Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየዘላቂ ልማት የጀርባ አጥንት

የዘላቂ ልማት የጀርባ አጥንት

ቀን:

በታደሰ ገብረማርያም

ከኢትዮጵያ ጠቅላላ መሬት ውስጥ ወደ 15.5 በመቶ ያህሉ በደን የተሸፈነ መሆኑ ይነገራል፡፡ ሽፋኑ በሳተላይት መረጃ ተመሠረተ ሲሆን፣ መረጃውም ተተንትኖ የተገኘ ውጤት ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ መረጃ አሰባሰብ የተከናወነው በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቁ ኤክስፐርቶችን በማሳተፍና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) የኢትዮጵያ ቢሮ ጋር በመተባበር ወይም በመቀናጀት መሆኑን የደን፣ አካባቢና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

በሚኒስቴሩ የብሔራዊ ሬድ ፕላስ ሴክሬታሪያት አስተባባሪ ይተብቱ ሞገስ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ የደን ሽፋኑ መጠን ሊታወቅ የቻለው በ2008 ዓ.ም. በተካሄደ ምዝገባና ቆጠራ ነው፡፡ ሽፋኑ በምዕራብ ቆላማ አካባቢዎች ማለትም መተማ፣ ቤንሻንጉል ጉምዝ፣ ጋምቤላ፣ ሁመራ፣ እንዲሁም በሶማሌና በአፋር አካባቢዎች የሚገኙ ግራርና ሌሎች ቆላማ ዛፎችን ያካትታል፡፡

ቀደም ሲል የአገሪቱ የደን ሽፋን 40 በመቶ ነበር፡፡ ከዚህም ወደ 16 በመቶ ቀጥሎም ወደ 2.7 በመቶ፣ ወዘተ አሽቆለቆለ የሚሉ የተለያዩ ሰነዶች እንዳሉ፣ እንዲህ ዓይነት ተለዋዋጭ የሆኑ ውጤቶች በምን ዓይነት መረጃና የትኛው የደን ትርጉም ተይዞ  ነው የተሠሩት? የሚሉትንና ሌሎችንም ተዛማጅ ጥያቄዎችን መመለስ ስላልቻለ እንደተተወ ነው የተናገሩት፡፡

‹‹ባለፉት 13 ዓመታት ውስጥ ብቻ በእርሻ መስፋፋት ሳቢያ ወደ 1.2 ሚሊዮን ሔክታር የሸፈነ ደን አጥተናል፡፡ በእነዚህ ተመሳሳይ ዓመታት ደግሞ 150,000 ሔክታር ወይም አንድ አራተኛውን የሸፈነ ደን አጠራቅመናል፡፡ ይህ ደግሞ ሲታይ ሽፋናችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጎዳና በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ደን አደጋ ላይ እንደሆነ ያመላክታል፡፡ ለዚህም ነው ሚኒስቴሩ ሬድ ፕላስ የሚባለውን አካሄድ መከተል የጀመረው፤›› ብለዋል፡፡

ሬድ ፕላስ የደን ጭፍጨፋ መቀነስንና የደን መስፋፋትን ዓላማው አድርጎ የሚንቀሳቀስና የአየር ንብረት ለውጥን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመከላከል የሚያስችል አሠራር ነው፡፡ በዚህም አሠራር ኢትዮጵያን ጨምሮ ወደ 100 የሚጠጉ ታዳጊ አገሮች ተሳትፈውበታል፡፡ አካሄዱ በሦስት ምዕራፎች እንደሚከናወን፣ የመጀመርያው የዝጅግት ምዕራፍ ሲሆን፣ ይህም ሥራው ተጠናቅቆ ወደ ሁለተኛው ምዕራፍ ማለትም መሬት ላይ የሚከናወኑ የኢንቨስትመንት ሥራዎች ውስጥ እንደተገባ ነው አስተባባሪው የተናገሩት፡፡

ኢትዮጵያ በዝግጅት ምዕራፉ ላይ የ15 ዓመታት ፕሮግራም እንደጀመረችና ለዚህም ዕውን መሆን የደን መረጃዎች በሚገባ እንደተደራጁ፣ የመረጃዎች መተንተኛና ማደራጃ ላብራቶሪዎች በአራት ክልሎችና በፌዴራል ደረጃ እንደተቋቋሙ ገልጸዋል፡፡ ፕሮግራሙ አገርንና ኅብረተሰቡን በሚጠቅምና አካባቢን በማይጎዳ መንገድ እንዲተገበር የሚረዱ መቆጣጠሪያ መሣሪያዎች (ሴፍ ጋርድ ኢንስትሩመንትስ) ተዘጋጅተዋል፡፡

ከዚህ አንፃር በሬድ ፕላስ አሠራር ከታቀፉት አገሮች ውስጥ የተጠቀሰውን ፕሮግራም ፈጥነው በመተግበር ላይ ከሚገኙት አሥር ውጤታማ አገሮች መካከል፣ ኢትዮጵያ አንዷ እንደሆነች ከአስተባባሪው ማብራሪያ ለመረዳት የተቻለው፡፡

በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ከዓለም ባንክ ጋር ወደ ኢንቨስትመንት የገባች ሲሆን፣ ለዚህም ከዓለም አቀፉ ድርጅት፣ ከዴንማርክ፣ ከኖርዌይና ከስዊድን በድምሩ ወደ 150 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አግኝታለች፡፡ ድጋፉም የሚውለው በሬድ ፕላስ አካሄድ አዲስ ደን ለመፍጠርና ያለውንም ኅብረተሰቡን ባሳተፈ መንገድ ለማስጠበቅ ነው፡፡

በዚህም መሠረት በኦሮሚያ ደቡብ (ኢሊባቦር፣ ከፋ) እና በጋምቤላ ደጋማ አካባቢዎች የሚገኘውንና በብዝኃነቱ (ባዮዳይቨርሲቲ) የታወቀውን ደን አሳታፊ አስተዳደርን ተግባራዊ በማድረግ፣ ኅብረተሰቡ እየጠበቀ እንዲጠቀም የሚያደርግ ሥራ ይከናወናል፡፡ ወደ ሰሜንና መሀል ኢትዮጵያ የሚገኙ የተጋለጡ ተራራዎችን ደግሞ ገቢ የሚያስገኝና ለአፈር ጥበቃ የሚውሉ ደኖችን የማልማት ሥራ ለማከናወን የገንዘቡ ድጋፍ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡

15.5 በመቶ ሽፋን ውስጥ ከሚገኘው ደን መካከል በአብዛኛው የተፈጥሮ ደን ነው፡፡ ስለሆነም ይህ ደን እንዲጠበቅ ይፈለጋል፡፡ በሬድ ፕላስ አካሄድ አማካይነት የተጠቀሰው ደን ሲጠበቅና ሰፊ መሠረት ያለው አዲስ ደን ሲኖር ነው አረንጓዴ ልማት ዕውን የሚሆነው ተብሏል፡፡

ከአስተባበሪው ገለጻ ለመረዳት እንደተቻለው፣ አረንጓዴ ልማትን ማሳካት ከተፈለገ የእርሻ መስፋት መልክ ይዞ ባለው ላይ የተሻለ ምርታማ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ ማገዶም ለደን መመናመን ከፍተኛ ምክንያት እንደሆነ፣ የማገዶ አጠቃቀም የተሻሻሉ ምድጃዎችን መጠቀም፣ አማራጭ ካለ አማራጩ እንዲታይ ማድረግ፣ የሚቻል ከሆነ ደግሞ የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲስፋፋና በዚህም የገጠር ከተሞች ከማገዶ ይልቅ ወደ ኤሌክትሪክ ኃይል ትኩረት እንዲያደርጉ ማድረግ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ግን ያለውን ደን መጠበቅ ፈታኝ ነው የሚሆነው ብለዋል፡፡

የሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል መሬት ደግሞ ከ3,000 ዘመን ጀምሮ ሲታረስ የቆየ እንደመቆየቱ መጠን ለሙ አፈር ተበልቶ ማለቁን፣ ይህም በደን ልማት እንደገና ተመልሶ እንዲያገግም ካልተደረገ እየታሰበ ያለው ዘላቂ ልማት ላይመጣ እንደሚችል፣ ለዚህም ዕውን መሆን የመሬት ዕቅድ ወይም ማስተር ፕላን ፈጥኖ መውጣት እንዳለበትና በአገር አቀፍ ደረጃ ማስተር ፕላኑ ከወጣ ክልሎች፣ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ደን፣ የግጦሽና የእርሻ መሬቶችን በሕግና በኃላፊነት እንደሚወስዱ መታወቅ አለበት ሲሉም አስረድተዋል፡፡

‹‹የማስተር ፕላኑ ጉዳይ ከ1980ዎቹ ጀምሮ እየተሠራ ነው ተብሎ ይነገራል፡፡ ነገር ግን እስካሁን ምንም የታየ ነገር የለም፡፡ ማስተር ፕላኑ የኢትዮጵያን መሬት ከጉስቁልናና ከመጥፎ ዕድል ለማዳንና ደንን ማስጠበቅ እንደሚቻል፣ የደን መሬት የተባለውን ደግሞ ለይቶ መልማት ያለበትን እያቀዱ ማልማት እንደሚያስችል አጠቃላይ የማስተር ፕላኑ መወጣት ለአረንጓዴ ልማት ማሳካት የበኩሉን አስተዋጽኦ ያደርጋል፤›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡  

በዓለም የሙቀት መጠን የመጣው ከግሪን ሐውስ ጋዝ ልቀት የተነሳ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ 80 በመቶ ያህሉ ልቀት ያደጉ አገሮች ለትራንስፖርት፣ ለኢንዱስትሪና ለነዳጅ ከሚጠቀሙባቸው ከድንጋይ ከሰልና ነዳጅ የመጣ መሆኑን፣ አሥር በመቶ ያህሉ ደግሞ ከትሮፒካል ዲፎርስቴሽን መሆኑንን ስለዚህ 20 በመቶውን ታዳጊ አገሮች፣ 80 በመቶውን ደግሞ የበለፀጉ አገሮች ቢይዙት በጣም አዋጪ በሆነ መንገድ ልቀትን መቀነስ እንደሚቻል አስተባባሪው ገልጸዋል፡፡

የፓሪስ ስምምነትም እያንዳንዱ አገር በፈቃደኝነት እቀንሳለሁ የሚለውን ሥራ ‹ለዩናይትድ ኔሽን ፍሬምወርክ ኮንቬንሽን ኦን ክላይሜት ቼንጅ (ዩኤፍሲሲሲ)› ይጠይቃል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ አገሮች ቃል የገቡትን የቅነሳ ፕሮግራም የሚፈለገውን የዓለም ሙቀት ከሁለት ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ በላይ መወጣት የለበትም፣ ቢቻል ቢቻል ከአንድ ነጥብ አምስት ሴንቲ ግሬድ በታች መቀመጥ አለበት ከሚለው ደረጃ ላይ የሚደርስ አይደለም ሲሉም አክለዋል፡፡  

በዚህም መሠረት አሜሪካ፣ ቻይናና ሌሎችም ዋና ዋናዎቹን ጨምሮ 80 በመቶውን የልቀት መጠን ለመቀነስ ቃል ገብተው እንዲተገበሩ መደረግ አለበት የሚል ድምዳሜ ላይ መደረሱን ገልጸዋል፡፡ በዚህ በኩል ትልቅ ለውጥ እንዲያመጣ ከተፈለገ ኢኮኖሚው ወደ ታዳሽ ኃይል (ኃይድሮ፣ ሶላር፣ ንፋስ ጂኦተርማል) መግባት እንዳለበት፣ ኢትዮጵያም በዚህ የአረንጓዴ ልማት የከባቢ ልቀትን በ2022 ዓ.ም. በ64 በመቶ በፈቃደኝነት እቀንሳለሁ ብላ ለኤፍሲሲሲ ማሳወቋን፣ ቃል ከገባችው 64 በመቶ ቅነሳ ውስጥ 50 በመቶው በደን አካባቢ እንደሚሠራ አስረድተዋል፡፡  

የደን ሽፋን በሚከናወንባቸው ወረዳዎችና ቀበሌዎች ውስጥ ደግሞ ባለሙያ፣ ሎጂስቲክ፣ ሞተር ብስክሌት፣ እንዲሁም የመሬት አጠቃቀም ፕላን አለመኖሩን፣ ፖሊሲውም ግልጽ እንዳልሆነ፣ ስለዚህ ለአፈጻጸሙ ድርብርብ ችግር እንዳለ መታወቅ ይኖርበታል ብለዋል፡፡

‹‹አሁን ያለነው ችግኝ ተከላ ላይ ነን እንጂ፣ ደንን ማልማት ገና አልቻልንም፡፡ ደን ማልማት የሚቻለው ከተከላ በኋላ በሚደረጉ እንክብካቤዎችና ከተከላ በፊት ደግሞ ትክክለኛውን ዝርያ መምረጥ፣ ችግኙ በአግባቡና በሚፈለገው ጥራትና መጠን መዘጋጀቱና ለአካባቢው ተስማሚ ሆኖ መመረጡ ወሳኝነት አለው፡፡ ከዚህም ሌላ ከእንስሳትና ከሰው ንኪኪ ነፃ መሆን፣ ባለቤት ኖሮት በጋው እስኪያልፍ ድረስ ውኃ መጠጣት እንዳለበትና በዘፈቀደ ችግኝ ተክሎ መመለስ ውጤታማ አያደርግም፤›› ሲሉ አመልክተዋል፡፡

‹‹ተወደደም ተጠላም ኢትዮጵያ ተራራማና የውኃ ማማ ናት፡፡ ውኃ ላይ ልማት ሊመጣ ይችላል፡፡ ከልማቱም መካከል ኤሌክትሪኩና መስኖ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ከዚህም ሌላ በዙሪያ ያሉ ደረቃማ አገሮች በመሆናቸው ውኃ ልንሸጥላቸው እንችላለን፡፡ አልፎ ተርፎ የደን ሽፋን በጨመረ ቁጥር የተሻለ ዝናብ እንደሚገኝ መረጃዎች እየጠቆሙ ነው፤›› ብለዋል፡፡  

የኢትዮጵያ ጅረቶች ውኃ የሚያገኙት ከውቅያኖስ ሳይሆን ከደን ዑደት መሆኑን፣ ለቱሪስት መስህብ የሆኑ ብርቅዬ የዱር እንስሳት ደኑ እንደ ቤት ወይም እንደ መጠለያ ሆኖ እንደሚያገለግልላቸው፣ ከተመነጠረና ከተመናመነ ግን ብርቅዬ የዱር እንስሳቱ እንደማይኖሩ፣ ከዚህም በተጨማሪ ተራሮች በደን እስካልተሸፈኑ ድረስ ጉስቁልናው እንደሚቀጥል፣ ‹‹ብልፅግናችን እንዲመጣ ከተፈለገ የኢትዮጵያ ደጋማ ቦታዎች በደን መሸፈን አለባቸው፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...