- በተከለከሉ ዘርፎች በተሰማሩ የውጭ ዜጐች ላይ ሰፊ ምርመራ እየተካሄደ ነው
የንግድ ሚኒስቴር ሰፊ የመልካም አስተዳደር ንቅናቄ መጀመሩ ሲሰማ፣ ለቻይና ዜጐች የንግድ ፈቃዳቸውን ያከራዩ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም በሕገወጥ መንገድ የንግድ ፈቃድ አውጥተው ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች ብቻ በተፈቀዱ ሥራዎች የተሰማሩ የውጭ ዜጐች ላይ ትኩረት ተደርጓል፡፡
የንግድ ሚኒስቴር የመልካም አስተዳደር ንቅናቄን በተመለከተ ሪፖርተር ያገኘው ሠነድ እንደሚያመለክተው፣ ሚኒስቴሩ ወደ ዕርምጃ ከመግባቱ አስቀድሞ ሰፊ ግምገማ አካሂዷል፡፡
በዚህ ግምገማም በንግድ ሚኒስቴር በኩል ከተለዩ የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባሮች መካከል የንግድ ምዝገባና ፈቃድ ወረፋን መሸጥ፣ የሥነ ምግባር ችግር ያለባቸው አመራሮች ላይ ዕርምጃ አለመውሰድ፣ ፋይሎችን በመሰወርና ከደላሎች ጋር በመመሳጠር ለግል ጥቅም ገንዘብ መሰብሰብ፣ የነዳጅ መለኪያዎችን በተቀመጠው ስታንዳርድ መሠረት ካሊቢሬት ያለማድረግ፣ ከደረጃ በታች የሆኑ አስገዳጅ የኢትዮጵያ ደረጃ ያላቸው ምርቶችን በሙስና ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ ማድረግና የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡
የተጠቀሱትን ችግሮችን መሠረት በማድረግም የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አራት ዳይሬክተሮች፣ አንድ ምክትል የጽሕፈት ቤት ኃላፊ፣ ስድስት የቡድን መሪዎች፣ ስድስት የገቢና ወጪ ጥራት ቁጥጥር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች ከኃላፊነት እንዲነሱ መደረጉን ሠነዱ ያስረዳል፡፡
በንግድ ማኅበረሰብ በኩል ያሉ ችግሮችን በመለየት ረገድም ፈቃድ ባወጡበት ዘርፍ ያለመሰማራት፣ ከደረጃ በታች የሆኑ ምርቶችን ወደ አገር ማስገባት፣ ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ የተገዛን የኤክስፖርት ምርት ለአገር ውስጥ ገበያ ማዋል፣ ለአገር ውስጥ ዜጐች ብቻ በተፈቀደ መስክ የተገኘን ንግድ ፈቃድ በማከራየት የውጭ ዜጐችን ማሠራት፣ የውጭ አገር ዜጋ ሆኖ ለዜጐች ብቻ የተከለከሉ የንግድ ሥራዎች ላይ መሰማራት የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡
የተጠቀሱትን ችግሮችን መሠረት በማድረግም ዕርምጃ መውሰድ የተጀመረ መሆኑን የሚያስረዳው ሠነዱ፣ በዚህ ረገድ የቻይና ዜጐችን የቀጠሩ በማስመሰል የንግድ ፈቃዳቸውን ያከራዩ አራት ድርጅቶች መታሸጋቸውን ይገልጻል፡፡ እነዚህን ድርጅቶች በቅርቡ ወደ ሕግ ለማቅረብ ይቻል ዘንድም ማስረጃዎችን የማደራጀት ሥራ በመሠራት ላይ መሆኑን ይጠቁማል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተከለሉ የንግድ ሥራዎች በሕገወጥ መንገድ የንግድ ፈቃድ ያወጡ የውጭ ዜጐችን የመለየት ሥራ ከኅብረተሰቡ ጋር በመሆን እየተከናወነ እንደሚገኝ ሠነዱ ያስረዳል፡፡
በዚህ በኩልም እስካሁን በተሰበሰበው ጥቆማ 22 የውጭ ዜጐች የተለዩ መሆናቸውንና ሕጋዊ ዕርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ማስረጃዎችን የማደራጀት ሥራ በመሥራት ላይ መሆኑንና ይህ ዓይነቱ እንቅስቃሴም በቀጣይነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ሠነዱ ይገልጻል፡፡
ደረጃቸውን ያልጠበቁ ምርቶችን ወደ አገር በማስገባትና ለሕዝብ ደኅንነት ሳይጨነቁ ለገበያ ያቀረቡ 200 ነጋዴዎችን የመለየትና ማስረጃዎችን የማደራጀት ሥራ ተጠናቆ፣ ለሕግ የማቅረብ ሥራው በሒደት ላይ እንደሚገኝ ከሠነዱ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ምርት ገበያ የሚሳተፉ 24 የገበያው አባል የሆኑና ወንበር ያላቸው ነጋዴዎች በግብይት መድረኩ ኦፊሰሮች ጋር በመመሳጠር አድራሻቸው ለማይታወቅና አንዳንዶቹም የቡና ላኪነት ፈቃድ ለሌላቸው 54 ግለሰቦች የኤክስፖርት ቡና ገዝተው እንደሰወሩ በማድረጋቸው ከምርት ገበያው አባልነት ታግደው ለሕግ እንዲቀርቡ መደረጉንም ሠነዱ ይገልጻል፡፡