በደቡብ ክልል ጌዴኦ ዞን ኮቸሬ ወረዳ ጨለለቆ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ የገባነው፣ ሐምሌ 27 ቀን 2010 ዓ.ም. ከረፋዱ አራት ሰዓት አካባቢ ነበር፡፡ ጣውላ በሚመስል እንጨት የታጠረው የቅጥሩ መግቢያ ላይ ራሱ ላይ ሻሽ የጠመጠመ፣ በአፉ ፊሽካ በቀኝ እጁ ክላሽ ጠመንጃ ያነገተና ተፈናቃዮችን ከሰርጎ ገብና ከድንገተኛ ጥቃት ለመከላከል በሚመስል በተጠንቀቅ የቆመ ጠባቂ ቆሟል፡፡ ጨለለቆ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተማሪዎች መዋያ ሳይሆን፣ 2,300 አባወራዎች የተጠለሉበት የክፉ ቀን መጠጊያ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ እያንዳንዱ አባወራ ከስምንት እስከ 17 ልጆቹን ይዞ ነው ትምህርት ቤቱን የሞላው፡፡
በጎጂና በጌዲኦ ዞኖች መካከል በተቀሰቀሰ ግጭት ከሚያዚያ 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ከ1.2 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የጉጂና የጌዲኦ ነዋሪዎች ከቀዬአቸው መፈናቀላቸው ይታወሳል፡፡ በኮቸሬ ወረዳ ከሚገኙ 45 መጠለያዎች ውስጥ በሁለቱ የሚገኙ ከአሥር ሺሕ በላይ የሚሆኑ ተፈናቃይ አባውራዎች፣ በቀይ መስቀልና በዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ማኅበራት የሚደረግላቸውን ዕርዳታ ለመቀበል ከንጋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ ተሠልፈዋል፡፡
ትምህርት ቤቱ በአንድ ወቅት ራሳቸውን ችለው ይኖሩ የነበሩ፣ ቀን ጥሏቸው ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ የሚበሉትንና የሚጠጡትን ለማግኘት የለጋሾችን እጅ ለማየት በተገደዱ ተፈናቃዮች ተሞልቷል፡፡ የለበሱት ያደፈ ልብስ፣ የተጎሳቆለ ገጻቸው ሰላምና መረጋጋት ከምንም በላይ መሆኑን ይመሰክራል፡፡ ከዚህም ከዚያም የሚሰማው የሕፃናት ዋይታና ለቅሶም ዕረፍት ይነሳል፡፡ ላይ በላይ የተወለዱ ሕፃናት ታናሽና ታላቅ መለየት የሚቻለው ተዛዝለው ሲታዩ ነው፡፡ አዛዩ ታላቅ፣ ታዛዩ ደግሞ ጀርባው ላይ ሆኖ የማያባራ ለቅሶ የሚያሰማው ይሆናል፡፡
በቀጭን ሲባጎ ለሁለት በተከፈለው ግቢ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ዕርዳታ ጠባቂዎች ተኮልኩለዋል፡፡ የሚያጠቡ እናቶች፣ በዕድሜ ጫና በሰው እየተመሩ የሚሄዱ አዛውንቶች፣ ጎልማሶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ በተጎሳቆለ ገጻቸው ቁጣና እልህ የሚፈራረቅበት፣ ተስፋ መቁረጥ የሚታይበት በርካታ ወጣቶች፣ ከሰባት እስከ አሥር ዓመት የሚሆናቸው እልፍ ሕፃናት፣ ብቻ ከሁሉም የማኅበረሰቡ ክፍል የተውጣጡ ምንዱባን ጨለለቆን አጨናንቀዋታል፡፡
በሲባጎው አጥር ውስጥ ሆነው በረደፍ የተከመረውን የዕርዳታ ቁሳቁስ አሻግረው ያያሉ፡፡ ጊዜው ደርሶ ዕደላ ከመጀመሩ በፊት የወረዳው አስተዳዳሪ የዕርዳታ ቁሳቁስ ተረጂዎች መሸጥና ለሌላ ተግባር ማዋል እንደማይቻል፣ ለራሳቸው ጥቅም ብቻ እንዲያውሉ ቀጭን ትዕዛዝ ከማስጠንቀቂያ ጋር ሰጡ፡፡ ዕደላው እንደተጀመረ ግን በሲባጎው ቁጥጥር ሥር የነበረው የተረጂዎች ሠልፍ በአንዴ ወደ ትርምስ ተለወጠ፡፡
ተረጋግቶ የነበረው ሠልፍ ፈንጂ እንደተጠመደበት ሕንፃ ድንገት ድርምስ አለ፡፡ አንዱ በአንዱ ላይ እየተረማመደ ወደ ፊት ገሰገሰ፡፡ ቦታው በአንዴ ቀውጢ ሆነ፡፡ ሕፃናትና እናቶች ወድቀው ተረጋገጡ፡፡ በነበረው መገፋፋትና መጓተት ብዙዎች ያደፈ ልብሳቸው ተቀዶ እርቃናቸውን ቀሩ፡፡ መግቢያ በር ላይ ቆሞ የነበረው ጥበቃ ፊሽካውን እየነፋ እንዲረጋጉ ያረገው ሙከራም አልሠራም፡፡
ከደቂቃዎች በኋላ ግን በጥቂቱም ቢሆን መጋጋት ተፈጠረ፡፡ ዕርዳታ ሰጪዎችም ያላቸውን ልምድ ተጠቅመው እናቶችና ሴት ልጆች ቅድሚያ እንዲያገኙ በማድረግ ዕርዳታው ቀጠለ፡፡ ነገር ግን አፍታም ሳይቆይ እንደገና ሁካታ ተፈጠረ፡፡ የያዘውን መሣሪያ ከትከሻው አውርዶ በእጁ ይዞ እየተንጎራደደ በስልክ ይነጋገር የነበረው ጥበቃ ዕርዳታው ከሚሰጥበት በኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሁለት ሰዎች መገደላቸውን፣ ሕዝቡም ተቆጥቶ አደባባይ መውጣቱን ሰምቶ ለዕርዳታ ተቀባዮቹ ነገራቸው፡፡ ሰላም ርቋቸው የቆዩ እናቶችና ልጆች ተጨነቁ፡፡ ሮጦ ለማምለጥ አቅም የሌላቸው አዛውንቶችም የሚደበቁበት አጡ፡፡
ወጣቶች በእልህና በቁጣ የመጣውን ለመመከት የግቢውን አጥር እየነቀሉ ተሯሩጠው ወጡ፡፡ ግቢው ትንፋሽ አጣ፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ ዕርዳታው ተቋረጠ፡፡ ቀጥሎ ምን ሊፈጠር እንደሚችል አይታወቅምና ጭንቀትና ውጥረት ነገሠ፡፡ ወዲያውም በቁጣ የገነፈሉ ከ100 የማይበልጡ ወጣቶች በቀይ ክላሰር ያነገቡትን መፈክር በጩኸት እያሰሙ በትምህርት ቤቱ አጠገብ አለፉ፡፡ ግቢው ውስጥ የነበሩም ተቀላቀሉዋቸው፡፡
ወደ ከተማ ወጥተው ብሶታቸውን ለማሳማት ያደርጉት ሙከራም አደገኛ ውጤት ይኖረዋል በሚል ሥጋት እንዲበተኑ ጥረት ማድረግ ተጀመረ፡፡ በማግባባት መበተን ስላልተቻለ ወደ ላይ መተኮስ ነበረበት፡፡ ተኩሱ የፈጠረው ድንጋጤ ከባድ ነበር፡፡ በግቢ ውስጥ ያሉ ሕፃን አዋቂ ሳይሉ ባሉበት በደረታቸው ለጥ አሉ፡፡ ከዚያም ሁሉም እግሩ ወደ መራው መሯሯጥ ጀመረ፡፡
አሁንም ያ የፈረደበት ጥበቃ ሰቅጣጭ ድምፅ የሚያወጣ ፊሽካውን እየነፋ እንዲረጋጉ ጥረት ማድረግ ጀመረ፡፡ ሰዎች ወደ ቀልባቸው መመለስ ሲጀምሩም ተቋርጦ የነበረው የዕርዳታ አሰጣጥ እንዲቀጥል ተደረገ፡፡ ዕርዳታው መንግሥት በሰጠው ኩፖን መሠረት የሚታደል ሲሆን፣ በተፈጠረው ግርግር ኩፖናቸው የጠፋባቸው ነበሩ፡፡ ይህና የተራዘመው የዕርዳታ አሰጣጥ ሒደት ያሰለቻቸው ቁጣቸውን በጉርምርምታ ይገልጹ ጀመሩ፡፡ ለሦስተኛ ጊዜ ሊቋረጥ የነበርው የዕርዳታ አሰጣጥ ተጨማሪ ፖሊሶች፣ የወረዳውና የዞኑ አስተደደር ሰዎች በመገኘት ተረጂዎችን አረጋግተው ሊቀጥል ቻለ፡፡ ቢሆንም ግን ከአንደኛው መጠለያ ጣቢያ የመጡ ተረጂዎች ወደ መጠለያቸው ሲመለሱ፣ መንገድ ላይ ምን ያጋጥመን ይሆን የሚል ሥጋት አድሮባቸው ነበር፡፡
ባለፉት ስድስት ወራት የጀመረውና መቋጫ ያልተገኘለት ግጭት ከ1.2 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎችን ከሞቀ ጎጇቸው እንዲበተኑ ምክንያት ሆኗል፡፡ በክልሉ በተለይ በጌዴኦ ዞን አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ አንድ አባወራ አሥር ያህል የቤተሰብ አባል እንደሚኖረው ይገመታል፡፡ በዞኑም መፈናፈኛ ባለመኖሩ ዛሬ እነዚህ የተፈናቀሉ የኀብረተሰብ ክፍሎች በግለሰብና በትምህርት ቤቶች፣ በዕድር ቤቶች፣ በመጋዘን፣ በድንኳን፣ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና በኢንዱስትሪ ዞኖች ተጠልለው ይገኛሉ፡፡
መንግሥት ለአንድ ሰው ቀለብ በወር 15 ኪሎ እህል የሚሰፍር ሲሆን፣ የዕርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ደግሞ ቁሳቁሰ እያቀረቡ ናቸው፡፡ በክልሉ ከሚገኙ 45 መጠለያ ጣቢያዎች መካከል የሆነው በክልሉ ኢንዱስትሪና ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የይርጋ ጨፌ ከተማ አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማምረቻ ማዕከል ደማሶ ይባላል፡፡
በዚህ ሥፍራ ስድስት ትልልቅ መስኮትና በር አልባ መጋዘን መሰል ቤቶች ይገኛሉ፡፡ በውስጣቸውም ሦስት ሺሕ ያህል ተፈናቃይ አባወራዎች ተጠልለዋል፡፡ ግቢው ጥሎ በነበረው ከባድ ዝናብ ጨቅይቷል፡፡ ከወገብ በታች ራቁታቸውን የሆኑ ሕፃናት በአንድ እግር ጫማ በጭቃው ውስጥ ወዲያ ወዲህ ይላሉ፡፡ በጉልበታቸው የሚድሁ እንቦቃቅሎችም አሉ፡፡ አዋቂዎች ደግሞ በቡድን በቡድን ሆነው ያወራሉ፡፡ ከመግቢያው በስተቀኝ አንድ በጎኑ የወደቀ፣ ሁለት ደግሞ ትልልቅ ባዶ የውኃ ታንከሮች ቆመዋል፡፡
የአንዱን መጋዘን ግድግዳ ታኮ ጣራቸው በሰፋፊ ኮባ ቅጠል የተሸፈነ በማዳበሪያ፣ በፕላስቲክ እንደ ነገሩ በቆመ እንጨት ተወጥረው ከውስጥ የሚወጣውን ጭስ ባገኙት ቀዳዳ የሚያስወጡ ማብሰያ ኩሽናዎችም ተደርደረዋል፡፡ ኩሽናዎቹ በተራ የሚሠራባቸው ናቸው፡፡ ሪፖርተር በሥፍራው ሲደርስ አንድ እናት ልጇን እያጠባች፣ አንድ ሕፃን ከጀርባዋ ቆሞ፣ ሁለት ሴት ሕፃናት ከፊት ለፊቷ ቁጭ ብለው ከእርጥቡ እንጨት የሚወጣው ጭስ እያጨናበሳቸው በሰፊው ብረት ምጣድ የምትጋገረው ትንሽ ቂጣ መድረሷን በጉጉት ይጠባበቁ ነበር፡፡
በአዳራሹ ዙሪያውንና መሀል ላይ ለመኝታ ብቻ የሚዘረጉ የተጠቀለሉ ላስቲኮችና ሸራዎች፣ እንዲሁም በብዛት በፌስታል የተቋጠሩ ልብሶች ይታያሉ፡፡ መሀል ላይ ደግሞ ለፋብሪካ አገልግሎት የሚሰጡ ከጣራው ቁልቁል የተንጠለጠሉ ሶኬቶች ይታያሉ፡፡ የሚገባውን ብርድ ለመከላከል የተለያዩ ልብሶች ደራርበው አንገታቸውን ጉልበታቸው ሥር ቀብረው ጥግ ጥጉን ይዘው የተቀመጡ አዛውንቶችና አካል ጉዳተኞችም አሉ፡፡
ቀን ገፍቶ ከቤታቸው ካፈናቀላቸው ከእነዚህ ምንድባኖች መካከል ወይዘሮ ዳመነች ንጉሤ ይገኙበታል፡፡ መኖሪያቸው ጀልዱ በሚባለው አካባቢ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ከሦስት ወራት በፊት በመኖሪያ ሥፍራቸው በተቀሰቀሰ ግጭት ስምንት ልጆቻቸውን አስከትለው፣ ተመሳሳይ ችግር ከገጠማቸው አንድ እርጉዝ ጎረቤታቸውና ሌሎች ወደ 20 የሚጠጉ ተፈናቃዮች ጋር ነበር ከቀዬአቸው የተፈናቀሉት፡፡ በርካታ ኪሎ ሜትሮችን በእግር በመጓዝ እንዳመለጡ ያስታውሳሉ፡፡ ወይዘሮ ዳመነች ከ40 ዓመት በላይ ከኖሩበት ቀዬ ሲፈናቀሉ፣ ሸክማቸውንና ጭንቀታቸውን ከባለቤታቸው ጋር መጋራት አልቻሉም ነበር፡፡
የትዳር አጋራቸው ይሙቱ ይኑሩ አያውቁም፡፡ ስምንት ልጆቻቸውን ያሳደጉትም ለብቻቸው ነው፡፡ ኑሯቸውን የሚደጉሙት ያላቸውን አነስተኛ መሬት እያረሱ በሚያገኙት ገቢ ነው፡፡ ‹‹ግጭቱ ሲከሰት ከሩቅ ነበር የሰማሁት፣ ተኩስና ጫጫታ ነበር፡፡ ወደ ማታ አካባቢ ወደኛ መንደር ደረሰ፡፡ በወቅቱ ማን ምን እንደሆነ አናውቅም፡፡ ልቀቁ ይህ የእናንተ አገር አይደለም የሚሉ ሰዎቸ ቤቶቻችን ማቃጠል፣ እርሻችንን መነቃቀል ሲጀምሩ ልጆቻችንን ብቻ ይዘን እንደወጣን ቀረን፡፡ መንገድ ላይ አስከሬኖች፣ የተቃጠሉ ቤቶች ይታዩ ነበር፡፡ አብራኝ የወጣችው ነፍሰ ጡር ጎረቤቴም ከአንድ ሰው ጋር በመሆን ጫካ ውስጥ ነው ያዋለድናት፤›› በማለት ብዙ ችግሮችን አልፈው ከአድካሚ ጉዞ በኋላ ወደ መጠለያው መግባታቸውን ይገልጻሉ፡፡
ወ/ሮ ዳመነች በመጠለያው የበጎ ፈቃደኛ አገልግሎት የሚሰጡ ሲሆን፣ በጨለለቆ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚሰጠውን ዕርዳታ እንደሳቸው ካኪ ከለበሱ በጎ ፈቃደኞች ጋር በመሆን ሲያስተባብሩ ነበር ሪፖርተር ያገኛቸው፡፡ ‹‹እኔ ይኼ አይደለም የሚያስጨንቀኝ፡፡ እዚህ አንድ ቀን ባደርኩ ቁጥር ወደ ቤቴ የመመለስ ተስፋዬ እየራቀብኝ እንደሆነ፣ በዚህም ሜዳ ላይ ተበትኜ እንደቀረሁ ዓይነት ስሜት ነው የሚሰማኝ፡፡ የመጠለያ ኑሮ ከባድ ቢሆንም ያልፋል፤›› ያሉት በዕንባ ታጅበው ነበር፡፡
በደቡብ ክልል ከመንግሥት ጋር በመሆን የተፈናቃዮችን ጉዳይ ከሚያስተባብሩት አንዱ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ነው፡፡ በክልሉ የማኅበሩ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተሾመ ታከለ፣ በወቅቱ በተፈጠረው ችግር ላይ ምን እየሠሩ እንደሆነ ባደረጉት ገለጻ፣ ቀይ መስቀል አስተባባሪ በመሆን በዚህ ዓመት ብቻ በደረሱ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ከሺሕ በላይ አባወራዎችን ለመርዳትና የሰብዓዊ አገልግሎት ለመስጠት የቻለ ነው፡፡ በቅርቡ በሁለት ዞኖች በተፈጠረው ግጭት ደግሞ፣ ግጭቱ ከተከሰተ ጀምሮ ከ49 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የቁሳቁስና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሰጠ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ችግሩ ከባድና የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱን አቅም እየተፈታተነው ይገኛል ሲሉም እያጋጠመ ያለው ችግር አሳሳቢ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ማኅበሩ በመሠረተ ልማት የሚሳተፍ ሲሆን፣ ይኼንን ገንዘብ ሰላም ቢሆን ከአምስት በላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን መገንባት ያስችል እንደነበር አስረድተዋል፡፡ ችግሩ በቶሎ ተቀርፎ ተፈናቃዮች ወደመኖሪያቸው የማይመለሱ ከሆነ፣ ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ ሊፈጠር ይችላል በማለት ያላቸውን ሥጋትም ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሰሎሞን ዓሊ (ዶ/ር)፣ ከዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ጋር በመተባበር ለአሥር ሺሕ አባወራዎች 20 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ዕርዳታ የቀረበ መሆኑን፣ ድንኳኖች ሙሉ የኩሽና ዕቃ፣ ብርድ ልብስ፣ ምንጣፍ፣ የንፅህና መጠበቂያ ሳሙናዎች መስጠታቸውን አስረድተዋል፡፡ በቅርቡም ከዕርዳታ ሰጪዎች በተገኘ 27 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ትልልቅ የውኃ ታንከሮችን ጨምሮ ሌሎች ድጋፍ ማኅበሩ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡
የጌዲኦ ዞን ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊና በዞኑ የተፈናቃይ ጉዳዮች አስተባባሪው አቶ ዘሪሁን ማሞ፣ ‹‹ችግሩ እየቆየ የሚሄድ ከሆነ በዞኑ ላይ ከባድ ጫና ይፈጥራል፡፡ ዞኑ የራሱን ችግር ለመፍታት እያደረገ ያለውን ሥራም ወደኋላ ይጎትታል፡፡ በዚህ ዓመት በዞኑ በተደረገ ጥናት 14 ሺሕ አባወራዎች መሬት አልባ ሲሆኑ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ከስምንት ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ለድርቅ እንደሚጋለጥ በመገመቱ፣ የእኛን ድርሻ በመውሰድ ለመከላከልና ሌሎች ተዛማጅ ሥራዎችን በጥናቱ መሠረት በተፈቀደልን 27 ሚሊዮን ብር ለመጀመሪያ ዙር እየሠራን ባለንበት ወቅት ነው ይኼ ችግር ያጋጠመን፤›› ብለዋል፡፡
ተፈናቃዮቹን የማስተናገዱ ሥራ ከተለያዩ የመንግሥትና የዕርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ጋር እየተሠራ ቢሆንም፣ ዞኑ ሙሉ ጊዜውንና ሀብቱን እዚህ ላይ እያዋለ በመሆኑ ከፍተኛ ጫና እያደረበት እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ በዞኑ ያሉ ትምህርት ቤቶች በሙሉ የተፈናቃዮች መጠለያ በመሆናቸው፣ በውስጣቸው ያሉ የመማሪያ ዴስኮች ለማገዶነት እየዋሉ ናቸው ብለዋል፡፡ እነዚህን ጠግኖ በመጪውን ዘመን ትምህርት ለማስጀመር አዳጋች ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል ሲሉ ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
በጌዴኦና በጉጂ ዞኖች መካከል የተጀመረው ዕርቅ ታች ድረስ ወርዶ እያንዳንዱ ተፈናቃይ ያለ ሥጋት ወደ አካባቢው እንዲመለስ ውይይት እየተደረገ ሲሆን፣ ተፈናቃዮችም ላለመመለስ እንደ ችግር ከሚያነሷቸው ምክንያቶች አንዱ የአጥፊዎች በፍጥነት በሕግ አለመጠየቅ ነው፡፡ ይህም ሥጋት እንደሆነባቸው ይናገራሉ፡፡ ‹‹ችግሩ ከተፈታ ማቋቋሙን በተመለከተ ወደ ሚመለሱበት አካባቢ እንደ ጉዳታቸው እየታየ በሚደረግ ድጋፍ፣ ለዘለቄታው ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ ቀላል ነው፤›› ሲሉ ኃላፊው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
የጉጂና የጌዴኦ ዞን ግጭት የጀመረው በ1997 ዓ.ም እንደሆነ ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡ በ2002 ዓ.ም. ሙከራ እንደነበርና በአገር ሽማግሌዎችና በአባገዳዎች ዕርቅ ተፈጽሞ አጥፊዎችም ተቀጥተው በሰላም መኖር እንደቻሉም ያስረዳሉ፡፡