[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ ቢሯቸው ገባች]
- ምን ፈልገሽ ነው?
- እንግዶች አሉ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- የምን እንግዳ ነው?
- ጋዜጠኞች ናቸው፡፡
- ጋዜጠኞች?
- አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን ፈልገው መጡ?
- ያው አንዳንድ የመሥሪያ ቤታችንን ሥራዎች አስመልክተው ሊያናግሩዎት ነው፡፡
- እኔ ሥራ እንጂ መቼ ወሬ እወዳለሁ?
- ክቡር ሚኒስትር ቀጠሮ ተይዞላቸው እኮ ነው የመጡት?
- የወሬ የለውም ፍሬ አይደል እንዴ ተረቱ?
- ክቡር ሚኒስትር እነሱም እኮ ለሥራ ነው የመጡት፡፡
- ምን ሥራ አላቸው? ወሬኛ ብቻ ተሰብስቦ፡፡
- እኛም እኮ የምንሠራውን ሥራ ለሕዝቡ ማሳወቅ አለብን፡፡
- ሳናወራም ሕዝቡ ሥራችንን ማየት ይችላል፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ቀጠሮ ስለተያዘላቸው ግን መግባት አለባቸው፡፡
- ለመሆኑ የመንግሥት ጋዜጠኞች ናቸው?
- ኧረ የግል ጋዜጠኞች ናቸው፡፡
- እነሱማ ጭራሹኑ አይመቹኝም፡፡
- ለምን ክቡር ሚኒስትር?
- የሚያወሩኝ ስለግል ሕይወቴ ነዋ፡፡
- ስለግል ሀብትዎ ማለትዎ ነው?
- ምን ትዘባርቂያለሽ?
- ምንም፡፡
[ጋዜጠኞቹ ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ ገቡ]
- እንዴት ናችሁ ወዳጆቼ?
- እንዴት ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
- እናንተ እያላችሁ እኛ ምን እንሆናለን?
- ትጋለጣላችሁ እንጂ ምን ትሆናላችሁ?
- ምን አልከኝ?
- ያው አንዳንድ ነገሮች ላይ ብንነጋገር ብለን ነው፡፡
- በነገራችን ላይ ጋዜጠኞችን በጣም ነው የማከብረውና የምወደው፡፡
- እውነት ክቡር ሚኒስትር?
- አዎን ባይገርምህ በዚህ ሳምንት እኮ የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን ይከበራል፡፡
- አውቃለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እናም ይኸውልህ ሁልጊዜ ለትንሳዔ አንድ ፍየል፣ ለዳግማዊ ትንሳዔ ደግሞ ሌላ ፍየል ነበር የማርደው፡፡
- እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- በዚህኛው ዓመት ግን የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን በሁለቱ በዓላት መካከል ስለዋለ ሦስተኛ ፍየል ገዝቻለሁ፡፡
- የሚገርም ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እናም በቃ ይህቺ አገር ያለእናንተ የትም እንደማትሄድ አውቃለሁ፡፡
- በነገራችን ላይ ግን ክቡር ሚኒስትር ደመወዝዎት ይታወቃልና ለበዓል ከየት አምጥተው ነው ሦስት ፍየል የሚገዙት?
- ምን አልከኝ?
- ልድገምልዎት ጥያቄውን?
- ሠርቼ ነዋ የምገዛው፤ ድሮ ከየት አመጣዋለሁ?
- በዚሁ አያይዤ ልጠይቅዎትና መሥሪያ ቤትዎ ውስጥ ከፍተኛ ሙስና አለ ይባላል፡፡
- ሐሰት፣ ሐሰት ይህ የጠላት ወሬ ነው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር በመሥሪያ ቤትዎ የሚፈጸሙ ግዥዎች ያለጨረታ ነው ይባላል፡፡
- እኛ እኮ ጨረታን ያስቀረነው ቢሮክራሲን ለማጥፋት በምናደርገው ጥረት ነው፡፡
- እና ያለጨረታ ግዥ መፈጸሙ ትክክል ነው እያሉኝ ነው?
- ውሸት ነው እንዲህ የሚባል ነገር የለም፡፡
- ቢሮክራሲ ለማስቀረት ነው እንደዛ የምናደርገው ብለውኝ ነበር፡፡
- ሰውዬ የተሰጠህ ሰዓት አልቋል፡፡
- ገና መጀመራችን እኮ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ሥራ አለኝ አልኩህ?
- ከተማችን መሀል ላይ ያለው ሕንፃም የእርስዎ ነው ይባላል፡፡
- የእኔ?
- አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እና የእኔ ቢሆን ምን አለበት? ምቀኛ ሁሉ፡፡
- በልጅዎትና በባለቤትዎም ስም የተለያዩ ቪላዎችን ገንብተዋል ይባላል፡፡
- እና ምን ችግር አለው? እንኳን ቪላ ይኸው ግድቡን ራሱ እየገነባን አይደል እንዴ?
- ግድቡስ በሕዝብ ገንዘብ ነው የሚገነባው፣ የእርስዎ ቪላዎች ከየት በመጣ ገንዘብ ነው የሚገነቡት?
- ከሕዝብ፡፡
- እሺ ክቡር ሚኒስትር፣ ውጭም ቤት አለዎት ይባላል፡፡
- ሰውዬ በቃ የተሰጠህ ጊዜ አልቋል፡፡
- መቼ ጀመርንና?
- እኔ እኮ ስለልማቱ የምታወራኝ መስሎኝ ነው ዕድል የሰጠሁህ?
- ስለልማቱ እኮ ነው እያወራን ያለነው፡፡
- ስለየትኛው ልማት?
- ስለእርስዎ ልማት!
[አንድ ባለሀብት ለክቡር ሚኒስትሩ ደወለላቸው]
- ሄሎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን ፈልገህ ነው?
- ክቡር ሚኒስትር በአስቸኳይ መገናኘት አለብን፡፡
- ለምን ተብሎ?
- በስልክ ላወራዎት አልችልም፣ መገናኘት አለብን፡፡
- እሺ ቢሮ ና፡፡
[ባለሀብቱ ቢሯቸው መጣ]
- ክቡር ሚኒስትር ችግር ውስጥ ነኝ፡፡
- የምን ችግር?
- የእርስዎ ዕርዳታ በጣም ያስፈልገኛል፡፡
- ይኸው ለማንም የማይፈቀድ ኤልሲ አስፈቅጄልሃለሁ አይደል እንዴ? ሌላ ደግሞ ምን ፈለግክ?
- ዕቃውማ ተገዝቶ እዚህ ደርሷል ግን እጄ ሊገባ አልቻለም፡፡
- ለምን?
- የገዛሁት ብረት ጥራቱን ያልጠበቀ ስለሆነ ሊለቀቅልኝ አልቻለም፡፡
- እና ምን ላድርግልህ?
- ያው ክቡር ሚኒስትር እንዲያስለቅቁልኝ ነዋ፡፡
- የሰሞኑን ወሬ መቼም ሰምተሃል አይደል?
- የትኛውን ወሬ?
- የፈረሰውን ፎቅ ነዋ፡፡
- እሱንማ ሰምቻለሁ፡፡
- እና ሌላ ፎቅ እንዲፈርስ ነው ጥራቱን ያልጠበቀ ብረት የማስለቅቅልህ?
- ፎቁ ቢፈርስም እኮ ሰው እስካልጐዳ ድረስ ችግር የለውም፡፡
- ምን አልክ?
- እኔ ደግሞ ለዚህ ጥሩ መፍትሔ አለኝ፡፡
- ምን ዓይነት መፍትሔ?
- ፎቁ ቢፈርስ እንኳን በሌሊት እንዲፈርስ እፀልያለሁ፡፡
- በል አትቀልድ እዚህ ውስጥ አልገባም፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ያን ሁሉ ነገር አድርጌልዎት እንዲህ አሉኝ?
- ስማ በነፃ አይደለም እኮ ያደረክልኝ?
- ለማንኛውም እኔ የማደርገውን አውቃለሁ፡፡
- ምን ልታደርግ ነው?
- እንደ ፎቁ አፈርስዎታለሁ፡፡
- ካፈረስከኝ ግን በእንትን አፍርሰኝ፡፡
- በምን?
- በሌሊት!
[የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸው ቢሯቸው ገባ]
- ይኸው ሪፖርቱ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- አመሰግናለሁ፡፡
- ትናንትና አንጀቴ ቅቤ ጠጣ፡፡
- ምን ተገኝቶ?
- ሌስተር አሸነፈ እኮ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- የእኔ ደግሞ አንጀቴ ቆስሎ ነው ያደረው፡፡
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- ምንም ታሪክ የሌለው ቡድን እንዴት ያሸንፋል?
- እሱ አይደል እንዴ ደስ የሚለው፡፡
- ቡድኑ የሕዝብ ተቀባይነት አለው ወይ? የሚለው ጥያቄ መመለስ አለበት፡፡
- ሁሌ እኮ ታዋቂ ቡድን ሲያሸንፍ ደስ አይልም፡፡
- ምን ነካህ? ሁሌም ልምድ ያለው ቡድን ነው ማሸነፍ ያለበት፡፡
- እኔ ግን ክቡር ሚኒስትር ሌስተር ብዙ ነገር አስተምሮኛል፡፡
- ምንድን ነው ያስተማረህ?
- ያው ክቡር ሚኒስትር ጠንክረው ከሠሩ መድረስ የማይችሉት ነገር እንደሌለ በደንብ አሳይቶኛል፡፡
- ሌላስ ምን ተማርክ?
- የድሮ ታሪክ የትም እንደማያደርስ ደግሞ በነቼልሲ ተመልክተናል፡፡
- እ…
- ይኸው ባለፈው ዓመት ዋንጫ በልቶ በዚህኛው ዓመት ሚድ ቴብል ላይ ይዳክራል፡፡
- እነሱ አይደሉ እንዴ እኔን ያቃጠሉኝ፡፡
- ለመሆኑ የማን ደጋፊ ነዎት?
- የሰማያዊዎቹ፡፡
- የሰማያዊ ፓርቲ?
[ክቡር ሚኒስትሩ ከሾፌራቸው ጋር ወደ ቤት እየሄዱ ነው]
- ክቡር ሚኒስትር ሰምተዋል?
- ምኑን ነው የምሰማው?
- ሰሞኑን የተፈጸመውን ጉድ ነዋ፡፡
- የምን ጉድ ነው? መቼም አንተ ጉድ አታጣ፡፡
- ተደራጅተው ባንክ ስለዘረፉት አልሰሙም?
- በመሣሪያ ነው የዘረፉት?
- ኧረ የለም ሐሰተኛ ሰነዶችን አዘጋጅተው ነው ባንኩን የዘረፉት፡፡
- ምን ያህል ገንዘብ ነው የተዘረፈው?
- ወደ 28 ሚሊዮን ብር ይጠጋል፡፡
- ለመሆኑ ከየትኛው የግል ባንክ ነው የተዘረፈው?
- ኧረ ከመንግሥት ባንክ ነው የተዘረፈው፡፡
- ይኼማ ውሸት ነው፣ ሊሆን አይችልም፡፡
- እንዴ በሚዲያ ተዘግቧል እኮ?
- እኔ ትናንት ቴሌቪዥን ስመለከት አልነበር እንዴ መቼ ሰማሁ?
- አይ ይኼ ጋዜጣ ላይ ነው የወጣው፡፡
- በየትኛው ጋዜጣ?
- የግል ጋዜጣ ነው፡፡
- እኮ ለዛ ነው ውሸት ነው ያልኩህ፡፡
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- የትኛው የግል ጋዜጣ ስለመንግሥት ባንክ ጥሩ ነገር ያወራል ብለህ ታስባለህ?
- ኧረ ክቡር ሚኒስትር ጉዳዩ እኮ ፍርድ ቤት ቀርቧል፡፡
- የትኛው ፍርድ ቤት? የግል ወይስ የመንግሥት?
- የግል ፍርድ ቤት ደግሞ አለ እንዴ?
- ሊኖር አይችልም?
- ለነገሩ የራሳቸው እስር ቤት ያላቸው ባለሀብቶች ያሉበት አገር ስለሆነ፣ የግል ፍርድ ቤትም ሊኖር ይችላል፡፡
- በአጠቃላይ ይኼን ወሬ እኔ አላምንም፡፡
- ለማንኛውም ክቡር ሚኒስትር እኔም አንድ ነገር ገብቶኛል፡፡
- ምንድን ነው የገባህ?
- በጥቃቅንና አነስተኛ መደራጀት እንዳለብኝ ገብቶኛል፡፡
- ምን ለማድረግ ነው የምትደራጀው?
- ለመዝረፍ!