣሚ መነጋገር እንደጀመሩ ታስታውሳለች፡፡

እንደ ሊንዳ የመልካም ምኞት መግለጫዎች የሚያስደስቷቸው እንዳሉ ሁሉ ትርጉም አልባ የሚሆንባቸውም ገጥመውናል፡፡ ሰዎች ቴክስት ቢልኩላቸውም መልስ አይሰጡም፡፡ ስጦታ መለዋወጥ ወይም መደዋወልም አስፈላጊነቱ አይታያቸውም፡፡ መደዋወሉም መልዕክት መመላለሱም ካርድ መጨረስ ነው የሚሉም አይታጡም፡፡

የፋብሪካ ሠራተኛዋ ወ/ሮ ሳሳሁልሽ ደምሴ በዓል ትልቅ ውለታ ለዋሉላቸው ሰዎች መልካም ምኞት የሚገልጹበት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ባለቤታቸው በታመሙበት ወቅት ላከማቸው ዶክተር፣ ልጃቸው ለሚወዳት አስተማሪና በተቸገሩበት ጊዜ ለደረሱላቸው የቀድሞ ጎረቤታቸውና አብሮ አደጋቸው በየበዓሉ ይደውላሉ፡፡ ‹‹በዓል አብሮነት የሚጠናከርበት ነው፡፡ በሃይማኖትም በባህልም መልካም መመኘቱ ይደገፋል፤›› ይላሉ፡፡ ባለቤታቸው ውጭ አገር ለሚኖሩ ዘመዶቻቸው ቀን መቁጠሪያ፣ ፖስት ካርድ ወይም ሌላ ነገር ገዝተው ለበዓላት ይልካሉ፡፡

ወ/ሮ ሳሳሁልሽ በጠቀሷቸው መንገዶች ለሚያደርጉት የመልካም ምኞት መግለጫ የተለየ በጀት ይይዛሉ፡፡ በዓል ባለባቸው ወራት የቤት ስልካቸው ከሌላው ጊዜ በበለጠ ይቆጥራል፡፡ ባለቤታቸው ለዘመዶቻቸው የሚልኳቸው ስጦታዎችን ለመግዛት የሚያወጡት ገንዘብም ቀላል አይደለም፡፡

በማስታወቂያ ድርጅት የሚሠራው ምኞት አዲሱ ከጊዜ ወደ ጊዜ መልካም ምኞት የሚገልጽ ቴክስት የሚልክላቸው ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ እንደመጣ ይናገራል፡፡ ‹‹ቀድሞ ስልኬ ላይ ከኤ እስከ ዜድ ላሉ ሰዎች በሙሉ ቴክስት እልክ ነበር፤ አሁን ግን ለሥራ ባልደረቦቼና ለቅርብ ጓደኞቼ ብቻ ነው የምልከው፤›› ይላል፡፡ ሁለተኛ ደረጃና ኮሌጅ አብረውት የተማሩ ሰዎችን ጨምሮ በአንድ አጋጣሚ ያገኛቸው ነገር ግን ጓደኞቹ ላልሆኑ ሰዎችም ቴክስት ይልክ ነበር፡፡ ስልኩ የሌላቸው ወይም የረሱት ሰዎች ቴክስቱ ከደረሳቸው በኋላ ማን ልበል? ብለው የደወሉለት አጋጣሚም ነበር፡፡ እሱ ግን እንደሚልክላቸው ሰዎች ሃይማኖት ለሙስሊም ለክርስቲያንም በዓል ከመላክ ወደ ኋላ አይልም፡፡

አሁን ግን ነገሮች እየተለወጡ ይመስላል፡፡ ቀድሞ ሰዎች ቴክስት ሲደረግላቸው ደስ እንደሚላቸው ስለሚያምን በየበዓሉ ወደ 150 ለሚሆኑ ሰዎች ቴክስት ይልክ ነበር፡፡ ቀስ በቀስ ቁጥሩ ወርዶ አሁን ለአሥር ሰዎች ብቻ ይልካል፡፡ ‹‹አሁን ላይ ቴክስት መላኬ ለሰዎች ደስታ የሚጨምርላቸው ስለማይመስለኝ አልክም፡፡ ለሥራ ባልደረቦቼ የምልከውም ከበዓል በኋላ ስለሚወቅሱኝ ነው፤›› ይላል፡፡ ምኞት ለአለቆቹና በሥሩ ላሉ ሰዎችም ነው ቴክስት የሚልከው፡፡

አንዳንዶች ከሥራ ባልደረቦቻቸው ወይም ከአለቆቻቸው ጋር ጥሩ ግንኙነት ለመፍጠር በበዓላት መልካም ምኞት መግለጫ ቴክስት ይልካሉ፡፡ ለአለቃቸው ያላቸውን አክብሮት በመግለጽ በአለቃቸው ዘንድ የሚሰጣቸውን ግምት ከፍ ማድረግን የሚያስቡም አሉ፡፡ የተቀየሟቸውን ይቅርታ ለመጠየቅ ወይም አዲስ ከተዋወቋቸው ሰዎች ጋር ያላቸውን ወዳጅነት ለማጥበቅ የሚጠቀሙበትም ብዙዎች ናቸው፡፡

የመልካም ምኞት መግለጫ ቴክስት የተላከበትን ጊዜና ይዘቱን ከግምት የሚያስገቡም ገጥመውናል፡፡ አንዳንዶች የግሩፕ ቴክስት ሲላክላቸው ደስ አይላቸውም፡፡ ስማቸውና ቤተሰቦቻቸው ተጠቅሰው እንዲላክላቸው ይፈልጋሉ፡፡ ሌሎች በበዓል ዋዜማ ወይም በበዓሉ ዕለት ጠዋት ካልተላከላቸው ቅር ይሰኛሉ፡፡

በውጭ ተራድኦ ድርጅት የምትሠራው ሰመሀል ግደይ ለምታውቃቸው ሰዎች እንደየቅርበታቸው የመልካም ምኞት መግለጫ ታስተላልፋለች፡፡ በጣም ለምትቀርባቸው ዘመዶቿ ትደውላለች፡፡ ለምትቀርባቸው ጓደኞቿ ደግሞ ልዩ ቴክስት ትልካለች፡፡ ለሥራ ባልደረቦቿና ለተራራቁ ጓደኞቿ የግሩፕ ቴክስት ትልካለች፡፡ ‹‹ቴክስት አንብበው መረዳት ለማይችሉ ትልልቅ ሰዎች ዘመዶቼ እደውላለሁ፡፡ ከጓደኞቼ ጋር ቴክስት መደራረግ የተለመደ ስለሆነ አይቀርም፤›› ትላለች፡፡ ብዙ ጊዜ ሃይማኖታዊ ጥቅሶች በአማርኛ ቴክስት ትልካለች፡፡ የበዓል ዕለት ጠዋት ላይ የሚደርሳት ቴክስት ጥሩ ከሆነ ደግሞ ለሌሎችም መልሳ እሱን ትልካለች፡፡

ሰመሀል እንደምትለው፣ በዓል ላይ በጎ ምኞት መግለጽ መልካም ስሜት ቢፈጥርም ቴክስት መላላክ ግዴታ መሆን የለበትም፡፡ አንዳንድ ሰዎች ለማይቀርቧቸው ሰዎች ቴክስት ልከው እንዲመልሱላቸው መጠበቃቸው አግባብ እንዳልሆነ ታምናለች፡፡ ‹‹ሰዎች ቴክስት መላክን ወይም ሲላክላቸው መመለስን እንደግዴታ ስለሚቆጥሩት ኔትወርክ ይሆናል እንጂ ልኬያለሁ የሚል ምክንያት ያቀርባሉ፤›› ትላለች፡፡ ብዙ ጊዜ የኔትወርክ ችግር ቢኖርም ሰዎች ችግሩ በሌለበት ቀንም የውሸት ምክንያት ከሚጠቀሙ፣ መልዕክት መላላክ እንደማይፈልጉ ቢገልጹ ይሻላል የሚል አስተያየት ሰንዝራለች፡፡

በበዓላት ዋዜማና በበዓል ዕለት የሚሞሉትን ካርዶች መጠን ማወቅ የሚቻልበት መንገድ መኖሩን የጠየቅናቸው የኢትዮ ቴሌኮም የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አብዱልራሒም አህመድ፣ ስለበዓላት ካርዶች ቁጥር የተሠራ ጥናት እንደሌለ አሳውቀውናል፡፡ ድርጅቱ ወርሐዊ የካርድ ሽያጭን የሚያሳይ የፋይናንስ ሪፖርት እንዳለውና፣ የበዓላትና በአዘቦት ቀን መካከል ያለውን ልዩነት ለማወቅ የሪፖርቱን ግራፍ ማጥናት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ ‹‹እስካሁን በዓል ላይ የተሠራ ጥናት ባይኖርም፣ ለበዓላት የሚሞሉ ካርዶች ቁጥር እንደሚጨምር መገመት ይቻላል፤›› ብለዋል፡፡

  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመገረም እየተመለከቱ አገኟቸው]

ምንድነው እንዲህ ቀልብሽን የሳበው? ስለሰላም ኖቤል ሽልማት ዜና እየተመለከትኩ ነበር። እና...

የወሎ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ መመሥረትና የአማራ ክልል ጥያቄ

አማራ የኢሕአዴግ አንዱ መሥራችና አጋር ከሆነው ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ...

የሽንኩርት ዋጋ ሰማይ የነካበት ምክንያት ምንድነው?

ባለፉት ሁለትና ሦስት ሳምንታት የሸማቾችን ኪስ ካስደነገጡ መሠረታዊ ከሚባሉ...

የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ኤግዚቢሽን ማዕከልን እንዲያስተዳድር የተሰጠው ኮንትራት ለምን ተቋረጠ?

በአዲስ አበባ ከተማ ለንግድ ትርዒት ዝግጅት ብቸኛ በመሆን የሚጠቀሰው...