Monday, November 28, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -

  የተመረጡ ፅሑፎች

  አንዳንዴ እኮ መርሳትን የመሰለ ነገር የለም!

  ሰላም! ሰላም! የዛሬን አያድርገውና ቀደም ባለው ጊዜ እንዲህ እንደ ፋሲካ ያለው የመብል ዓውደ ዓመት ሲመጣ ብዙ ሰው ሆዱን ያመው ነበር አሉ። ዘንድሮ ቆረጠኝ፣ አማጠኝ፣ ለበለበኝ የሚል ሰው አላየሁም። ምናልባት የበጉና የዶሮው ተመን የወር ደመወዛችንን ስለበለጠው ‘የአንድ ወር ደመወዜን አርጄ በልቼማ አልጋ አልይዛትም’ ብለን ችለነውም ይሆናል። የማንችለው የለማ። ታዲያ እኔ ሰው በሥጋ ሲፈስክ  በነገር ፈስኬላችሁ ሳይርበኝና ሳይጠማኝ ጭንቅላቴ ፈረሰ። ምንድነው ነገሩ ካላችሁኝ እዚህ አገር ከምግቡ ይልቅ የምንበላው ነገር ስለሆነ አንድ በአንድ አጫውታችኋለሁ። እስከዚያ ከበዓል የተራረፈ ነገር ካለም አንጀታችሁ ላይ እየጎዘጎዛችሁ ብንጫወት ሳይሻል አይቀርም። ምናልባት እኔን ያቃጠለኝ እናንተን ካቃጠላችሁ በባዶ ሆድ እንዳያቃጥላችሁ ብዬ እኮ ነው። በዳግማዊ ትንሳዔ በነገር ‘ሰቀለን’ ብላችሁ ደግሞ ኋላ ጲላጦስና አይሁድ ላይ እንደሆነው ለሁለት ሺሕ የትዝብት ዓመታት ብታጽፉብኝ ኋላ የለሁበትም። እንኳን በባዶው ጠግበንም የነገር ችንካሩን አልቻልነውም ዘንድሮ!

   እናላችሁ የተነጀስኩት ልክ የፋሲካ ዕለት ነው። የዕለቱ ዕለት። ቃተኛ ተቀብቶ ቡና ተፈልቶ በጉን ላርደው ስል ማንጠግቦሽ፣ “ውይ ረስቼው ማነው ስሙን ሳልጠራው?” ብላ መሰንዘሪያውን ነጠቀችኝ። ‘ማን ነው ስሙ’ ብላ ስሙን ማስታወስ ያቃታት ጎረቤታችን በጃንሆይ ጊዜ የታወቁ ከበርቴ የልጅ ልጅ ነው። ነኝ እንደሚለው ነው እንጂ በማስረጃ አልተረጋገጠም። የማስረጃ እጥረት እኛ ሠፈር አልተጀመረም። እንኳን ወንዝ የማያሻግረው ይኼ ይኼ ቀርቶ ስንቱን ሠርቶ አዳሪ ባለጉዳይ በረከቱን አፍኖ ይዞ ሲያንከራትተው የምናየው፣ ይኼው የመረጃና የማስረጃ እጥረት ነው ለነገሩ። ካላመናችሁ አንድ ቀን ውልና ማስረጃ ሄዳችሁ ዋሉ። ደግሞ ከጀርባችሁ ያለው ማን ነው ስትባሉ አንበርብር ደላላው ነው አሉ አሉዋችሁ፡፡ ሚስጥርና ማስረጃ ስለተምታታብን ማለቴ ነው!

  ለነገሩ እኮ ያልተምታታብን ነገር የለም። የተምታታብንን ነገር አምታትቼ እያሳየኋችሁ ከማምታታቴ በፊት የጀመርኩትን ልጨርስላችሁ። ማንጠግቦሽ ተንሰፍስፋ ሄዳ ሰውዬውን ከአልጋው ጎትታ አውርዳ ይዛው መጣች። ሲጀምረኝ ይኼን ሰምቼ ነው። “አልነሳልኝ ብሎ በስንት መከራ ከአልጋው ጎትቼ አውርጄ ይዤው መጣሁ፤” አለች። ጎረቤት አለ። ባሻዬ አሉ። ልጃቸው አለ። እንግዲህ ይኼ ሁሉ ሰው እያለ አልጋን ሰበብ አድርጌ ብጣላ ነገ መንደሩ በውኃ እጥረት፣ በመብራት መቆራረጥ፣ በኑሮ ውድነት ሰበብ ድንገት (ድንገት ነው ያልኩት) ቢታመስ ‘መተራመሱን የሚመራው አንበርብር ምንተስኖት ነው። በቀደም ለፋሲካ አልጋን ሰበብ አድርጎ ከሚስቱ ጋር ዓውደ ዓመት ነው ሳይል ሲኳረፍ ያየነው እሱን ነው’ እባላለሁ ብዬ ዝም አልኩ። ይኼ ቀላል ነው ግድ የለም።

  የቤተሰቦቹን ጥሪትና ክብር በመቁጠር በየቤቱ ዓመት በዓል በመጣ ቁጥር ልብ የሚጎትተው ጎረቤቴ ገና ከመግባቱ እንኳን አደረሳችሁ ሳይል፣ ‘እንዴት አደራችሁ’ ሳይል፣ ገና ከመግባቱ ነው የምላችሁ፣ “በዓል ድሮ ቀረ!” ብሎ ከቤቱ አባወራ አንበርብር ምንተስኖት ሌላ የማይደፍረው ሶፋ ላይ ሄዶ ተቀመጠ። የባሻዬ ልጅ ነገሩ ገብቶት ይስቅብኛል። ባሻዬ ደግሞ አመሉን እያወቁ፣ “ድሮ ከቀረ ታዲያ ከሞቀ አልጋህ ምን አስነሳህ?” አሉት። ቆይቼ ሳስበው ለካ ምፀት ነው። ምክንያቱም የኖረውም ያልኖረውም አፍቃሪ ድሮ ነኝ ካለ አልጋውን ከማሞቅ ሌላ ሥራ ሲሠራ አላየንማ። እውነቴን ነው የማወራችሁ። አንዳንድ ሰው የለም የሰው መኪና እያሞቀ በስሙ ያዞረው የራሱ መኪና የሚመስለው? አልጋ ማሞቅም ከዚህ የተለየ አይመስለኝም። እንዲያ ባይሆን ታዲያ በቅስቀሳና በፕሮፓጋንዳ ናላችን ይፈርስ ነበር? ንገሩኛ!

  ድሮውና አልጋው የሚመሳሰሉት ጎረቤታችን ከቀማመሰ በኋላ ማንጠግቦሽ ውኃ ቀዳችለት። ይኼኔ ዘወር ብሎ እንኳ ሳያየኝ፣ “ይገርምሃል አንበርብር አያቴ ነፍሳቸውን ይማረውና የሚያስጥሉት ጠጅ አቻ አልነበረውም ይባላል። ጃንሆይ እንኳ ገና ሁዳዴ ሲገባ ነው አሉ ‘ስለማሩ አታስብ ብቻ የጠጄን ነገር አደራ’ ብለው ይልኩባቸው የነበር፤” እያለ ውኃውን ግጥም አድርጎ ጠጣ። ባሻዬ ይኼኔ ብሽቅ ብለው፣ “እኔ ምለው?” አሉት። “ጌታው! ጃንሆይ ናቸው ወይስ አያትህ ናቸው?” ብለው ቀና ብለው እንኳ ሳያዩ ጠየቁት። “ምነው ባሻዬ ጃንሆይ ናቸዋ ጃንሆይ፤” አላቸው። “ታዲያ እጅ ሊነሱ ቤተ መንግሥት ሲገቡ ጃንሆይ ራሳቸው ‘ወዲህ ና’ ብለው በጆሯቸው መንገር እየቻሉ በአደባባይ በተላላኪ ‘ጠጄን አደራ’ ብለው የሚልኩት ሰው ሰምቶ ያውም ሥዩመ እግዜሩን ‘ጠጪ ናቸው’ እንዲላቸው ነው? መቼም እኛ ስናውቅ ንጉሡ አናት ላይ ከአብዮት ቀድሞ ጌሾ አልወጣም፤” አሉልኛ።

  ይኼኔ ደግሞ ምሁሩ ልጃቸው ቀበል አድርጎ፣ “የለም አባዬ ምናልባት አያታቸውም እንደ እሳቸው ስለአያታቸው ሙያና ክብር ሠፈር ለሠፈር ሲነዙ እጅ ለመንሳት ጊዜ አልነበራቸው ይሆናል፤” ብሎ ቤቴን በሆታ ሳቅ ምች አስመታው። “ምን አለበት ሌላ ጨዋታ ብንጫወት? ቢራ አቀዝቅዣለሁ እኮ ላምጣ? እኔማ ጥብሱን ቀማምሰን ብዬ ነበር፤” አለች ወደ ዲስኩራሙ ጎረቤቴ ማንጠግቦሽ ጠጋ ሽብርክ ብላ። እንዳላያት እንዳልሰማት ሆኖ ምን ቢል ጥሩ ነው? “አይገርምም ባሻዬ? አሁን ይኼ ዘመን ይባላል? በፋሲካ ምድር በሃይማኖታዊ ክብረ በዓል ቀን ስፖንሰርና ማስታወቂያው ሁሉ የቢራ ብቻ ሲሆን አያሳፍርም?” ሲላቸው አላስደሰኩር ስላሉት ተቅለስልሶ፣ “በሥዩመ እግዜራውያን ዘመን በጠጅ ተፈሰከ ካልን ሰፊው ሕዝብ በነገሠበት ዘመንማ ምን ያሳፍራል?” ብለው ቆለፉልኝ። በነገራችን ላይ ይኼን ጨዋታ ስፖንሰር ያደረገላችሁ የጎረቤቴ አያት ጠጅ ነው! ይመቻችሁ!

  ነጃሹና ተነጃሹን ባለበት እንዳለ እንተወውና ሌላ ጨዋታ ላጫውታችሁ። ለዓመት በዓል ቀላል ወጪ እንዳላወጣሁ የታዳሚውን ብዛት ስነግራችሁ ታዝባችኋል። ቆጭቶኝ አይምሰላችሁ ያነሳሁት፡፡ ለምን ይቆጨኛል? በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ዓመቱን ሙሉ፣ ለራሱ ሳይበቃው፣ ለልማትም ለጥፋትም እያዋጣ ዶሮና በግ ለመሸመት የተሸነፈ ወገኔን በቻልኩት አቅም ሰብስቤ ማብላቴንማ አልፀፀትበትም። “ምነው እናብላው ብለው እየሰበሰቡ የሚበሉበት ሳይፀፀቱ ደግሞ እኔ ልፀፀት እንዴ?” ስል የባሻዬ ልጅ ጎትጉቶኝ፣ “የዋህ ነህ እኮ አንበርብር፤” ብሎ ሳቀ። ሳቁ ደስ አላለኝም። “ምነው?” ስለው ምን ቢለኝ ጥሩ ነው። “እኛ እኮ ስንበላ እንጂ ስናበላ ወትሮም አንፀፀትም። በገዛ እጅህ ጠላት በማፍራትህ ግን ልትፀፀት ይገባል፤” አይለኝ መሰላችሁ? አዙሬ አላየው ብዬ ለካ ብዙ ሊያስረዳኝ ጥሯል።

  ቆም ብዬ ሳስብ ይኼው የመጣ የሄደውን ትውልድ ራዕይና ተስፋ አዳፍኖ ያስቀረ ክፉ አመላችን ለካ ‘እንዴት እሱ መክሮኝ? እንዴት ከእሱ እጅ በልቼ?’ ነበር። ቁልቁል ስናይ እንጂ ሽቅብ ሳናይ፣ ዳገትም ስለማንወድ ጭምር መሰለኝ እኛም ቆመን ሌላውን አስቁመን የቀረነው። አይደለም እንዴ? ይኼን የባሻዬ ልጅ የገለጠልኝን ነገር እያሰብኩ ከበዓሉ በፊት አሻሽጬ ኮሚሽኔን ያልተቀበልኩበትን ቪላ ቤት ገንዘብ ልወስድ ወደ ባንክ ሄድኩ። እግሬ የባንኩን ደጃፍ ከመርገጡ በስልኬ የጽሑፍ መልዕክት ተንጣጣ። ሳየው ከሳምንት በፊት ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለሚማር የዘመዴ ልጅ የላኩለትን አምስት መቶ ብር ተመልሶ መጥቷል ይላል። ግራ ገብቶኝ ስደውልለት ዘግቶብኝ ሲያበቃ፣ “ስለአምስቱ አመዶችህ አመሰግናለሁ፤” ብሎ ጻፈልኝ። ኋላ ሳጣራ የመቶ ብር ተለዋጭ ስም ‘አመድ’ መሆኑን ደረስኩበት። እኔን እንዲህ ካለ አገሩን ምን ሊል ይሆን ብዬ ዝም አልኩኝ። አመድ ዱቄትን የሚሳደብበት ዘመን? እግዚኦ!

  በሉ እንሰነባበት። ደንበኛዬ ኮሚሽኔን በጊዜው አስገብቶልኝ ኖሮ ከዚያች ላይ የተወሰነች ቆንጥሬ ወደ ተመለደችዋ የእኔና የባሻዬ ልጅ መቃጠሪያ ግሮሰሪ ተጣደፍኩ። አንድ ታክሲ ልይዝ አንድ አስፓልት መንገድ መሻገር እንደቀረኝ ቅድም ያነሳሁላችሁን ያምታታንና የተምታታንበትን ነገር አስተዋልኩ። ልሻገር ዜብራዬን ይዤ ቆሜያለሁ። እግረኛ እንዲሻገር አሽከርካሪ እንዲቆም መብራቶቹ አዘዋል። በአካባቢው የትራፊክ ፖሊስ የለም ተብሎ ይሁን የተሽከርካሪው ብዛት አነስተኛ ነው ተብሎ (ሰበብ ካለ በሕግ ላይ የበላይ መሆን አለ የተባለ ይመስል) አሽከርካሪው ሁሉ እየጣሰ እየነዳ አላሳልፈን አለ። ሥርዓት ይዞ የነበረው መስመር ተዘጋጋ። አንድ መኪና ብቻ መብራት እስኪለቀቅ ይጠብቃል። ሌላው ወደዚያ አሽከርካሪ እየተገላመጠ፣ “ወገኛ! አንተን ብሎ ሕግ አክባሪ! አቦ አታካብድ ንዳው!” እያለው ያልፋል። ተገርሜ፣ ተገርሜ ጉድ ስል ሠፈሬ ደርሼ ወደ ግሮሰሪዋ ገባሁ።

  የባሻዬ ልጅ አግሎ ጠበቀኝ። መፍዘዜን አይቶ አንድ አንድ ‘ሻት’ አዘዘ። በዚህ ላይ ‘ሻት’ ተጨምሮበት ብዬ “ይቅርብኝ” አልኩ። “ምን ሆነሃል?” ሲለኝ ያየሁትን ተራ ጉዳይ የመሰለ ታላቅ የኅብረተሰብ ህሊና አመላካች ክስተት አጫወትኩት። “ምን ታደርገዋለህ?” ትከሻውን ሰበቀ። “መጀመሪያ ‘መንገድ የለ!’ ‘መሄጃ የለ’ ስንል ኖርን። መንገዱ ሲሠራ ‘መብራት የለው!’ ‘ሕግ የለው!’ ‘ቀለም የለው’ ብለን ተቸን። ሁሉም ሲኖረው ግን እኛ ጠፋን። ቆይ ግን በምን አፋችን ነው እንዲህ በትንሹ እየተገማመትንና እየተዛዘብን ስናበቃ ‘ቢዝነስ በቼይን ሆኗል፣’ ‘ቅጥር በዘመድ ነው፣’ ‘ሥልጣን በወገን ነው፣’ ‘ፍትሕ በገንዘብ ነው’ ብለን የምንተቸው? በመንገድ አካሄድና ሥርዓት ያልታመንን ለፍትሕ፣ ለዴሞክራሲ፣ ለመልካም አስተዳደር መሻሻል ታማኝ የምንሆነው በምን መሥፈርት ነው?” ስለው፣ “ተወኝ እባክህ! እኛ እኮ ከተምታታብን ቆየ፤” ብሎ አረሳሳኝ። አንዳንዴ እኮ እንዲህ የሚያረሳሱ ካልተገኙ ብዙ ችግር አለ፡፡ አንዳንዴ እኮ መርሳትን የመሰለ ነገር የለም፡፡  መልካም ሰንበት!       

  Latest Posts

  - Advertisement -

  ወቅታዊ ፅሑፎች

  ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት