Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህል‹‹ሀገር እግር አለው ይጓዛል እንደ ሰው ጀግና በየበሩ ቆሞ ካልመለሰው›› ሥነ...

‹‹ሀገር እግር አለው ይጓዛል እንደ ሰው ጀግና በየበሩ ቆሞ ካልመለሰው›› ሥነ ቃል

ቀን:

የፋሽስት ኢጣሊያ ወራሪ ሠራዊት ድል የተመታበትን 75ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዩ በዓል ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀው የባህል ሲምፖዚየም፣ ለድሉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ ሥነ ቃሎች ሊሰባሰቡ እንደሚገባ ተገልጾበታል፡፡ በጦርነቱ ወቅት አርበኞች አዝማሪዎች ሌሎች ኢትዮጵያውያንም የተገለገሉባቸው ሥነ ቃሎች በተዋቀረ መልኩ ተሰንደው ለቀጣዩ ትውልድ መተላለፍ እንዳለባቸውም ተመልክቷል፡፡

የአልማዝ ኢዮቤልዩ በዓሉን አስመልክቶ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የተለያዩ ዝግጅቶች ያሰናዳ ሲሆን፣ የባህል ሲምፖዚየሙ የዚህ አንድ አካል ነው፡፡ ሚያዝያ 19 ቀን 2008 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ብሔራዊ የባህል ማዕከል የተካሄደው ሲምፖዚየም ካስተናገዳቸው ጥናቶች አንዱ ‹‹የፋሽስት ወረራን የተዋጉ ሀገራዊ የሥነ ቃል ትሩፋቶች›› የተሰኘው የአቶ መስፍን መሰለ ጥናት ነው፡፡ አጥኚው ሥነ ቃሎች ጠላትን በመዋጋት ሒደት የነበራቸውን ከፍተኛ ቦታ ገልጸው፣ ሥነ ቃሎቹን በማሰባሰብ ረገድ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ኃላፊነት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

‹‹ፉከራ፣ ሽለላ፣ ቀረርቶ፣ መዲናና ዘለሰኛ እና ሙሾ ጠላትን ለመዋጋት የተጫወቱት ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ ከአርበኞች፣ ከአጥኚዎችና ከተቋሞች ተሰባስበው ታትመው ከትውልድ ትውልድ ሊተላለፉ ይገባል፤›› ብለዋል አቶ መስፍን፡፡ እሳቸው እንደተናገሩት፣ ታሪኩ በተፈጸመበት ወቅት የነበሩ የዓይን እማኞችና ተመራማሪዎች ጥቂት ሥነ ቃሎችን ለመመዝገብ ቢሞክሩም፣ ሥነ ቃሎቹ የትና በምን ምክንያት ጥቅም ላይ እንደዋሉ ከመግለጽ ባለፈ አልተጠኑም፡፡ አንዳንድ ግለሰቦችና አጥኚዎች ያደረጓቸው ሙከራዎችም በጥቂት ሥነ ቃሎች የተወሰነ ነው፡፡

‹‹ትንንሽ ሙከራዎችና ጅማሮዎች ከመደረጋቸው ባለፈ በስፋት አልተሠራም፡፡ በቃል ያለውን ታሪክ ከአርበኞች በመሰብሰብና ጥናት በማድረግ ባለሙያዎች መሳተፍ አለባቸው፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በጦርነቱ ወቅት ታዋቂ የነበሩ ፉከራዎች፣ ሽለላዎች፣ ቀረርቶዎችና የለቅሶ ግጥሞችን ለታዳሚዎች አሰምተዋል፡፡ ሥነ ቃሎቹ በጦርነቱ የትኛው ወቅት፣ በምን ምክንያትና በማን እንደተባሉ አያይዘው ለማቅረብም ሞክረዋል፡፡  

በጦርነቱ መጀመሪያ አካባቢ አርበኞችን ለማነሳሳትና ጀግኖች የሀገር ድንበርን በመጠበቅ ያላቸውን ሚና ለማሳየት

‹‹ሀገር እግር አለው ይጓዛል እንደ ሰው፤

ጀግና በየበሩ ቆሞ ካልመለሰው፤›› ተብሎ ነበር፡፡ ጦርነቱ በሚካሄድበት ወቅት በአንድ አካባቢ ላይ ድል ያደረጉ ጀግኖችን በማወደስ ሌላ አካባቢ ያሉትን ለማበረታታት የሚውሉ ሥነ ቃሎችም ተያይዘው ይጠቀሳሉ፡፡ በሽለላ ሀገር ላይ የደረሰውን በደል ተናግሮ ምን መደረግ እንዳለበት በመግለጽ የአገሪቱ ዜጐች ከየቦታው ጦርነቱን እንዲቀላቀሉ ይደረግም ነበር፡፡

‹‹ከ1928 – 1933 ዓ.ም. በነበረው ጦርነት የኢትዮጵያ አርበኞች በኢጣሊያ ወገን ይዋጉ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ባንዳዎችን የሚያንቋሽሹበት በሽለላ ነበር፤›› ብለዋል አጥኚው፡፡ ባንዳዎች ‹‹እንሂድ እንሂድ ሔደን እናምሰው፤ ምን ይመክተናል ደጀን የሌለው ሰው፤›› ሲሉ አርበኞች ደግሞ ሀገራቸውን ከድተው ለጣልያን የሚዋጉ ባንዳዎችን መልሰው ያንቋሽሻሉ፡፡

አርበኞች ቁጭ ብድግ እያሉ፣ እየተንበረከኩ፣ በፈረስ ላይ ሆነው ጦር እየሰበቁ ሲፎክሩ የሌሎች አርበኞችንና መላው ኢትዮጵያዊን ስሜት በሚቀሰቅስ መንገድ እንደሆነ በጥናቱ ተመልክቷል፡፡ ሕይወታቸው ያለፈ ጀግኖች የለቅሶ ግጥሞች ጀግኖቹን የሚያወድሱ ነበሩ ብለዋል አጥኚው፡፡ ጥናቱ እየቀረበ ስለ ፉከራና ሽለላ ሲወሳ ወኔያቸው የተነሳሳ አባት አርበኛ እየፎከሩ ከመቀመጫቸው ሲነሱ እንዲቀመጡ ተደርገዋል፡፡ የበዓሉ ዋነኛ አካል አርበኞች ሆነው ሳለ ተጋድሏቸውን የሚያስታውሳቸውን ፉከራ ድንገት ሲያሰሙ ከመከልከል ይልቅ ጊዜ ሊሰጣቸው ይገባ እንደነበር አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል፡፡

አባት አርበኛው ነሽጧቸው ፉከራውን ሲያቀልጡ የመድረኩ አጋፋሪዎች እንዲያቆሙ ማስገደዳቸው አስገምቷቸዋል፡፡ ፉከራ ከሽለላና ከቀረርቶ ተከትሎ የሚመጣ በመሆኑ አርበኛው እንዲቀመጡ ከተደረጉ በኋላ አጥኚው ቀጥለዋል፡፡ በጥናታቸው መሠረት አዝማሪዎችም አርበኞችን እያወደሱ ያዜሙ ነበር፡፡ በሥነ ቃሎቹ ጀግኖች ክብር ሲሰጣቸውና በሥራቸው ሲመሰገኑ ጠላት ደግሞ ይወገዛል፡፡ ጀግና ሲበረታታ ፈሪ በተቃራኒው ይሰደባል፡፡ መጪው ትውልድ አርበኞች ስለከፈሉት መስዋዕትነት እንዳይዘነጋ የሚያደርጉ ሥነ ቃሎች ብዙ ናቸው፡፡ ሥነ ቃሎቹ በተለያዩ ቋንቋዎች ይቀርቡ እንደነበረም በጥናቱ ተመልክቷል፡፡   

‹‹አቶ ሞሶሎኒ ምን አቅበጠበጠው፤

አልነገረውም ወይ ከዓድዋ ያመለጠው፤›› የሚለው ቀደምት አርበኞች በዓድዋ ላይ ስለተቀዳጁት ድል በማውሳት ጀግኖችን ለማነሳሳት ከዋሉ ሥነ ቃሎች አንዱ ነበር፡፡ ይህና ሌሎችም በርካታ ሥነ ቃሎች ተሰብስበው ለሕዝብ መቅረብ እንዳለባቸው አቶ መስፍን በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡

የድል በዓሉ ከሚያዝያ 19 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በተመሳሳይ ሲምፖዚየሞች፣ በዐውደ ርዕይና ሌሎችም ዝግጅቶች እየተከበረ ነው፡፡ በባህል ሲምፖዚየሙ ላይ ከሥነ ቃሎች በተጨማሪ ሥነ ጽሑፍ፣ ሥዕል፣ ሙዚቃና ተውኔት በጦርነቱ ወቅት ስለነበራቸው ሚና ጥናቶች ቀርበዋል፡፡  

ሲምፖዚየሙን የከፈቱት የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን፣ የሀገሪቱ ባለውለታ የሆኑ አርበኞች የሚደገፉበት መንገድ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ ታሪክ ተረካቢ የሆኑ ወጣቶች ለበዓሉ የተዘጋጁ መርሐ ግብሮችን እንዲታደሙም ጠይቀዋል፡፡ ‹‹በጠየቅነው መሠረት የኢጣሊያ ባለሥልጣኖች በድል ሐውልታችን ላይ የአበባ ጉንጉን ማስቀመጣቸው ትልቅ ነገር ነው፡፡ የአሁኑ ትውልድ አባቶችና እናቶች መስዋዕት የከፈሉባትን ሀገር ተረክቦ ባለው ነባራዊ ሁኔታ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት መትጋት አለበት፤›› ብለዋል፡፡

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ኢንጅነር አይሻ መሐመድ በበኩላቸው ፋሽስት ኢጣልያ ድል የተመታበት በዓል ከኢትዮጵያ አልፎ የመላው አፍሪካ ድል እንደሆነ ገልጸው፣ በነፃነት ተጋድሎው ጥበባትና ባህል የነበራቸው ሚና ጐልቶ መታየት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...