Tuesday, July 23, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ለተፈጥሮ ማን ዘብ ይቁም?

 በኢሳያስ ፈለቀ 

የአገሬ ሰው የውስጡን ቁጭት መግለጽ ቢከብደው አሁንም አሁንምወይ ነዶ!  ወይ ነዶ!› ይላል፡፡ ለማንስ አቤት ይባላል? እንዴትስ ሰሚ ይታጣል? ለምንስ ዝምታን እንመርጣለን? ወይም የእኛ አይደለምን? ብሔራዊ ሀብታችንስ፣ ማንነታችንስ አይደለምን? ለዚህ ሁሉ ጥያቄ መልስ ባጣለት ሰሚ ባገኝ መልስ ባገኝለት ብዬ፣ ለተከበሩት ኢትዮጵያዊነት ሱሳቸው ለሆነው አዲሶቹ አመራሮች ጥያቄዬን ለማቅረብ ተገደድኩኝ፡፡ ይህንንም እንድል የሚያስገድደኝ እውነታ ለተፈጥሮ ጥበቃ ሲሉ ሙያዊ ግዴታቸውን እየተወጡ ክቡር ሕይወታቸውን በዱር በገደሉ እየገበሩ ያሉትን የዱር እንስሳት ቁጥጥርና ጥበቃ ባለሙያዎች ዘወትር ባሰብኩ ቁጥር፣ የተፈጥሮ ሀብት የአንድ ወገን ድርሻ ሆኖ መወሰዱ ስለሚከነክነኝ ነው፡፡ 

ይህንን እውነታ አስመልክቶ አገራችን ውስጥ ያለውን የተፈጥሮ ሀብት ውድመት ጥቂቶች ሐሳባቸውን በተለያየ መንገድ ሰሚ ያገኝ ዘንድ ለፍፈዋል፡፡ ያም ቢሆን ግን ዳሩ ጉዳዩ የብዙዎች ትኩረትን ማግኘት አልቻለም፡፡ ዛሬም እውነታው ያው ቢሆንም የግሌን ሐሳብ ሰሚ ካለ ለማድረስ ተገድጃለሁ፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ ኢትዮጵያዊነት መሠረታዊ ጉዳያቸው ያልነበረ አመራሮች ስለነበሩ የኢትዮጵያ ሀብቶች፣ መገለጫዎች፣ ማንነቷ የሆኑት የተፈጥሮ ሀብቶችና የዱር እንሰሳቶች ሲወድሙና ሲጠፉ ሰምተው እንዳልሰሙ፣ ዓይተው እንዳላዩ መሆንን በመምረጣቸው ሲወድሙ ቆይተዋል፡፡ አሁንም እየወደሙ ነው፡፡

በየትኛው የዓለም ጥግ ስንጓዝ ዓለም የተፈጥሮ ሀብት ባዳና የውበት መካን እየሆነች መምጣቷን ማስተዋል አያዳግተንም፡፡ ይህንን ለማለት ዓብይ የሆኑ ማስረጃዎቻችን ባደጉት አገሮችና በአንዳንድ የገፈቱ ቀማሾች የሚደርሰው ተፈጥሯዊ አደጋዎች ናቸው፡፡ ስለሆነም ምንም እንኳን ዓለም በሥልጣኔና በቴክኖሎጂ ከፍተኛ ልቀት ላይ ብትደርስም እንኳ፣ ተፈጥሮ መሠረት ካላደረገ የሽቅብ ዕድገቱ ሁሉ የዜሮ ድምር ጨዋታ መሆኑን አስረጂ የማያሻ እውነት ነው፡፡ አስረጂም የሚያሻ ቢሆን በየወቅቱ በዓለም ላይ በተደጋጋሚ በተፈጥሮ አደጋ የሚመቱ አካባቢዎችን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ ለነገሩ የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪው እየሆነ የመጣው ራስ ወዳድነትና አንዱ ሲጎዳ አይቶ እንዳላየ የማለፍ አባዜ ተጭኖት የእውነታ ሀቁን ይደብቅበታል እንጂ፣ የተፈጥሮ ሀብት የወደመበትን ደረጃ ለማወቅ አቅል የሚያሳጣ ሙቀትና ቅዝቃዜ ሲፈራረቅበት እርም ለመውሰድ ባልዳዳው ነበር፡፡ ነገር ግን ራስ ወዳድ በመሆኑ ለመጪው ትውልድ ቀርቶ አሁን ላለውም ምቾት የምትነሳ ምድር እየሆነች መጥታለች፡፡ በዚህም ምክንያት በየዓመቱ ከምድረ ገጽ እየጠፉ ያሉት የዱር እንስሳት ዝርያዎች ቀላል የሚባሉ አይደሉም፡፡ ትልልቅ የሚባሉትና በተለይም አዳኝ የድመት ዝርያ የዱር እንስሳት እንደ አንበሳ፣ ነብርና አቦ ሸማኔ ያሉት ዝርያዎች በሰዎች ጫናና በተፈጥሮ ውድመት የተነሳ ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እጅግ በሚባል ፍጥነት እየቀነሰ መጥቷል፣ ህልውናቸውም አደገኛ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ 

21ኛው ፍለ ዘመን የቴክኖሎጂ ማማ ላይ የተንጠላጠሉ አገሮች በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የተፈጥሮ ሀብቶቻቸውን አውዳሚ በሚባል ደረጃ አሟጠው በመጠቀማቸው፣ ልዕለ ኃያላን አገሮች መሆን ችለዋል፡፡ በዚህም ለዜጎቻቸው የቅንጦት ሕይወት በቴክኖሎጂ እየታገዙ ኑሯቸውን እንዲመሩ ማድረግ ችለዋል፡፡ ነገር ግን በዚህ ሁሉ ሒደትም እንኳ በየጊዜው የሚደርስባቸውን የተፈጥሮ አደጋ ማስቆም አልቻሉም፡፡ ይህንንም ከረፈደ ቢረዱትም የተፈጥሮ ሀብት ለመንከባከብ አንድ ብለው መጀመራቸውን ሲመለከቱ፣ እንዳወደሙትና ለምንስ ለመመለስ እጅግ ከፍተኛ ገንዘብና ጉልበት አፍስሰው ይረባረባሉ? የሚያሰኝ ጥያቄ ይጭራል፡፡ መልሱ ግልጽ ይመስለኛል፡፡ የተፈጥሮ ሀብትን ማዕከል ያላደረገ ብልፅግና የትም እንደማያደርስ መገንዘብ የቻሉት ዘግይተው በመሆኑ ነው፡፡ እዚህ ላይ የኛዋን ኢትዮጵያ በብሔራዊ ተአብዮ የተሞላ የተፈጥሮ አደጋ ሥጋት እንደማይገጥማት የሚለፍፍ አባይ አይጠፋም፡፡ ተወደደም ተጠላም ግን እውነታው በተቃርኖው ነው፡፡ ችግሩ እንኳን ጓዙን ጠቅልሎ መጥቶ ይቅርና ድንገት ደመና ከሰማይ ሲበተን ጠኔ የሚዞርብን ለመሆናችን፣ ከእኛ አልፎ ዓለም የሚያውቀው ሀቅ መሆኑን መላልሰን መልሰን የምንመረምረው ጉዳይ አይደለም፡፡ 

ከዚህ የዓለም እውነታና ውጣ ውረድ ያልተማረችው ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቶቿ ጥፋት እየተባባሰ መሆኑን ለማስረዳት፣ የግድ የተፈጥሮ ሀብት ኤክስፐርት ወይም የአየር ንብረት ባለሙያ መሆን አያሻም፡፡ ይህንንም ለማለት ያስደፈረኝ ከጊዜ ወደ ጊዜ በአየር ለውጥ ምክንያት በተደጋጋሚ በድርቅ መጠቃታችን ማሳያ በመሆኑ ሲሆን፣ ይህን ለአብነት አነሳነው እንጂ ለእኛ አገር እንግዳ የሆነው የአፈር መንሸራተት ተከስቶ በርካታ ወገኖቻችንን መጨረሱ የቅርብ ጊዜ አሳዛኝ ክስተት ነበር፡፡ ይህም የተፈጥሮ ሀብታችን መመናመን ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ ለሚረዳው ትልቅ ምልክት ይመስለኛል፡፡  በእርግጥ የአረንጓዴ ልማት እንደምንከተል ከአገር አልፈን ለዓለም ለማሳወቅ ደፋ ቀና ያልነውን ያህል፣ በሥራው ላይ ትኩረት ብንሰጥ ምን ያህል ውጤታማ መሆን በቻልን ነበር፡፡ ዳሩ ግን ከፈረሱ ጋሪው ቀደመና ከእኛ አልፈን አፍሪካን ወክለን የአረንጓዴ ልማት ጥበቃ መሪነታችንን ለዓለም የለፈፍነውን ያህል፣ ሥራችን ላይ ትኩረት የሰጠነው አይመስለኝም፡፡ እዚህ ላይ ልብ እንዲባልልኝ የምፈልገው ለአረንጓዴው ልማት አንድ ፈርጅ ስለሆነው የተፈጥሮ ሀብት እያወራሁ እንደሆነ እንዲታወቅልኝ ነው፡፡ እርግጥ ነው እንደኛ ላሉ የተፈጥሮ ሀብታቸው በእጅጉ ላልተጎዳ አገሮች ያላቸውን ሀብትን በከፍተኛ ሁኔታ መንከባከብ ከሁሉ  የላቀውን ድርሻ ይይዛል፡፡ ያለውን እያጠፉ የማያፀድቁትን የሪፖርት ችግኝ ለመትከል ደፋ ቀና ማለት በራስ ሀብትና ጉልበት ከመቀለድ ያለፈ ፋይዳ ያለው አይመስለኝም፡፡ 

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም መስከረም 2010 ዓ.ም. ባሳተመው መረጃ መሠረት፣ የአረንጓዴ ልማት መሠረታዊ (ነጥቦች) ብሎ ከዘረዘራቸው መካከል ተፈጥሮ ሀብትን (ውኃን፣ ደንንና አፈርን. . .) ጠብቆ በማቆየት በዘላቂነት ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ወሳኝ ተግባር እንደሆነ ያትታል፡፡ በኢትዮጵያችን እየተከሰተ ያለው ከዚህ በተቃራኒው እንደሆነ መረዳት አያዳግትም፡፡ ለአብነት ያህል በጋምቤላ ክልል የተደረገውን የመሬት ወረራ ማንሳት ተገቢ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ባለፉት ዓመታት እጅግ በርካታ የአገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስተሮች በእርሻ ልማት ሰበብ ማኅበረሰቡ ለዘመናት ጠብቆ ያቆየውን ጫካ በመመንጠር፣ በኢትዮጵያ እምብዛም ለምግብ ሰብልነት የማይውለውን የሩዝ ሰብል ለማምረት ብዝኃ ሕይወቱንና ሥነ ምኅዳራዊ ጥፋት እንዲደርስ ማስቻሉ የምናውቀው ሀቅ ነው፡፡ በዚህ አካባቢ ተፈጥሮ ሀብቱ ብቻ አልነበረም ጉዳት የደረሰበት፡፡ ዓሳ ከባህር ወጥቶ መኖር እንደማይችል ሁሉ እኛም ከጫካችን ተነጥለን መኖር አንችልም የሚለው ማኅበረሰብ ጭምር የችግሩ ገፈት ቀማሽ መሆኑን ልብ ሊባል ይገባል፡፡ ከተፈጥሮ ጋር ተስማምቶ አለመኖር በሐሳብ ልዩነት መኖር እንደሚችሉት አካል ጉዳዩ ቀላል የሚመስላችሁ ካላችሁ፣ ያኔውኑ የጥፋት ውኃችሁን ማሞቅ ጀመራችሁ፡፡ 

ይህ ሁሉ የተፈጥሮ ሀብት ውድመት ሲደርስ ሒደቱን መንግሥት በበላይነት እየመራው መሆኑ ሲታሰብ ወይ ነዶ ባለቤት ማጣት ያስብላል፡፡ ምሥጋና ይግባውና የአሜሪካ የተራድኦ ድርጅት (USAID) ይህን ሁሉ የተፈጥሮ ሀብት ውድመት ሲያይ በክልሉ በመገኘት፣ የጎደሬ ኢንሼቲቭን እ.ኤ.አ. 2016 በመመሥረት የተቀረውን የተፈጥሮ ሀብት ከመሬት ወራሪዎች ለመታደግ ከማኅበረሰቡ ጋር በጋራ በመሆን በብዝኃ ሕይወቱ ስብጥር ተጠቃሽ የሆነውን የጎደሬ አካባቢ ደንን ማዕከል ያደረገውን ፕሮጀክት በመደገፍ በአካባቢው እየተገበረው ይገኛል፡፡ እንደዚህ ዓይነት የልማትናበጎ አድራጎት ተግባራት በሌሎችም አካባቢዎች ማኅበረሰቡን ማዕከል ባደረገ መንገድ የመልሶ ማልማትና የቀሩትንም የተፈጥሮ ሀብቶች የመጠበቅና የመንከባከብ ተግባር ለነገ የሚባል አይደለም፡፡ ለቀጣዩ ትውልድ ማስረከብ ያለብን ሀብት የወደመና የተጎሳቆለ ሳይሆን፣ ቢያንስ ለመኖር አመቺ የሆነ እንኳን ባይሆን ሕይወትን ለማስቀጠል የሚያስችል አካባቢ ፈጥረን ማለፍ ከሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚጠበቅ የዜግነት ግዴታ ሊሆን ይገባል፡፡ 

ሌላው የተፈጥሮ ሀብትና የዱር እንስሳት ውድመት እየደረሰበት የሚገኘው በኦሞ ብሔራዊ ፓርክ ላይ ነው፡፡ ይህም ከጋምቤላው የሚለየው በቀጥታ በብሔራዊ ፓርኩ ውስጥ በመንግሥት የሚፈጸም ከባድ ጥፋት መሆኑ ነው፡፡ ቀድሞ የሥራ ባልደረባዬ የነበሩት በአቶ ሰለሞን ወርቁ በዚህ በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ‹‹የጨው ምድር እንዳናወርስ›› በሚል ርዕስ በጻፉት ጽሑፍ፣ በኦሞ ብሔራዊ ፓርክ በስኳር ፕሮጀክት አማካይነት እያደረሰ ያለውን የተፈጥሮ ሀብትና የዱር እንስሳት ውድመት ጥሩ አድርገው ከትበውታል፡፡ ጸሐፊው ይህን ማድረጋቸው ከዜግነትም ሆነ ከሥራ ግዴታቸው የሚጠበቅ ነው፡፡ ከዚያም ባለፈ ሌሎች በሚገባ አውቀውት ትኩረት እንዲሰጡት በማሰብና በመቆርቆር ስሜት የተጻፈ ነው፡፡ በጽሑፉ እንደተመለከተው እየደረሱ ላሉ ችግሮች አሁንም ምንም ዓይነትማስተካከያ ዕርምጃ እየተደረገባቸው አለመሆኑ ነው፡፡ በተጨማሪም ይህ በኦሞ ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ በስኳር ኮርፖሬሽን አማካይነት እየተከናወነ ያለው የብዝኃ ሕይወት ውድመት ከመነሻው በተገቢው መንገድ በጥናት ያልተደገፈ፣ አንድን ዓላማ ብቻ ለማሳካት ታስቦ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ከጽሑፉ መረዳት ይቻላል፡፡ ነገር ግን የቀድሞ መሪዎቻችን የተፈጥሮ ሀብትን ማዕከል ያላደረገና ግንዛቤ ውስጥ ያላካተተ ልማት ዘላቂነት የሌለው መሆኑን ካደጉት አገሮች ሊረዱት ይገባ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተፅዕኖ እያዩ እንዳላዩ፣ እያወቁ እንዳላወቁ መሆኑ በአሁኑም ሆነ በመጪው ትውልድ ላይ የሚያደርሰው አደጋ ቀላል አይደለም፡፡ ስለሆነም ለዚህ መሰል ጥፋት ሁላችንም ድምፃችንን ከፍ አድርገን በማሰማት ግዴታችንን ልንወጣ ይገባል፡፡ 

ጸሐፊው የተፈጥሮ ሀብትን በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ አንዱ የልማትና የጥበቃ አካል መሆኑን አበክረው ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ በተግባር በኦሞ ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ እየተፈጸመ ያለው የተፈጥሮ ሀብት ውድመት ከዚህ በተቃራኒው ነው፡፡ በተለይም ደግሞ ግርምትን የሚጭረው የብሔራዊ ፓርኩ የበላይ ጠባቂ የሆነው የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን ለስኳር ኮርፖሬሽኑ ይሁንታን ሰጥቶ የጥፋቱ ተባባሪ መሆኑ ሳያንሰው፣ እየተፈጠረ ላለው የተፈጥሮ ሀብት ውድመትና ጥፋት ጆሮ ዳባ ልበስ ማለቱ ነው፡፡ ይህ ሆኖ ሲገኝ ደግሞ የጉዳዩ አሳሳቢነት የከፋ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ 

ይህም ሆኖ አሁን በቅርቡ ደግሞ እየሰማንና እያነበብን ያለነው የስኳር እንኳን አገር ሊጠቅም ቀርቶ የተቋቋመበትን ዓላማ ከዳር ለማድረስ ተስኖት በቢሊዮን ብር የሚቆጠር የአገርና የሕዝብ ሀብት መባከኑን፣ ራሱ ኮርፖሬሽኑ እየገለጸ ይገኛል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ በእጃችን ላይ የነበረውን የተፈጥሮ ሀብትና ብዝኃ ሕይወት አሳጥቶን የበይ ተመልካች አድርጎን፣ ከዳር ቆሞ የሚመለከትበት ሒደት ተፈጥሯል ማለት ነው፡፡ ግን እዚህ ላይ ሊረሳና ሊዘነጋ የማይገባው የወደሙትና የጠፉት የተፈጥሮ ሀብቶቻችን ከመካነ መቃብራቸው ሆነው ድምፃቸውን እንድናሰማላቸው ዛሬም ነገም ይጠይቁናል፡፡   

አሁንም ጊዜው ያረፈደና ያልመሸ መሆኑ ታውቆ ባለቤት አልባና ተቆርቋሪ አጥተናል ብለው ዝም ላሉት የተፈጥሮ ሀብቶቻችንና የዱር እንሰሳቶቻችን፣ ለብቻቸው ቀን ከሌሊት በመጠበቅ እየወደቁ ላሉት ስካውቶች ሁላችንም ድምፃችንን ልናሰማላቸውና አለንላችሁ ልንላቸው ይገባል፡፡ ሳይሆን ለምናጣው የተፈጥሮ ሀብት ሁላችንም ከተጠያቂነት አናመልጥም፡፡ የትውልድም ተወቃሾች እንሆናለን፡፡ 

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው   [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡ 

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles