‹‹የምንኖርባት ዓለም የትግል ሜዳ ናት፤ የዕለት ተዕለት ኑሮአችን ሁሉ በትግል የተሞላ በመሆኑ በሥጋዊም ሆነ በመንፈሳዊ ኑሮአችን ከትግሉ ማምለጥ አንችልም፤ እውነቱ ይህ ከሆነ የሚያዋጣው ከትግሉ መሸሽ ሳይሆን ታግሎ ማሸነፍ ነው፡፡››
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ፣ የዘንድሮውን የፋሲካ በዓል ምክንያት በማድረግ ካስተላለፉት መልእክት የተወሰደ፡፡ የኢትዮጵያ ክርስቲያኖችና በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ኦርቶዶክሳውያን የፋሲካን በዓል ሚያዝያ 23 ቀን 2008 ዓ.ም. አክብረዋል፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በፋሲካ ሌሊት በፓትርያርክ ወርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ማትያስ ቀዳማዊ መሪነት፣ የትንሣኤውን ብሥራት የሚያመለክተው ‹‹ቅዱስ እሳት›› የተለኮሰ ሲሆን፣ ሥርዓተ ቅዳሴውም ተከናውኗል፡፡ በእሥራኤል ኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ዴር ሱልጣን ገዳምም በተመሳሳይ ሥርዓት ተከብሯል፡፡