የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በሳምንቱ ካሳለፋቸው ውሳኔዎች ውስጥ የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ከነበሩት አቶ ዮሐንስ ሳሕሌና ረዳቶቻቸው ጋር የነበረውን የውል ስምምነት የቋጨበት መንገድ ተጠቃሽ ነው፡፡ የተቋሙ ውሳኔ በአሠልጣኙና ረዳቶቻቸው ሳይወሰን የፌዴሬሽኑን ብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴ ጭምር እንዲበተን ማድረጉ ተጨማሪ መነጋገሪያ እንደሆነ ይነገራል፡፡
ለብሔራዊ ቡድኑ ቀሪ ሁለት ጨዋታዎች የጊዜያዊ አሠልጣኝ ሹመት ማጽደቁም ታውቋል፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ከብሔራዊ ቡድኑ ውጤት ጋር ተያይዞ ለሚነሱበት ጫናዎች የመጨረሻ መፍትሔ አድርጎ ሲወሰድ የሚስተዋለው አሠልጣኝ ማሰናበትና በምትኩ አዲስ አሠልጣኝ መሾም ብቻ ከሆነ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ይህንኑ አሁን በኃላፊነት ላይ ያለው የፌዴሬሽኑ አመራርም ቀጥሎበታል፡፡ ከድሮ ጀምሮ እስካሁን ባለው ሁኔታ ብቻ ሳይሆን ወደፊትም አሠራሩ ያለውን ቅርፅና ይዘት እንደያዘ የሚቀጥል ስለመሆኑ የሚያጠያይቅ አይመስልም፡፡ ምክንያቱና ለዚህ እንደማሳያ የሚያግዘውን ዳግም መመልከት ይቻላል፡፡
የታሪክ ድርሳናት እንደሚያመላክቱት ከሆነ የአገሪቱ እግር ኳስ በ1936 ዓ.ም. የማስታወቂያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ በነበሩት አቶ ዐምደሚካኤል ደሳለኝ አማካይነት በተደረገ ድጋፍና በአቶ ይድነቃቸው ተሰማ ኃላፊነትና ጥረት የመጀመርያው የኢትዮጵያ ስፖርት ቢሮ በማስታወቂያ ጽሕፈት ቤት ግቢ ውስጥ ተቋቁሟል፡፡ እግር ኳሱ በአገሪቱ ሕጋዊ ህልውና አግኝቶ መንቀሳቀስ ከጀመረ ከሰባት አሠርታት በላይ ማስቆጠሩን መረዳት ይቻላል፡፡ በአዛውንትነቱና በዕድሜ ጠገብነቱ የሚታወቀው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ዛሬም ዕድሜ ከማስቆጠር የዘለለ እንቅስቃሴ እያደረገ ላለመሆኑ ከሚከውናቸው ተግባሮች መረዳት እንደሚቻል አሁንም የብዙዎች እምነት ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ አበው ‹‹ጉልቻ ቢቀያየር ወጥ አያጣፍጥም፤›› እንዲሉ ለአገሪቱ እግር ኳስ ዕድገት በመፍትሔነት አሠልጣኞችን በመሾምና በመሻር ሥራ ተቋሙ ዛሬም ተጠምዶ ይገኛል፡፡ ሆኖም የአገሪቱ እግር ኳስ አሁንም ከዕድገቱ ይልቅ ውድቀቱን እያፋጠነ መሆኑ ለማንም የተሰወረ እንዳልሆነ የሚከተለው ዘልማዳዊ አሠራር ምስክር ነው፡፡
አሠልጣኞችን በመሾምና በመሻር መለወጥ የሚቻል ቢሆንም ኖሮ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከ2002 ዓ.ም. ሰኔ ወር ጀምሮ አምስት ብሔራዊ አሠልጣኞችን ቀያይሮ ስድስተኛውን ደግሞ ከሰሞኑ ይፋ ማድረጉ በማሳያነቱ ከበቂ በላይ ስለመሆኑ የሚናገሩ አሉ፡፡ ከሰኔ ወር 2002 እስከ መጋቢት ወር 2003 ዓ.ም. ድረስ ስኮትላንዳዊው ኢፊ ኦጉራ፣ ከ2003 ዓ.ም. መጨረሻ ጀምሮ ደግሞ ቤልጄማዊው ቶም ሴንቲፌት፣ ከ2004 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ እስከ 2006 ዓ.ም. ድረስ ለተከታታይ ሁለት ዓመታት ያህል በዋና አሠልጣኝነት የቆዩት አሠልጣኝ ሰውነት ቢሻው ሲሆኑ የእሳቸው ጊዜ ከስኮትላንዳዊውና ቤልጄማዊው አሠልጣኞች በተሻለ ብሔራዊ ቡድኑን ከ31 ዓመታት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ በማብቃት ተጠቃሽ ሆነው ይጠራሉ፡፡ እሳቸው በተቋሙ የተለመደ አሠራር እንዲሰናበቱ መደረጉም አይዘነጋም፡፡ በዚህ ምክንያት በፖርቱጋላዊው ማሪያኖ ባሬቶ ቢተኩም የተናፈቀውና ጭላንጭል የታየበት እግር ኳስ ሳይጠበቅ እንዲጠፋ ሆነ፡፡ በውጤቱ ማሽቆልቆል መነጋገሪያ የሆኑት ፖርቱጋላዊው ማሪያኖ ባሬቶም ከ11 ወራት ቆይታ በኋላ ፌዴሬሽኑ አሁንም እንደ ብቸኛ መፍትሔ አድርጎ በሚወሰደው ውሳኔ የአሠልጣኙ የስንብት ውሳኔ ይፋ ሆነ፡፡ አሁንም ከአሠልጣኙ ሹም ሽር ጎን ለጎን የሌሎች አገሮች ተሞክሮ ምን ይመስላል? የሚለውን ቆም ብሎ ለማሰብ ፍላጎት ያሳየ አመራርም ሆነ ባለሙያ አልተገኘም፡፡
የማሪያኖ ባሬቶን ስንብት ተከትሎ ደግሞ በትውልድ ኢትዮጵያዊ በዜግነት አሜሪካዊ የሆኑት አሠልጣኝ ዮሐንስ ሳሕሌ ከሚያዝያ 2007 ዓ.ም. ጀምሮ የስንብታቸው ዜና እስከተሰማበት ሚያዝያ 2008 ዓ.ም. ድረስ ዋልያዎቹን በዋና አሠልጣኝነት ይዘው ቆዩ፡፡ ይኼ ሁሉ ሲሆን ግን ዛሬም ሕዝብና መንግሥት የሚናፍቁት የአገሪቱ እግር ኳስ ውድቀቱ ካልሆነ ስለትንሣኤው ሲነገር መደመጥ አልቻለም፡፡ ጊዜያዊ ተቃውሞዎችንና ጩኸቶች በማብረጃነቱ የሚታወቀው የአሠልጣኞች ሹም ሽር እንዲቀጥል ተደርጓል፡፡ አሁንም ለምን? ብሎ የሚጠይቅ አካል አልተገኘም፡፡
እግር ኳሱን በበላይነት የሚያስተዳድረው ብሔራዊ ፌዴሬሽኑም ሆነ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት አሁንም ሌላ አሠልጣኝ ተሹሞ እንዲሞከር ከማድረግ ባለፈ ቆም ብሎ ማሰብ የሚችል አዕምሮ አላገኙም፡፡ ቀጣዩን የኃላፊነት ወንበር የሚረከቡት አዲሱ አሠልጣኝ እንደተለመደው የተመቻቸላቸው ምንም ነገር ሳይኖር ማንነታቸው ታውቋል፡፡ እንደ ሪፖርተር ምንጮች ከሆነ አዲሱ የዋሊያዎቹ አሠልጣኝ የመከላከያው አሠልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ 90 በመቶው ለሹመቱ ቅርብ ናቸው፡፡ ከእሳቸው ጋር ዕጩ ሆነው ከቀረቡት ውስጥ የሐዋሳ ከነማው ውበቱ አባተ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ ፀጋዬ ኪዳነማርያምና የአዳማ ከነማው አሠልጣኝ አሸናፊ በቀለ በቅደም ተከተሉ የተቀመጡ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ቀጣዩን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከወር በኋላ የሌሴቶ አቻውን ከሜዳው ውጪ የሚገጥም ሲሆን፣ የመጨረሻ ማጣሪያውን ደግሞ በሜዳው የሲሼልስ አቻውን እንደሚያስተናግድ ይጠበቃል፡፡
********
የአዲስ አበባ ብስክሌት ትኩረት እያገኘ ነው
በደረጀ ጠገናው
ከእግር ኳስና አትሌቲክስ ቀጥሎ በአገሪቱ በተወዳጅ ስፖርትነቱ ይጠቀሳል፡፡ በአሁኑ ወቅት በይፋ ሊጀመር የሦስት ወር ዕድሜ ብቻ በቀረው የሪዮ ኦሊምፒክ አገሪቱ ከአትሌቲክሱ ቀጥሎ የምትወከልበት የስፖርት ዓይነት መሆኑም ታውቋል፡፡ የብስክሌት ስፖርት በኢትዮጵያ ቀደምት መሆኑ ቢነገርለትም የዕድሜውን ያህል ውጤታማ አለመሆኑም ይነገርለታል፡፡
የአዲስ አበባ ብስክሌት ፌዴሬሽን ታሪካዊውን የብስክሌት ስፖርት ወደ ቀድሞ ዝናውና ክብሩ ለመመለስ በከፍተኛ ደረጃ እንቅስቃሴ እያደረጉ ከሚገኙ ክልሎች አንዱ ስለመሆኑ የአዲስ አበባ ብስክሌት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ረዘነ በየነ ይናገራሉ፡፡ እንደ ኃላፊው ስፖርቱ በአዲስ አበባና በሌሎችም ክልሎች ተጠናክሮ መቀጠል ይችል ዘንድ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ በተለያዩ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ወጣቶች የሚሳተፉባቸው የብስክሌት ውድድሮች ካለፈው ዓርብ ሚያዝያ 22 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ሻምፒዮናዎች በመከናወን ላይ እንደሚገኙ፣ የፍጻሜውና የመጨረሻው ውድድር ደግሞ የፊታችን እሑድ የሚጠናቀቅ መሆኑ ታውቋል፡፡
በወጣው ፕሮግራም መሠረት ባለፈው ዓርብ በተከናወነው ዓመታዊ የኮርስ ብስክሌት በመጀመርያውና 74.8 ኪሎ ሜትር በሚሸፍነው የግል ውድድር ኤርትራዊው ስደተኛ ዳንኤል ተክላይ ርቀቱን 1፡3፡46 በሆነ ጊዜ አጠናቆ አሸናፊ መሆኑ ታውቋል፡፡ የኤሌክትሪኩ አሰግድ ኃይሉና የኢትዮጵያ ወጣቶች አካዴሚው ዳዊት ገብረ ኢየሱስ ርቀቱን 1፡33፡46 እና 1፡33፡47 በሆነ ጊዜ አጠናቀው ሁለተኛና ሦስተኛ በመሆን አጠናቀዋል፡፡ ለተወዳዳሪዎቹ የ3,500፣ 3,000 እና 2,500 ብር ወጪ የተደረገላቸው የዓመት በዓል በጎችና በጥሬ ገንዘብ ደግሞ 1,500፣ 1,000 እና 800 ብር ተሸላሚ ሆነዋል፡፡
በሁለተኛውና 44 ኪሎ ሜትር በሚሸፍነው ማውንቴን ብስክሌት ደግሞ ብሩክ ሀብቴ ከኤሌክትሪክ 1፡12፡26፣ ብርሃኔ አበራ ከወጣቶች አካዴሚ 1፡12፡27 እና ቴድሮስ ታደሰ ደግሞ ከጋራድ 1፡12፡48 አጠናቀው፣ ከአንድ እስከ ሦስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል፡፡ ተመሳሳይ የበግና የገንዘብ ሽልማትም ተበርክቶላቸዋል፡፡ በመጨረሻም 15.4 ሜትር በሚሸፍነው ታዳጊዎች ደግሞ በግል የተወዳደሩት አበርታ ጉደታ፣ ይበልጣል ደርብና እሱእንዳለው ሥዩም ተከታትለው በመግባት አሸናፊ መሆናቸው ታውቋል፡፡ የገንዘብ ሽልማትም ተበርክቶላቸዋል፡፡ ሰኞ ሚያዝያ 24 ቀን 2008 ዓ.ም. 60 ኪሎ ሜትር በሚሸፍነው የቡድን ውድድር ደግሞ የኢትዮጵያ ወጣቶች አካዴሚ፣ ጋራድና የኤሌክትሪክ ብስክሌተኞች ተከታትለው በመግባት ማሸነፋቸው ታውቋል፡፡ ውድድሩ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ከፍተኛ ትብብርና ድጋፍ ያደረገ መሆኑንም አቶ ረዘነ አክለው ገልጸዋል፡፡