በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ቅጥር ውስጥ በ5 ሚሊዮን ዶላር አዲስ ብሔራዊ የደም ባንክ ሊገነባ መሆኑ ተገለጸ፡፡ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ቅጥር ውስጥ የሚገነባው ሕንፃው ለ26 ሚሊዮን ዜጐች አገልግሎት የመስጠት አቅም እንዳለውም ተገልጿል፡፡ በ5,300 ካሬ ሜትር ላይ የሚያርፈው ይህ ባለአምስት ፎቅ ሕንፃ የግንባታ ወጪን የሚሸፍነው ዩኤስኤ አይዲ (USAID) መሆኑን ረቡዕ መጋቢት 26 ቀን 2008 ዓ.ም. በጤና ጥበቃ በተደረገው የመሠረት መጣል ፕሮግራም ላይ ተገልጿል፡፡
ግንባታው ሲጠናቀቅ በአዲስ አበባና በዙሪያዋ ላሉ አካባቢዎች የሥልጠና፣ የጥናትና የምርምር ማዕከል ሆኖ እነደሚያገለግል በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሜዲካል አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል ዶ/ር ዳንኤል ገብረሚካኤል ተናግረዋል፡፡ ‹‹ካለው የሕዝብና የበሽታ ብዛት እንዲሁም ከሚፈለገው የደም መጠን አንፃር ያለው ደም ባንክ የሚሰጠው አገልግሎት በጣም ዝቅተኛ ነው፤›› ያሉት ዳይሬክተሩ የደም ባንኩ በቀን 200 ከረጢት ደም ያልበለጠ እንደሚሰበስብ፣ አዲስ የሚገነባው ግን በቀን እስከ 1,000 ከረጢት የመሰብሰብ አቅም እንዳለው ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም ብሔራዊ ደም ባንኩ ይሰጥ ከነበረው አገልግሎት በተጨማሪ በደም ውስጥ ያሉ ሌሎች ፕሮቲኖች ጥቅም ላይ እንዲውሉ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ይኖረዋል፡፡ ይህም እንደ ደም መርጋትና ደም መፍሰስ ላሉ በሽታዎች መፍትሔ እንደሚሆን ዶክተሩ አክለዋል፡፡
በመላው አገሪቱ የሚገኙ 24 የደም ባንኮችን የማጠናከር ሥራ እንደሚሠራም ታውቋል፡፡ በተጨማሪም በቅርቡ ለተጀመረው የኩላሊት ንቅለ ተከላና ወደፊት ሊሰጡ ለሚችሉ ሌሎች ተመሳሳይ አገልግሎቶች የሚውል የውስጥ አካል ስጦታዎች ማሰባሰቢያ ሆኖ እንደሚያገለግል ተገልጿል፡፡ ካለው የአገልግሎቱ ተፈላጊነትና ተደራሽነት አኳያ በተቻለ መጠን ግንባታው ተፋጥኖ በአጭር ጊዜ ውስጥ አገልግሎት መስጠት እንዲጀምር የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶ/ር ከሰተብርሃን አድማሱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አሁን ባለው ማዕከል የሚሰበሰበው 50 በመቶ የሚሆነው ደም ለወላድ እናቶች ይውላል፡፡ ከእናቶች ቀጠሎ አብዛኛው ደም የሚውለው ለትራፊክ አደጋ ሰለባዎች ነው፡፡ ነገር ግን ካለው የአገልግሎቱ ውስንነት እንዲሁም የለጋሾች ቁጥር ማነስ አኳያ የሚፈለገውን ያህል ደም ማግኘት እየተቻለ አይደለም፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት ባወጣው መሥፈርት መሠረት አገሪቱ በየዓመቱ ከ900,000 ከረጢት ደም በላይ ያስፈልጋታል፡፡ ይሁን እንጂ ይህን ማሳካት አልተቻለም፡፡ ባለፈው ዓመት ለመሰብሰብ የተቻለው 28,000 ከረጢት ደም ብቻ ነበር፡፡ ይህ ትልቅ የቤት ሥራ መኖሩን ጠቋሚ ሲሆን የዩኤስኤ አይዲ ሚሽን ዳይሬክተር ዴኒስ ዊለር እንዳሉት ማዕከሉ ግንባታው ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር በደም እጦት የሚሞቱ እናቶችን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ የመቀነስ አቅም አለው ብለዋል፡፡