Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊሴቶችን በአይሲቲ ዘርፍ

ሴቶችን በአይሲቲ ዘርፍ

ቀን:

ሳሬም በላቸው የአሥረኛ ክፍል ተማሪ ስትሆን ቢዝነስ ውስጥ የመግባት ህልም አላት፡፡ በመላው ዓለም ብዙ ሸማቾችን በቀላሉ ለመድረስም አብዛኛውን ሥራዋን ማከናወን የምትሻው በኮምፒዩተር በመታገዝ እንደሆነ ትናገራለች፡፡ ‹‹ሰዎች የሚገበያዩትና እርስ በርስ የሚገናኙትም በኤሌክትሮኒክስ መገልገያዎች ስለሆነ ለቢዝነሴ ኮምፒዩተር መጠቀም እፈልጋለሁ፤›› ትላለች፡፡ ታዳጊዋ ስለኦንላየን ግብይትና ሌሎችም ቢዝነስና ቴክኖሎጂን ስለሚመለከቱ ነገሮች መረጃ ቢኖራትም ጠለቅ ያለ እውቀት የምታገኝበት መንገድ አላገኘችም፡፡

በምትማርበት ሳንፎርድ ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት በኩል ገርልስ ኢን አይሲቲ ደይ ወደተሰኘ ዝግጅት መጋበዟ መልካም አጋጣሚ ተፈጠረላት፡፡ ከዝግጅቱ ኮምፒዩተር ነክ እውቀቶችን እንደምታገኝም ተስፋ አደረገች፡፡ በዝግጅቱ ላይ ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ሴት ተማሪዎች የተገኙ ሲሆን፣ የኮምፒዩተር እውቀታቸውን የሚያዳብሩ ጽሑፎች ቀርበውላቸዋል፡፡ ከተለያዩ አገሮች የተውጣጡና በትልልቅ የአይሲቲ ተቋሞች የሚሠሩ ሴቶችም ተሞክሯቸውን አካፍለዋቸዋል፡፡ ‹‹እንደ ፌስቡክ ባሉ ግዙፍ የአይሲቲ ተቋሞች የሚሠሩ ሴቶች ካካፈሉን ተሞክሮ፣ ማንኛዋም ሴት በኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ (አይሲቲ) ዘርፍ ተሰማርታ ውጤታማ መሆን እንደምትችል ተረድቻለሁ፤›› ትላለች ሳሬም፡፡

በኢንተርናሽናል ቴሌኮሙዩኒኬሽን ዩኒየን (አይቲዩ) የሚዘጋጀው ገርልስ ኢን አይሲቲ ደይ ዓመታዊ ዝግጅት ሲሆን፣ ላለፉት አራት ዓመታት በ150 አገሮች ተካሂዷል፡፡ በዓለም ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ታዳጊ ሴቶችን የሚያሳትፈው ገርልስ ኢን አይሲቲ፣ በአፕሪል ወር በአራተኛው ሐሙስ ይካሄዳል፡፡ ኢትዮጵያም ዝግጅቱን ከሚያስተናግዱ አገሮች አንዷ ናት፡፡ የዘንድሮው ዝግጅት ሐሙስ ሚያዝያ 20 ቀን 2008 ዓ.ም. በአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ ሲካሄድ ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ሴት ተማሪዎች ተገኝተው ነበር፡፡

ተማሪዎቹ የአይሲቲ ዕውቀታቸውን የሚመዝኑ ፈተናዎች ተሰጥተዋቸው፣ ከየትምህርት ቤቱ ያሸነፉት ተማሪዎች የሁዋዊ ስማርት ፎን ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ ከተሸላሚዎቹ አንዷ የሆነችው ሳሬም፣ በሽልማቱ እንደተደሰተችና ጥሩ ማበረታቻ እንደሆናት ትናገራለች፡፡ ሴቶች በአይሲቲ ዘርፍ እንዲሰማሩ መበረታታት እንዳለባቸው ታምናለች፡፡ ሴቶች ከማኅበረሰቡና ከአይሲቲ ተቋሞች ከሚደረግላቸው ማበረታቻ በተጨማሪ፣ ጠንክረው ማንኛውንም ፈተና መጋፈጥ እንዳለባቸውም ትናገራለች ታዳጊዋ፡፡

የገርልስ ኢን አይሲቲ ዝግጅት እንደ ሳሬም ያሉ ታዳጊዎች በአይሲቲ ዘርፍ እንዲሰማሩ ለማበረታታት ያለመ ዝግጅት እንደሆነ የአይቲዮ የአፍሪካ ቅርንጫፍ ዳይሬክተር ሚስተር አንድሪው ሩጄጄ ይናገራሉ፡፡ ዳይሬክተሩ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ዝግጅቱ ታዳጊ ሴቶች በአይሲቲ ዘርፍ ያሉ የሥራ አማራጮችን እንዲያውቁ መረጃ ይሰጣል፡፡ ‹‹ብዙዎች የአይሲቲ ዘርፍ የወንዶች ብቻ እንደሆነ ያስባሉ፡፡ ይህ ስህተት ነው፤›› የሚሉት ዳይሬክተሩ፣ ሴቶች ከወንዶች እኩል ዕድሉ ከተሰጣቸው ስኬታማ እንደሚሆኑ ያስረዳሉ፡፡

