ባንኮች ለአስመጪዎች በሚፈቅዱት የውጭ ምንዛሪ መጠንና ነጋዴዎች በሚያስመጧቸው ዕቃዎች መካከል ከፍተኛ ልዩነት እየታየ በመሆኑ፣ መንግሥት ጉዳዩን የሚመረምር ኮሚቴ አቋቋመ፡፡
ይህንን ጉዳይ ለመረዳትና ዕርምጃ ለመውሰድ የተቋቋመው ኮሚቴ አባላት ንግድ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንና የፋይናንስ ደኅንነት ኤጀንሲ ናቸው፡፡
የዚህ ኮሚቴ አባል የሆኑት የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የጉምሩክ ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ሞገስ ባልቻ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የጉምሩክ ቀረጥ መክፈያ ዋጋ መነሻ የሚያደርገው ነጋዴዎች ዕቃ ገዝተው ባመጡት ደረሰኝ ላይ ነው፡፡ ‹‹ነጋዴዎች የሚያቀርቧቸው ደረሰኞችና ባንኮች የሚፈቀዱት የውጭ ምንዛሪ፣ እንዲሁም ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በተለያዩ መረጃዎች ላይ ተመሥርቶ የሚያስከፍለው የመጨረሻ ዋጋ ከፍተኛ ልዩነት አለው፤›› በማለት በዘርፉ ችግር እንዳለ አቶ ሞገስ አመልክተዋል፡፡
አቶ ሞገስ የመንግሥትን የጥርጣሬ መነሻ በግልጽ ባይናገሩም የሪፖርተር መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ ነጋዴዎች ከባንኮች የሚያገኙትን የውጭ ምንዛሪ ሙሉ በሙሉ ዕቃ ገዝተው ወደ አገር እንደማያስገቡ፣ በዚህም ምክንያት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወደ ውጭ እየሸሸ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የጉምሩክ ክፍያዎችን አሳንሶ ለመክፈል የሚደረግ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
አቶ ሞገስ እንደሚሉት የሚቀርቡት አብዛኛዎቹ ደረሰኞች ከዓለም ገበያ አንፃር ዝቅተኛ የሚባሉ ናቸው፡፡ በመሆኑም ይህ ጉዳይ ሊታይ የሚገባው ነው ተብሏል፡፡
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የችግሩ ምክንያቶች ሁለት ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ዕቃዎቹ የተገዙባቸውን ዋጋ ዝቅ አድርጎ በማቅረብ የጉምሩክ ክፍያዎች እንዲቀንሱ ማድረግ ነው፡፡ ሁለተኛው በተፈቀደው የውጭ ምንዛሪ ሙሉ በሙሉ ባለመጠቀም፣ የተወሰነውን የውጭ ምንዛሪ እዚያው ማስቀረት ነው፡፡ ኢትዮጵያ በዓመት እስከ 15 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ዕቃዎች ነዳጅን ጨምሮ ከውጭ ለማስገባት ታወጣለች፡፡ ይህ ገንዘብ ሙሉ ለሙሉ ጥቅም ላይ ውሏል ወይ የሚለው ጉዳይ በብዙዎች ዘንድ አነጋጋሪ ነው፡፡
በተጨማሪም የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ታቦ ሚምቤኪ በሚመሩት የአፍሪካ የፋይናንስ ሚኒስትሮች ከፍተኛ ፓናል ላይ በቅርቡ እንደተነገረው፣ በሕገወጥ መንገድ ከኢትዮጵያ በዓመት አሥር ቢሊዮን ዶላር ይወጣል፡፡
ይህም በመሆኑ ኢትዮጵያ 14 ዓመታት የፈጁባትን የምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦች ስኬት፣ በዘጠኝ ዓመታት ብቻ ልታጠናቅቅ ትችል እንደነበር በከፍተኛ ፓናሉ ተመልክቷል፡፡
አቶ ሞገስ በጥናቱ ግኝት ላይ ተመሥርቶ መንግሥት ዕርምጃ እንደሚወስድ ጠቁመዋል፡፡
‹‹ባንኮች የሰጡት የውጭ ምንዛሪ ምን ተግባር ላይ እንደዋለ ማየት አለባቸው፡፡ ሥልጣንም አላቸው፤›› በማለት አቶ ሞገስ ጉዳዩ ትኩረት እንደተሰጠው አስረድተዋል፡፡