Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየሰማያዊ ፓርቲ የቀድሞ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሽብር ወንጀል ክስ ተመሠረተባቸው

የሰማያዊ ፓርቲ የቀድሞ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሽብር ወንጀል ክስ ተመሠረተባቸው

ቀን:

– ድርጊቱን ፈጽመዋል የተባለው በፌስቡክ ገጻቸው ላይ መሆኑ ተጠቁሟል

የሰማያዊ ፓርቲ የቀድሞ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ከኅዳር 24 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በሚጠቀሙበት የፌስቡክ ገጻቸው ላይ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ተፈጥሮ የነበረውን አመጽ፣ ረብሻና ብጥብጥ እንዲቀጥል የተለያዩ መልዕክቶችን የያዙ መጣጥፎችን በመጻፍ፣ የሽብር ተግባር ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው ሚያዝያ 26 ቀን 2008 ዓ.ም. ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ባቀረበው ክስ እንደገለጸው፣ አቶ ዮናታን የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የአገሪቱን ፖለቲካዊ፣ ሕገ መንግሥታዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ተቋማትን ለማናጋትና ለማፈራረስ በማሰብ፣ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች የሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ክልል ልዩ ዞኖች የተቀናጀ ማስተር ፕላንን አስመልክቶ የተቀሰቀሱ አመጽና አድማዎች እንዲቀጥሉ በፌስቡክ ገጻቸው መሳተፋቸውን አስረድቷል፡፡

- Advertisement -

ተከሳሹ ከታኅሳስ 8 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት በፌስቡክ ገጻቸው በጻፏቸው መጣጥፎች፣ በተጠቀሱት ዞኖችና ወረዳዎች ኅብረተሰቡ መንገድ በመዝጋት የመንግሥት ሥራ እንዲስተጓጉል ማድረግ እንዳለበት መስበካቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡

የአንድ ሰው ነፍስ ከሚጠፋ ለጭቆና መሣሪያነት የሚያገለግሉ ማናቸውም ቁሳቁሶችን በቃጠሎ ማውደም፣ የሰላማዊ ትግል ዘዴ መሆኑን አቶ ዮናታን በፌስቡክ ገጻቸው እንደገለጹ ዓቃቤ ሕግ ጠቁሟል፡፡

ኢሕአዴግ ችግር ማዳፈን እንጂ መፍታት የሚያስችል አቅም እንደሌለው፣ ሰዎችን በመግደል ችግርን የፈታ እንደሚመስለውና ሕዝቡ ወደማይቀረው አመጽ እየተንደረደረ መሆኑን የሚያሳይ የሕዝብ አመጽ እየታየ በመሆኑ፣ ሌሎች እንዲነሱ የሚቀሰቅስ መጣጥፍ በገጻቸው ማስፈራቸውን በክሱ አብራርቷል፡፡

አቶ ዮናታን በተደጋጋሚ ከአሥር ጊዜያት በላይ በፌስቡክ ገጻቸው የጻፉት፣ ‹‹ሁሉም ነገር አንተ በሕይወት ስትኖር ነው፣ ማናቸውም ንብረትም ሆነ ቁስ አንተ ህልውናህን ካጣህ ትርጉም የለውም፣ አንተ የዘመን ተጋሪዬ ሰምተሃል፣ የኢሕአዴግ መጨቆኛ መሣሪያ የሆነውን ንብረት አውድም፤›› የሚሉ ቀስቃሽ መጣጥፎች እንደሚገኙ ዓቃቤ ሕግ በክሱ አካቷል፡፡

ኢሕአዴግን ማመን ጉም መዝገን መሆኑን፣ መታለል እንደሚበቃ፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንደሚፈልጉ፣ ሕዝባዊ መንግሥት መመሥረት አስፈላጊ መሆኑንና መሸወድ ማብቃት እንዳለበት የሚገልጹ መጣጥፎችን አቶ ዮናታን በፌስቡክ ገጻቸው ማስፈራቸውንም ዓቃቤ ሕግ አክሏል፡፡ ‹‹አትነሳም ወይ አትነሳም ወይ የሚሞተው ወገን ያንተ አይደለም ወይ? የአገሩ መሬት ያንተ አይደለም ወይ? ያባትህ ቁጭት አይገድህም ወይ? የገበሬው ጣር አይጠራህም ወይ? አታላይ ገዥ አይበቃህም ወይ?›› የሚሉ ቀስቃሽ መፈክሮችንም በፌስቡክ ገጻቸው በመለጠፍ፣ ኦነግ ያነሳሳውን ብጥብጥ እንዲቀጥል ማድረጋቸውን በክሱ አብራርቷል፡፡

ሙስሊሞች ቤተ እምነታቸውን መነጠቃቸውን፣ የኦሮሞ ተወላጆች መሬታቸውን እየተነጠቁ መሆኑን፣ የአማራ ተወላጆች በያሉበት እየተፈናቀሉ መሆኑን፣ የጋምቤላ ተወላጆች ከመሬታቸው እየተነቀሉ መሆኑን፣ የትግራይ፣ የአፋር፣ የወሎ፣ የሐረርጌ፣ የሶማሌ ነዋሪዎች ታፍነው በረሃብ አለንጋ እየተገረፉ መሆናቸውን፣ ወጣቱ በበረሃና በባህር እየተሰደደ መሆኑን፣ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ተረግጦ፣ ተዋርዶና ታፍኖ ግፍ እየተሠራበት መሆኑን የሚገልጹ አመጽ ቀስቃሽ መጣጥፎች በፌስቡክ ገጻቸው እያሰፈሩ፣ የኦነግን ዓላማ መደገፋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሯል፡፡

አቶ ዮናታን በአጠቃላይ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 4 በመተላለፍ፣ ዮናታን ተሬሳ ረጋሳ በሚል ስያሜ ፌስቡክ ገጻቸው ላይ ቀስቃሽ ጽሑፎችን በመጻፍ፣ የሽብርተኝነት ድርጊት ለመፈጸም በማቀድ፣ በመዘጋጀት፣ በማሴርና በማነሳሳት ወንጀል መከሰሳቸውን የዓቃቤ ሕግ የክስ ማመልከቻ ያስረዳል፡፡

አቶ ዮናታን ክሱ ከተነበበላቸው በኋላ የቅድመ ክስ መቃወሚያ ካላቸው ተጠይቀው እንዳላቸው በመናገራቸው፣ የክስ መቃወሚያቸውን ለመጠባበቅ ፍርድ ቤቱ ለግንቦት 15 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡   

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...