Tuesday, May 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበሬዲዮ ጥገና የተፍታቱ እጆች

በሬዲዮ ጥገና የተፍታቱ እጆች

ቀን:

ማኅበራዊ ኑሮ ጎልቶ በሚታይበት፣ ቤቶች ግድግዳ ብቻ ሳይሆን በረንዳም በሚጋሩበት፣ ጎረቤታሞች እሳት ከጎረቤት ወስደው ምድጃቸውን ለማሞቅ በማያመነቱበት፣ የአንዱ ልጅ ሲገረፍ አንዱ በሚገለግልበት ኢትዮጵያዊነት ባየለበት ደጃች ውቤ ሠፈር ነው ትውልዱ፡፡ በዚህ የአብሮነት ሕይወት ውስጥ ሙያ ከጎረቤት የሚለው ብሂል ሳትሸራረፍ በተግባር ትውላለች፡፡ አንተነህ ታዬ እንደ ዕድሜ እኩዮቹ ውጭ ወጥቶ ኳስ ከማልፋት ባለፈ ሌላ የሚስበው የኤክትሮኒክስ ሙያም ጎረቤቶቹ የሚሻሙበት ልጅ አድርጎት ነበር ያደገው፡፡

አንተነህ ከመዳፍ ትንሽ ከፍ የሚትለውና ከአቅሟ በላይ ድምፅ የምታዥጎደጉደው የሬዲዮ ጉድ በልጅ አዕምሮው ሲያስገርመው ቆይቶ በኋላ ግን ደፍሮ ይነካካት፣ ከፋፍቶ ያያት ጀመረ፡፡ ቆይቶ ደግሞ ስትታመም የሚያክማት ሐኪሟ ለመሆን እንደቻለ ያስታውሳል፡፡ ገና የሰባተኛ ክፍል ተማሪ ሳለ ሬዲዮ እንደሚሠራ የሰሙ የደጃች ውቤ ነዋሪዎችም ልጅ ነው ብለው ሳይንቁት ሬዲዮናቸውን ያሠሩት ገቡ፡፡ በዚህ የጀመረው የኤሌክትሮኒክስ ፍቅር የኤሌክትሪካል ኢንጂነር እንዲሆን መሠረት እንደሆነው ይናገራል፡፡

የኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ትምህርቱን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ2006 ዓ.ም. የወሰደው አንተነህ የሚፈልገውን ትምህርት መማር እስኪችል ድረስ የተለያዩ መንገዶችን ማለፍ እንደነበረበት ይናገራል፡፡ የ12ኛ ክፍል ትምህርቱን አጠናቆ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሲገባ የተመደበው በሚወደው በኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ዲፓርትመንት ሳይሆን በስታስቲክስ ነበር፡፡ ይህ ግን ተስፋ አላስቆረጠውም ነበረና የስታስቲክስ ትምህርቱን አጠናቆ በሙያው ለወራት ከሠራ በኋላ ወደ ሚፈልገው ትምህርት የሚወስደውን መንገድ ማስተካከል ጀመረ፡፡

ሲፒዩ ኮሌጅ ገብቶ ኮምፒውተር ሜንቴናንስ ኤንድ ኔትወርኪንግም ተማረ፡፡ ከልጅነቱ ጀምሮ አጥብቆ የሚፈልገው ትምህርት ነበረና በማዕረግ ለመመረቅ እንደቻለ ያስታውሳል፡፡ ይህም የቴክኖሎጂ ፋኩልቲ ገብቶ አብዝቶ የሚወደውን የኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ትምህርት እንዲማር ዕድሉን ሰጠው፡፡ ለወትሮው የተበላሹ ኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን በመጠገን ለሚታወቀው አንተነህ ፍላጎቱ በትምህርት መዳበሩ ለሙያው አዲስ ምዕራፍ ከፈተለት፡፡

አንተነህ የራሱን አዳዲስ ፈጠራዎች ወደ መሥራት የተሸጋገረው ጊዜ ሳይወስድ ነበር፡፡ ‹‹ያለን ነገር መሥራት ሳይሆን ችግር መፍታት የሚችሉ አዳዲስ ነገሮች መሥራት ደስ ይለኛል፤›› የሚለው አንተነህ የመጀመርያ ሥራው የኢትዮጵያውያን ብቻ ችግር ስለሆነ አንድ ጉዳይ መፍትሔ የሚሰጥ መሣሪያ ነበር የሠራው፡፡ መሣሪያው የገበሬውን ድካም፣ የሚባክነውን እህል በከፍተኛ መጠን ማዳን የሚችል የጤፍ መውቂያ ማሽን ነበር፡፡

‹‹ጤፍ ከማሳው ሲነሳ ጀምሮ ትልቅ ብክነት አለ፡፡ ሲያጭዱም በቀላሉ ማሳው ላይ ስለሚረግፍ በከባድ ጥንቃቄ ነው፡፡ እንደዚያም ሆኖ የሚባክነው ብዙ ነው፡፡ ከማሳው አንስቶ ወቅቶ ለማስቀመጥ መሣሪያ ቢኖር ቀላል ነው፡፡ ነገር ግን ጤፍ የኛ ብቻ ስለሆነ ለጤፍ ተብሎ የተዘጋጀ ማሽን የለም፤›› ይላል አንተነህ፡፡ ብዙ ተስፋ የተጣለበት የጤፍ መውቂያ ማሽኑ ከአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ በዘለዘለ ያተረፈበት ነገር የለም፡፡ በጋዝና በኤሌክትሪክ ይሠራል የሚለውን ማሽን ለመሥራት ወደ 40 ሺሕ ብር አውጥቷል፡፡ በቀን ከ80 እስክ 120 ኩንታል ጤፍ የመውቃት አቅም እንዳለው፣ ገለባውን ለብቻው አስሮ ማስቀመጥ የሚችል እንደሆነም አንተነህ ይገልጻል፡፡ የማሽኑ መጨረሻ ምን ሆነ ሲባል ‹‹በቃ እዚያ ጋ አበቃ›› ይላል ጥሩ ፈጠራ ተብሎ ከመሞካሸት ውጪ መሬት ላይ አለመውረዱ እያበሳጨው፡፡

‹‹የምሠራው እንደ ሥራ ሳይሆን እንደ ጊዜ ማሳለፊያ ደስ እያለኝ ነው የምሠራው፤›› የሚለው አንተነህ ባገኛቸው አጋጣሚዎች ሁሉ የሰው ልጆችን ሕይወት ቀለል ማድረግ የሚችሉ ፈጠራዎችን መሥራት ሥራዬ ካለ ቆይቷል፡፡ በለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች የሚያጋጥሙ እያንዳንዳቸው መሰናክሎችና ሽንቁሮች ለአንተነህ አዲስ ሐሳቦች ናቸውና ይዘምትባቸዋል፡፡

የሥራው ባህሪ በብዛት ከተማ ውስጥ እንዳይቆይ የሚያደርገው በመሆኑ የኤሌክትሪክ፣ የውኃና የሌሎችም አገልግሎቶች ክፍያን ወቅቱ ጠብቆ ለመፈጸም ይቸግራል፡፡ ከተማ ውስጥ እያለም ቢሆን ክፍያ ለመፈጸም የመክፈያ ሥርዓቱ ለጊዜው አገልግሎት አቁሟል በሚል ከሚኖርበት ለገጣፎ አካባቢ ተነስቶ ሥርዓቱ ያልተቋረጠበትን መክፈያ ጣቢያ ፍለጋ ከተማዋን ሲያስስ የሚውልባቸው ጊዜያት ቀላል አይደሉም፡፡ ‹‹መብራት ሲጠፋ አንተነህም አብሮ ይቆማል፤›› ይላል፡፡

ስለዚህም ሰዎች የኤሌክትሪክ ሒሳባቸውን ባሉበት ሆነው በቀላሉ በሞባይል ስልካቸው ላይ መክፈል የሚችሉበትን አሠራር ፈጠረ፡፡ ይህ ዘዴ በአንድ በኩል የአገልግሎት ክፍያ መፈጸም የሚቻልበት፣ በሌላ በኩል ደግሞ የቅድመ ክፍያ ሒሳብ መሙላት የሚቻልበት ነው፡፡ ይህንንም ለማድረግ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽንና ቴሌ ኮሙዩኒኬሽን  የኤሌክትሪክ አገልግሎት ክፍያ በሞባይል ካርድ መክፈል እንዲቻል መስማት ብቻ ነው፡፡

 ይህ አሠራር በሥራ ላይ ከዋለ ተጠቃሚዎች ቀሪ ሒሳባቸውን ጨርሰው ኃይል ከመቋረጡ በፊት ቅድመ ማስጠንቀቂያ ስለሚደርሳቸው ኃይል ከመቋረጡ በፊት ሒሳብ መሙላት ይችላሉ፡፡ ከዚህ ባሻገርም ከሞባይል ስልካቸው ላይ ለአንድ ቀን የሚሆናቸውን  በአምስት ብር ገዝተው መጨመር ሁሉ ያስችላቸዋል፡፡ በተጨማሪም ጠርቀም ያለ ኃይል ካለው ጎረቤት ኃይል በስጦታ ወደ ቋታቸው ሊገባላቸው እንደሚችል አንተነህ ይገልጻል፡፡ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠሩ የቤት ውስጥ መገልገያ ዕቃዎች ማለትም አምፖል፣ ማቀዝቀዣ፣ ማጠቢያ ማሽንና የመሳሰሉትን በሞባይል መቆጣጠር፣ ማብራትና ማጥፋት የሚያስችል ፈጠራም እንዲሁ ሠርቶ ጨርሷል፡፡

ላጋጠሙትና በሰዎች ሲደርሱ ለሚያያቸው ችግሮች መፍትሔ መስጠት ዝንባሌው ያደረገው አንተነህ ከሚኮራባቸው ሥራዎቹ መካከል አንዱን ‹‹ሰሞኑን ይፋ ሳደርገው ትጽፊዋለሽ፤›› ሲል በልበ ሙሉነት ይናገራል፡፡ አንዱን ደግሞ ለሐሳቡ መነሻ የሆነውን አጋጣሚና የሥራውን ሒደት እንዲህ በዝርዝር አስታውሷል፡፡

 ለሐሳቡ መነሻ የሆነው ክስተት ያጋጠመው ለአንድ ጉዞ በረራ ለማድረግ ወደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ባቀናበት ወቅት ነበር፡፡ ፍተሻ ወደ ሚደረግበት አዳራሽ ሲገባ ወለሉ እየተፀዳ ስለነበር መንገደኞች በእርጥብ ወለሉ ላይ ሲንቀሳቀሱ እንዲጠነቀቁ የሚያሳስብ ጽሑፍ የሰፈረበት ፕላስቲክ ተደርድረዋል፡፡ በዚህ መካከል ግን አንድ ጠና ያሉ ሰውዬ ወለሉ አዳልጧቸው ክፉኛ ይወድቁና ከባድ ጉዳት ይደርስባቸዋል፡፡

አንተነህ በሁኔታው ብስጭት ብሎ ‹‹እያዩ አይሄዱም እንዴ?›› ሲል ተቆጣ፡፡ ወዲያውም ‹‹ብትራቸው ዓይን የለውም አያይም ጂኒየስ፤›› የሚል ምፀት ያዘለ ንግግር ጆሮው ገባ፡፡ ያኔ ነበር ወድቀው ጉዳት የደረሰባቸው ግለሰብ የሚያነቡት በብሬይል እንጂ ማንኛውንም ጽሑፍ አለመሆኑን የተረዳው፡፡ በንግግሩ ተፀፅቶ ብቻ ግን አላለፈም እርጥብ ወለል መለየት የዓይነ ሥውር በትር (ኬን) የመሥራት ሐሳብ መጣለት፡፡

‹‹አውሮፕላን ውስጥ እንደገባሁ ነው ሥራውን የጀመርኩት፡፡ ጎግል ሳደርግ ያገኘሁት ነገር ቢኖር ዓይነ ሥውራን እርጥብ ወለል ላይ ክፉኛ እንደሚወድቁና ለዚህም የተለየ መፍትሔ አለመኖሩን ነው፤›› ይላል ጅምሩን ሲያስታውስ፡፡ እርጥብ መሬት መለየት የሚችል መሣሪያ በቀላሉ ማግኘት እንደሚችል ቢያውቅም መልዕክቱን እንዴት ማስተላለፍ እንደሚችል ግራ ገብቶት ነበር፡፡

ኬኑ እርጥብ መሬት ሲነባ ንዝረት እንዲኖረው ለማድረግም አስቦ ነበር ነገር ግን ይህም ብዙ አጥጋቢ አልነበረምና ሌላ አማራጮችን መፈለግ ነበረበት፡፡ እስከዚያ ድረስ ግን በሙከራ ደረጃ እንዲያየው ሴንሰር የተገጠመለትን በትር ለአንድ ዓይነ ሥውር ይሰጠዋል፡፡

አንተነህ እንደሚለው፣ የዓይነ ሥውሮች በትር በጣም ውድ ነው፡፡ አንዱ 3,000 ብር ነው የሚሸጠው፡፡ የሚያመጡትም ጥቂት ሰዎች ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ 4.2 ሚሊዮን ሰዎች ዓይነ ሥውር ናቸው፡፡ ከተለያዩ የዕርዳታ ተቋማት የሚያገኙትን የገንዘብ ድጋፍም በብዛት ለኬንና ለሌሎች ቁሳቁሶች መግዣነት ነው የሚያውሉት፡፡ የዚህን ያህል ትልቅ ትኩረት የሚደረግበት ኬን በተፈጥሮው ጠንካራ ቢሆንም እኛ አገር ዓመት እንኳን አይጠቀሙበትም፡፡ ዓመት ሳይሞላው ስለሚሰባበርባቸው የመጥረጊያ እንጨት መያዝ ይጀምራሉ፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያትም በጣም ያሳዝናል፡፡

ዓይነ ሥውሮች ሲንቀሳቀሱ ከሌላው በተለየ ውሾች ያስቸግሯቸዋል፡፡ እንደ ሌላው ሰው ሮጠው ማምለጥ ስለማይችሉ ያላቸው አማራጭ በኬናቸው የቆሙበትን መሬት እየደበደቡ ውሻ እንዳይጠጋቸው ማድረግ ነው፡፡ ስለዚህም ረዘም ላሉ ዓመታት መቆየት ሲችል ኬናቸው በዚህ ምክንያት ያለ ጊዜው ተሰባብሮ ያልቃል፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ አንተነህ እርጥብ መሬት እንዲለያቸው የሠራው ኬን ላይ የተገጠመው መሣሪያ (አልትራሶኒክ ሴንሰር) ውሾችንና ሌሎች እንስሳት መቋቋም የማይችሉት ሞገድ የሚለቅ ነበር፡፡ የመጀመርያ ሙከራ ያደረገበት ዓይነ ሥውር ሰውም አንተነህ የሠራው ኬን እርጥብ ወለል ለይቶ ከመናገር ውጭ የተሻለ ጥቅም እንዳለው ሲነገረውም በሀሴት ነበር፡፡ ሰውየው የአንተነህን ኬን ይዞ ሲንቀሳቀስ ውሾች እንኳን እንደ ድሮ ከበው ሊያዋክቡት ገና ሳይደርስባቸው ከርቀት ጭራቸውን ቆልፈው ሲሸሹት ዋሉ፡፡ ከእርጥብ ወለል ይልቅ ሳይታሰብ ቀመር ውስጥ ያገባው ውሾችን የማባረር አቅሙ ይበልጥ እንደተወደደለት አንተነህ ይናገራል፡፡

ባልጠበቀው ነገር ትልቅ ችግር መፍታት የሚችል ፈጠራ በመሥራት ደስተኛ የሆነው አንተነህ ብትሯ ተጨማሪ ነገሮች እንዲኖራት ብዙ መሥራት እንዳለበትም ተሰማው፡፡ እያንዳንዱን የምርምር ሒደቱን ከዓይነ ሥውር ጓደኛው ጋር እየተማከረ ዱላዋን ረቂቅ ማድረግ ቻለ፡፡ መጀመርያ በንዝረት መልዕክት ታስተላለፍ የነበረችውን ብረት ‹‹እርጥብ ወለል›› ስትል በድምፅ እንድትገልጽ አስቻላት፡፡

 ከዚያም በተጨማሪ በእንቅስቃሴያቸው ሁሉ የሚያጋጥሟቸውን ነገሮች እየለየች ከአደጋ ራሳቸውን መጠበቅ እንዲችሉ ፈጣን መልዕክት ማስተላለፍ እንድትችል ሆነ፡፡ በዚህ አላበቃም የአንተነህ ምርምር ቀጠለ ዱላዋ የሬዲዮ ፕሮግራሞን ማስተላለፍ እንድትልች አስፈላጊው ነገሮች ተደረጉላት፡፡ የብትሯ ይዘት ሳይቀየር ባለችበት ሁኔታ ሌሎችም ተጨማሪ ነገሮች ማካተት ቻለች፡፡

ከሁሉ ለየት ያለውና ምናልባትም ዓይነ ሥውራኑ ባለባቸው የማየት እክል ብዙ የሚቀርባቸው ነገር እንዳይኖር የሚያስችለው የፈጠራው አካል ግን ሌላ ነበር፡፡ የአንተነህ ኬን ከመነጽር ጋር ተቀናብራ የምትሠራው ተዓምር ኢትዮጵያውያንን የሚያኮራ ነው፡፡ ብትርና መነጽሩ በብሉቱዝ የሚገናኙ ሲሆን፣ የተገጠመላቸው አትራሶኒክ ሴንሰር ሲጨመር በመነጽሩ ላይ የተገጠሙ ትንንሽ ካሜራዎችና የጆሮ ማዳመጫ አንድ ላይ ሆነው ዓይነ ሥውራን አካባቢያቸውን በሚገባ እንዲያውቁ ያስችላሉ፡፡

መነጽሩ ላይ ያሉት ካሜራዎች እንደ ኮምፒውተር አዲስ ነገር ተቀብለው የሚያስቀመጡ፣ ያስቀመጡትንም ሳይዘነጉ የሚሰጡ ናቸው፡፡ ዓይነ ሥውራን ያለ ብሬይል ማንበብ እንዲችሉም ያደርጋሉ፡፡ ካሜራዎቹ ማንኛውንም ጽሑፍ፣ ምሥል  ማስቀረት የሚችሉ ሲሆን፣ በማዳመጫው ደግሞ ምሥልም ሆነ ጽሑፍ  በማዳመጫቸው በኩል በድምፅ ይደርሳቸዋል፡፡

አንድ ቀን ስሙን ጠርተው ያናገሩትን ሰው ምስልና ስም በማስቀረትም  በሌላ ጊዜ ሲገናኙ እከሌ ነው ብሎ መረጃ ይሰጣል፡፡ በአጋጣሚ ሰላም ሳይልዎ የሚያልፉን እንኳን ስሙ ጠርተው ማናገር የሚያስችል ነው፡፡ ዓይነ ሥውር ወገኖች በትራቸው በእንቅስቃሴያቸው ሁሉ የሚያወራቸው፣ ማንበብ ቢፈልጉ መጽሐፉ በጆራቸው የሚያንቆረቁርላቸው ታዛዥ ጓደኛቸው ነው፡፡

አዳዲስ ነገሮች ለመፍጠር የማይሰንፉት የአንተነህ እጆች ሌሎችም ተጨማሪ ጥቅሞች እንዲኖራት ከማድረግ አይቦዝኑም፡፡ ፊቱን ወደ ሌላ ፈቺ ፈጠራ እስኪያዞር የፈረደባት የዓይነ ሥውር በትር ሮቦት ሊያደርጋት ሁሉ ይችላል፡፡ ችግሩ እነዚህ የፈጠራ ሥራዎች በአንተነህ ኪስ ላይ ብቻ የተመሠረቱ መሆናቸው ነው፡፡ ‹‹ባለሀብት ጋር ብትወስጂ ለፈጠራሽ ከማጨብጨብ ባለፈ ምንም አያደርግም፤›› ሲል ፈጠራዎቹ የበርካቶችን ሕይወት የመለወጥ አቅም ቢኖራቸውም የእሱ ብቻ ሆነው እንዲቀሩ ያደረገውን የኢንቨስትመንት ችግር ይኮንናል፡፡

እስካሁን የምሠራቸውን ሥራዎች ኢንጂነሪንግ ፕሮቶታይፕ ለመሥራት የራሴን ገንዘብ ነው የምጠቀመው፡፡ የፕሮዳክሽን ፕሮቶታይፑን ግን እዚህ አገር መሥራት በጣም ከባድ ነው፡፡ አሁን እንኳን 3ዲ ፕሪንት ስላለ ትንሽ ቀላል ነው፡፡ ችግሩ ግን ወደ ውጭ ተልኮ ፕሪንት ማድረግ የፈጠራው ሚስጥራዊነቱን እንዲያጣ ያደርገዋል፡፡ ከዚህ ሲያልፍ ደግሞ የምንከፍለውን ገንዘብ በዶላር ከየት እናገኘዋለን? እኔ የፈጠራ ባለሙያ ነኝ፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ የጻፈልኝ የድጋፍ ወረቀት አለኝ 20 ዶላር ስጡኝ ብል የሚሰማኝ የለም እንደዚህ ዓይነት አሠራርም የለም፡፡ በሁለት ዶላር ምናምን የምገዛቸውን ጥቃቅን ዕቃዎች እዚህ ሲደርሱ 250 ብር ቀረጥ እከፍልበታለሁ፡፡ 53 ኢንች ቲቪ ከታክስ ነፃ እንዳስገባ ከሚፈቀድልኝ ምርምር ላይ የሚውሉ በፍሬ የሚገቡ ግብዓቶች ከታክስ ነፃ ቢገቡ ደስ ይለኛል፡፡ በማለት በአገር ዕድገት ላይ የራሳቸውን አሻራ ማኖር የሚችሉ የፈጠራን ሰዎች መንግሥት ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርግላቸውና ፈጠራዎቻቸው በተግባር እንዲውሉ አንተነህ ይጠይቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመስቀል አደባባይ የመግቢያ ክፍያ ለምን?

ወጣቶች፣ ሕፃናትና አረጋውያን ሳይቀሩ መንፈሳቸውን የሚያድሱበት እንዲሁም ሐሳባቸውን በነፃነት...

በሕገ መንግሥቱ የተዋቀረው ‹‹የብሔር ፖለቲካ›› እና ‹‹ሥርዓቱ›› ያስከተለው መዘዝና መፍትሔው

(ክፍል አራት) በዓቢዩ ብርሌ (ጌራ) ባለፈው ጽሑፌ (በክፍል ሦስት) አሁን ያለው...

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብና የመንግሥት መሪ ምሥል

በበቀለ ሹሜ በ2015 ዓ.ም. መጋቢት ወር ውስጥ ይመስለኛል በ‹ሸገር ካፌ›...

ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ያደረገው አዋጅ የፍትሐዊነት ጥያቄ አስነሳ

በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ስምንት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ በማድረግ ተቋማዊና...