Friday, September 29, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኤክስፖርት ገቢ በአሳሳቢ ሁኔታ እያሽቆለቆለ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሁለኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ትግበራ በገባበት 2008 በጀት ዓመት ይጠበቅ የነበረው የኤክስፖርት ዘርፍ ገቢ በእጅጉ ያሽቆለቆለ መሆኑን መረጃዎች አመለከቱ፡፡

የንግድ ሚኒስቴር የዘጠኝ ወራት የኤክስፖርት ዘርፍ ሰነድ እንደሚያሳየው  ከግብርና፣ ከኢንዱስትሪና ከማዕድን ዘርፎች 2.91 ቢሊዮን ዶላር በዘጠኝ ወራት ውስጥ ለማግኘት ታቅዶ፣ ማግኘት የቻለው 2.05 ቢሊዮን ዶላር ወይም የዕቅዱን 70.46 በመቶ ብቻ ነው፡፡

ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ይፋ ከሆነ በኋላ አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች አፈጻጸማቸው ከእውነታው ጋር የተቀራረበ እንዲሆን ዕቅዱን ከልሰውታል፡፡ ከላይ የተደረገው ንፅፅር ከተከለሰው የአገሪቱ ዕቅድ አንፃር የተደረገ ሲሆን፣ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ በየዓመቱ ከተጣለው ግብ አንፃር ሲመዘን አፈጻጸሙን እጅግ ያሽቆለቆለ ያደርገዋል፡፡

በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ በ2008 ዓ.ም. ይገኛል ተብሎ የተጣለው ግብ የሸቀጦች የወጪ ንግድ ገቢ 5.01 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን፣ የንግድ ሚኒስቴር በኤክስፖርት ዘርፍ የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም 2.05  ቢሊዮን ዶላር በመሆኑ፣ የበጀት ዓመቱ ሊጠናቀቅ የሦስት ወራት ዕድሜ ብቻ እየቀረው አፈጻጸሙ ከተጣለው ግብ በ50 በመቶ በታች ነው፡፡

የዘጠኝ ወራት የኤክስፖርት ገቢ በዘርፉ ሲታይም ከግብርና ምርቶች የወጪ ንግድ 3.43 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት በዕቅዱ ላይ ግብ የተጣለ ቢሆንም፣ በተከለሰው የመንግሥት ዓመታዊ ዕቅድ ከዘርፉ 1.95 ቢሊዮን ዶላር በዘጠኝ ወራት ውስጥ የማግኘት ዕቅድ ተይዞ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ አፈጻጸሙ 1.5 ቢሊዮን ዶላር ወይም 79 በመቶ ነው፡፡

ከማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ 1.06 ቢሊዮን ዶላር በ2008 በጀት ዓመት ለማግኘት በአምስት ዓመቱ ዕቅድ ግብ የተጣለ ቢሆንም፣ በተከለሰው የመንግሥት ዕቅድ ግን ይህ የገቢ ዕቅድ ዝቅ እንዲል ተደርጓል፡፡ በዚህ መሠረት በዘጠኝ ወራት ውስጥ ከማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ 508.06 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ ማግኘት የተቻለው ግን 258.58 ሚሊዮን ዶላር ወይም የዕቅዱ 51 በመቶ ብቻ መፈጸሙን የንግድ ሚኒስቴር የኤክስፖርት ዘርፍ አፈጻጸም ሰነድ ያሳያል፡፡

በሌላ በኩል ከማዕድን ዘርፍ በ2008 በጀት ዓመት 603 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት በዕቅዱ ግብ የተጣለ ሲሆን፣ በተከለሰው የመንግሥት ዕቅድ በዘጠኝ ወራት ውስጥ 458.4 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ አፈጻጸሙ 223.4 ሚሊዮን ዶላር፣ ይህም የዕቅዱ 48.5 በመቶ መሆኑን ሰነዱ ይጠቁማል፡፡

የዘጠኝ ወራቱ አጠቃላይ የአገሪቱ የኤክስፖርት አፈጻጸም ቅናሽ ያሳየው ከዕቅዱ ጋር ሲነፃፀር ብቻ አይደለም፡፡ ካለፈው 2007 በጀት ዓመት በ5.9 በመቶ ወይም በ129.2 ሚሊዮን ዶላር መቀነሱንም ሰነዱ ይጠቁማል፡፡

የኤክስፖርት አፈጻጸሙ ያሽቆለቆለበትን ምክንያት በተመለከተ በዋናነት በዓለም ገበያ ላይ ያለው የግብርና ምርቶች ዋጋ መቀነስና የፍላጎት ማነስ፣ እንዲሁም የግብርና ምርቶች አቅርቦትን በጥራትም ሆነ በመጠን ያለማሳደግ እንደሆነ ይገልጻል፡፡

በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለታየው የኤክስፖርት ገቢ መሽቆልቆል በምክንያትነት የተጠቀሰው ደግሞ የኢንዱስትሪ ግብዓት አቅርቦትና የጥራት ችግር መኖር፣ የአገር ውስጥ ዋጋው ሳቢ በመሆኑ አምራቾች ወደ አገር ውስጥ መሳባቸው፣ እንዲሁም በኢንቨስትመንት ሒደት ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች በወቅቱ ወደ ማምረት አለመሸጋገር ዋናዎቹ ሲሆኑ፣ በማዕድን ዘርፍ ደግሞ የዓለም የወርቅ ዋጋ መቀነስ በዋና ምክንያትነት ተጠቅሷል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች