አዲሶቹ የካቢኔ አባላት በፍጥነት ወደ ሪፎርም ሥራዎች እንዲገቡ መመርያ ተሰጠ
ዓርብ ነሐሴ 4 ቀን 2010 ዓ.ም. አስቸኳይ ስብሰባ የተጠራው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት፣ መሠረታዊ በሚባል ደረጃ የካቢኔ ሹም ሽር አካሄደ፡፡ በዕለቱ ሹመት ከተሰጣቸው 18 የቢሮ ኃላፊዎች መካከል አራቱ ብቻ ነባር ሲሆኑ፣ የተቀሩት በሙሉ አዳዲስ ተሿሚዎች ናቸው፡፡
ከካቢኔ አባላት ውጪ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታቦር ገብረ መድኅን (ዶ/ር) ተነስተው የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሲሆኑ፣ ወ/ሮ አበበች ነጋሽ ደግሞ የከተማው ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ሆነው ተሰይመዋል፡፡
በአዲስ አበባ ካቢኔ ውስጥ የነበራቸውን ቦታ ማስጠበቅ የቻሉት የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ፎኢኖ ፎላ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ ሺሰማ ገብረ ሥላሴ፣ የአዲስ አበባ ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ዮናስ አያሌው (ኢንጂነር) እና ቀደም ሲል የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ የነበሩት አቶ ንጋቱ ዳኛቸው የጥቃቅንና አነስተኛ ቢሮ ኃላፊ ሆነው ተሹመዋል፡፡
ከታቦር (ዶ/ር) በስተቀር በወጣቶች የተሞላው አዲሱ ካቢኔ አራት ሴት የቢሮ ኃላፊዎችን አግኝቷል፡፡ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ያቀረቧቸው የካቢኔ አባላት በከተማው ምክር ቤት አባላት ሙሉ ድጋፍ አግኝተዋል፡፡
የምክር ቤት አባል አቶ ኃይለ ገብርኤል አዳነ እንደገለጹት፣ የካቢኔ አባላት ለውጥ ዘገየ ካልተባለ በስተቀር በጣም ወሳኝ ነው፡፡
‹‹ይህ ሹም ሽር መደረግ የነበረበት ኢሕአዴግ ጥልቅ ተሃድሶ ባካሄደበት ወቅት ነበር፡፡ ነገር ግን ለውጡ ሳይካሄድ በመቆየቱ ከተማው ብዙ ችግሮች ደርሰውበታል፡፡ የለውጡ አካል ሆነው ወደ ከተማው ከመጡት ኃላፊዎች ብዙ ይጠበቃል፤›› ብለዋል፡፡
ምክትል ከንቲባ ታከለ አዲሱን ካቢኔ ይፋ ባደረጉበት ወቅት እንደተናገሩት፣ አዲስ አበባ ለነዋሪዎቿ ምቹ እንድትሆን ብሎም የኢትዮጵያ፣ የኦሮሚያና የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ እንደመሆኗ በርካታ ሥራዎች ይጠብቁታል፡፡
አዲስ የተሾሙት የካቢኔ አባላት
- ወ/ሮ አልማዝ አብርሃ የሴቶችና ሕፃናት ቢሮ ኃላፊ – የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሴቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ነበሩ፡፡
- ወ/ሮ ፍሬሕይወት ተፈራ የፍትሕ ቢሮ ኃላፊ – የአዲስ አበባ ምክር ቤት የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነበሩ፡፡
- አቶ ጀማሉ ጀምበር የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ – የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም አስተባባሪ የነበሩ፡፡
- አቶ ሺሰማ ገብረ ሥላሴ የገቢዎች ቢሮ ኃላፊ – ቀደም ሲል የከተማው ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ ነበሩ (በቅርቡ የገቢዎች ባለሥልጣን ኃላፊ ነበሩ)፡፡
- ፍሬሕይወት ገብረ ሕይወት (ዶ/ር) የፐብሊክ ሰርቪስ ቢሮ ኃላፊ – የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የልማት ማኔጅመንት ክፍል ኃላፊ ነበሩ፡፡
- አቶ አሰፋ ዮሐንስ የቴክኒክና ሙያ ቢሮ ኃላፊ – የኢትዮጵያ ፓወር ኢንጂነሪንግ ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩ፡፡
- ኤርሚያስ ኪሮስ (ኢንጂነር) የኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ – በግል ኢንዱስትሪዎች ውስጥ የነበሩ፡፡
- አቶ አብዱልፈታ የሱፍ የንግድ ቢሮ ኃላፊ – በአዲስ አበባ የተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ውስጥ የቆዩ ናቸው፡፡
- አቶ ፎኢኖ ፎላ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ቢሮ ኃላፊ – እዚሁ ቢሮ የነበሩ፡፡
- ዮናስ አያሌው (ኢንጂነር) የኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ – እዚሁ ቢሮ የነበሩ፡፡
- ሽመልስ እሸቱ (ኢንጂነር) የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ – በኦሮሚያ ክልል መሬትና ልማት ክፍል እየሠሩ የነበሩ፡፡
- አቶ ደረጀ ፈቃዱ የፕላን ኮሚሽን ኮሚሽነር – የፌዴሬሽን ምክር ቤት የልማት በጀት ቀመር ላይ የሠሩ፡፡
- አቶ ዘውዱ ቀፀላ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ – በኦሮሚያና በአዲስ አበባ መሰል ተቋማት የሠሩ፡፡
- ዮሐንስ ጫላ (ዶ/ር) የጤና ቢሮ ኃላፊ – በዘውዲቱ ሆስፒታል የቀዶ ጥገና ክፍል ኃላፊ የነበሩ፡፡
- ሰናይት ዳምጠው (ኢንጂነር) የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ – በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ የቆዩ፡፡
- አቶ ነብዩ ባዬ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ – የብሔራዊ ቴአትር ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበረ፡፡
- ታቦር ገብረ መድኅን (ዶ/ር) የትምህርት ቢሮ ኃላፊ – የአዲስ አበባ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ የነበሩ፡፡
- አቶ ንጋቱ ዳኛቸው የጥቃቅንና አነስተኛ ቢሮ ኃላፊ – የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ የነበሩ፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር)፣ አዲስ የተሾሙ የካቢኔ አባላት በፍጥነት ወደ ሪፎርም ሥራዎች እንዲገቡ መመርያ ሰጥተዋል፡፡
ዓርብ ነሐሴ 4 ቀን 2010 ዓ.ም. የቀድሞ ከንቲባ ድሪባ ኩማ ካቢኔ ፈርሶ፣ የምክትል ከንቲባ ታከለ አዲስ ካቢኔ ተዋቅሮ ሥራ ጀምሯል፡፡ የአዲስ አበባ ምክር ቤት የ18 ካቢኔ አባላትን ሹመት ካፀደቀ በኋላ፣ የመጀመርያው የካቢኔ ስብሰባ የተካሄደ ሲሆን፣ በዚሁ ዕለት አቶ ታከለ የአዲስ አበባ ከተማ ችግር ጊዜ የሚሰጥ ባለመሆኑ ተሿሚዎች በፍጥነት ሪፎርም እንዲያካሂዱ መመርያ ሰጥተዋል፡፡
የካቢኔ አባላት አሿሿምን በሚመለከት ለምክር ቤቱ ማብራሪያ የሰጡት አቶ ታከለ፣ የከተማውን ቁልፍ ከተረከቡ በኋላ በነበሩት ሦስት ሳምንታት ውስጥ የተከናወኑ ሥራዎችን ይፋ አድርገዋል፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ መጠነ ሰፊ የለውጥ እንቅስቃሴ መጀመሩንና የሕዝብ የለውጥ ፍላጎትም እጅግ መጨመሩን ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ የኢትዮጵያ ነፀብራቅ እንደመሆኗ የአገልግሎት አሰጣጥ የተሻለ ለማድረግ፣ የተጀመሩ የፕሮጀክት ሥራዎችንም በሚገባ ማካሄድ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡ የአገልግሎት አሰጣጦችን የተሻለ ለማድረግ በሦስት ሳምንታት ውስጥ ከተሠሩ ሥራዎች መካከል፣ የአዲስ አበባ ከተማን ከማዕከል እስከ ወረዳ ድረስ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እንዲመራ ለማድረግ አሠራር ተዘርግቷል ሲሉ ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል፡፡
ይህንን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ተቋም ማቋቋም ብቻ ሳይሆን፣ የሰው ኃይልም እንዲሟላለት መደረጉን ምክትል ከንቲባው አብራርተዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከንቲባው እንዳሉት፣ የአዲስ አበባ ከተማ መታወቂያ አሰጣጥ ላይ ማስተካከያ ይደረጋል፡፡ ይህም አዲስ አሠራር በጥቂት ቀናት ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡
በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የቆየው መታወቂያ ኢትዮጵያዊነትን ከማንፀባረቅ ይልቅ ዘር ላይ ትኩረት የሚያደርግ በመሆኑ ከፍተኛ ቅሬታ ሲቀርብበት ቆይቷል፡፡ ምክትል ከንቲባው እንዳሉት የመታወቂያ ጉዳይ ትንሽ ቢመስልም፣ ብዙዎችን እያበሳጨ በመሆኑ ማስተካከያ ይደረግበታል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በከተማው መገናኛ ብዙኃን ኤጀንሲ፣ በውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን፣ በደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ፣ በደንብ ማስከበር ቁጥጥር ሥርዓት ላይ ለውጥ የሚያመጡ ዕርምጃዎች መወሰዳቸውን ምክትል ከንቲባው አብራርተዋል፡፡ ከእነዚህ መሠረታዊ ጉዳዮች በተጨማሪም አዲስ አበባ ዘመናዊና የነዋሪዎቹን ፍላጎት የምታረካ ከተማ ለማድረግ በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን ከንቲባው ተናግረዋል፡፡