በኢትዮጵያ ሕጋዊ ዕውቅና ኖሯቸው የተለያዩ ስፖርቶችን በመምራትና በማንቀሳቀስ ላይ ከሚገኙ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች መካከል የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ይጠቀሳል፡፡ ፌዴሬሽኑ በአሁኑ ወቅት በውጤትም ሆነ በአደረጃጀት ከተቀሩት ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች በብዙ መልኩ የተሻለ መንገድ መከተል የጀመረ ተብሎ እየተጠቀሰ ይገኛል፡፡ ይሁንና ይህ ተቋም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከሚታየው ውጤት አኳያን አሉታዊ ጎኑ ሚዛን መድፋት ጀምሯል በሚል አስተያየትና ወቀሳ እያስተናገደ ይገኛል፡፡
የሻምበል አበበ ቢቂላን እግር እየተከተለ በትውልድ ቅብብሎሽ ዛሬ ላይ የደረሰው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ፣ በየወቅቱ አዳዲስ የውድድር ፈርጦችን እያፈራ በታላላቅ የውድድር መድረኮች የአገሪቱ የስፖርት አምባሳደር ሆኖ ከመቆየቱም በላይ፣ ‹‹አረንጓዴው ጎርፍ›› የተሰኘ ዘመን ተሻጋሪ የቅፅል ስም አትርፎ መቆየቱ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ አሁን ላይ ከውጤትና ከውክልናም አልፎ የኢንቨስትመንት አማራጭ እየሆነ መምጣቱ በሁሉም ዘንድ ትኩረትና ተስፋ እንዲቸረው አድርጓል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የወቅቱ አመራርም ከሁለት ዓመታት በፊት ለኃላፊነት እንዲበቃ የተደረገው ዘርፉ የሚጠይቀውን የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት ስፖርቱን እንዲያጎለብት ተፈልጎ እንዲሆን የሚናገሩ አሉ፡፡
የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ በበኩሉ፣ ብዙዎች እንደሚያምኑት ብቻ ሳይሆን፣ የእሱና የባልደረቦቹ ህልምና ምኞትም ቀውስ ውስጥ እንደገባ በተደጋጋሚ ሲነገርለት የቆየውን የአትሌቲክሱን ውጤታማነት ማሻሻል ነው፡፡ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት እንደመሆኑ በዚህ ረገድ መግባባት የግድ እንደሚል ያምናል፡፡
በአልጀሪያ ከሐምሌ 25 እስከ 29 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ በተካሄደው 21ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያ በ64 አትሌቶች ተወክላ ሁለት የወርቅ፣ ሦስት የብርና አምስት የነሐስ፤ በድምሩ አሥር ሜዳሊያዎች አስመዝግባ መመለሷ ይታወሳል፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑም ለአትሌቶቹ ከ800 ሺሕ ብር በላይ በማውጣት በአራራት ሆቴል ባዘጋጀው ሥነ ሥርዓት የዕውቅናና የማበረታቻ ሽልማት አበርክቷል፡፡ ውጤቱ ከሁለት ዓመታት በፊት በደቡብ አፍሪካ ደርባን ከተማ ላይ ተከናውኖ በነበረው 20ኛው ሻምፒዮና በወርቅ፣ በብርና በነሐስ ከተገኘው የሜዳሊያ ቁጥር አኳያ የተሻለ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ነገር ግን በቂ ነው እንደማይባል፣ ይልቁንም ፌዴሬሽኑ ለዝግጅት ካዋለው ፋይናንስም ሆነ የሰው ኃይል አኳያ ክፍተቱና ድክመቱ እንደሚያመዝን በፕሮግራሙ የታደመው ኃይሌ መናገሩ ይታወሳል፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ ሪፖርተር ያነጋገረው ኃይሌ፣ ምንም እንኳ ውጤቱ በሜዳሊያ ደረጃ ተሻሽሏል ቢባልም፣ አጥጋቢ ነው ተብሎ በፍፁም ሊወሰድ እንደማይገባ ያምናል፡፡ ምክንያቱን ሲያብራሩም፣ ‹‹በእያንዳንዱ ዝግጅት ቦታው ድረስ በመሄድ እንደታዘብኩት ከሆነ ከቀን ወደ ቀን የምመለከተው አዲስ ነገር ከልምምድና ሥልጠና ይልቅ የፀጉር ስታይል ነው፡፡ ይኼ ደግሞ እኔም ሆንኩ ሌሎች የፌዴሬሽኑ አመራሮች እንዲሁም የአትሌቲክሱ ቤተሰብ የምንፈልገውን ውጤት ማስመዝገብ ቀርቶ ለማሰብ ከባድ ያደርገዋል፤›› በማለት ስለሚታየው ድክመት ተናግሯል፡፡
ኃይሌን ጨምሮ በርካታ የስፖርቱ ግምቱዎች በሩጫው አልፈው በአሁኑ ወቅት ብሔራዊ ፌዴሬሽኑን እንዲያስተዳድሩ የተደረገው፣ ከሙያው ጋር የተዛመዱ በመሆናቸው ብቻ ሳይሆን፣ ለአትሌቲክሱ የውጤት የትንሳዔ ፋኖ ይሆናሉ ተብሎ አልነበረም ወይ? የሚሉ አሉ፡፡ ይህን መሰሉን አስተያየት የሚቀበለው ኃይሌ፣ ‹‹ችግሩ የሚጀምረው አትሌቶች ለአሠልጣኞች ከሚሰጡት ግምት ነው፡፡ እውነቱን እንነጋገር ከተባለ አንዳንዶቹ አትሌቶች በሁሉ ነገር ከአሠልጣኙ አቅም በላይ ናቸው፡፡ በዚያ ላይ ለውጤት የሚመጥን ሥልጠናና ዝግጅት የሚያደርግ የለም፡፡ ሁሉም አቋራጭ ፈላጊ ሆኗል፤›› ብሏል፡፡
የቀድሞ አትሌቶች አኅጉራዊም ይሁን ለዓለም አቀፍ ውድድሮች በሚዘጋጁባቸው ሥልጠናዎች ወቅት ከነበረው ጠንካራ ልምምድ የተነሳ ወደ ላይ እያላቸው ሲያስመልሱና ሥጋት ድካም ሲያሳልፉ የሚታዩ አሁን ግን ማስመለስ የድካም ስሜት ቀርቶ አክታ እንኳ የማይወጣቸው አትሌቶች መብዛታቸውን የሚናገረው ኃይሌ፣ ‹‹ይኼ የሚነግረን የአትሌቲክስ ዝግጅት ፍፁም ቀልድና ማሾፊያ እየሆነ መውጣቱን ነው፡፡ በመሆኑም ተቋሙና ልጆቹ በጉዳዩ ፊት ለፊት የሚነጋገሩበት ወቅት አሁን ነው፡፡ አመራሩን ጨምሮ አሠልጣኞችና አትሌቶች ሊገባን የሚገባው አትሌቲክሱ አደጋ ላይ መሆኑ ነው፤›› ያለው ኃይሌ አክሎም፣ ‹‹ማንኛውም አትሌት ከለፋና ከደከመ ውጤት ያገኛል፡፡ ለዚህ ትክክለኛ ማሳያ ሊሆነን የሚገባው ኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያ አይደለም፡፡ ለመፎካከር እንኳ በሚያዳግታት የውድድር ዓይነት በ20 ኪሎ ሜትር የዕርምጃ ውድድር የወርቅ ሜዳሊያ አስመዝግባለች፤›› ይላል፡፡
ከውጤቱ ጋር ተያይዞ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የዘርፉ ሙያተኞች፣ ለአትሌቲክሱ ውጤት መቀዛቀዝ የየራሳቸውን ሙያዊ አስተያየት ይሰጣሉ፡፡ ብዙዎቹ ከአመራሩ ሊደርስባቸው የሚችለውን ሙያዊ ተፅዕኖ ከመፍራት አኳያ ማንነታቸውን ለመግለጽ አይፈልጉም፡፡ በብዙ ውጣ ውረድ ለዚህ ኃላፊነት የበቁት እነ ኃይሌ፣ ትልቁ ስህተታቸው ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዩ መለያ በመሆን ለዓመታት የዘለቀውንና በአንድ ማዕከል ይተዳደርና ይመራ የነበረውን የብሔራዊ ቡድን ዝግጅት እንዲበተን ማድረጋቸው ስህተት እንደሆነ ያምናሉ፡፡ በሌላ በኩል የብሔራዊ ቡድኑ መበተን እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ምርጫን በተመለከተ ፌዴሬሽኑ የሚከተለው ደንብና መመርያ በሙያና ብቃት ላይ የተመሠረተ አለመሆኑ፣ ሌላው ተቋሙ እከተለዋለሁ የሚለው ደንብና መመርያ ተግባራዊ የሚሆነው በቀረቤታ መሆኑ ጭምር ለስፖርቱ ውጋት እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡
አስተያየት ሰጪዎቹ ሲያክሉም፣ እነ ኃይሌም ሆኑ በፌዴሬሽኑ በተለያዩ የኃላፊነት እርከን ላይ የሚገኙ ከፍተኛ አመራሮች ፍላጎትና ህልማቸው የኢትዮጵያን አትሌቲክስ ማሳደግ ከሆነ፣ ማድረግ ያለባቸው የብሔራዊ አትሌቶችን የመምረጫ መሥፈርት ጨምሮ ደንብና መመርያው ቀደም ተብሎ ይመለከታቸዋል የሚባሉ ባለድርሻ አካላት ተካተውበት አስተያየት እንዲሰጥበት ማድረግ፣ በዚሁ አግባብ አሠልጣኞችም ሆነ አትሌቶች ሲመረጡ ምንም ዓይነት ጣልቃ ገብነት ሳይኖር፣ ተጠያቂነትና ግልጽነት ባለው አሠራር ተቋማዊ ቁመናውን መፈተሸና ክፍተቱን መሙላት እንደሆነም ይመክራሉ፡፡
ይሁንና አሁን ባለው አካሄድ ኦሊምፒክም ይሁን የዓለም ዋንጫ አለያም ሌሎች አኅጉራዊ ውድድሮች በተቃረቡ ቁጥር ደንብና መመርያዎች እየተዘጋጁ ነው የሚሉት እነዚሁ አስተያየት ሰጪዎች፣ ይህ ደግሞ በአትሌቶችም ሆነ በሙያተኞች መካከል ሊኖር የሚገባውን ሰላማዊ ግንኙነት የሚያበላሽ ከመሆኑም በላይ፣ ፌዴሬሽኑ የሚፈልገውን አትሌትና አሠልጣኝ በሚፈልገው መልኩ ለመመልመልና ለመመደንብ እንዲያመቸው የሚያደርገው ነው በማለት ይከራከራሉ፡፡ ይህም ለአትሌቲክሱ ውጤት መውደቅና ማጥፋት አንዱና ትልቁ ተግዳሮት እንደሆነም ያምናሉ፡፡
የዚህ አካሄድ ሌላው ችግር በማለት የጠቀሱት፣ ለአትሌቲክሱ ዕድገት መሠረታዊ እንደሆነ ለሚታመነውና ታዳጊዎችን ከታች ጀምሮ ለማፍራት በሚያስችለው የአሠራር ሥርዓት ላይ ንቅፋት መሆኑ ነው፡፡ ለዚህ በማሳያነት የሚያቀርቡትም በሙያቸው አንቱ የተባሉ አሠልጣኞች ለጊዜያዊ ውጤት ሲባል ተለፍቶባቸውም ይሁን በአጋጣሚ የበቁ አትሌቶች ላይ ብቻ ትኩረት እንዲያደርጉ አቋራጭ እንዲሆናቸው ሰበብ እየሆነ መምጣቱን ያመላክታሉ፡፡
የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ኃይሌ በበኩሉ፣ ምክንያቱ ‹‹የእምዬን ወደ አብዬ፤›› ካልሆነ አሠልጣኞች ከምልመላ እስከ ሥልጠና ማንም ጣልቃ እንደማይገባባቸው፣ ‹‹እኔም ሆንኩ ሌሎች አመራሮች ባለን ልምድና ተሞክሮ እንዲህ ቢደረግ ብሎ ሐሳብ ከመስጠት ያለፈ ምንም ዓይነት ጣልቃ ገብነት የሚባል ነገር የለም፤›› ይላል፡፡ ይሁንና እንደ ፌዴሬሽን አመራር ለሚመጣው ውጤትም ሆነ ውድቀት ለምንና እንዴት ብሎ መጠየቅ ተገቢና ትክክለኛ አካሄድ መሆኑን፣ አሠራሩም ዘላቂነት እንዲኖረው መደረግ እንዳለበት አበክሮ ይጠቅሳል፡፡
በሙያተኞቹ እንደ ቅሬታ ሲቀርብ የሚደመጠው ሌላው ጉዳይ፣ በፌዴሬሽኑ ባለው የደንብና የመመርያ ክፍተት ምክንያት ከአትሌቶቹ ጋር ለወራት የቆዩ አሠልጣኞች ባላቸው ውጤትና ብቃት ስለማይመረጡ፣ አትሌቶቹ ጥንካሬና ድክመታቸውን የማያውቁ አሠልጣኞች በሚረከቧቸው ወቅት ዝግጅት የሚጀምሩት እንደገና ከዜሮ በመጀመር ስለሚሆን ይኼንንም ክፍተት ማጣጣም እንደሚያስፈልግ ይጠቅሳሉ፡፡ እንደ ፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ከሆነ ግን፣ አሁን ከአመራሩ ጭምር በምክንያት እያሰቡ ለመኖር ጊዜው አይፈቅድም፡፡ አትሌቱ፣ አሠልጣኙና አመራሩ በዚህ አስተሳሰብ መቀጠል እንደማይችሉ የሚናገረው ኃይሌ፣ ‹‹በግሌ ፌዴሬሽኑን በፕሬዚዳንትነት ለመምራት ስመጣ አንድ ነገር ለመሥራት ነው፡፡ ስለሆነም ከእንግዲህ መሆን ስለሚገባው መነጋገር ካለብን እንነጋገራለን፡፡ በዚህ አኳኋን መሄድ የማንችል ከሆነ ደግሞ ፌዴሬሽኑ እንዲሁ የተቋምና የሕዝብ ገንዘብ ማፍሰሱ ተገቢ ስለማይሆን እንችላለን ካልን መሥራት አለብን፡፡ አንችልም ካልን ግን ኃላፊነቱን ማስረከብ ነው፡፡ ምክንያቱም ኅብረተሰቡ ውጤት እፈልጋለሁ እያለ ነው፡፡ አሠልጣኞችና አትሌቶች እንዲሁም አመራሩ ሰፊ ጊዜና ሰዓታችንን ለሞባይል ጌምና ለፌስ ቡክ በማዋል ውጤት መጠበቅ ስለማይቻል አንዱን መምረጥ የግድ ነው፤›› በማለት ቆንጠጥ ያለ ሐሳቡን አስተላልፏል፡፡
ሙያተኞቹ አሳዛኝ በማለት የሚገልጹት ሌላው ጉዳይ፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ከቤተሰብ በውርስ እንደተላለፈ ርስት በጥቂት ግለሰቦች ፈላጭ ቆራጭነት የመመራቱን ጉዳይ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ከሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ግማሽ ያህሉ ወጣት ሙያተኞች፣ በስፖርት ሳይንስ የመጀመርያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን እያገኙ ባለበት በዚህ ወቅት፣ ተቋሙ ይህንኑ ግምት ውስጥ በማስገባት አማራጮችን መመልከት አለበት ይላሉ፡፡ ይኼ ጉዳይ በብዙዎች ዘንድ እንደ ክፍተት ሲነሳ ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ የአትሌት ማናጀሮችና የማናጀር ተወካዮች ሳይቀሩ ችግሩን በገሃድ ከመጋፈጥና ፊት ለፊት ከማውራት ይልቅ የወደፊት ሥራችን ላይ ችግር ይፈጥርብናል በሚል ፍራቻ እንዲሸሹ ምክንያት ሆኖ መቆየቱ ይነገራል፡፡
ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ውድቀት አንዱና መሠረታዊ ችግር ተደርጎ የሚጠቀሰው፣ አሁን ባለው የአትሌቲክሱ ተጨባጭ ሁኔታ የትራክ ውድድሮች እየጠፉ በጎዳና ውድድሮች መተካታቸው ነው፡፡ ፌዴሬሽኑም ይህንኑ ያምናል፡፡ በሌላ በኩል ፌዴሬሽኑ ሁሉንም አትሌቶች በብቃትና ችሎታቸው ላይ አምኖ ትክክለኛውን አሠራር ማስፈን ከቻለና ስለሁኔታው በትራክ ከሚታወቁ አትሌቶች ጋር ቢመካከር ችግሩ ሊቃለል እንደሚችል የሚገልጹ አሉ፡፡ ችግሩ እኔ ብቻ የሚል ሥርዓት መንሰራፋቱ እንደሆነም ያምናሉ፡፡ ለሙያተኞቹ ሪፖርተር ያነሳው ሌላው ጥያቄ፣ አሠልጣኞች አትሌቶች በሚፈልጉት የአመራር ዘይቤ ይመሯቸዋል ወይ? የሚል ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ክፍተት እንዳለ የሚያምኑ እንዳሉ ሁሉ፣ በሌላ በኩል በፍትሕ መጓደል ካልሆነ በስተቀር ማንኛውም አትሌት በሚያምንበት አሠልጣኝ ቢሠለጥን ተጠቃሚ እንጂ ተጎጂ እንደማይሆን ስለሚያውቅ፣ አሠልጣኙን የማያከብርበት ምክንያት ሊኖር እንደማይችል ይናገራሉ፡፡
ይሁንና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለአትሌቲክሱ ውድቀት በዋናነት እንደ ምክንያት ሲጠቀስ የሚደመጠው፣ ትልልቅ ዓለም አቀፍ ወድድሮች ማለትም ኦሊምፒክና የዓለም ዋንጫን የመሳሰሉት ላይ ለመሳተፍ ብሔራዊ ዝግጅቶች ሲኖሩ፣ ‹‹አትሌቶች በሚያምኑባቸው አሠልጣኞች፤›› በሚል ሽፋን ክፍፍል መኖሩ የአደባባይ ምስጢር ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት የሚሰጡ ሙያተኞች ይህ ዓይነቱ አካሄድ የሚቀጥል ከሆነ በወደፊት የስፖርቱ ውጤት ላይ የከፋ አደጋ እንደሚያስከት ያሳስባሉ፡፡ ዓለም አቀፍ ስታንዳርዱን የጠበቀ አንድ ወጥ ሥልጠናና ዝግጅት ማድረግ ከተጠያቂነትም አኳያ አዋጭ እንደሆነም ይጠቅሳሉ፡፡ ኃይሌና አመራሩም በዚህ እንደ ማይደራደሩ አስታውቋል፡፡