ዕቃ ከውጭ አስመጥተው ደረቅ ወደብ ከደረሰ በኋላ ለረዥም ጊዜ የማያነሱ ነጋዴዎች እንዲታገዱ የሚያደርግ አሠራር ተግባራዊ ሊደረግ ነው፡፡ ግዴታቸውን በአግባቡ አልተወጡም የተባሉ አስመጪዎች ከየትኛውም ባንክ የውጭ ምንዛሪ እንዳያገኙ ይደረጋል ተብሏል፡፡
የጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 859/2006 አንቀጽ 51 ንዑስ አንቀጽ 7 በባህርና በየብስ የሚገቡ ዕቃዎች በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ፣ በአውሮፕላን የሚገቡ ዕቃዎች በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ እንዲያነሱ ይደነግጋል፡፡
ነገር ግን የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ኢንተርፕራይዝ በሚያስተዳድራቸው ደረቅ ወደቦች፣ በተለይም በሞጆ ደረቅ ወደብ ከሁለት ሺሕ በላይ ኮንቴይነሮች ከ60 እስከ 1,450 ቀናት ሳይነሱ መቆየታቸው ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ከስድስት ወራት በላይ የቆዩ ኮንቴይነሮችን ከሰኞ ግንቦት 1 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ እንደሚወርስ አስታውቋል፡፡ ከስድስት ወር በታች፣ ከሁለት ወር በላይ የቆዩ ኮንቴይነሮች ደግሞ በአንድ ወር ጊዜ ካልተነሱ እንደሚወርስ አስታውቋል፡፡ ባለሥልጣኑ ከወረሳቸው ንብረቶች የተበላሸውን ካስወገደ በኋላ ጠቃሚውን በመለየት ለጨረታ ያቀርባል፡፡
ባለፈው ረቡዕ ሚያዚያ 26 ቀን 2008 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንና የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ኢንተርፕራይዝ ዕቃዎችን ከወደብ ማንሳት ያልቻሉ ኩባንያዎችን ጠርተው አነጋግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ኢንተርፕራይዝ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አህመድ ቱሳ በውይይቱ ወቅት እንደተናገሩት፣ በአሁኑ ወቅት በሞጆ ደረቅ ወደብ ከሁለት ወር በላይ የቆዩ ሁለት ሺሕ ኮንቴይነሮች ቦታ ይዘው ሌሎች ዕቃዎች እንዳይስተናገዱ እንቅፋት እየሆኑ ነው፡፡
በደረቅ ወደቦች ብቻም ሳይሆን በአሁኑ ወቅት በጂቡቲ ወደብ 15 ሺሕ ኮንቴይነሮች ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የሚበዙት ከሁለት ወር በላይ የቆዩ መሆናቸውን አቶ አህመድ ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ደረቅ ወደቦች 250 ኩንታል ለሚይዝ አንድ ኮንቴይነር በቀን 43 ብር ይከፈላል፡፡ በጂቡቲ ወደብ ደግሞ ለአንድ ኮንቴይነር 11 ዶላር ይከፈላል፡፡ አቶ አህመድ እንዳሉት መሥሪያ ቤታቸው በደረቅ ወደብ የጀመረውን ሥራ እንደጨረሰ ወደ ጂቡቲ ወደብ ፊቱን ያዞራል፡፡
ከዚህ ባሻገር በደረቅ ወደቦች ሳይነሱ ለሚቆዩ ኮንቴይነሮች በየቀኑ አምስት ዶላር እንደሚከፈል ተገልጿል፡፡ ‹‹ይህ ሁኔታ ጭራሽ ተቀባይነት የለውም፡፡ አገሪቱ በችግር የምታገኘውን የውጭ ምንዛሪ ኪራይ ለመክፈል መዋል የለበትም፤›› በማለት አቶ አህመድ መንግሥት በዚህ ጉዳይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የሕግ ማስከበር ምክትል ዳይሬክተር አቶ አለባቸው ንጉሤ፣ በውጭ ምንዛሪ ዕቃ አስገብተው የማያነሱ ኩባንያዎች በቀጣይ ስለሚወሰድባቸው ዕርምጃ አመላክተዋል፡፡
አቶ አለባቸው እንዳሉት፣ በገቡት ውል መሠረት ግዴታቸውን የማይወጡ አስመጪዎች በቀጣይ ከባንኮች የውጭ ምንዛሪ እንዳያገኙ ይደረጋል፡፡ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን፣ የሎጂስቲክስ ኢንተርፕራይዝና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በጋራ እየሠሩ መሆናቸውን አቶ አለባቸው ተናግረዋል፡፡
ይህንን የመንግሥት አቋም የዕቃዎቹ ባለቤቶች አልተስማሙበትም፡፡ ባለሀብቶቹ የገዛ ዕቃቸውን ማንሳት ያልቻሉበትን ምክንያት ሲያስረዱም የመንግሥት ክፍያዎች የሚዘገዩ በመሆናቸው የገበያ መቀዛቀዝ፣ የቀረጥ ነፃ መብት አሰጣጥ መዘግየት፣ በኦሮሚያ ክልል ተከስቶ የነበረውን አለመረጋጋትና የባንክ ብድር አለመኖር እንደ ችግር አንስተው ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጣቸውና ዕቃዎቹን አውጥተው ሸጠው የሚጠበቅባቸውን ቀረጥ ለመክፈል ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
በመድረኩ የተሰጠው ምላሽ ግን የጠበቁት እንዳልነበር ሪፖርተር ያነጋገራቸው ባለሀብቶች ተናግረዋል፡፡ ‹‹ቀድመው ከወሰኑ እዚህ ድረስ ለምን ይጠሩናል? ሲጠሩን የጋራ መፍትሔ እንፈልግ ብለው ነበር፤›› በማለት ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ዕቃ የሰነበተባቸው ባለሀብት ብስጭታቸውን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በ500 ቀናት ያላነሱ፣ በመቀጠልም በ250 ቀናት ዕቃቸውን ያላነሱ ባለሀብቶች ተወርሶባቸው ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት በ180 ቀናት ባላነሱ ላይ ዕርምጃ የሚወሰድ ሲሆን፣ በቀጣይ ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት በ60 ቀናት ባላነሱ ባለሀብቶች ንብረት ላይ ዕርምጃ እንደሚወሰድ ተገልጿል፡፡