Wednesday, February 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ በዋና ኦዲተር ላይ በሰጡት አስተያየት ከፓርላማው ተቃውሞ ገጠማቸው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ አብተው ሚያዚያ 25 ቀን 2008 ዓ.ም. ለፓርላማው ባቀረቡት ሪፖርት የፌዴራል ዋና ኦዲተር በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ላይ ያቀረበውን የኦዲት አስተያየት ለመቀበልና ለመተግበር እንደሚቸገር መግለጻቸው፣ በምክር ቤቱ አባላት ዘንድ ትችት እንዲሰነዘርባቸው አደረገ፡፡

የምክር ቤቱ የውጭ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ዳባ ‹‹ሚኒስትሩ ጥሩ የሕግ አማካሪ የላቸው ይሆናል፤›› በማለት የዋና ኦዲተሩ አስተያየትን አለመተግበር እንደማያዋጣ መክረዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በ2006 በጀት ዓመት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሒሳብ ላይ ባካሄደው ኦዲት ካገኛቸው ግድፈቶች መካከል፣ የመንግሥትን ሕግና መመርያ ሳይከተሉ ሚኒስትሩ ክፍያዎችን ፈጽመዋል የሚል ነው፡፡

ከእነዚህም መካከል ሁለቱን ተቋማት እያወዛገበ የሚገኘው ከሕግና መመርያ ውጪ ለሠራተኞች ማበረታቻ ብሎ 198,783 ብር አላግባብ መከፈሉን፣ በህንድ አገር ለሚማሩ ሠራተኞች 124,264 ብር መክፈሉ፣ ቢሸፍቱ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት በተዘጋጀ ሥልጠና ላይ ለሠራተኞች የመኝታና የምግብ አበል ከተከፈለ በኋላ ተጨማሪ 82,950 ብር አላግባብ ከፍሏል የሚሉ ይገኙበታል፡፡

ሚያዚያ 25 ቀን 2008 ዓ.ም. የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርታቸውን ለማቅረብ በፓርላማው የተገኙት ሚኒስትሩ አቶ አህመድም፣ በእነዚህ የኦዲት ግኝቶች ላይ ያደረጉትን ማስተካከያ እንዲያስረዱ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል፡፡

አቶ አህመድ በወቅቱ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ያልነበሩ ቢሆንም፣ ይኼንን የኦዲት ግኝት የማስተካከል ግዴታን በዋነኛነት እንዲወጡ ፓርላማው ኃላፊነት ሰጥቷቸው እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ አቶ አህመድ ጉዳዩን በተመለከተ በሰጡት ምላሽ፣ ዋና ኦዲተር የሰጠው አስተያየትን እንደማይቀበሉት የሚገልጽ ነው፡፡

ደብረ ዘይት ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ገብተው የምግብና አልጋ ተቆርጦላቸው ካሪኩለም በመቅረጽ ላይ የነበሩት ሠራተኞች የጫማ ማስጠረጊያ እንዲሰጣቸው በጠየቁት መሠረት፣ በወቅቱ የነበሩት ሚኒስትር ከሌሎች አመራሮች ጋር ተማክረው በቀን 50 ብር እንዲከፈላቸው ማድረጋቸውን በመጠቅስ ‹‹ችግሩ ምኑ ላይ ነው?›› ሲሉ አቶ አህመድ ጠይቀዋል፡፡

‹‹ሚኒስትሩ ይኼንን ገንዘብ ያስመልስ ነው የሚለው ኦዲተሩ? ምን ማለት ነው? እነዚህ ሰዎች እኮ ሠርተዋል ብለን ብንከራከርም፣ ሚኒስትሩ በዚህ መንገድ ክፍያ የመፈጸም ሥልጣን የላቸውም በሚል ኦዲተሩ በአቋሙ ፀንቷል፡፡ እኛ ደግሞ ማን ከልክሏቸው፣ የሥራ ማስኬጃ በጀት እያላቸው  እያልን ነው፤›› ሲሉ የምክር ቤቱን አባላት አስፈግገዋል፡፡

እነዚህ ሰዎች ወደ ደብረ ዘይት ሥራ አመራር ኢንስትቲዩት የገቡት ካሪኩለም ለመቅረጽና በእዚህም ውጤት መገኘቱን የተናገሩት ሚኒስትሩ አቶ አህመድ፣ ‹‹ካሪኩለሙ ተቀርጾ የመጣው ፋይዳ ነው መታየት ያለበት ወይስ ለአንድ ሰው ለምን 50 ብር ከፈልክ ብሎ መከራከር? ለዛውም ሕግ ሳይከለክል፤›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ለሠራተኞች ማበረታቻ ተብሎ የተከፈለው 198 ሺሕ ብርን በተመለከተም ተመሳሳይ ምክንያት እንዳለው ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

የአዳማ ዩኒቨርሲቲ ከኮሪያ መንግሥት ተቋም ጋር በመሆን የኢንዱስትሪ ዘርፍ ፍኖተ ካርታ ለመቅረጽ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ውስጥ፣ እንደ ባለድርሻ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ባለሙያዎች መሳተፋቸውን ገልጸዋል፡፡ እነዚህ ባለሙያዎች ፍኖተ ካርታውን ለመቅረጽ ማንበብና ማጥናት የሚጠይቃቸው በመሆኑ፣ ከመደበኛ ሥራችሁ ጋር ደርባችሁ ሥሩት ማለት አስቸጋሪ በመሆኑ ማበረታቻ ተብሎ ክፍያ እንደተፈጸመላቸው ገልጸዋል፡፡

ዋና ኦዲተሩ ግን ይኼንን ለማድረግ ሚኒስትሩ ሥልጣን ስለሌላቸው የወጣው ገንዘብ እንዲመለስ በማለት በአቋሙ መጽናቱን ገልጸዋል፡፡

‹‹ኦዲተሩ የኦዲት አስተያየት ማቅረብ እንጂ ውሳኔ ሰጪ አይደለም፡፡ ውሳኔ ሰጪ ይኼ ምክር ቤትና መንግሥት ናቸው፡፡ በመሆኑም አስተያየቱን መቀበልና መፈጸም ስለምንቸገር ጉዳዩን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳውቀናል፡፡ ውሳኔ እየጠበቅን እንገኛለን፤›› ብለዋል፡፡

በሚኒስትሩ ምላሽ ቅር ከተሰኙ የምክር ቤቱ አባላት መካከል የመንግሥት ወጪ አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት ዶ/ር አድሃነ ኃይሌ ይገኛሉ፡፡

‹‹ሚኒስትሩን ማን ከልክሏቸው የሚለው ንግግር ትክክል አይመስለኝም፡፡ ምክር ቤቱ በጀት ሲመድብ የፋይናንስ ሕግ እንዳለ ተገንዝቦ ነው፡፡ በዚህ መሠረትም እንደሚሠራ ተማምኖ ነው፤›› ብለዋል፡፡ በዚህ መሠረት ለመሥራት አስቸጋሪ ሁኔታ ካጋጠመ አሁን በስተመጨረሻ ላይ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ለማሳወቅና ውሳኔ ለማግኘት በተካሄደበት መንገድ ቀድሞውኑ ተካሂዶ ቢሆን ኖሮ ዋና ኦዲተርም አይጠይቅም ነበር ብለዋል፡፡

ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ተስፋዬ ዳባ ‹‹ሚኒስትሩ ጥሩ የሕግ አማካሪ ላይኖራቸው ይችል እንደሆነ እንጂ እንደ ፋይናንስ፣ ኢንቨስትመንት፣ ንግድ ያሉ ሕጎች የሚተረጎሙት በጠባቡ ነው፤›› በማለት ሚኒስትሩን የሚከለክል ሕግ የለም በማለት ሚኒስትሩ ያቀረቡትን መከራከሪያ ነጥብ አጣጥለውታል፡፡

የሕግ ባለሙያው አቶ ተስፋዬ፣ ‹‹በሕግ ያልተከለከለ እንደተፈቀደ ይቆጠራል የሚለው እሳቤ በወንጀል ዘርፍ መከራከሪያ ሊሆን ይችላል፡፡ በፍትሐ ብሔር ጉዳዮች ካልተፈቀደ አልተፈቀደም ነው፡፡ ስለዚህ አልተከለከልኩም የሚለው ክርክር አያዋጣም፤›› ሲሉም የሕጉን መርህ አብራርተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች