በመንገድና በባቡር መንገድ መሠረተ ልማቶች ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ የቻይና ኩባንያዎች ትኩረታቸውን ወደ ኢንዱስትሪ ፓርክ እያደረጉ ነው፡፡ በባቡር መሠረተ ልማት ግንባታዎች ላይ በመሳተፍ እየተፎካከሩ የሚገኙት ሁለት ኩባንያዎች፣ የኮምቦልቻና የመቐለ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለመገንባት ባለፈው ሐሙስ ሚያዝያ 27 ቀን 2008 ዓ.ም. ውል ፈርመዋል፡፡
የኮምቦልቻና የመቐለ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለመገንባት በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የተመረጡት የቻይና ሲቪል ኢንጂነሪንግ ኮንስትራክሽን ኩባንያ (የመቐለ የኢንዱስትሪ ፓርክ)፣ እንዲሁም ቻይና ኮሙዩኒኬሽን ኮንስትራክሽን ኩባንያ (CCCC) (ለኮምቦልቻ የኢንዱስትሪ ፓርክ) ናቸው፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሲሳይ ገመቹ ስምምነቱን ከሁለቱ ኩባንያ ተወካዮች ጋር ተፈራርመዋል፡፡ ሁለቱ ኩባንያዎች የኢንዱስትሪ ፓርኮቹን በስድስት ወራት ውስጥ ገንብተው የማስረከብ ኃላፊነት የሚጠበቅባቸው ሲሆን፣ መንግሥት በአጠቃላይ 250 ሚሊዮን ዶላር በአጠቃላይ እንደሚከፍላቸው አቶ ሲሳይ ገልጸዋል፡፡
የቻይናው ሲቪል ኢንጂነሪንግ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ወደ ኢትዮጵያ የገባው ከሚኤሶ ድሬዳዋ ድረስ ያለውን የባቡር መስመር በ1.2 ቢሊዮን ዶላር ለመገንባት ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ይህን ፕሮጀክት አስረክቦ ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ፊቱን አዙሯል፡፡
በኢትዮጵያ የመጀመርያውን የኢንዱስትሪ ፓርክም በሐዋሳ ላይ እየገነባ ሲሆን፣ በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይም አጠናቆ ያስረክባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የዚህ የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ ወጪም 240 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
የኮምቦልቻውን የኢንዱስትሪ ፓርክ በስድስት ወራት ውስጥ ለመገንባት ውል የገባው ሁለተኛው ኩባንያ ቻይና ኮንስትራክሽን ኮሙዩኒኬሽን ኩባንያ ሲሆን፣ ወደ ኢትዮጵያ የገባው የአዲስ አበባ-አዳማ የፍጥነት መንገድ ግንባታን ለማከናወን መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት የቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ማረፊያ ማስፋፊያንም በ340 ሚሊዮን ዶላር እያከናወነ ይገኛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የመቐለ – ሃራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክትን በ1.6 ቢሊዮን ዶላር በማከናወን ላይ ነው፡፡
ሁለቱ ኩባንያዎች በመቐለና በኮምቦልቻ የሚገነቧቸው የኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚያርፉት በ75 ሔክታር መሬት ላይ ሲሆን፣ እያንዳንዳቸው 30 ሼዶች እንደሚኖሯቸው አቶ ሲሳይ ገልጸዋል፡፡
ሁለቱ ኩባንያዎች ለሚገነቧቸው የኢንዱስትሪ ፓርኮች እያንዳንዳቸው 125 ሚሊዮን ዶላር የሚያገኙ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ በይበልጥ የሚጠይቀው የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት መሆኑን የሚናገሩ ባለሙያዎች፣ ይህ ሥራ ለቻይና ኩባንያዎች ቀላል የገንዘብ ምንጭ እንደሆነላቸውና ከፍተኛ ፉክክር ውስጥ እንደከተታቸው ይናገራሉ፡፡
አገር በቀል የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች በዚህ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ለመሳተፍ ከፍተኛ ፍላጎት ቢኖራቸውም፣ እስካሁን ጨረታውን ለማሸነፍ የቻለ የለም፡፡