የንግድ ፈቃዳቸውን ለውጭ ዜጐች በማከራየት ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀደ የንግድ ሥራ የውጭ ዜጐች እንዲሰማሩ አድርገዋል በሚል ጥርጣሬ ንግድ ሚኒስቴር ዕርምጃ ከወሰደባቸው ድርጅቶች መካከል ተጐጂ የሆኑት ትውልደ ኢትዮጵያዊ፣ ንግድ ሚኒስቴር ድርጅታቸውን በማሸግ የወሰደውን ዕርምጃ ግብታዊና በመረጃ ላይ ያልተመሠረተ ሕገወጥ ድርጊት ነው ሲሉ ቅሬታቸውን አቀረቡ፡፡ ለጠቅላይ ሚኒስትሩም አቤቱታ አቅርበዋል፡፡
ትውልደ ኢትዮጵያዊው አቶ አብርሃም ሥዩም ለውጭ ዜጐች በተከለከለ ሥራ የውጭ ዜጐች እንዲሰማሩ ማድረግ ሕገወጥ ተግባር መሆኑን ጠንቅቀው እንደሚያውቁ፣ በዚህ ተግባር ላይ የተሰማሩ ሕጋዊ ዕርምጃ ሊወሰድባቸው እንደሚገባም እንደሚያምኑ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ንግድ ሚኒስቴር የካቲት 22 ቀን 2008 ዓ.ም. በላካቸው ተቆጣጣሪ ሠራተኞች አማካይነት በእርሳቸው የመለዋወጫና የትራንስፖርት ድርጅት ላይ የወሰደው ዕርምጃ ግን፣ አስከብረዋለሁ የሚለውን ሕግ የሚጥስ የመልካም አስተዳደር በደል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በአሜሪካ ቆይታቸው ያፈሩትን ሀብትና በኢትዮጵያ የሚገኝ መኖሪያ ቤታቸውን በማስያዝ ከባንክ ባገኙት ብድር የንግድ እንቅስቃሴ መጀመራቸውን የሚናገሩት አቶ አብርሃም፣ ቻይና ናሽናል ሄቪ ዲዩቲ ትራክ ግሩፕ ከሚባለው የሲኖትራክ የጭነት ተሽከርካሪ አምራች ኩባንያ ጋር የሲኖትራክ ተሽከርካሪ ኦሪጅናል መለዋወጫዎችን በኢትዮጵያ ለማቅረብ ውል ፈጽመው ለዓመታት ሲሠሩ መቆየታቸውን ይገልጻሉ፡፡
ከዚሁ ድርጅት ጋር በገቡት ውል መሠረትም በመለዋወጫ ዕቃዎች ላይ ልዩ ዕውቀት ያላቸውን ቻይናውያን ቴክኒሻኖች እንደቀጠሩ ያስረዳሉ፡፡ ቅጥሩ የተፈጸመውም የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሕጋዊ ፈቃድና ይሁንታ ሰጥቶ፣ በኢሚግሬሽን በኩልም ሕጋዊ ዕውቅና አግኝቶ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
የቻይናዎቹ ተቀጣሪዎች ኃላፊነትም የመለዋወጫ አቅርቦት ለሚፈልጉ በምሥል የተደገፈ የቴክኒክ ድጋፍ በማድረግ ተገቢውን የመለዋወጫ ግዥ እንዲፈጽሙ መርዳት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
አቶ አብርሃም ከቻይናውያኑ ጋር የፈጸሙትን የሥራ ቅጥር ውል ከነመዘርዝሩ፣ እንዲሁም ከቻይናው የሲኖትራክ ተሽከርካሪ አምራች ኩባንያ ጋር የፈጸሙትን የውል ማስረጃዎች ለሪፖርተር አቅርበዋል፡፡
ቻይናውያኑ ከአብርሃም ሥዩም መለዋወጫና የትራንስፖርት ድርጅት ጋር ያላቸውን ግንኙነት በሰከነና ሕግን በተከተለ ምርመራ የንግድ ሚኒስቴር ማጣራት እየቻለ፣ የካቲት 22 ቀን 2008 ዓ.ም. የላካቸው ሁለት ተቆጣጣሪዎች በድርጅታቸው በመገኘት ቻይናዊያኑን ያለፈቃዳቸው ፎቶ በማንሳትና ይዘቱ የማይታወቅ ሰነድ በወቅቱ ሥራ ላይ የነበረችን የሽያጭ ሠራተኛ በማስፈረም፣ እሳቸውን ሳያገኙና ሳያናግሩ ድርጅቱን አሽገው እንደሄዱ ይገልጻሉ፡፡
የካቲት 22 ቀን ከቀኑ 7፡00 ሰዓት ላይ በድርጅታቸው በመገኘት ድርጅቱን አሽገው የተመለሱት የቁጥጥር ሠራተኞች ለወሰዱት ዕርምጃ በጽሑፍ ያቀረቡት፣ ድርጅቱ ፈጽሟል ያሉት የሕግ ጥሰትና በኋላ ላይ በሌላ ደብዳቤ የደረሳቸው ምክንያት የሚጣረሱ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡
ከሚኒስቴሩና ከአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የተውጣጡት ተቆጣጣሪዎች ስለወሰዱት ዕርምጃ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የንግድ ቁጥጥርና ክትትል ሥራ መከታተያ ፎርም ቁጥር 103552 ላይ ድርጅቱ የተገኘበት የጥፋት ዓይነት በሚል ያሠፈሩት፣ ‹‹ለውጭ ዜጋ ባልተፈቀደ የንግድ ሥራ ሲሠሩ መገኘት›› የሚል መሆኑን ያቀረቡት ማስረጃ ያሳያል፡፡
የንግድ ሚኒስቴር በበኩሉ ስለድርጅቱ መታሸግና መረጃ ማቅረብን አስመልክቶ ለግለሰቡ በጻፈው ደብዳቤ ላይ፣ ‹‹የውጭ ዜጋ የሆኑ ቻይናውያን በሽያጭ ሥራ ላይ ተሰማርተው በመገኘታቸው›› መሆኑን ይጠቅሳል፡፡
ይኼው የንግድ ሚኒስቴር ደብዳቤ በማከልም፣ ‹‹በድርጅቱ ላይ በተደረገው ኢንስፔክሽን ከተሰበሰቡት መረጃዎች በተጨማሪ፣ በድርጅቱ በኩል ከላይ የተጠቀሰውን ሊያስተባብል የሚችል ማንኛውንም ማስረጃ እስከ የካቲት 29 ቀን ማቅረብ የሚችሉ መሆኑን እያሳሰብን፣ ይህ ሳይሆን ቢቀር ግን የንግድ ፈቃዱን የምንሰርዝ መሆኑንና ጉዳዩንም ለሕግ እንደምናቀርብ እንገልጻለን፤›› ይላል፡፡
ድርጅታቸው በታሸገ ማግሥት ቻይናዊያን ሕጋዊ ተቀጣሪዎች ስለመሆናቸውና ከመለዋወጫ አምራቹ ጋር የፈጸሙትን ውልና ሌሎችንም ማስረጃዎች ማቅረባቸውን የሚገልጹት አቶ አብርሃም፣ ስላቀረቡት ማስረጃ ምላሽ እንዳልተሰጣቸውና ይባስ ብሎም ሚያዝያ 11 ቀን 2008 ዓ.ም. የንግድ ሚኒስቴር የንግድ ምዝገባና ፈቃድ ዳይሬክቶሬት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በጻፈው ደብዳቤ፣ ድርጊቱ በሕግ ውሳኔ እስከሚያገኝ ድረስ የንግድ ሥራ ፈቃዳቸው መታገዱን ገልጾላቸዋል፡፡
‹‹ኢትዮጵያዊ ነጋዴ ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት የውጭ ዜጋ የመቅጠር መብት አለው፡፡ ነገር ግን የውጭ ዜጐች በድርጅቱ ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተከለለ ሥራ ተሰማርተዋል በሚል ምክንያት ዕርምጃ ከወሰዱ በኋላ ተፈጽሟል ያሉትን የሕግ ጥሰት የማስተባበል ሸክም መልሶ በደል ለተፈጸመበት ወገን ማሸከም ሕግን የተከተለ አሠራር አይደለም፡፡ ከሁሉም በላይ የሚያስከፋው ደግሞ ለማስተባበል ያቀረብኩትን ማስረጃ በአግባቡ ስለመመልከታቸው ሳይገልጽላቸው፣ ተጨማሪ ማስረጃ ለማቅረብ እንዲችሉም የሚኒስቴሩ ታዛቢ ባሉበት ከታሸገው ድርጅት ተጨማሪ ሰነዶችን ለማውጣት ያቀረብኩት ጥያቄ ሰሚ ጆሮ አለማግኘቱ ነው፤›› ሲሉ ምሬታቸውን ገልጸዋል፡፡
መብታቸውን ለማስከበር እስካሁን ድረስ ወደ ሚኒስቴሩ እንደሚሄዱና በአንድ አጋጣሚም ሚኒስትሩን አግኝተው መብታቸውን ለማስከበር የሚያደርጉትን ጥረት በማድነቅ፣ የሚኒስቴሩ የንግድ አሠራርና ሬጉላተሪ ዘርፍ በጥልቀት እንዲያየው እንደሚደረግ ተስፋ እንደሰጧቸው ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ የሚመለከታቸውን የሬጉላተሪ ዘርፍ ኃላፊዎች ለማግኘት ያደረጉት ሙከራ ሊሳካ አለመቻሉን ይገልጻሉ፡፡
‹‹በር ዘግቶ ሕግ ማስከበርና መልካም አስተዳደርን ማስፈን እንዴት ይቻላል?›› ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡
ድርጅታቸው የመለዋወጫ የንግድ ሥራ ላይ የተሰማራና የታሸገበት ምክንያትም የውጭ ዜጐችን በተከለከለ መስክ እንዲሰማሩ አድርጓል የሚል ሆኖ፣ ከሕጉ በተቃራኒ የሕዝብ ጤናና ደኅንነት ላይ ጉዳት እንዳደረሰ መታሸጉ ሌላው ፍትሐዊ ያልሆነ ተግባር እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡
ድርጅታቸው ላለፉት ሁለት ወራት ፍትሐዊ ባልሆነ መንገድ በመታሸጉ ማንም እንደማያተርፋ የሚገልጹት አቶ አብርሃም፣ በተወሰደባቸው ዕርምጃ ገቢያቸው በመቋረጡ የባንክ ዕዳቸውን ለመክፈል መቸገራቸውን፣ በዚህ የተነሳም አበዳሪው ባንክ ማስጠንቀቂያ ደብዳቤ እንደጻፈባቸው የሚገልጽ ማስረጃ ለዝግጅት ክፍሉ አቅርበዋል፡፡
ጉዳዩን በተመለከተ የንግድ ሚኒስቴር የመሠረታዊ ሸቀጦች ክትትል ኢንስፔክተርና የኢንስፔክሽን ቡድኑ ተወካይ አቶ አሸናፊ ማሙዬ ተጠይቀው፣ በሕግ የተያዘ በመሆኑ መረጃ ለመስጠት እንደሚቸገሩ ገልጸዋል፡፡
አቤቱታ አቅራቢው ግን የፍርድ ቤት ጥሪ እስከ ዓርብ ሚያዝያ 28 ቀን 2008 ዓ.ም. አመሻሽ ድረስ እንዳልደረሳቸው አረጋግጠዋል፡፡
ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ረቡዕ ሚያዝያ 26 ቀን 2008 ዓ.ም. በወጣው ዕትም ‹‹የንግድ ፈቃዳቸውን ለቻይናዊያን በሚያከራዩ ላይ ዕርምጃ መውሰድ ተጀመረ›› በሚል ርዕስ በወጣው ዘገባ፣ ንግድ ሚኒስቴር አራት የኢትዮጵያ የንግድ ድርጅቶችን ማሸጉን መዘገባችን ይታወሳል፡፡