Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

እንዴት ተቀለደ እባካችሁ?

እነሆ መንገድ! ከአያት ወደ መገናኛ ልንጓዝ ነው። የሄድንበትን ደግመን ልንሄድበት  የተጓዝንበትን ደግመን ልንጓዘው አቀበቱንም ቁልቁለቱንም ተያይዘነዋል። ይህም ለዛሬ ድልና ሽንፈት ሆኖ ይቆጠራል። ታሪክ ጸሐፊ ያለፈውንና የሚመጣውን አቀናጅቶ በሚያሰናኝበት የብራና ቅኝቱ የሚከተብና የማይከተብ ሀቅ እዚህ ጎዳና ላይ ይቀመራል። የታክሲያችን ወያላ የሚጠግብ አይመስልም።  “እህ ትሄጃለሽ እሙዬ? እ? አጎቴ? አክስቴ? አባቴ? እናቴ?” እያለ ያልተዛመደውን እያዛመደ አፉ ሰው ያጠምዳል። “ኧረ እንሂድ? ከቤት እስኪወጡ ልትጠብቃቸው ነው? ሞልቷል እኮ፤” ይሉታል መጨረሻ ወንበር የተቀመጡ። “የት  ለመድረስ ነው ይህን ያህል ችኮላ? ግፋ ቢል አንድ እንቁጣጣሽ፣ አንድ ገና፣ አንድ ዓረፋ፣  አንድ ረመዳንና አንድ ፋሲካ ናቸው የሚቀሩን። ስንገፋው የማይገፋ ስናልፈው የማያሳልፍ የመፈጠር ዕዳ፤” ብሎ ወያላው ወደ ሾፌሩ እየተገላመጠ ምልክት ሰጠው። ሾፌሩ ማንቀሳቀስ ጀመረ።

 “አንዳንድ ስትላቸው ቀላል ይመስላሉ። ሲመጡ ጭንቁን የምናውቀው የወለድነውና የከበድነው ነን።  እናተማ ምን አለባችሁ?” ብለው መሀል መቀመጫ ላይ የተቀመጡ ወይዘሮ አጠገባቸው ለተቀመጠ ጎልማሳ አጉተመተሙ። “እኛ እነማን ነን?” አላቸው ወያላው። “ወጣቶች! በየሄዳችሁበት ለምዳችሁ ያገኛችሁትን ተካፍላችሁ በጎደለባችሁ ተጽናንታችሁ ታልፉታላችሁ። የወለደ ግን ስንት ጭንቅ አለበት መሰለህ? ልጅ የለመደውን ነገር በቀላሉ አይረሳልህም። የኑሮ ውድነት፣ የቤት ኪራይ፣ የገንዘብ የመግዛት ዋጋ ማሽቆልቆል ለእሱ ምንም ናቸው፤” ሲሉት፣ “እዚህ ሠፈርም ኑሮ ይወደዳል እንዴ? አይመስለኝም ነበር። ለማንኛውም ለሚመጣው እሱ ያውቃል አይዞን፤” ብሎ እጁ ላይ ያለውን ገንዘብ መቁጠር ጀመረ። “ምን አልፎ ነው ለሚመጣው እሱ የሚያውቀው? ሌላ ጎርፍ ጎረፈ እንዴ?” ብላ መጨረሻ ወንበር የተሰየመች ወጣት ስትጠይቅ “ኧረ ዝም በይው። በሰላም አገር በሰላም ያለፍነው ዓውደ ዓመት እኮ ነው እንዲህ ምጸት ያስመስለው፤” ይላታል ከጎኗ። ድሮስ ደስታና እርካታ ለጎደለበትና ላልጎደለበት እኩል ነው እንዴ?!

ጉዟችን ከተጀመረ ቆይቷል። ከሾፌሩ ጀርባ የተቀመጠ ወጣት፣ “ከእንግዲህ ፆም መቼ ነው?” ብሎ ይጠይቃል። “ምንድነው ነገሩ? ገና ከመፍታታችን ፆም ይለናል እንዴ?” ጎልማሳው ይበሳጫል። “ወዶ መሰለህ? ኑሮ እኮ ነው እንዲህ የሚያናግረው?” ትለዋለች ወይዘሮዋ። “እንግዲህ ረቡዕም ዓርብም የለለት። ምን ሊሆን ነው ታዲያ?” ትላለች መጨረሻ ወንበር ከተሰየሙት ወጣቶች። “ካልታወጀ መፆም አይቻልም ማለት ነው?” ይላል ሌላው። “ኧረ ይቻላል። አፍ ብቻ ሆነን እንጂ፤” አለ ጎልማሳው። “እንዴት?” አለው ወሬውን የጀመረው ወጣት። “እንዴት ጥሩ ነበር እንዴት ባይ ባይጠፋ፤” ካለ በኋላ ጉሮሮውን ጠራርጎ “ፆም ሲባል እኛ የሚመስለን አፍ የሚቀምሰውና የማይቀምሰውን ጎራ መለየት ነው። ከዚያ በዘለለ ግን የፆም አዋጅ ሲታወጅ አናከብር አናስከብር ብለን ይኼው እንተራመሳለን፤” ሲል ወይዘሮዋ አቋርጣ “የምን አዋጅ ነው?” አለችው።

“አስጨርሱኛ ሺሕ ዓመት አላወራ። ሆሆ! . . .  ለምሳሌ የሙስና ፆም አውጁ ብለን በመልካም አስተዳደርና በፍትሕ ዕጦት ተማረን ካሳወጅን ስንት ጊዜ ሆነን? የሥጋና የአትክልት ተዋጽኦ ምግቦች መለየቱ ላይ የሚያክለን የለም። ፃድቅና ኃጥያተኛ ብሎ ለመፈረጅ የሚደርስብን የለም። የአገርና የሕዝብ ጥቅም የማስጠበቅ ፆም ላይ ግን ዜሮ ነን። አንተባበርም። ሙሰኛ አላስኖረን አለ እያልን እሪ ስንል ውለን ከመድረክ ስንወርድ ቀንደኛ አባባሾቹ፣ ሸጓጮቹ፣ አባባዮቹና አደፋፋሪዎቹ እኛው ሆነን እንገኛለን፤” ብሎ ሲያበቃ በረጅሙ ተነፈሰ፡፡ “ለካ ከምንፆመው የምናፈርሰው የፆም ብዙ ነው እናንተ?” ስትል ወይዘሮዋ ንግግሩን ተረድታ “አዋጅ ቢንጋጋ ልብ ለሀቅና ለህሊና ካልተዋጀ ምን ዋጋ አለው?” ብለው መጨረሻ ወንበር ተጨናንቀው የተቀመጡ አዛውንት አጉረመረሙ። የማናጉረመርምበት ነገር የለ መቼስ!

ጨዋታው ደርቷል። ወያላው ሒሳብ እየተቀበለ ነው። ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተቀመጠ ወጣት ስልክ ተንጫጫ። አነሳውና ማውራት ጀመረ። ዘመዱን እንደሚያናግር ገብቶናል። አጠር አጠር አድርጎ መልሶ በዓል በመልካም እንዳለፈለት አብሥሮ ከዘጋው በኋላ፣ “ይቀልዳል እንዴ?” ሲል ሰማነው። “ምነው?” አለው አጠገቡ የተሰየመ ሌላ ወጣት። “ለበዓል ምነው ሳትደውልልኝ?’ ብሎ አኩርፌሃለሁ ይለኛል። ደመወዜ ስንት እንደሆነ ያውቃል? የቤት ኪራይ ስንት እንደምከፍል ያውቃል? ካርድና ቴሌ እንደ ሜሲና ሱዋሬዝ እንዴት በቅንጅት እያጠቁን እንዳሉ ያውቃል? ስንቱን አስታውሼ ስንቱን እተዋለሁ?” አለው። “ኧረረረረረረረረ! የካርድን ነገርማ አታንሳው። የዘንድሮ ዳኛና ቴሌ አንድ ሆነዋል እኮ፤” አለች መጨረሻ ከተቀመጡት አንዷ። “የምን ዳኛ?” አሏት አዛውንቱ ግራ ገብቷቸው። “የኳስ ነዋ። ደግሞ ሌላ ዳኛ አለ እንዴ? ስትላቸው፣ “እሱስ ላይ በሰማይ ከተመጠው ሌላ ዳኛ ጠፍቷል ዘንድሮ። እንዲያው ብቻ ምን ለማለት እንደፈለግሽ አልገባኝም ነበር፤” አሏት።

 “በቃ ቴሌንና አንድ የእግር ኳስ ግጥሚያ የሚዳኝን ዳኛ ሲያመሳስላቸው የማየው ነገር ስላለ ነው። ዘንድሮ ቢጫ ሳያሳዩ ከጨዋታው ኔትወርክ በቀይ የሚያሰናብቱት ዳኞች ኳሱ ላይ በዝተውብኛል። ቴሌም ድሮ ድሮ  ‘ሒሳብዎ እያሽቆለቀለ ነው’፣ ‘ተንጠንቁ’፣ ‘ታክል አታብዙ’፣ ወዘተ ማስጠንቀቂያዎች ነበሩት። እህ? ብቻ ገና ካርዱ ከመግባቱ በይቅርታ አሳበው ቀይ!” ስትል አንዳንዱ ሳቀ። “ታዲያ መፆም ነዋ፤” አሏት አዛውንቱም እየሳቁ። “ከምኑ?” ግራ ገብቷት። “ከወሬው! እኛም እኮ አይታወቀንም እንጂ ብዙ እናወራለን፤ ሲሉ ጎልማሳው ጣልቃ ገብቶ፣ “እኮ ታዲያ በምን እንደበር?” አላቸው። “እንዲህ እያላችሁ እኮ ነው የዛሬ ልጆች የሚደበርባችሁ የበዛው። አማራጭ መፍጠር፣ መንቀሳቀስና መሥራት ነዋ። አገሩን፣ ሲስተሙንና መንገዱን ለመረከብ መዘጋጀት። ከዚያ በሰላም መውሰድ። የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ምን አሉዋችሁ? እናንተ መጥታችሁ ካልወሰዳችሁት ማንም እንኩ ብሎ አይሰጣችሁም አላሉም? ግን አደራ መንጠቅና መቀበል ይለያያል ብለዋል እሳቸው፤” ትዝ ያለውም ያላለውም በናፍቆት አሽካካ። ሳቁ ሲያባራ ዝምታ። ፖለቲካና ኮረንቲን አጣምሮ ለሚመለከት ተሳፋሪ መንጠቅም ሆነ መቀበል ያስፈራል፡፡ ከእሳት አሎሎ ጋር ማን ይጫታል? እውነትም ግን መደበሪያ ጠፍቷል!

ወያላው መልስ እየመለሰና በመኃል አቋርጦ ትርፍ እየደረበ ጉዟችን ቀጥሏል። “ምናለበት የበላነው እስኪንሸራሸር ባትደርብብን፤” አለች ወይዘሮዋ ተደርቦ አጠገቧ የተቀመጠው ተሳፋሪ አጨናንቋት። “በሚቀጥለው ፋሲካ እንደምንም ስፖንሰር ፈልገን አምቦ ውኃ እናዘጋጃለን፤” አላት እየሳቀ። “የምን አምቦ ውኃ? ቢቻል አሚር ነው እንጂ፤”  መጨረሻ ወንበር። “ተይ እንጂ ልጄ። እንዲሁም ይኼ ማዳበሪያ ጉድ እየሠራን ተቸግረናል ጭራሽ ሌላ ኬሚካል?” አሏት አዛውንቱ። ከአዛውንቱ በስተግራ ጥጉን ይዞ የተቀመጠ ኮስታራ ወጣት፣ “ምን እኮ ዘንድሮ የተፈጥሮ ሒደቱን የጠበቀ ምግብ መመገብ አልቻልንም፤” ብሎ ተሳፋሪውን ቃኘው። “ኧረ እህል ባፋቸው ቀርቶ በዓይናቸው የማያዩ ወገኖች ያሉባት አገር ናት ተው ጡር ፍሩ፤” ብላ ጋቢና የተቀመጠች ልጅ እግር ጮኸች።

“ታዲያ በጩኸት ነው ጡር የምንፈራው? የአንዳንዱ ሰው ትችት ለማደንቆር እንጂ ለማስተማር አይመስልም እኮ እናንተ፤” ብሎ ጎልማሳው ተቀየማት። “ምን ታድርግ በሎጂክና በውይይት እንዳንማማርማ ጠረጴዛው በሞኖፖል እየተያዘ ተቸገርን፤” አለ ከሾፌሩ ጀርባ ከጎኔ የተቀመጠው ተሳፋሪ። “ፓርላማውን ማለትህ ነው?” ስትለው ከጀርባችን አንዷ፣ “ምነው ምን አደረኩሽ የእኔ እህት? ፈሪሳውያንን ይመስል የሐሰት ክስ ትፈልጊያለሽ፤” አላት። ይኼኔ ወያላው ታክሲዋን እስቁሞ ሎተሪ አዟሪ ጫነ። ሎተሪ ሻጩ የጉዞ ተመኑን ከፍሎ ወጪውን ሊያጣጣ፣ “አሥር ሚሊየን አለ በቅርቡ የሚወጣ፤” ማለት ጀመረ። “እኔ አንተን ቢያደርገኝ ዕጣው እስኪወጣ ሌላ ሥራ እየሠራሁ ከዚህ ሁሉ ቁጥር አንዱን እጠባበቅ ነበር፤” ብትለው ወይዘሮዋ፣ “ዕድሌን አገሬ በልጅነቴ ስትነጥቀኝ ስላየሁ በዕድል አላምንም፤” ብሏት አረፈው። ታክሲያችን መለስተኛ ፓርላማ ባትሆነን ኖሮ ታዲያ ዶሮ ሳይጮህ ተከዳድተንና ተሰቃቅለን አናልቅም ነበር? ዕድልና ባለዕድል ያልተቀያየሙባት አገር ማን ትሆን ግን?

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ጫጫታውና ግርግሩ ጎዳናውን ቀልብ ነስቶት እያየን ታክሲያችን ጥጓን ይዛ እስክታራግፈን አሰፍስፈናል። “አይ አንተ ጎዳና?” አለ አንዱ። “ጎዳናው ምን አደረገን እኛ ነን እንጂ፤” አለው አጠገቡ። “እኛ ምን አደረግን? እነሱ ናቸው እንጂ፤” አለች ከጋቢና። “እነሱና እኛ አንድ አይደለንም እንዴ?” አሉ አዛውንቱ። “ኧረ ምንድነው የኮድ መዓት? ግልጽ አድርጉት አቦ፤” ብሎ መጨረሻ አንዱ ሲጮህ፣ “ግልጽ የሆነው እየተድበሰበሰ የተድበሰበሰውና የማይረባ የማይረባው እየገነነ እያየህ ለምን ግልጽ አድርጉት ትለናለህ?” አለ ጎልማው። “እኮ ምኑን?” አለች ወይዘሮዋ። “ስለጎዳናችን ነው የምንጫወተው፤” ሲላት፣ “ጎዳናችን ምን ሆነ?“ አፈጠጠችበት። “ፍርደ ገምድል በዛው እያለሽ ነው፤” አላት አጠገቤ የተቀመጠው ዞሮ።

“አልገባኝም?” አሁንም ወይዘሮዋ አጥብቃ ስትይዘው፤ “መሰቀል ያለበት ሰቃይ እየሆነ እስከ መቼ ድረስ ነው ቆይ . . . ?” ብሎ ሳይጨርስ፣ “ታዲያ ይኼ ብርቅ ነው? ዓለምና የተዛባ የፍርድ ሚዟና እንደሆኑ ያሉ የነበሩ ወደፊትም የሚኖሩ ጥንዶች ናቸው። እኔ ደግሞ ደህና ነገር የምታወሩ መስሎኝ፤” ስትበሳጭ አዛውንቱ ቀበል አድርገው፣ “እርግጥ ያለና የነበረ ነው። ግን እንዴት ወደፊትም የሚኖር ብለን አብረን እንደረባለን? ካልታገልን መኖራችንን በምን እናውቀዋለን? ካልተፍጨረጨርን ምኑን መተንፈሳችን ይገባናል?” እያሉ ያዙዋት። “እና ምን አድርጉ ነው?” ወይዘሮዋ መለሳለስ ስትጀምር፣ “የማይሞገሰውን ባለማሞገስ፣ ክብር የሚገባውን በማክበር፣ ቅድሚያ የሚሰጠውን በመስጠት፣ መደመጥ ያለበትን በማድመጥ፣ መማር ካለብን በመማር፣ መገሰጽ ያለበትን በመገሰጽ፣ ዓይቶ እንዳላየ ሰምቶ እንዳልሰማ ባለማለፍ የበኩልን ሚና መጨዋት ነዋ፡፡ ይኼም እኮ እስካለን ድረስ ነው፤” ሲሏት ታክሲያችን ጥጓን ይዛ ነበር። ወያላው “መጨረሻ” ብሎን ወርደናል። ጎዳናው እውነትን ሰቅሎ ሐሰትን አሽሞንሙኖ ኩሎ ክቧታል። “ኑ ሐሰትን ሰቅለን እውነትን እናንግሥ፤” የሚል ቢልቦርድ የናፈቀው የበዛ ይመስላል፡፡ በዚህ መሀል ግን ህሊና እንዴት ተቀለደ እባካችሁ እያለ የአዳምን ዘር ይሞግተዋል፡፡ መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት