Friday, June 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሐሰተኛ ሰነዶችን በመጠቀም ኮንስትራክሽን ሚኒስቴርን በማጭበርበር የተጠረጠሩ ታሰሩ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሐሰተኛ ሰነዶችን በማዘጋጀት፣ ከቲኤስኤፍኤል ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርና ከሌሎች በርካታ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ከተሰማሩ ድርጅቶች ጋር በመመሳጠር፣ ኮንስትራክሽን ሚኒስቴርን አጭበርብረው የተለያዩ ደረጃ ያላቸው የኮንስትራክሽን ሥራ ፈቃድ በመውሰድ የተጠረጠሩ አምስት ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ዋሉ፡፡

ከላይ ከተጠቀሱት የኮንስትራክሽን ማኅበራት ጋር በጥቅም በመመሳጠርና ሐሰተኛ ሰነድ አዘጋጅተው በመቅረብ፣ ኮንስትራክሽን ሚኒስቴርን በማጭበርበር ተጠርጥረው የታሰሩት አቶ ብርሃኑ ገብረ ኪዳን፣ አቶ ታምራት ሽታ፣ አቶ ላቀው ዘካርያስ፣ አቶ ዓለም የኋላሸትና አቶ ናኦድ ፀሐዬ የሚባሉ ግለሰቦች መሆናቸው ታውቋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ከ15,000 ብር እስከ 150,000 ብር የሚደርስ ኮሚሽን በመቀበል ሐሰተኛ ሊብሬ፣ የውክልና ሰነዶችን፣ የባንክ የብድር ዋስትና ደብዳቤዎችን፣ የንግድ ፈቃድንና የመመሥረቻ ጽሑፎችን በማዘጋጀት የኮንስትራክሽን ሥራ ፈቃድ ለሚሰጠው የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በማቅረብ፣ ከ2005 ዓ.ም. እስከ 2008 ዓ.ም. ድረስ የደረጃ 5፣ የደረጃ 4 እና የደረጃ 3 የኮንስትራክሽን የሥራ ፈቃድ በማውጣት እንዲገለገሉ ማድረጋቸውም ተገልጿል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ሐሰተኛ ሰነዶቹን የሚሠሩት የኮንስትራክሽን ሥራ ፈቃድ ለማውጣት፣ ለዘርፉ የሚያገለግሉ ተሽከርካሪዎች እንደ አንድ መሥፈርት መቀመጣቸውን ተከትሎ መሆኑም ታውቋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር ሊውሉ የቻሉት ለባንክ እየቀረበ ያለው ሰነድ የሌለ ወይም በዋስትና ያልተያዘ መሆኑ በሚኒስቴሩ በመረጋገጡ ነው፡፡ ድርጊታቸው ተጠቅሶ ለፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ዳይሬክቶሬት በመቅረቡ ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በተጠረጠሩበት ወንጀል ተከሰውና ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ ከአሥር ዓመታት በላይ እንደሚቀጡ መርማሪው ጠቁሞ፣ የዋስትና መብታቸው እንዲከለከልና በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ ጉዳያቸውን እያየው ለሚገኘው ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁለተኛ ወንጀል ችሎት አመልክቷል፡፡

የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች የፌዴራል ፖሊስ የምርመራ ቡድን ያቀረበውን ጥያቄ በመቃወም በሰጡት ምላሽ፣ መርማሪው ያቀረበው ጥያቄ ድፍን ያለና በተጠርጣሪ ደንበኞቻቸው ላይ ዓቃቤ ሕግ ክስ ሳያቀርብ በመሆኑ የሕግ መሠረት እንደሌለው አስረድተዋል፡፡ የዋስትና መብታቸው እንዲከበርም ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የሁለቱንም ወገኖች ክርክር ከሰማ በኋላ ብይን ሰጥቷል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ የተጠረጠሩበት የወንጀል ጉዳይ ከአሥር ዓመት በላይ በሆነ ጽኑ እስራት የሚያስቀጣ ከሆነ፣ በዋስትና መለቀቅ እንደማይችሉ በተሻሻለው የፀረ ሙስና ልዩ ሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ ማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 882/07 አንቀጽ 3(1) መደንገጉን አሳውቋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ተጠርጣሪዎቹ የተጠረጠሩበትን ጉዳይ ሊያርፍበት የሚችልበትን የሕግ ድንጋጌ ከግምት ውስጥ በማስገባት ባደረገው ምርመራ ጉዳዩ የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 23(2) ሥር የሚወድቅ ሆኖ እንዳገኘው ገልጿል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ሠርተዋቸዋል የተባሉት ሐሰተኛ ሰነዶች፣ የኮንስትራክሽን ፈቃድ ከደረጃ 5 እስከ ደረጃ 3 መሆናቸውን ጠቁሞ፣ ሕጋዊነት በሌላቸውና ከፍተኛ ዕውቀት (ፈቃድ) በሌላቸው ባለሙያ የሚሠሩ ግንባታዎች፣ በሕዝብና በመንግሥት ላይ የሚያደርሱት ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን ከወዲሁ መገመት እንደሚቻል ገልጿል፡፡ በመሆኑም ድርጊቱ (የወንጀሉ አፈጻጸም) ከባድ ሆኖ ከተገኘ፣ ከአምስት ዓመታት እስከ 25 ዓመታት ጽኑ እስራት ሊያስቀጣ እንደሚችል በሕጉ መደንገጉን በመጠቆም ተጠርጣሪዎቹን የዋስትና ጥያቄ እንደልተቀበለው አስታውቋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ ምርመራውን ማጠናቀቁን ተከትሎ በ15 ቀናት ውስጥ ክስ እንዲመሠረት ትዕዛዝ በመስጠት፣ ለግንቦት 11 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

 

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች