Thursday, July 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

ባለፈው ዓመት ክረምት ከለገሐር ወደ ሽሮሜዳ በሚያመራው ታክሲ ውስጥ ተሳፍሬአለሁ፡፡ የታክሲው ወያላ ውጪ ሆኖ እየተጣራ ተሳፋሪዎችን ያስገባል፡፡ አንድ ተሳፋሪ የሚመስል ሰው በሩ ላይ ቆሞ ወደ ውስጥ እየተመለከተ ቆሟል፡፡ ረዳቱ ወደ ሰውየው ቀረብ ብሎ፣ ‹‹ወንድም በሩን አትዝጋው ከገባህ ግባ፤›› አለው፡፡ ሰውየው ወደ ወያላው ፊቱን መልሶ፣ ‹‹የት ነው የምትጭኑት?›› አለው፡፡ ወያላውም፣ ‹‹አይሰማህም እንዴ አራት ኪሎ፣ ስድስት ኪሎ፣ ሽሮ ሜዳ እያልኩ ስጣራ?›› አለው በተበሳጨ ድምፅ፡፡ ሰውየው ወያላውንና እኛን እያየ ይስቅ ጀመር፡፡ ታክሲው ውስጥ የተቀመጥነው ጥቂት ሰዎች በመገረም እያየነው ነው፡፡

በዚህ መሀል ሰውየው፣ ‹‹እኔ እኮ ስድስት ኪሎ ጂኒ ጃንካ መሄዳችሁን መቼ አወቅኩ…›› ሲል ጤነኛ እንዳልሆነ ገባኝ፡፡ ምንም እንኳ እጅግ በጣም ንፁህ ሙሉ ልብስ ከከረባት ጋር ቢለብስና ንፁህና የሚያብረቀርቅ አዲስ ጥቁር ጫማ ቢጫማም የሆነ ችግር አለ አልኩ፡፡ መልኩ ቀላ ብሎ በምቾት የተያዘ ሰው ቢመስልም፣ አንድ ልክ ያልሆነ ነገር ጠረጠርኩ፡፡ አንገቴን ሰገግ አድርጌ፣ ‹‹ወንድም የት መሄድ ነው የፈለግከው?›› አልኩት፡፡ ሰውየው ፈገግ ብሎ እያየኝ፣ ‹‹እኔማ ወደ ማርስ የምትሄዱ መስሎኝ እኮ ነው ልሳፈር የነበረው፤›› ሲል ደነገጥኩ፡፡ እንደኔ ሌሎች ተሳፋሪዎችም ሆኑ ረዳቱ ደንግጠዋል፡፡

ሰውየውን በሐዘኔታ እያየን ሳለ ድንገት ሁለት ውብ ወጣት ሴቶች መጥተው አጠገቡ ቆሙ፡፡ አንደኛዋ ፈገግታዋን በሚገባ ለግሳው፣ ‹‹ሚኪ ከምኔው እዚህ ጋ መጣህ? እኛ እኮ ከአጠገባችን ስትጠፋ ተጨነቅን፡፡ በል እንሂድ እነ ማሚና ባቢ ይጠብቁናል፤›› ካለችው በኋላ ወገቡን እቅፍ አድርጋ ስትይዘው፣ ሌላኛዋም እጁን  ይዛው መንቀሳቀስ ጀመሩ፡፡ ይኼኔ ምን እንደገፋፋኝ አላውቅም ከታክሲው ወርጄ ተከተልኳቸው፡፡ ግራ የሚያጋባ ድንገተኛ ነገር ሲያጋጥመኝ የማወቅ ፍላጎቴ ስለሚጨምር ነው መሰል ተከትያቸው ሄድኩ፡፡

አለፍ ብሎ መኪናቸውን ያቆሙበት ቦታ ሲደርሱ አንደኛዋ ወጣት የጥቁር መርሰዲስ መኪና በር ከፍታ ከገባች በኋላ፣ ለሰውየውና ለልጅቷ እንዲገቡ በሮቹን ከፈተችላቸው፡፡ ሰውየው የፊት በሩን ከፍቶ ሲገባ አጠገቡ የነበረችውን ወጣት ጠጋ ብዬ ሰላምታ አቀረብኩላት፡፡ ማን ይሆን በሚል ስሜት እያየችኝ ሰላም አለችኝ፡፡ ቀረብ አልኳትና ታክሲው ውስጥ ሆኜ የገጠመኝን ትዕይንት ከነገርኳት በኋላ፣ ‹‹ይኼን የመሰለ ሰው ምን ሆኖ ነው?›› በማለት ጥያቄ አቀረብኩላት፡፡ ‹‹አንዴ?›› አለችኝና መኪናውን ወደ ምታሽከረክረው ወጣት ዘንድ ሄዳ ጥቂት ከተነጋገረች በኋላ ተመልሳ መጣች፡፡ ያችኛዋም ተከተለቻት፡፡

ወጣቷ፣ ‹‹ይኼ የምታየው ሰው ታላቅ ወንድማችን ነው፡፡ ቢያንስ ከሃያ ዓመት በላይ ይበልጠናል፡፡ አሜሪካ ከመሄዱ በፊት የተማረው ሴንት ጆሴፍ ትምህርት ቤት ነው፡፡ ከዚያም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ በኢንጂነሪንግ በዲግሪ ተመርቋል፡፡ አሜሪካ ደግሞ ማስተርሱንና የዶክትሬት ዲግሪውን አግኝቷል፡፡ በአሜሪካ ታዋቂ ኩባንያዎች ውስጥ በከፍተኛ ኃላፊነት ሠርቷል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የአዕምሮ ሕመም ስለገጠመው ሕክምናውን እየተከታተለ ነው፡፡ እዚህ የመጣው ደግሞ ለጠበል ነው፤›› ብላ አስረዳችኝ፡፡ እህትየውም አክላ እንደነገረችኝ አሁን ከበፊቱ በተሻለ ሁኔታ ላይ ይገኛል፡፡ ‹‹ምንም እንኳን እንዳንዴ በመጠኑ ዘብረቅ ቢያደርግም እግዚአብሔር ይመሥገን ደህና ነው፤›› አለች፡፡

ተሰነባብቻቸው ልንለያይ ስንል አንደኛዋ፣ ‹‹ሰው በጣም ስለሚወድ እስኪ አናግረው፤›› አለችኝ፡፡  ጠጋ ብዬ ‹‹ሰላም እንዴት ነው?›› አልኩት፡፡ በሩን ከፍቶ እየወጣ፣ ‹‹እንዴ ታክሲ ውስጥ አይቼሃለሁ፡፡ ተነጋግረን ነበር አይደል?›› አለኝ፡፡ ትክክል መሆኑን ካረጋገጥኩለት በኋላ፣ ‹‹ታክሲው ወደ ማርስ ስለማይሄድ እኔም ወረድኩ፤›› በማለት እየሳቅኩ ነገርኩት፡፡ እሱም እየሳቀ፣ ‹‹አንተ ቀልደኛ ትመስላለህ፡፡ እኔ እኮ ትንሽ ላዝናናችሁ ብዬ ነው እንጂ ታክሲ ወደ ማርስ እንደማይሄድ አጥቼው አይደለም፤›› ካለኝ በኋላ በነገራችን ላይ፣ ‹‹ምንድነው የተማርከው?›› በማለት ያላሰብኩትን ጠየቀኝ፡፡ በሒሳብ ተመርቄ የአስተዳደር ሥራ በግዳጅ እንደምሠራ ነገርኩት፡፡ በመገረም እያየኝ፣ ‹‹አሠሪዎችህ ወፈፍ ሲያደርጋቸው አንተም አብረሃቸው ታብዳለህ?›› ብሎ ሲቆጣኝ የአዕምሮ ታማሚው እኔ ወይስ እሱ አልኩ በልቤ፡፡

 ላለፉት 15 ዓመታት ያባከንኩት ጊዜ ወለል ብሎ እየታየኝ እሱን እንደ ጤነኛ፣ ራሴን ደግሞ እንደ ወፈፌ አድርጌ ሰዎቹን ተሰናብቼ ጉዞዬን ቀጠልኩ፡፡ በዚህ አጋጣሚ መነሻ ሁለተኛ ዲግሪዬን በሒሳብ ትምህርት ለማግኘት ትምህርቴን የጀመርኩ ሲሆን፣ የምወደውን ሙያዬንም በትግል አግኝቻለሁ፡፡ ላለፉት ዓመታት ከነበርኩበት አዙሪት ውስጥ ያወጣኝ ያ ሰው አሁን በመልካም ሁኔታ ላይ መሆኑንና ሥራ መጀመሩንም ከእህቶቹ ተረድቻለሁ፡፡ አንዳንዴ ሳስበው ግን ጤነኛ ነን ብለን ከምንመፃደቀው ወፈፍ የሚያደርጋቸው ሳይበልጡ ይቀራሉ? እስኪ ራሳችንን እንፈትሽ፡፡

(ወሰንሰገድ ማስረሻ፣ ከስድስት ኪሎ)  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...