Friday, April 19, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ከጫት ሱሰኝነት እንዴት መላቀቅ ይቻላል?

በሰላማዊት ተስፋዬ

የተለያዩ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ጥናቶች እንደሚያረጋግጡት ኢትዮጵያ በጫት ምርትና ሽያጭ ከዓለም ቀዳሚውን ደረጃ ይዛ ትገኛለች፡፡ በኮክሬን ኦልና ኦሬጋንዲ (2016) የተደረገ ጥናት እንደሚያመለክተው፣ ባለፉት 15 ዓመታት በኢትዮጵያ ለጫት ምርት ጥቅም ላይ የሚውለው የመሬት መጠን በ160 በመቶ ሲጨምር የአጠቃላይ የአገሪቷ የጫት ምርት ደግሞ በ246 በመቶ ከፍ ብሏል፡፡ በቀደምት ጊዜያት የጫት ተጠቃሚነት በውስን የአገራችን ክፍሎችና በተወሰኑ አካባቢዎች ይዘወተር የነበረ ቢሆንም፣ አሁን አሁን ግን የተጠቃሚው ቁጥር በተለይም በከተማዎች አካባቢ በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል፡፡ ዕድሜ፣ የትምህርት ደረጃና ባህል ሳይገድበው በየአካባቢያችን በበርካታ ሰዎች ሲዘወተር ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ በተለይ በወጣቱ አካባቢ አሁን አሁን ይህ ሁኔታ ጎልቶ ይታያል፡፡ የጫት ተጠቃሚዎች ቁጥር በጨመረ መጠን፣ የሱሰኞችም ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ በተለያዩ አጋጣሚዎች ይነሳል፡፡

ሱስ በጣም ውስብስብ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው፡፡ በሱስ የመያዝ ምክንያቶችም እንደ ሰው፣ እንደ አካባቢውና እንደ አኗኗራችን ሊለያይ ይችላል፡፡ በአጠቃላይ ግን ሰዎችን ለሱስ ይዳርጋሉ ወይም ተጋላጭ ያደርጋሉ ተብለው ከሚታመንባቸው ምክንያቶች መካከል ለችግር ወይም ለጭንቀት መፍትሔ የማጣት ስሜት፣ ለችግር ወይም ለጭንቀት ቀጥተኛ መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ ሱስን እንደ ጊዜያዊ መጠለያ መጠቀም፣ እንደ አጋጣሚ ተጀምሮ ራስን ማላቀቂያ መንገዶችን አለማወቅ፣ ተስፋ መቁረጥ፣ ለራስ ያለ ክብር ወይም ስለራስ ያለ አመለካከት ዝቅ ማለት፣ የአቻ ግፊት፣ በአቻዎች ተቀባይነትንና ተወዳጅነትን መሻት ወዘተ. የሱስ መነሻ ምክንያቶች ሊሆኑ ከሚችሉ ሁኔታዎች መካከል ይገኙበታል፡፡ በዓለም የጫት አቅርቦት የመሪነትን ደረጃ አንደመያዟ ኢትዮጵያ ከዓለም ከፍተኛ የጫት ተጠቃሚ አገሮች እነ የመን፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ መካከል ትመደባለች፡፡ በአገራችን የጫት ሱስ ተቀዳሚውን ሥፍራ ከሚይዙ የሱስ ዓይነቶች አንዱ ነው፡፡ በዩኤንኦዲሲ በተደረገ ዳሰሳ ላይ እንደተቀመጠው፣ እ.ኤ.አ. በ1993 በአማኑኤል ሆስፒታል አልጋ ይዘው የአዕምሮ ሕክምና ከሚከታተሉ ታካሚዎች መካከል 43 በመቶው የአዕምሮ ሕመማቸው ከሱስ ጋር የተገናኘ ነበር፡፡ የጫት ሱስ ቀዳሚውን ሥፍራ ከሚይዙት መነሻ ምክንያቶችም ይመደባል፡፡  

በተለያዩ አጋጣሚዎች ከተለያዩ የጫት ተጠቃሚ የቅርብ ወይም የሩቅ ጓደኞቼ ጋር ስለጫት፣ ስለ ጠቀሜታዎቹና ጉዳቶቹ፣ ስለ ጫት ሱስና ሱሰኝነት ተወያይቻለሁ፣ ተከራክሬአለሁ፡፡ ከሁሉም የሚያስገርመኝ ነገር ግን ከማውቃቸው የጫት ተጠቃሚዎች አንዳቸውም ሱስ ሊኖርባቸው እንደሚችል አለማሰባቸው ወይም ለማሰብ አለመፍቀዳቸው ነው፡፡ ስለጫት ወሬዎች ሲወሩ ከመካከል ጫት የሚቅም  አንድ ግለሰብ ጫት ምንም በደል አለመፈጸሙንና እሱ ጫት ቢጠቀምም ሱሰኛ አለመሆኑን ሊያስረዳን የሚሞክርበት አጋጣሚ በርካታ ሊሆን ይችላል፡፡ ሁላችንም ሱሰኛ ካልሆንን ታዲያ የጫት ሱሰኛ ማነው? እቅማለሁ ግን ሱስ የለብኝም ከሚለው ዓረፍተ ነገር በመቀጠል ከጫት ተጠቃሚዎች በተደጋጋሚ ከምሰማቸው የመከላከያ ሐሳቦች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡

በጫት ላይ የተደረገም ጥናት የለም?

አንዳንድ የጫት ተጠቃሚዎች ጫት በተፈጥሮ የሚገኝ ቅጠል በመሆኑ ጉዳት እንደማይኖረው ሲናገሩ እንሰማለን፡፡ ጫት ተፈጥሯዊ ይሁን እንጂ የበርካታ ጎጂ ንጥረ ነገሮች ቅንጅት ነው፡፡ በዋንኛነት አነቃቂና ሱስ አምጪ የሆነው ካቶኒን ንጥረ ነገር ይገኝበታል፡፡ እነዚህም የተለያዩ ንጥረ ነገሮች የጎንዮሽ ውጤታቸው እንደበቀሉበት አካባቢና እንደ ዝርያቸው የተለያየ ሊሆን ይችላል፡፡ በአጠቃላይ ግን የዓለም ጤና ድርጅትን ጨምሮ በተለያዩ አካላት የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያትቱት፣ ጫት አሉታዊ ተፅዕኖ ከሚያሳድርባቸው የሰው ልጅ የአካል ክፍሎች መካከል ነርቭ (ነርቨስ ሲስተም)፣ ጨጓራና አንጀት ይገኙበታል፡፡ እንዲሁም በአሜሪካ ድራግ ኢንፎርስመንት ኤጀንሲ የተደረገ ጥናት እንደሚያስረዳው ከጫት ዘለቄታዊ የጎንዩሽ ውጤቶች መካከል የጉልበት (ኃይል) ማነስ፣ ተነሳሽነት (ሞቲቬሽን) ማጣት፣ የፀበኝነት (ቫዮለንት) ባህሪ፣ ጥልቅ የሆነ የድብርት ስሜት (ዲፕሬሽን)፣ ራስን የማጥፋት ሐሳቦችና ባህሪዎች፣ አለመረጋጋት (መቁነጥነጥ)፣ ሐሉሲኔሽንስ (የቁም ቅዠት)፣ ከእውነታ የራቀ የፍርኃትና የሥጋት ስሜት (ፓራኖያ)፣ እንዲሁም ለአዕምሮ ሕመሞች ተጋላጭነት መጨመር (ሳይኮሲስና ማኒያ) ይገኙበታል፡፡

አቅምን ለመጠቀምና ምናብ እንዲሰፋ ያደርጋል?

በርካታ ሰዎች ጫት ሲቅሙ ሥራ የመሥራት አቅማቸው ከፍ እንደሚል ሲናገሩ እንሰማለን፡፡ በተቃራኒው ጫት ላይ ሆነው የጻፉትን ጽሑፍ በኋላ መረዳት እንደሚያቅታቸው አንዳንድ ሰዎች ሲናገሩ ሰምቻለሁ፡፡ በዓለም ጤና ድርጅት የተደረገ ጥናት ጫት በመቃም ሒደት ውስጥ የሚፈጥረውን የምርቃና ስሜት ከገለጸ በኋላ፣ በምርቃና ወቅት ጥርት፣ ኩልል ያሉ በርካታ ሐሳቦች በአዕምሮ ይመላለሳሉ፡፡ ነገር ግን የአትኩሮት (ኮንሰንትሬሽን) ብቃት በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል ይላል፡፡ በሌላ በኩል እንደሚስተዋለው የጫት ተጠቃሚዎች (ከዝግጅት እስከ ምርቃና፣ ከምርቃና እስከ ሰበራ ወዘተ.) በጫት ላይ የሚያሳልፉት  ሒደት የሚወስደው ጊዜ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ በአንዳንድ ሁኔታዎች ጫት መቃም በጀመርንበት መጀመርያ አካባቢ የሥራ ሒደትን ሊያፋጥን የሚችልበት ሁኔታ ቢኖርም፣ በጊዜ ሒደት ግን ተመሳሳይ ውጤት ለማግኘት የምንቅመው የጫት መጠን በከፍተኛ ደረጃ መጨመርና ሥራችንን ያለ ጫት ማከናወን አለመቻል ወይም ጥገኝነት ሊከሰቱ የሚችሉ ሁኔታዎች ናቸው፡፡

የሚደረደሩ ምክንያቶች

ይህንን በአብዛኛው የምንሰማው ካለፍ አገደም እቅማለሁ እንጂ የሕይወቴ አካል አይደለም ከሚሉ ጓደኞቻችን ወይም ወዳጆቻችን ሊሆን ይችላል፡፡ ነገሩ የእውነት እንደገለጹት ነው ብንል እንኳን ይህ አካሄድ ምንም ዓይነት ጉዳት የለውም ማለት አይቻልም፡፡ ‹‹ሱስ ሲጀምር አሽከር ነው በኋላ ግን ጌታ ይሆናል፤›› እንዲሉ ሱስ አስያዥ ነገሮችን በተቻለ መጠን ከራሳችን እንድናርቅ፣ ወይም በጤነኛ መዝናኛ መንገዶች እንድንተካ ከሚመከሩባቸው ምክንያቶች መካከል እንደ ቀልድ ተጀምረው በሒደት፣ በሕይወት ውጣ ውረድ እንዲሁም እንዳለንበት ሁኔታ  የአጠቃቀማችን መጠን ሊጨምር ስለሚችልና ለሱስ ያለንን ተጋላጭነት ከፍ ስለሚያደርገው ነው፡፡ ሌላው አንዳንዴ ተጠቃሚዎች ያሉበትን የጥገኝነት ደረጃ ባለመረዳትም ሱስ እንደሌለባቸው እንዲያስቡ (ዲናያል ውስጥ እንዲሆኑ) ሊያደርጋቸው ይችላል፡፡ አንዳንዴ ያለንበትን ሁኔታ በይበልጥ ለመረዳት ቤተሰብን፣ ወዳጅን ወይም የሚያምኑት ጓደኛን ከጫት ተጠቃሚነት ጋር በተያያዘ ስለኛ ያላቸውን አስተያየት መጠየቅ የተለየ ምልከታ ሊሰጥ ይችላል፡፡

አጋላጭ ምክንያቶች

በርካቶች ሱስ ሳይሆን ጫት ላይ ከወዳጆቻቸው ጋር የሚያደርጓቸው ጥልቅ ውይይቶች ከጫት እንዳይርቁ እንደሚያደርጋቸው ሲናገሩ ይሰማሉ፡፡ ነገር ግን በአብዛኛው ጫት ላይ ከጓደኞቻችን ጋር የሚነሱ ሐሳቦችን በተግባር ሕይወታችን ላይ ልናውላቸው እንዲሁም ልንጠቀምባቸው የምንችላቸው ናቸው ወይ? ብለን ራሳችንን ልንጠይቅ ይገባል፡፡ ሌላው ጥያቄ የእረፍት ቀን ከከተማ ወጣ ብላችሁ ወይንም በቅርብ ያለ የምትወዱት ሌላ የመዝናኛ ቦታ ሆናችሁ፣ ከተቻለ ለየት ያለ ምግብ እየበላችሁ ወይም እንዲያው በቆሎና በውኃ ብቻ እነዚያን ጥልቅ ሐሳቦች እያነሳችሁ ጫት አልባ ውይይት ማድረግ ትችላላችሁ? ይኼንን ጥያቄ ራስን መጠየቅ ቁምነገሩ ጫቱ ነው ወይስ ጨዋታው ላይ የሚለውን ይመልስልናል፡፡ አንድ የጫት ተጠቃሚ እንዳጫወተኝ፣  ‹‹ጫት ላይ ብዙ ሐሳቦች ይነሳሉ፡፡ በአብዛኛው ግን ውይይቶቹ ለረጅም ጊዜ አይዘልቁም … በተለይ አብሮ መቃሙ በተደጋገመ ቁጥር አዳዲስ ሐሳቦች መነሳታቸው ይቆምና ውይይቶቹ፣ ቀልዶቹ፣ ፍልስፍናዎቹ ሁሉ ድግምግሞሽ የበዛባቸውና አሰልቺ ይሆናሉ፡፡ ስለዚህ አሁንም አብሮ ሆኖ ብቻውን እንዳለ ሁሉ ሁሉም ወደ ቁዘማው፣ ስልክ፣ ኮምፒዩተር፣ ወይም እጁ ላይ ወዳለው ማንኛውም ነገር ትኩረቱን ያዞራል፡፡››

ጫት ብዙ ዓይነት ሰዎችን ያስተዋውቃል?

አንዳንድ ሰዎች ጫት ላይ ብዙ መሳጭ (ኢንተረስቲንግ) ሰዎችን እንደሚያገኙና እንደሚተዋወቁ ይነግሩናል፡፡ ጫት ከሚያዘወትሩበት ምክንያቶችም ይህንን እንደ አንደኛው ይጠቅሳሉ፡፡ እርግጥ ነው በአሁኑ ወቅት በርካታ ሰዎች የጫት ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ነገር ግን ‹‹ኢንተረስቲንግ›› ሰዎች ሁሉ ጫት እየቃሙ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ከጫት ውጭ ልናገኛቸው ስለምንችላቸው ሰዎች ማሰብ የተለየ ምልከታ ሊሰጥ ይችላል፡፡ ጊዜያችንን ጫት ላይ በማሳለፋችን ውጭ ካሉ የተለያዩ ዕድሎች፣ ጠቃሚ አጋጣሚዎች እንዲሁም ሕይወታችንን ሊቀይሩ ከሚችሉ ሰዎችና ሁኔታዎች ራሳችንን እያራቅን ቢሆንስ? በሌላ በኩል ሌሎች ጫት ላይ የሚያገኟቸው ሰዎች ቁም ነገረኛ እንዳልሆኑና በዋል ፈሰስ እንደሚሆኑባቸው ሲናገሩ ይሰማሉ፡፡ ብሩክ (ትክክለኛ ስሙ አይደለም) እንዲህ ሲል አስቀምጦታል፣ ‹‹የጫት ጓደኝነት ላይ በአብዛኛው መደጋገፉ ያለው በጫት ዙሪያ ነው፡፡  ብዙ ጊዜ ጓደኝነቱ ጠንካራ መሠረት የሌለውና የላይ የላይ ነው፡፡ በጫት ዙሪያ ሚደረገው ትብብር ሌሎች የማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ግን አይታይ፡፡፤›› በጫት ሱስ ከተጠመደ ሰው ጋር የፍቅር ወዳጅነት መሥርታ በጣም ከባድ እንደሆነባት የነገረችኝ አንዲት ጓደኛዬ ያለችውን ልጥቀስ ‹‹ቀጠሮ ተቀጥሮ አይመጣ፣ ድግስ ተጠርቶ አይመጣ፤ አስፈላጊ ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ መገኘትም መከራው ነው፣ ስልችት ነው ያለኝ…›› ከሱሰኝነት መገለጫ ባህሪያት አንዱ ከሱሱ ውጪ ላሉ ጉድኝቶቻችን፣ ለቤተሰብ፣ ለቅርብና ለምንወዳቸው ሰዎች ተገቢውን ጊዜና ትኩረት መስጠት አለመቻል ነው፡፡

ሌላ የእረፍት ጊዜ ማሳለፊያ የለም?

ጫት በምርቃና ወቅት ዘና ያድርግ እንጂ ምርቃና ሲያልፍ በጎ ያልሆኑ ስሜቶችን ያስከትላል፡፡ ከእነዚህም መካከል ጥልቅ የድብርት ስሜት፣ ስሜታዊነትና ነጭናጫነት፣ የምግብ አለመስማማት፣ እንቅልፍ ማጣት ወይም የተረበሸ እንቅልፍ መተኛት የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡ በተጨማሪም ከጫት ጋር በተያያዥነት እየተለመዱ የመጡ ሌሎች ሱስ አስያዥ ነገሮች ለምሳሌ ሲጋራ፣ መጠጥ፣ ሐሽሽ የየራሳቸው የጎንዮሽ ውጤቶች እንዳሏቸው ይታወቃል፡፡  ብዙ ጊዜ የጫት ሱሰኞች በምርቃና ወቅት ከሚፈጠረው ስሜት ውጪ ከፊትና በኋላ ያሉ አሉታዊ ገጽታዎቹን ወይም ስሜቶቹን ከግምት አለማስገባት ይመርጣሉ፡፡

በአገራችን የእረፍት ጊዜ ማሳለፊያ ሥፍራዎች አለመኖር በተደጋጋሚ ከምንሰማቸው መከላከያ ሐሳቦች መካከል ይገኙበታል፡፡ አሁን አሁን ሁኔታዎች እየተቀየሩ ቢመጡም ሐሳቡ ከእውነት የራቀ ላይሆን ይችላል፡፡ የተለያዩ ምርጫዎችን ያካተቱ በርካታ የመዝናኛ ሥፍራዎች ባይኖርም ቆም ብለን ብናስብ፣ በሕይወታችን ከጫት ሌላ ማድረግ የምንወደው ወይም የሚያዝናናን ነገር የለም ማለት ያዳግተናል፡፡ ለጫት ሥነ ሥርዓት የሚወጣ ወጪን ወደሌሎች ነገሮች ማዞርን ማሰብም ይረዳል፡፡ ጊዜ ወስደን ጊዜ ቢኖረን ልናደርጋቸው የምንፈልጋቸውን ነገሮች ዝርዝር በወረቀት ብናሰፍር ሊያስገርመን ይችላል፡፡

የጫት ሱስ ከእንጀራ ሱስ በምን ይለያል?

በምዕራቡ ዓለም ከምግብ ሱስ ከሱሶች መሀል ከተመደበ ሰነባብቷል፡፡ በተለይም ከፍተኛ ውፍረት (ኦቤሲቲ) ከመስፋፋቱ ጋር በተያያዘ ጉዳዩ ትኩረትን አግኝቷል፡፡ ነገር ግን ብዙ ኢትዮጵያውያን መመገቢያ ሰዓታቸው በደረሰ ቁጥር በተደጋጋሚ እንጀራ  መብላት መምረጣቸውና እንጀራ ካላገኙ በከፍተኛ ደረጃ መናፈቃቸው ብቻውን የእንጀራ ሱሰኛ ላያደርጋቸው (ላያደርገን) ይችላል፡፡ መሪ ጥያቄ መሆን ያለበት ሰዎች አንድን ነገር በተደጋጋሚ ማድረጋቸው ሳይሆን ድርጊቱ በሕይወታቸው፣ በአካላቸውና በአዕምሯቸው ላይ እያስከተለ ያለው ውጤት ምንድነው? የሚለው ነው፡፡ እናም ከዚህ አንፃር ስንመለከተው የጫት ሱስ ከሻይ ሱስ፣ ከቡና ሱስም ሆነ ከእንጀራ ሱስ በእጅጉ ይለያል፡፡

በአጠቃላይ በአገራችን የጫት ተጠቃሚዎች ቁጥር ከዕለት ዕለት እየጨመረ እንደመምጣቱ የጫት ጥገኝነት (ዲፔንዳንሲ) እና ሱስም አብረውት ከፍ እያሉ እንደሆነ ይስተዋላል፡፡ የጫት ሱስ ሕይወታቸው ላይ በጎ ያልሆነ አንድምታ እንዳለው ሲያወሱ የሚሰሙ ግን ጥቂት ናቸው፡፡ በአገር ደረጃም እንደ ችግሩ ጥልቀት ውይይቱ በሰፊውና ለውጥ በሚያመጣ መንገድ እየተካሄደ አለመሆኑ ይስተዋላል፡፡ ለውጥ ከራስ ይጀምራል እንዲሉ የጫት ተጠቃሚ ከሆንን ከላይ በተነሱት ሐሳቦች መሠረት ራስን መርምሮ ለውጥ ያስፈልገኛል? ወይስ አያስፈልገኝም? የሚለውን መጠየቅ ያለንበትን ደረጃ ተረድተን ነገሮች ይበልጥ ሳይከብዱ መፍትሔ ለማግኘት ያስችለናል፡፡ በግላችንና በአካባቢያችን ዕገዛ መፍትሔ ማግኘት ካልቻልን በቂ አይሁን እንጂ፣ በአገራችን በአንዳንድ ተቋማት ከጫት ሱሰኝነት የመላቀቂያና የማገገሚያ አገልግሎቶች ይሰጣሉ፡፡ የባለሙያ ዕገዛን ማግኘትም ወደ ምንፈልገው አቅጣጫ እንድንጓዝ ይረዳል፡፡

የጫት ሱሰኛ እንደሆኑ ከተሰማዎ ወይም ከጫት ሱሰኝነት ጋር በተያያዘ ዕገዛ ካስፈለግዎ፣ አገልግሎቱን ከሚሰጡ ተቋማት መካከል የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የሳይኪያትሪ ሕክምና ክፍል ይገኝበታል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊዋን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡ 

 

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles