Tuesday, November 28, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከ19 ሺሕ ሜትሪክ ቶን በላይ ቡና ሰውረዋል የተባሉ ነጋዴዎች ታገዱ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለሕግ ይቀርባሉ ተብሏል

ንግድ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ምርት ገበያ መቀመጫ ያላቸው 24 ቡና ነጋዴዎች ከ19,000 ሜትሪክ ቶን በላይ ቡና ሰውረዋል በመባላቸው እንዲታገዱ ትዕዛዝ ሰጠ፡፡

ንግድ ሚኒስቴር እነዚህ ቡና ነጋዴዎች በምርት ገበያ ያላቸውን መቀመጫ በመጠቀም፣ ግምቱ 7.6 ሚሊዮን ዶላር የሆነ 19,343.84 ሜትሪክ ቶን ቡና መሰወራቸውን ማረጋገጡ ታውቋል፡፡

የንግድ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አያና ዘውዴ ሚያዝያ 17 ቀን 2008 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ ምርት ገበያ በጻፉት ደብዳቤ፣ ከ2000 ዓ.ም. እስከ 2008 ዓ.ም. አጋማሽ ድረስ እነዚህ 24 ነጋዴዎች ቡና ወደ ውጭ ኤክስፖርት ለሚያደርጉ 54 ላኪዎች የሚያቀርቡት ቡና መሰወሩን ገልጸዋል፡፡

‹‹ይህ ድርጊት ደግሞ የቡና ግብይት በሚፈጸምባቸው ሕጎች የተከለከለ በመሆኑ በወንጀል ያስቀጣል፡፡ ጉዳዩ በቡና ግብይት ሥርዓትና በአገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ ያስከተለ ድርጊት በመሆኑ፣ በአባልነት ወንበራቸው ቡናው እንዲሰወር የተባበሩ በሕግ ይጠየቃሉ፤›› በማለት በአቶ አያና ፊርማ የወጣው ደብዳቤ ያመለክታል፡፡

ይህን ሕገወጥ ድርጊት የፈጸሙ ነጋዴዎች በሕግ የሚጠየቁ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ግብይት እንዳይፈጽሙ እንዲደረግ ለምርት ገበያው ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡

ከቡና ግብይት እንዲታገዱና በቀጣይነት በሕግ ይጠየቃሉ ከተባሉት መካከል ኤጂኤን ጄኔራል ቢዝነስ፣ አዲስ ኤክስፖርተር፣ ዴቭላም ትሬዲንግ፣ ሆራ ትሬዲንግ፣ ኤፍኤስኤስ ትሬዲንግ፣ ሃርማ ጄኔራል ትሬዲንግ፣ ጃዊ ማንቡክ ኮሚሽን ኤጀንት፣ በሰማ ትሬዲንግ፣ ቦር ቡና፣ ቴስቲ ትሬዲንግ፣ ጎማ ቡና ቢዝነስ፣ ቻንድለር ትሬዲንግ፣ ኤስ ሳራ ቡና እና ቬራ ኢንተርናሽናል ይገኙበታል፡፡ የቡናና ሻይ ግብይት ባለሥልጣን  የቡና ግብይት ዳይሬክተር አቶ ጌታሁን ቢኮራ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ እነዚህ ነጋዴዎች ለውጭ ንግድ መዋል የነበረበትን ቡና መሰወራቸው በመረጋገጡ እንዲታገዱ ውሳኔ ተላልፏል፡፡

‹‹ነገር ግን ጉዳዩ ወደ ሕግ የሚሄድ በመሆኑ ዝርዝር መረጃ ለመስጠት እቸገራለሁ፤›› በማለት አቶ ጌታሁን ጉዳዩ ያለበትን ደረጃ ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ የቡና ግብይት የተወሳሰበና ሕገወጥ ተግባራት በየጊዜው የማያጣው እንደሆነ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ በዘርፉ ያለውን ችግር ለመፍታት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ኅዳር 15 ቀን 2008 ዓ.ም የቡናና ሻይ ግብይት ባለሥልጣን አቋቁሟል፡፡ ባለሥልጣኑ ተጠሪነቱ ለግብርና ሚኒስቴር መሆኑ አሁንም እያነጋገረ ቢሆንም፣ ከንግድ ሚኒስቴር የግብይት ዘርፍ፣ ከግብርና ሚኒስቴር ደግሞ የቡናና ሻይ ዳይሬክቶርት ይዞ ራሱን የቻለ መሥሪያ ቤት ሆኖ ተቋቁሟል፡፡

የቡናና ሻይ ግብይት ባለሥልጣን እንዲመሩ ቀደም ሲል የደቡብ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ሳኒ ረዲ ተሹመዋል፡፡ ነገር ግን ይህ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት እስካሁን በይፋ ሥራ አለመጀመሩ ተነግሯል፡፡

ተሰወረ በተባለው ቡና በቀጥታ ተጠያቂ የሆኑት ነጋዴዎች ለንግድ ሚኒስትሩ አቶ ያዕቆብ ያላ ቅሬታቸውን እያቀረቡ መሆኑም ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ቡና ዘርፍ 25 ሚሊዮን ቤተሰቦች የሚተዳደሩበትና የአገሪቱ ዋነኛ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ ነው፡፡ በ2007 ዓ.ም. ምርት ዘመን 548 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ቡና የተመረተ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 183 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ወደ ውጭ ተልኳል፡፡

በ2008 ዓ.ም. ግማሽ ዓመት 104 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ቡና ወደ ውጭ ተልኮ 350 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቷል፡፡ ነገር ግን ይህ የሥራ አፈጻጸም በንግድ ሚኒስቴር መልካም የተባለ ቢሆንም፣ ወደ ውጭ መላክ የነበረበት ቡና በሕገወጥ መንገድ ከአገር እንደሚወጣ፣ በአገር ውስጥም በተለያዩ ገበያዎች እየተቸበቸበ መሆኑ ይነገራል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች