Monday, December 4, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ዘለዓለማዊ ክብር ለጀግኖች አርበኞቻችን ይሁን!

ከ120 ዓመታት በፊት በዝነኛው የዓድዋ ድል ድባቅ የተመታው የኢጣሊያ ወራሪ፣ ከ40 ዓመታት በኋላ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተደራጅቶ ወረራ ሲፈጽም የተመከተውና የተባረረው በዱር በገደሉ በተሰማሩት በጀግኖች አርበኞቻችን ተጋድሎ ነው፡፡ በቤኒቶ ሙሶሎኒ የፋሽስት ፓርቲ የሚመራው የኢጣሊያ ወራሪ ሠራዊት ዳግም ኢትዮጵያን ቅኝ ለመያዝ በተለያዩ አቅጣጫዎች በከፈተው ጥቃት፣ ወደር የሌለው መስዕዋትነት የከፈሉ ጀግኖች አርበኞች ለዘለዓለም ይታወሳሉ፡፡ ለዓለም ጥቁሮች መመኪያ የሆነውን ታላቁን የዓድዋ ድል በተጎናፀፉት ጀግኖች አባቶችና እናቶች እግር የተተኩት ወጣቶቹ አርበኞች፣ በተከታታይ ትውልዶች በምሳሌነት የሚወሳውን ፀረ ፋሽስት ትግል በድል ከተወጡ እነሆ 75 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

ከ40 ዓመታት በኋላ የዓድዋን ሽንፈት ለመበቀል ለዳግም ወረራ የዘመተው የኢጣሊያ ፋሽስት ሠራዊት በዘመኑ በጣም የሠለጠነ፣ እጅግ ዘመናዊ የሚባሉ የነፍስ ወከፍ መሣሪያዎች፣ መትረየሶች፣ መድፎች፣ ታንኮችና የጦር አውሮፕላኖች የታጠቀ ነበር፡፡ በተጨማሪም በዓለም የተከለከለውን የመርዝ ጋዝ ጭምር በመጠቀም ነበር አገሪቷን የተቆጣጠረው፡፡ በወቅቱ እጅግ በጣም አነስተኛ የሆነ ድርጅትና ከግል መሣሪያው (አሮጌ ጠመንጃ፣ ጋሻና ጦር) በስተቀር ያልነበረው የኢትዮጵያ ሕዝብና ጦር የነበረው ጥልቅ የሆነ የአገር ፍቅርና ወኔ ብቻ ነበር፡፡ ፋሽስቶቹ በታጠቁዋቸው ዘመናዊ መሣሪያዎችና የመርዝ ጋዝ አማካይነት ከባድ ጉዳት አድርሰው አገሪቷን ሲቆጣጠሩ፣ ጀግኖቹ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ‹‹ጥራኝ ዱሩ . . .›› ብለው የነፃነት ትግል ጀመሩ፡፡ እነዚህ ዘለዓለማዊ ክብር የሚገባቸው ጀግኖች በታሪክ ሞገሥ የሚያላብሳቸውን ጀግንነት አሳዩ፡፡

በታላቁ የፀረ ኮሎኒያሊስት ትግል በዓድዋ ድል ድባቅ የተመታው የተስፋፊዎች ዕቅድ እንደገና ያንሰራራ የመሰላቸው የፋሽስት ኢጣሊያ ግብረ አበሮች፣ ሙሶሎኒ በኢሰብዓዊ ፍጅት በኢትዮጵያ ላይ ያገኘውን ድል እንደ ታላቅ ስኬት ቢቆጥሩትም፣ ኢትዮጵያውያኑ ጀግኖች ግን ለአንዲት ሰከንድም ከዓላማቸው አልተዛነፉም፡፡ በጊዜው በነበረው ሊግ ኦፍ ኔሽንስ የኢትዮጵያን መወረር በፌዝ ያላገጡበት ጭምር እስከሚያፍሩ ድረስ በዱር በገደሉ የተፋለሙት ጀግኖች አርበኞች፣ የፋሽስት ኢጣሊያን ወረራ ቅዠት አድርገውታል፡፡ ለአምስት ዓመታት በወረራ የያዛትን አገር በቅጡ ማስተዳደር እስኪያቅተው ድረስ በአራቱም ማዕዘናት ፋታ ያሳጡት ጀግኖቻችን ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ በፋሽስቶች ተወራ ከጎኗ የሚቆም ወዳጅ ባጣችበት ጊዜ የታደጓት እነዚህ ዘለዓለማዊ ክብር የሚገባቸው ጀግኖች ልጆቿ ናቸው፡፡

በፋሽስት ኢጣሊያ ላይ የተገኘው ድል ሲወሳ ከአርበኞቻችን በላይ ማንም አይታሰብም፡፡ በወቅቱ ንጉሠ ነገሥቱ ለዲፕሎማሲያዊ ትግል ወጥተው አገሬው ያለ መሪ በቀረበት ወቅት፣ በዱር በገደሉ ተሰማርተው ጠላትን መውጪያ መግቢያ ያሳጡት ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ለድሉ መተኪያ የሌላቸው ዋናው ቁልፍ ነበሩ፡፡ በመጀመርያ ከጥቅማቸው አንፃር ከኢጣሊያ ጎን ተሠልፈው የነበሩት እነ እንግሊዝ፣ ከኢጣሊያ ጋር የነበራቸው ፍቅር ተሟጦ በኋላ ለኢትዮጵያ ድጋፍ ቢሰጡም ከጀግኖች አርበኞቻችን በላይ ለድሉ ተጠቃሽ የሆነ ማንም ኃይል አልነበረም፡፡ ለእናት አገራቸው መቼም ቢሆን ለመሰዋት የቆረጡት ጀግኖች አርበኞች በአገሪቱ አራቱም ማዕዘናት ተሠልፈው ባካሄዱት የሽምቅ ውጊያ የፋሽስት ወራሪን አንኮታኩተውታል፡፡ እነዚህ ዘለዓለማዊ ክብር የሚገባቸው ጀግኖች አርበኞች ለትውልድ አርዓያ የሚሆን የታሪክ ቅርስ ያኖሩ በመሆናቸው መጪዎቹ ትውልዶች ሳይቀሩ ይኮሩባቸዋል፡፡

የጀግኖች አርበኞችን ገድል ስናወሳ በወቅቱ በፍፁም ሊመክቱት ከማይችሉት ኃይል ጋር የተፋለሙበትን ንፅፅር ማየት ጠቃሚ ነው፡፡ በታሪክ ድርሳናት ላይ እንደሠፈረው የኢትዮጵያ ተዋጊዎች የታጠቁት መሣሪያ እጅግ በጣም ኋላቀር ነበር፡፡ ለምሳሌ ዘመን ያለፈባቸው 234 መድፎች፣ ከአንድ ሺሕ የሚያንሱ አሮጌ መትረየሶች፣ በሺዎች የሚቆጠሩ አሮጌ ጠመንጃዎች፣ በአንደኛው የዓለም ጦርነት ሥራ ላይ የዋሉ አሮጌ ተሽከርካሪዎች ነበሩዋቸው፡፡ አራት መቶ ሺሕ ያህል ተዋጊዎች እንደነበሩ ቢገለጽም፣ መደበኛ የውትድርና ሥልጠና የነበራቸው አንድ-አራተኛ አይሞሉም ነበር፡፡ ከዚህ በተቃራኒ የፋሽስት ኢጣሊያ የሠለጠነ ወራሪ ሠራዊት ቁጥሩ 685 ሺሕ ሲሆን፣ የወረራውን ድል የሚዘግቡ 200 ጋዜጠኞችን አስከትሎ ነበር፡፡ በዘመኑ እጅግ ዘመናዊ የተባሉ ስድስት ሺሕ መትረየሶች፣ ሁለት ሺሕ ዘመናዊ መድፎች፣ 599 ዘመናዊ ታንኮች፣ የዘመኑ ሥሪት የሆኑ 390 የጦር አውሮፕላኖች ከማሠለፉም በላይ፣ በዓለም የተከለከለውን የመርዝ ጋዝ ጭምር ታጥቆ ነበር፡፡ ጀግኖች አርበኞቻችን የተፋለሙት ከእንዲህ ዓይነቱ ግዙፍ ወራሪ ጋር ስለነበር ዘለዓለማዊ ክብር ይገባቸዋል፡፡

ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረ 75ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዩ ክብረ በዓል ላይ የደረሰው የጀግኖች አባቶችና እናቶች ገድል ሲዘከር፣ ከምንም ነገር በላይ ጉልህ ሆኖ መወሳት ያለበት ለእናት አገር ፍቅር የሚከፈለው መስዕዋትነት የዋዛ አለመሆኑ ነው፡፡ ከሕይወት መስዋትዕነትና በአካል ላይ ከሚደርስ ጉዳት በተጨማሪ፣ የአገር ፍቅር ስሜት ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሸጋገር የነፃነት ተጋድሎ መገለጫ ጭምር ነው፡፡ ከፀረ ፋሽስት ትግሉ በፊት አገሪቱን ለመቀራመት ያሰፈሰፉ በርካታ ወራሪዎችን አሳፍሮ የመለሰው ጀግናው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ የእናት አገር ፍቅር ስሜት ምን ማለት እንደሆነ በተለያዩ ትውልዶች አማካይነት አሳይቷል፡፡ በፀረ ፋሽስት ትግሉ ወቅት ግንባራቸውን ለጥይት ደረታቸውን ለጦር ያለስስት አሳልፈው የሰጡ ጀግኖችን ከመዘከር በላይ የሚያረካ ነገር የለም፡፡ እነሱን ከማወደስ በተጨማሪ በሕይወት ያሉትን መጦርና መንከባከብ የትውልዱ ድርሻ ነው፡፡ አሁንም ዘለዓለማዊ ክብር ለጀግኖች አርበኞቻችን ይሁን!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...

በሲሚንቶ ፋብሪካ ላይ የታየው ተሞክሮ በሌሎች ምርቶች ላይም ይስፋፋ!

ሰሞኑን በኢትዮጵም ሆነ በአፍሪካ ደረጃ ግዙፍ ስለመሆኑ የተነገረለትን የለሚ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአስተሳሰብና የአስተዳደር ዘይቤ ለውጥ ያስፈልጋል!

ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡን በጋራ አስተሳስረው የሚያኖሩ በጣም በርካታ ማኅበራዊ እሴቶች አሉ፡፡ እነዚህ ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገሩ የኖሩ እሴቶች አገር ለማቆም ትልቅ አስተዋፅኦ ነበራቸው፣...

ድጋፍና ተቃውሞ እኩል ይስተናገዱ!

ኢትዮጵያ ውስጥ ለረዥም ዓመታት ለመንግሥት ከሚቀርቡ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የመብት መከበር ጉዳይ ነው፡፡ ዜጎች ተፈጥሯዊም ሆኑ ሕጋዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው ለመንግሥት ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ ጥያቄው የቀረበለት...

ፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈለግላቸው!

መንግሥት ከኦነግ ሸኔ ጋር በታንዛኒያ ዳሬሰላም ከተማ ሲያካሂድ የነበረው ንግግር ያለ ውጤት መጠናቀቁን ካስታወቀ በኋላ፣ በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ሰላም ለማስፈን የነበረው ተስፋ...