የገርልስ ኢን አይሲቲ ቀን ሲዘጋጅ ታዳጊ ሴቶች ላይ የሚያተኩረው በአይሲቲ ከሌላው ማኅበረሰብ እኩል ዕድል ስላልተሰጣቸው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በአንድ ጊዜ ለውጥ ለማምጣት ባይቻልም ከጊዜ ወደ ጊዜ ሴቶች በአይሲቲ ያላቸው ተሳትፎ እየሰፋ እንደመጣ ያምናሉ፡፡ በዝግጅቱ ሴቶች ስለአይሲቲ መረጃ እንዲኖራቸው ከማድረጋቸው በተጨማሪ በማኅበረሰብ ድረገጾች ያላቸውን ተሳታፊነት ለማሳደግም ይሞክራሉ፡፡

በአፍሪካ ኅብረት የተካሄደውን ዝግጅት የታደሙት ታዳጊ ሴቶች አዲስ አበባ ውስጥ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ እንደመሆናቸው ስለአይሲቲ መጠነኛ እውቀት ሊኖራቸው የሚችልበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡ በሀገሪቱ ገጠራማ አካባቢዎች ያለው እውነታ ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ዝግጅቱ ከከተማ ቀመስ አካባቢዎች በተጨማሪ በኢትዮጵያ ገጠራማ አካባቢዎች የሚኖሩ ታዳጊ ሴቶችን ያማከለ ቢሆን የበለጠ ውጤታማ አይሆንምን? የሚል ጥያቄ ለሚስተር አንድሪው ቀርቦ ነበር፡፡ እሳቸው እንዳሉት፣ ከአዲስ አበባ ውጪ ያሉ ታዳጊ ሴቶችን የማሳተፍ ዕቅድ ይዘው ነበር፡፡ ዘንድሮ ባይሳካም በቀጣይ በክልል ከተሞች ያሉ ታዳጊ ሴቶችን በማሳተፍ ከከተማ ሴቶች ጋር ልምድ እንዲለዋወጡ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

ዳይሬክተሩ እንደተናገሩት፣ በዝግጅቱ ታዳጊዎቹ በአይሲቲ ዘርፍ ስኬታማ ከሆኑ ሴቶች ተሞክሮ የሚማሩበት ዕድል መፈጠሩ የጐላ ጥቅም አለው፡፡ ‹‹ስኬታማ ሴት የአይሲቲ ባለሙያዎች ወይም በአይሲቲ ተቋሞች የሚሠሩ ሴት ሚኒስትሮች የደረሱበትን ቦታ በማየት ታዳጊዎቹ በአይሲቲ ዘርፍ ለመሰማራት ይነሳሳሉ፡፡ ሴቶቹ የደረሱበት ቦታ ለመድረስ ማድረግ ያለባቸውንም ከሴቶቹ የሕይወት ተሞክሮ ይማራሉ፤›› ይላሉ፡፡  

ለታዳጊዎቹ ንግግር ካደረጉ ሴቶች አንዷ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ፎር ኢንፍራስትራክቸር ኤንድ ኢነርጂ ኮሚሽነር፣ ዶ/ር ኢልሀም መሐመድ አህመድ ኢብራሂም ናቸው፡፡ አይሲቲ በዓለም ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ዘርፍ እንደሆነና ሴቶች በዘርፉ ያላቸው ተሳትፎ መጨመር እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ ‹‹ሴቶች በአይሲቲ ላላቸው ተሳትፎ ትኩረት መሰጠት አለበት፡፡ ከአይሲቲ በተጨማሪ ሌሎችም ዘርፎች በስፋት ቴክኖሎጂ ስለሚጠቀሙ ስለአይሲቲ ያላቸው እውቀት መስፋት አለበት፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የኮሙዩኒኬሽንና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ኤፍራህ አሊ በብዙ ሀገሮች በአይሲቲ ተቋሞች ውስጥ የሚሠሩ ሴቶች ውስን እንደሆኑና አፍሪካ ውስጥ ደግሞ በጣም አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ሴቶች በዘርፉ እንደተሰማሩ ተናግረው፣ ለውጥ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡ ‹‹ሴቶች እያደገ ባለው የአይሲቲ ዘርፍ የሥራ ዕድል እንዲኖራቸው እንፈልጋለን፡፡ በአይሲቲ ዘርፍ ስላሉ የሥራ ዕድሎች ሴቶች ሊያውቁና ሊበረታቱ ይገባል፤›› ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት በዘርፉ የሚያደርገውን ጥረት እንደ አይቲዩ ያሉ ዓለም አቀፍ ተቋሞች እገዛ ሲታከሉበት የበለጠ ውጤታማ እንደሚሆን አክለዋል፡፡       

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...