Tuesday, July 23, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ዕውቀትን በቋንቋ መተካት አጥፍቶ ከመጥፋት አይተናነስም

በአንድነት ኃይሉ

ዓለም እዚህ የደረሰችው በዕውቀት እንጂ በቋንቋ አይደለም፡፡ ሰዎች ዓለምን የሠሯት ዕውቀትን እየተመጋገቡ ነው፡፡ ዕውቀትን ለመመጋገብ ቋንቋን ግብዓት አደረጉት እንጂ በቋንቋ ብቻ ታጥረው አልቀሩም፡፡ ሁላችንም ከሰማይ በታች ብንኖርም ሰማይን ምልክት አድርገነው አናውቅም፡፡ ቋንቋ ቢኖረንም መለያ ምልክት ማድረግ ሰማይን ምልክት እንደማድረግ ይቆጠራል፡፡ ቋንቋ የሚደነቅ ነገር የለውም፡፡ ቋንቋ የሰውን ልጅ የሚያመሳስልበትና የሚያለያይበት መሠረት የለውም፡፡

የተለያየ የቋንቋ ባለቤቶች መሆናችን የሚያሳዝን አጋጣሚ እንጂ፣ የሚያኮራ ነገር የለውም፡፡ ምክንያቱም የሰው ልጅ ሕይወት የዕውቀት እንጂ የቋንቋ ውጤት አይደለም፡፡ እውነት ነው የተለያየን ነን፣ አንድ ዓይነቶች አይደለንም፡፡ ሴት፣ ወንድ፣ እህት፣ ወንድም ብለን ነው ልዩነትን የጀመርነው፡፡ አንድ ዓይነት ሆነን አልተፈጠርንም፡፡ አንድ ዓይነት ሆነንም ተለያይተንም መኖር አንችልም፡፡ ልዩነት ያለን የቋንቋ ብቻ አይደለም የበርካታ ልዩነት ባለቤቶች ነን፡፡ ለዚህም ነው አንዳችን ያለ አንዳችን መኖር የማንችለው፡፡ ከአፈጣጠራችን ጀምሮ ያለው ልዩነት የተሳሰረበት አንድነት ነው የእኛ መሠረት፡፡

 ልዩነት ያለ አንድነት መኖር እንደማይችል፣ አንድነታችን ያለ ልዩነታችን መኖር እንደማይችል ከበርካታ ነገሮች መማር እንችላለን፡፡ የሰው ልጅ ተፈጥሮ ይኼንን ያክህል ልዩነት ባይኖረው፣ ተፈጥሮም የሰው ልጅም ሕይወት ባልቀጠለ ነበር፡፡

      ቋንቋ ሊያግባባ የሚችለውና ዘላቂ ጥቅም የሚኖረው ዕውቀት ጋ ሲደርስ ነው፡፡ አንድ መኪና በቂ ነዳጅ ሳይዝ ረጅም ርቀት መሄድ እንደማይችል ግልጽ ነው፡፡ ቋንቋም የማንኛውም ዜጋ ዕውቀት ድረስ ካልዘለቀ ረጅም ርቀት አያስጉዘውም፡፡ ዕውቀትን ለመስጠትም ለመቀበልም ቋንቋን መስጠትና መቀበል ስንችል ነው፡፡ እንደ አገር ረጅም ርቀት መጓዝ የምትችለው በሁሉም ቋንቋ የኅብረት ጥንካሬ የሚገለጽበት አባባል አለ፡፡ የቋንቋ ኅብረት ውጤት ዕውቀት ነው፡፡ የቋንቋ አንድነት በዕውቀት ነው ሊገለጽ የሚችለው፡፡ ያኔ ጠንካራ ግብይት፣ ገበያ፣ ምርት፣ ወዘተ. . .    ሊኖረን ይችላል፡፡ ቋንቋ ሲተባበር ውጤቱ ዕውቀትና አንድ ዓይነት ፍላጎት ነው፡፡

እኛ ደሃ የሆነው ቋንቋችንን መጠቀም ስላልቻልን ሳይሆን፣ ዕውቀታችንን ስላልተጠቀምንበት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ወጥ ፍላጎት ያለው ሰው ወጥና የተሟላ ዕውቀት አይኖረውም፡፡ አንድ ነን ስንል ማሰሪያው ሰዎች ነን ማለት ብቻ አይደለም፡፡ አንድ አገር፣ አንድ ሕግ፣ አንድ መገበያያ ገንዘብ፣ አንድ ድንበር ከሌለን ለመኖር የሚያስፈልገንን ሕግ፣ ግብይትና ገበያ እናጣለን፡፡ የሰው ልጅ ያለ ግብይትና የገበያ ሕግ መኖር አይችልም፡፡ በዚህ ዘመን ቋንቋ ውስጥ እየተቀበረ ያለን ግብይት በገበያ ሕግ ነፃ ለማውጣት በርካታ ሥራ ይጠብቀናል፡፡ አብዛኛው ሰው ዕውቀት ጎሎት ሳይሆን፣ ቋንቋ ጎሎት ዕውቀትና ፍላጎቱን እያባከነ ነው፡፡ በትምህርት ቤት ያመረትነው ዕውቀት ብቻ ሳይሆን፣ ሁሉም በአካባቢው ከዕውቀትና ከፍላጎቱ በላይ ቋንቋው ስለገዘፈ በዕውቀትና በፍላጎት ከሌላ ጋር መግባባት እያቃተው ነው፡፡ መግባባት አለመቻል ብቻ ሳይሆን አንድነትና ልዩነትን የሚያመዛዝንበት ዕውቀት ተዛብቷል፡፡ አንድ ነን ስንል በቋንቋ ከሆነ፣ ተለያይተናል ስንል በቋንቋ ከሆነ ትልቅ ኪሳራ ነው፡፡

የሰው ልጅ መኖር የማይችለው ከዕውቀት ውጪ እንጂ ቋንቋውን ረስቶትም ትቶትም እየኖረ እንዳለ የምናየው ነው፡፡ ውጭ አገር ተሰዶና ተዋልዶ የሚኖረው ኢትዮጵያ በዕውቀቱ እንጂ በቋንቋው አይደለም፡፡ ይህ ማለት ቋንቋ አያስፈልግም ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን ለሰው ልጅ ዕውቀት ግብዓት ይሆናል እንጂ፣ ሕይወት ምንም ግብዓት የለውም፡፡

የሰው ልጅ መኖር የሚችለው በዕውቀት ውጤት እንጂ፣ ቋንቋውን ረስቶትም ትቶትም እየኖረ እንዳለ የምናየው ነው፡፡ የሰው ልጅን ዕውቀትና ፍላጎት ሊያኖሩት የሚችሉት ግብይት ሲኖር ነው፡፡ የሰው ልጅ ቋንቋ ውስጥ ራሱን ከከተተው አደጋው ስለሌሎች ያለው አመለካከት መዛባት ብቻ ሳይሆን፣ ለሰው ልጅ መሠረታዊ የሆነውን ዕውቀትና የፍላጎት ልዩነት ያጠፋል፡፡ ያኔ ግብይትን ማከናወን ከባድ ይሆናል፡፡

      ቋንቋ ቋንቋን አያኖረውም፣ ቋንቋ ቋንቋን አይመግበውም፡፡ ዕውቀት ግን ቋንቋን ያኖረዋል፣ ይመግበዋል፡፡ ዓለም እዚህ የደረሰው በቋንቋ ሳይሆን፣ ዕውቀት እየተመጋገበ ነው፡፡ ዕውቀትን ለመመገብ የቋንቋን አጥር ማለፍ የሚያኮራ እንጂ የሚያሳፍር ነገር የለውም፡፡

 አገራችንን የሚለውጣት ዕውቀት ከየትኛው ቋንቋ ጀርባ እንዳለ ማንም አያውቅም፡፡ ይኼንን ዕውቀት ለመጠቀም ቋንቋን መሻገር ግድ ይላል፡፡ በአንድ አገር ውስጥ የቋንቋ መለያየት ለአገሩ ሕዝብ ዕውቀት እስር ቤት ይሆናል፡፡ አገር ይኼንን እስር ቤት ዕርምጃ በመውሰድ ዕውቀትን ነፃ ካላወጣችው፣ ለግለሰብ ደግሞ ቋንቋው ባርነትን ይፈጥርበታል፡፡ ሲከፋ ደግሞ ሲኦል ይሆንበታል፡፡ ዓለም በርካታ የተሳሳቱ ፍልስፍና ነበራት፡፡

ለዘመናት ቋንቋ መግባቢያ ነው ሲባል ነበር፡፡ የሰው ልጅ ግን በቋንቋ ተግባብቶ አያውቅም፡፡ የሰው ልጅ የሚግባባው በዕውቀት ነው፡፡ እንኳን የተለያየ ቋንቋ ባለቤቶች አንድ ዓይነት ቋንቋን የሚነጋገሩ ሰዎች የሚግባቡት በዕውቀት ነው፡፡ ቋንቋ ሦስት አካል ሲኖረው ድምፅ፣ ትርጉም፣ ዕውቀት ናቸው፡፡ ማንም ሰው የየትኛውንም ቋንቋ ድምፅ ሊሰማ ይችላል፡፡ የማይገባውና የማይግባባው የድምፅ ትርጉም ዕውቀት ስለሌለው ነው፡፡ አንድ ዓይነትን ቋንቋ የሚነጋገሩ ሰዎች በድምፅም በትርጉምም ቢግባቡ፣ አንዱ ዕውቀት ከሌለው ሊግባቡ አይችሉም፡፡ መግባባት ከድምፅ ትርጉም በላይ ዕውቀት ዘንድ መድረስ አለበት፡፡ ዛሬ ቋንቋ ጭራሽ ማንነት እየሆነ ነው፡፡ የሰው ልጅ በቋንቋ አይገለጽም፡፡

የሰውን ልጅ በቋንቋ መግለጽ ሰውን ማሳነስ ነው፡፡ የሰው ልጅ ያሉት መገለጫዎች በአንድ እንኳን ይገለጹ ቢባል፣ ከቋንቋ በላይ ዕውቀት ነው፡፡ ሊገለጽበት የሚገባው ምክንያቱም ቋንቋ ለሰው ልጅ አስፈላጊ ሊሆን የሚችለው ዕውቀት በሥራ ላይ መዋል ሲችል ነው፡፡ የሰው ልጅ በትክክል ሊገልጸው የሚችለው እምነቱ፣ ዕውቀቱና ፍላጎቱ ነው፡፡ ማንም ሰው አንድ ዓይነትም የተለያየም ቋንቋ ቢኖረው፣ የራሱ የሆነ እምነት ዕውቀት ፍላጎት ነው ያለው፡፡ የሰው ልጅ ካለው እምነት፣ ዕውቀት ፍላጎት ጋር ቋንቋው ሲነፃፀር ቋንቋ የሰው ልጅ እዚህ ላይ ለመድረስ ምንም ቦታ የለውም፡፡

ቋንቋ ለሰው ልጅ ያበረከተው ምንም ነገር የለም፡፡ የሰው ልጅ ቋንቋውን እዚህ ያደረሰው በዕውቀቱ ነው፡፡ በዚህም ነው የሰው ልጅ የቋንቋ ባለቤት መሆን የሚችለው፡፡ ይህ ባይሆን ሌሎች ቋንቋዎችን መለማመድ ባልቻልን ነበር፡፡

ቋንቋን ከዕውቀት ጋር ስናነፃፅረው በጣም የተለያዩ ነገሮች ከመሆናቸው የተነሳ በፍፁም የማይወዳደሩ ናቸው፡፡ የሰው ልጅ በቋንቋ ሳይሆን በዕውቀት መገለጽ ያለበት የሰው ልጅ በቋንቋ መኖር ስለማይችል ብቻ አይደለም፡፡ ቋንቋ አያያዙን ካልቻሉበት ዕውቀቱን ስለሚጋርድበት የዕውቀት ጮራ ጨለማም ስለሚሆን ነው፡፡ እኛ እዚህ የደረስነው ቋንቋውንና ግለሰቡን ባናውቅም የተለያዩ ቋንቋዎች ውስጥ የተወለዱ ዕውቀቶችን ተመግበን ነው፡፡ የሰው ልጅ ለቋንቋው የተተወ ቢሆን ኖሮ ምናልባት ይኼኔ ከምድር ላይ ጠፍቶ ነበር፡፡ የሰው ልጅ የቋንቋን አጥር መሻገር ስለቻለ ነው ዕውቀትን ተመጋግቦ ዕውቀትን ተጋርቶ ለዚህ የደረሰው፡፡ የቋንቋን ባርነት መሻገር ችሎ ነው ዓለምን ወደ ሥልጣኔ ያመጣው፡፡

አገራችን የዚህ ሁሉ ቋንቋ ባለቤት በመሆኗ የበለጠ ደሃ የሚያደርገን ከዕውቀት ይልቅ ቋንቋን የመረጥን ለታ ነው፡፡ ማንም ኢትዮጵያዊ የዕውቀት ብርሃናቸው ወደ በራ ወደ ሠለጠኑ አገሮች ሲሄድ ለቋንቋው ግድ የለውም፡፡ ምክንያቱም ከቋንቋ ይልቅ ዕውቀት እንደሚያኖርና እንደሚበልጥ ያውቀዋል፡፡ ችግሩ እኛ የዕውቀት ብርሃናችን ያልበራ ስለሆነ ነው ቋንቋ ብርቅ የሆነብን፡፡ አገር ውስጥ ስንኖር ከዕውቀት ይልቅ ለቋንቋ ቅድሚያ የሚሰጠው፣ በዕውቀት መኖር ስላልጀመርን ነው፡፡ ዕውቀታችን ቢበራ ከቋንቋ ይልቅ ለዕውቀት ቅድሚያ ይሰጥ ነበር፡፡

ዜጎች በአፍ ቋንቋ መማራቸው ለዕውቀታቸው አጥር አበጀ? ወይስ ብርሃን ሆነ? ውጤቱ ምን ሆነ? ቋንቋቸውን ለመሻገር ዕውቀትን ለመስጠት ለመቀበል ግብዓት ሆነ? የሥራ ዋስትናቸው የተማሩት ዕውቀት ወይስ ቋንቋቸው ሆነ? ዕውቀታቸው ቋንቋን ለመማማር ግብዓት ሆነ አንድ ግብይት ለመፍጠር የረዳ አይመስለኝም፡፡ ቋንቋ ዕውቀትን እያባከነው መሆኑን እያየነው ነው፡፡ ቋንቋን በተመለከተ የተቀመጠው ሕግ በአግባቡ አልተጠቀምንባቸውም፡፡ ሕዝቡም አልገባውም፡፡ አንቀጹን ስንተገብረው እንደሚገባው ቢሆን ኖሮ የቋንቋን አጥር ለመሻገር የሚረዳ ድልድይ ይሆን ነበር፡፡ ዕውቀቱ ዋስትናው የሆነን ዜጋ እንፈጥር ነበር፡፡

ሁሉም ከቋንቋው ለዕውቀቱ ቅድሚያ ይሰጥ ነበር፡፡ አንቀጽን አስቀምጦ ሕዝብን አንተ ዕውቀት እንጂ ቋንቋ አይደለህም ብለን፣ ዕውቀትንም ቋንቋንም ማስተማር ልንጠቀምበት ይገባ ነበር፡፡ ሁሉም ቋንቋ ቢለማመድ ሰው ከመሆን የዕውቀት የፍላጎት ባለቤት ከመሆን የሚጎለብት የለም፡፡ ሰው ከዕውቀት ሲሸሽ ከሰውነት ያንሳል፡፡ ሕጉ ሰዎች ከቋንቋ ባርነት የሚወጡበት መሆን ሲገባው ሰዎች ወደ ቋንቋ የሚጓዙበት መሆኑ ዛሬ ብዙ እያስከፈለን ነው፡፡

ሐሳቡ መልካም ነበር አተገባበሩ ግን ችግር አለበት፡፡ መኪና ተገልብጦ ገደል ውስጥ ስለሚገባ መኪና መጠቀምን አላቆምንም፣ በሚገባው መንገድ እንጠቀምበታለን፡፡ አንቀጹ አገርን ለቋንቋ አሳልፎ መስጫ መሣሪያ ሳይሆን፣ ለዕውቀት መስጫ ቢሆን ቋንቋ ያለና የነበረ፣ በመኖሩም የሚገልጽህ የምትገለጽበት ሳይሆን ወደሚገልጽህ ወደምትገለጽበት ዕውቀት ለምናደርገው ጉዞ ግብዓት መሆን እንድትችል ቋንቋን ወደ ውስጥህ አስገባ፡፡ የቋንቋ ትንሽም ትልቅም የለውም፡፡

ነገር ግን ቋንቋ ወደ ዕውቀት የሚደረገውን ጉዞ መሰናክል የመሆን ዕድል አለው፡፡ ሕዝብን ቋንቋህን እናከብራለን ማለት ግን የሚደነቅ ነገር የለውምና አናደንቀውም፡፡ በቋንቋ ምክንያት ትገፋ ነበር፡፡ ዛሬ ግን በቋንቋ ምክንያት እንዳትገፋንና ከዕውቀት መራቅ እንዳይመጣ ወደ ውስጥ ተጨማሪ ቋንቋ አስገባ፡፡ አለበለዚያ ዕውቀትን ቋንቋ ይቀማናል፣ ያባክንብናል፡፡ ዕውቀት ባክኖና ጠፍቶ አገር መኖር አትችልም፡፡ የአገር መሠረት የሆነው ሳይንስ፣ ፍላጎት፣ ግብይት ወዘተ. . . የቋንቋ ውጤት ወይም ከቋንቋ ጋር የሚያገናኛቸው ምንም ነገር የለም፡፡

ሰው ሌላ ቋንቋ፣ ሌላ ፍላጎት፣ ሌላ ዕውቀት፣ ግብይት፣ ገንዘብ፣ ገበያ ሁሉም፣ ሀብት ወደ ሥራ መግባት የሚችለው ሁሉም ሕዝብ መልማት የሚችለው በቋንቋ ሳይሆን፣ በዕውቀት ነውና ፍላጎትን እንድንጠቀም ቋንቋ ተማር፣ ቋንቋህን አስተምረን፡፡ ዕውቀት እንድትሰጥና እንድትቀበል ቋንቋን ተማር ብለን ነገሮችን ካላመቻቸንና የቋንቋ አያያዙን ካልቻልንበት መድኃኒት የሌለው ችግር ይሆናል፡፡

      በአገራችን ቋንቋን ለማስተናገድ የተጠቀምንበት ሕግ ከዕውቀት ይልቅ ለቋንቋ ያደላ ነው፡፡ ዕውቀትን ለመጠቀም የዕውቀት አንድነትን ለመፍጠር ወደ ቋንቋ አንድነት መምጣት ሲገባ፣ ወደ ቋንቋ ልዩነት በመጓዛችን የበለጠ የቋንቋው ጥገኛ የሆነ ትውልድን በመሥራታችን ዕውቀት በቋንቋ እየተተካ ነው፡፡ የሕጉ ውጤት ቋንቋን በዕውቀት መተካት መሆን ነበረበት፡፡ ዓላማውን የሳተው ለምንና እንዴት እንደሆነ በቦታው የነበሩት ይመልሱት ይሆናል፡፡

ድሮም ዛሬም ዕውቀት በቋንቋ ምክንያት ይባክናል፡፡ ድሮ ቋንቋ ተንቆ ዛሬ ደግሞ ዕውቀት በቋንቋ ተተክቶ፣ ሁለቱም የራሳቸው ችግር አለባቸው፡፡ የድሮውን ችግር ቢያንስ አሁን ባስቀመጥነው ሕግ ልንፈታው እንችል ነበር፡፡ አሁን እየተፈጠረ ያለውን ችግር ግን በምንም አንፈታውም፡፡ ይህ ደግሞ አጥፍቶ ከመጥፋት አይተናነስም፡፡ አሁንም ሳንዘገይ በዕውቀት መኖር ጀምረን ሕዝቡ ስለዕውቀቱ በገዛ ፍላጎቱ እንዲነቃ፣ ቋንቋው በገዛ ዕውቀቱና ፍላጎቱ መሰናክል እንዳይሆንበት ጥረቶችን እንዲያደርግ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትና ትስስር መሥራት ካልቻልን መድኃኒት ወደሌለው ችግር እየተጓዝን ነው፡፡

 ለገጠመን ችግር መፍትሔው አገርን በገዛ ዕውቀት፣ ገንዘብ፣ ገበያ መሥራት ብቻ ነው፡፡ ያኔ ሁሉም ዕውቀቱንና ፍላጎቱን የገበያ ተጠቃሚ ለማድረግ ማድረግ ያለበትን ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ እያየነውም ነው፡፡ ዜጎቻችን ቋንቋ ለምደው የሰው አገር የሚሰደዱት ለዕውቀታቸውና ለፍላጎታቸው ነው፡፡ ቋንቋን በዕውቀትና በፍላጎት ሊያስተካ የሚችል ግብይትና ተጠቃሚነት መፍጠር ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው  [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡ 

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles