Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየስብሐት ትውስታዎች

የስብሐት ትውስታዎች

ቀን:

በኢትዮጵያ ታሪክ ትልቅ ቦታ ከሚሰጣቸው ቀኖች አንዱ፣ ሚያዝያ 27  ኢትዮጵያውያን ጀግኖች አርበኞች የፋሺስት ኢጣሊያ ሠራዊትን ድል የነሱበት ዕለት ነው፡፡ መታሰቢያውም በየዓመቱ ይዘከራል፡፡ የዘንድሮው ሚያዝያ 27 ግን የድሉ 75ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዩ በመሆኑ መዘከር ብቻም ሳይሆን ደምቆ ተከብሯል፡፡ ዕለቱ በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ደማቅ አሻራቸውን ካኖሩ ጸሐፍት አንዱ ደራሲና ጋዜጠኛ ስብሐትለአብ ገብረእግዚአብሔር (ስብሐት) ወደዚህ ዓለም የመጣበትም ነው፡፡ ስብሐት የካቲት 12 ቀን 2004 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት ከመለየቱ በፊት የቅርብ ወዳጆቹ ልደቱን ሲያከብሩለት፣ ‹‹ልደቴን የሚያከብርልኝ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፤›› ይል እንደነበር እኚሁ ወዳጆቹ ይናገራሉ፡፡ የተወለደበት ቀን የጀግኖች አርበኞች ድል የሚወሳበት ቀን መሆኑን ይገልጽ ነበር፡፡

ስብሐት በሕይወት ሳለ እስከ 80 ዓመቱ ድረስ መኖር ይመኝ እንደነበር የቅርብ ወዳጆቹ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ማስታወሻ›› የተሰኘው ስለ ስብሐት ታሪክና ሥራዎቹ የሚያትተው መጽሐፍ ደራሲ ዘነበ ወላ ‹‹በአንድ ወቀት ስብሐትን እስከ ስንት ዓመትህ መኖር ትፈልጋለህ ብዬ ጠይቄው እስከ 80 ዓመቴ መኖር እፈልጋለሁ ብሎኛል፤›› ይላል፡፡ ዘነበ ስለስብሐት የሕይወት ታሪክ ለመጻፍ እንዲሁም በተለያዩ አጋጣሚዎች ስብሐትን ያገኘው ነበር፡፡ ከአጋጣሚዎቹ አንዱ ለአንድ የሥነ ጽሑፍ መርሐ ግብር ወደ ሐረርጌ ያመሩበት ነው፡፡ በቦታው ካቀረበለት ጥያቄዎች አንዱ እስከ ስንት ዓመትህ የምትኖር ይመስልሃል ነበር፡፡ ስብሐትም ለሌሎቹ ወዳጆቹ እንደሚለው እስከ 80 ዓመት ብሎ መልሶለታል፡፡ በወቅቱ 60 ዓመቱ ነበር፡፡ ህልሙ እውን ሳይሆን በ76 ዓመቱ ቢያርፍም ወዳጆቹ 80ኛ ዓመቱን ሚያዝያ 27 ቀን 2008 ዓ.ም. አክብረውለታል፡፡ ልደቱን ምክንያት በማድረግ አምስት ኪሎ በሚገኘው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ድህረ ምረቃ አዳራሽ የተለያዩ የኪነ ጥበብ ዝግጅቶችና የጥናት ጽሑፎች ቀርበዋል፡፡

ምሁራን ስብሐት ከአብዮት በፊትና በኋላ በሚል ርዕስ በሁለቱ ወቅቶች ስለነበረው ስብሐት ያላቸውን ምልከታ አቅርበዋል፡፡ ከስብሐት ሥራዎች መካከል በ‹‹ሰባተኛው መልአክ›› ላይ ገፀ ባህሪ ተኰር ትንተና የቀረበ ሲሆን፣ ‹‹አምስት ስድስት ሰባት›› ከተሰኘው አጭር ልቦለዱ የተቀነጨበ አጭር ተውኔትም ቀርቧል፡፡

‹‹ስብሐት ከአብዮት በፊት›› ን ያቀረቡት ፕ/ር ሽብሩ ተድላ ናቸው፡፡ የፕሮፌሰሩና የስብሐት ቤተሰቦች በጋብቻ ስለሚተሳሰሩ በቤተሰብ ዝግጅቶች ላይ ይገኛኙ ነበር፡፡ በሥራ የሚገኙበት አጋጣሚም ነበር፡፡ ፕ/ር ሽብሩ በ1960ዎቹ አካባቢ የሚያውቁት ስብሐት ከጥቂት ዓመታት በኋላ በአመለካከት ተለውጦ እንዳገኙት ይናገራሉ፡፡ ‹‹ስብሐት በ1964 ዓ.ም. አካባቢ ስለ እያንዳንዱ ነገር ጠያቂ ነበር፡፡ ከዓመታት በኋላ ግን ይህ ተለውጦ ስለነገሮች ብዙም አጥብቆ አይጠይቅም፤›› ሲሉ ይገልጻሉ፡፡ ደራሲው ስለ እንስሳት ባህሪ ሳይቀር ለማወቅ ይፈልግ ስለነበር ፕ/ር ሽብሩን ይጠይቃቸው ነበር፡፡ እርግቦች ጥንድ ከሆኑ በኋላ አለመለያየታቸውና ሴት አንበሳ ባሏ ከሞተ በኋላ ልጆቿ ካልሞቱ በስተቀር ከሌላ ወንድ አንበሳ ጋር አለመገናኘቷ ስለሚያስገርመው ደጋግሞ እንደጠየቃቸውም ያስታውሳሉ፡፡ ከዓመታት በኋላ ግን እነዚህን ስለመሰሉ ነገሮች መጠየቁን ትቶ ችላ ባይ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

‹‹ስብሐት ከአብዮት በኋላ›› በሚል ትውስታውን ያካፈለው ዓለማየሁ ገላጋይ፣  ከስብሐት ጋር ከተዋወቁበት ቅጽበት ጀምሮ ስለደራሲው ያለውን ምልከታ ተናግሯዋል፡፡ ብዙ ወጣት ደራሲያን እንዲሁም ሌሎችም የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ከስብሐት ጋር ረዘም ያለ ጊዜ ያሳልፉ ነበር፡፡ ጽሑፎቻቸውን እንዲገመግምላቸው የሚጠይቁት ደራስያንም ነበሩ፡፡ ከእነዚህ አንዱ ዓለማየሁ ነበር፡፡ ስብሐት በናቹራሊስት (ተፈጥሯዊ) አጻጻፍ ይታወቃል፡፡ ነፃ አስተሳሰቡ፣ አኗኗሩና አጻጻፉ ብዙዎችን ከመማረኩም በላይ ተከታዮች አፍርቷል፡፡

ዓለማየሁ ስብሐት ነገሮችን ቀለል አድርጎ የመመልከት ባህሪውንና በአካባቢው ላሉ ሰዎች ሁሉ ነፃነት መስጠቱን እንደሚያስታውስ ተናግሯል፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚሰጣቸው አስተያየቶች አመለካከቱን የሚያንፀባርቁ ሲሆኑ፣ ዓለማየሁ እንደ ምሳሌ የጠቀሳቸውም ነበሩ፡፡ በአንድ ወቅት ስብሐት ከደራሲ ኃይለመለኮት መዋዕል ጋር ሲሄድ በብዙ እሾህ የተከበበች ድጌረዳ አበባ ያያሉ፡፡ ስብሐት ‹‹ፈሪ! ለአንድ ነፍሷ ይሄ ሁሉ ጦር?››  ሲል ነበር ስለ አበባዋ የተሰማውን የገለጸው፡፡

‹‹የስብሐት ትዝታዎች›› በሚል ንግግር ያደረገው ዘነበ፣ ስብሐት ከሱ እንዲሁም ከሌሎች ወዳጆቹ ጋር ስለነበረው ትውስታ ተናግሯል፡፡ ስብሐት ከልጅነቱ ጀምሮ ብዙ መጻሕፍት ያነብ የነበረ ሲሆን፣ ‹‹ካላነበብክ መንጋ ትሆናለህ፤ አንብብ›› ይል ነበር፡፡ በዘነበ እይታ፣ ስብሐት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበረበት 1950ዎቹ የነበረው ትውልድ ለአገሪቱ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክትቷል፡፡ በስብሐት እጅ የተጻፉ ልቦለድና ኢልቦለድም ጽሑፎች እጁ ላይ እንደሚገኙ ዘነበ ተናግሯል፡፡ ‹‹ማስታወሻ››ን ለመጻፍ፡፡ ከስብሐት ጋር ያደረጋቸውን ንግግሮች የቀዳባቸውን ካሴቶች ተጠቅሟል፡፡ አሁን ያገኛቸውን ጽሑፎችም አቀናብሮ ወደ መጽሐፍ የመለወጥ እቅድ እንዳለውም አሳውቋል፡፡

ከስብሐት ተወዳጅ ሥራዎች አንዱ የሆነውን ‹‹ሰባተኛው መልአክ››ን ተንተርሶ የጥናት ጽሑፍ ያቀረበው በአዲስ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጽሑፍ አስተማሪ የነበረው መሠረት አበጀ፣ ከገፀ ባህሪያቱ መካከል የያሲንን የባህሪ ተቃርኖ ዳስሷል፡፡ ያሲን ቅዱስ፣ ነፃና ቀና ሰው ቢመስልም ከባህሪው የሚቃረኑ ነገሮች ሲያደርግ እንደሚታይ በጥናቱ ተመልክቷል፡፡ ያሲን ከነፃ ባህሪው በሚፃረር መልኩ የሴት ጓደኛው አይሪን በራሷ ፍቃድ እንዳትወሰን ሲያደርጋት ይታያል፡፡ ለሰዎች መልካም አድራጊ ሆኖ ቢቀርብም የሚፈልገውን ነገር ለማግኘት በሰዎች ሲጠቀም ይስተዋላል፡፡ መሠረት እነዚህንና ሌሎችም ምሳሌዎችን በማቅረብ በ ‹‹ሰባተኛው መልአክ›› ያለውን የገፀ ባህሪ ተቃርኖ ዳሷል፡፡ ከ‹‹አምስት ስድስት ሰባት›› ቀንጭቦ ተውኔት ያቀረበው ደግሞ ሄኖክ በሪሁን ነበር፡፡ ልጆቹንና ባለቤቱን በረሀብ ሳቢያ የተነጠቀውን አርሶ አደር በሱፍቃድ ወክሎ ተውኗል፡፡ በሱፍቃድ የሚወደው በሬ ሲሳይን ቤተሰቡን ለመመገብ  ሲል ለማረድ ቢገደድም ቤተሰቦቹን ከሞት ማዳን አልቻለም፡፡ አለኝ የሚለውን ነገር በሙሉ የተነጠቀው በሱፍቃድ ልጆቹና ባለቤቱ መቃብር ስፍራ ምሬቱን ሲገልጽ በተውኔቱ ይታያል፡፡

በዕለቱ ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ ስብሐትን መስሎ አጭር ድራማ አቅርቦ ነበር፡፡ ከስብሐት ጽሑፎች አንዱን አንብቧል፡፡ ጽሑፉ የሰው ልጅ በዚህ ምድር ላይ የሚያከናውናቸው ነገሮች ባጠቃላይ ትርጉም አልባ እንደሆኑና ዋናው ቁም ነገር አንድ ሰው ለሰዎች ያደረገው በጎ ምግባርና በሰዎች ልብ ያለው ቦታ እንደሆነ ያትታል፡፡ እንዳለጌታ ጽሑፉን ሲያቀርብ ስብሐት የሚያዘወትረውን ኮፍያ አድርጎ ነበር፡፡ ኮፍያው ለኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ሙዚየም በስጦታ ተሰጥቷል፡፡ ስብሐት በሕይወቱ የመጨረሻ ቀናት ይጽፍበት የነበረው እስኪርቢቶ፣ ሙሉ ልብሱና በእጁ የጻፋቸው ጽሑፎቹም በአዘጋጁ ኢጋ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን በኩል ለሙዚየሙ ተበርክተዋል፡፡

 ከዝግጅቱ ታዳሚዎች አንዷ ዶ/ር ኤልሳቤጥ ወልደጊዮርጊስ ስብሐት የተዘከረበት መድረክ መዘጋጀቱ መልካም እንደሆነ ተናግራለች፡፡ በደራሲያን ሕይወትና ሥራዎቻቸው ዙሪያ ውይይት የሚያደረግባቸው ዝግጅቶች መበራከት እንዳለባቸውም አክላለች፡፡ ሌሎች አስተያየት ሰጪዎችም ሐሳቧን ተጋርተዋል፡፡ ስብሐት ይመኘው የነበረው የ80ኛ ዓመት ልደቱ በወዳጆቹ መከበሩና ስለሥራዎቹ መወሳቱ ጥሩ ጅማሮ እንደሆነና በሌሎች ደራሲያንም መቀጠል እንዳለበት የተናገሩ ነበሩ፡፡

ስብሐት የተወለደው በ1928 ዓ.ም. በትግራይ ክልል ዓደዋ ከተማ ውስጥ ነበር፡፡ በአማርኛና በፈረንሣይኛ ከጻፍቸው መጽሐፍቱ በተጨማሪ ወደ እንግሊዝኛ የተተረጎሙ ሥራዎቹ ይጠቀሳሉ፡፡ በኢትዮጵያን ሄራልድ፣ በአዲስ ዘመንና መነን ጋዜጣ ላይ ይሠራ ነበር፡፡ ሌቱም አይነጋልኝ፣ ትኩሳት፣ ሰባተኛው መልአክ፣ እግረ መንገድ፣ ማስታወሻ፣ አምስት ስድስት ሰባትና የፍቅር ሻማዎች በአማርኛ ከተጻፉ ሥራዎቹ መካከል ናቸው፡፡ ሲድስ በዌንዲ ሲንደርድ ወደ እንግሊዝኛ የተተረጎመ ሥራው ነው፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...