Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉጠቅላይ ሚኒስትራችን አየር መንገዱ በከፊል ይሸጣል ማለታቸው ከኢኮኖሚ ትንተና አንፃር አሳሳቢ ስህተት...

ጠቅላይ ሚኒስትራችን አየር መንገዱ በከፊል ይሸጣል ማለታቸው ከኢኮኖሚ ትንተና አንፃር አሳሳቢ ስህተት ነው

ቀን:

በዓለማየሁ ገዳ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ትልልቅ የመንግሥት ድርጅቶቻችንን በከፊል ለመሸጥ ያቀረበውን ሐሳብ ስናስታውል ልብ ልንለው የሚገባን፣ ኢኮኖሚውን በሚመለከት ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት አብዮት ሳይሆን  ዝግመታዊ ለውጥ፣ የነጭ ካፒታሊዝም ነፃ ገበያ ሳይሆን በዕውቀት የታገዘና በዴሞክራሲያዊ ልማታዊ መንግሥት የሚመራው ነፃ ገበያ መሆኑን ነው፡፡ ስለሆነም የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ መንግሥት በአንድ ጀምበር የልማታዊ መንግሥት እሳቤን አሽቀንጥሮ ሊጥል፣ ወይም ደግሞ ብርቅዬ ንብረቶታችንን በመሸጥ መሠረቱን በብርቱ ሊገዘግዘው አይገባም፡፡ ምክንያቱም በአጭር ጊዜ ሲታይ የኢኮኖሚ አለመረጋጋት ከማምጣቱም በላይ፣ በረዥም ጊዜ ደግሞ የዴሞክራሲያዊ ልማታዊ መንግሥት እሳቤ በውሉ ከተያዘ፣ በዕውቀት ላይ ከተመሠረተ፣ በአገሪቱ ፈጣን ዕድገት ለማምጣትና ድህነትን በፍጥነት ለመቀነስ ከማንኛውም መንገድ የተሻለ መስመር እነደሆነ የኮሪያንና የቻይናን ታሪክ ማየት ብቻ ከበቂ በላይ ነው፡፡ የጠቅላያችንም ብርቱ ፈተና ምሥራቅና ምዕራብ ሳይሉ በሁለቱ መስመሮች መሀል የአገሪቱንና የደሃውን ብሔራዊ ጥቅም መነጽራቸው አድርው በጥበብ ማራመድ ነው፡፡

ሰሞኑን የመገናኛ ብዙኃን ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ከዓለም ባንክና ከዓለም የገንዘብ ድርጅት ባለሥልጣናት ጋር ገንቢ ውይይት አካሄዱ ሲሉ ዘግበዋል፡፡ እነዚህ ዓለም አቀፍ ተቋማት የአፍሪካን መንግሥታት በተመለከተ አስገድደው ያስተገበሯቸውን የፖሊሲ አቅጣጫ፣ ታሪክና ይኼም ፖሊሲ ያስከተለውን የኢኮኖሚ ውድቀትና ድህነት ለሚያስተውል ሰው ውይይቱና ዘገባው ሥጋትን እንጂ ብዙ ተስፋ አያስጭርም፡፡

እነዚህ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በመላው አፍሪካ አገሮች ውስጥ በ1980ዎቹና በ1990ዎቹ “የመዋቅራዊ ማስተካከያ ፖሊሲ” የሚባል “የነፃ ገበያን በግድ ተቀበሉ” ፖሊሲ በማምጣት ይህን ካልተገበራችሁ ብድር አንሰጣችሁም፣ ከበለፀጉ አገሮችም እንዳይሰጣችሁ እናደርጋለን በማለት መላው አፍሪካን ሲያስጨንቁ የኖሩ ናቸው፡፡ ይኼ ምክረ ሐሳባቸው የነፃ ገበያ ርዕዮትን ማስፋፋት፣ ማንኛውንም ክፍለ ኢኮኖሚ ለዓለም ገበያ መክፈት፣ የብር ተመንን መቀነስና መንግሥትን ከኢኮኖሚው ውስጥ ማስወጣት ነበር፡፡ የዚህ ፖሊሲ ውጤት ደግሞ የአፍሪካን መዋቅራዊ ለውጥ የማምጣት ህልም ቅዠት ብቻ ማድረግ ሳይሆን፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ዕድገት ኮስሶ ድህነት እንዲንሰራፋ ማድረግ ነበር፡፡ በመሆኑም  ይህ የዓለም ባንክና የዓለም የገንዘብ ድርጅቶች ጀብድ የተመላበት “የእኔን ፖሊሲ ተከተሉ” አካሄድ፣ በ1980ዎቹና በ1990ዎቹ የአፍሪካን ዕድገት በማሸመድመድ ከሁለት በመቶ በታች እንዲሆን አድርጓል፡፡ የፖሊሲ አቅጣጫውን አጠንክረው የተከተሉ የአፍሪካ አገሮችማ የኢኮኖሚ ዕድገታቸው ከዜሮ በታች ወርዶ እስከ ኔጋቲቭ ስምንት በመቶ እንደ ደረሰ፣ በጊዜው የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን አጥንቶ ይፋ ያደረገው ጉዳይ ነው፡፡ ድህነቱም እ.ኤ.አ. በ1981 ከነበረበት 163 ሚሊዮን ደሃ ሕዝብ በዕጅጉ አሻቅቦ በ2000 ደግሞ 313 ሚሊዮን አድርሶታል፡፡

በአንፃሩም ይህንን ምክረ ሐሳብ አንሰማም ብለው የራሳቸውን የልማታዊ መንግሥት ፖሊሲ የተከተሉ የምሥራቅ እስያ አገሮች ለምሳሌም እንደ ኮሪያ፣ ታይዋንና ቻይና የመሳሰሉ አገሮች ኢኮኖሚያቸው ላይ የሚደነቅ መዋቅራዊ ለውጥ ከማምጣታቸውም በላይ፣ የድህነታቸውን መጠን በአስገራሚ ሁኔታ ከ77 በመቶ ወደ 14 በመቶ እንዲወርድ አድርገዋል፡፡ ለምሳሌም ቻይናን ብቻ ብንወስድ ባለፉት 40 እና 50 ዓመታት የነበረባትን 88 በመቶ የድህነት መጠን በአሁኑ ጊዜ ወደ ስድስት በመቶ እንዲወርድ አድርገዋለች፡፡ ይህ ማለት በዚያን ጊዜ የነበረዉ ደሃ ቻይናዊ ከአንድ ቢሊዮን ሕዝብ ውስጥ 900 ሚሊዮን ሲሆን፣ በ894 ሚሊዮን ቀንሶ ዛሬ ስድስት ሚሊዮን የቻይና ሕዝብ ብቻ ነው ደሃ የሚባለው፡፡ ይኼ ነው እንግዲህ በውል የተያዘ ልማታዊ መንግሥት ማለት፡፡ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ግን ይህንን የእስያ አገሮች ልምድ በመተው በዘመናዊ መልክ እየመጣ ያለውን የእነዚህ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ሀብታም አገሮች ድርጅቶቻችሁን ሽጡ/ሸጡልን ምክር በመቀበል፣ እነዚህ የኒዮሊበራል አራማጆችና ከጀርባቸው ያሉ ሀብታም አገሮች እጅ ላይ ለመውደቅ እየዳረጋቸው ነው፡፡

ባለፋት ሦስት ዓመታት የዓለም ባንክና የዓለም የገንዘብ ድርጅት የኢትዮጵያን የወጪ ንግድ ለማጠናከር የብር የገንዘብ ተመን መቀነስ አለበት፣ ግሽበትም አያመጣም እያሉ መንግሥትን ሲያስጨንቁ ነበር፡፡ እኔም በተለያዩ ጽሑፎቼ ይህ ፖሊሲ የወጪ ንግድን የማያሻሽል፣ በአንፃሩ ግን የዋጋ ንረት አምጥቶ ደሃውን የሚጎዳ ነው ብዬ ስከራከር ነበር፡፡ አሁን በጊዜ ሒደት እንዳየነው የብር ተመን በመርከሱ የወጪ ንግዱም ሳይሻሻል የዋጋ ንረቱ ከፍ ብሎ ምክረ ሐሳባቸው ስህተት እንደነበረ ፍንትው ብሎ የሚታይ ሆኗል፡፡ ከዚህ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ የአፍሪካና የራሳችንም ልምድ እንደምናየው እኛን ለመምከር የሞራል ብቃቱም የላቸውም፣ ልንሰማቸውም አይገባም፡፡ ልብ ብሎ ላየው የምክረ ሐሳባቸው መሠረቱ ርዕዮተ ዓለማቸውን የማስፋፋት ፍላጐትና የሀብታም አገሮችን የኢኮኖሚ ጥቅም የማስጠበቅ ተልኮአቸው ነው፡፡ በመሆኑም ሙያዊ የኢኮኖሚ ትንታኔ እንኳ አያደርጉም፡፡

እንደሚታወሰው ባለፉት 27 ዓመታት እነዚህ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የኢሕአዴግን መንግሥት ትልልቅ ኩባንያዎችህን ካልሸጥክ ብለው በእያንዳንዱ ድርድር ሲያጨንቁት ነበር የከረሙት፡፡ ምንም እንኳን እንደ ቴሌ ዓይነቶች አንዳንድ ድርጅቶች ደካማ አገልግሎት እየሰጡ ያሉና ለግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ በተወሰነ ደረጃ ክፍት ቢሆኑ የተሻለ ቢሆንም፣ ኢሕአዴግ የእነዚህን ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጫና ተቋቁሞ እዚህ ድረስ በመድረሱ ምሥጋና ሊቸረው የሚገባ ነው፡፡ ምክንያቱም ለሚያዋጣው ፖሊሲ ባለቤት ነበርና፡፡ ከዚህ የሚኮራበት ባህልና ልምድ ባፈነገጠ መንገድ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ለምን ለእነዚህ ድርጅቶች ኩባንያዎቻችሁን ሽጡ/ልን ጫና እንደተሸነፉ፣ በተለይም ደግሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድን በከፊል ለመሸጥ ማሰባቸው ሊገባኝ አልቻለም፡፡ ቴሌን፣ መብራት ኃይልን፣ ባንክንና የመሳሰሉትን ኩባንያዎችን የመሸጡን ጉዳይ ትንታኔ ለሌላ ጊዜ በመተው በዛሬው ጽሑፌ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ አተኩራለሁ፡፡

ከኢኮኖሚ ትንታኔ አንፃር የመንግሥት ኩባንያዎችን ወደ ግል ለማዛወር ሁለት ምክንያቶች ሊቀርቡ ይችላሉ፡፡ አንደኛውና ኒዮሊብራሎች የሚያቀነቅኑት ነጥብ ከመንግሥት ይልቅ የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ስሉጥና ለብክነት ያልተዳረገ በመሆኑ በትንሽ ወጪ ትልቅ አገልግሎት ይሰጣል የሚለው ነው፡፡ ሁለተኛውና ለኢትዮጵያ መንግሥት አሁን ዋና የሚመስለው ምክንያት ደግሞ ያጋጠመን የውጭ ምንዘሪ እጥረት ችግር ይመስለኛል፡፡ የናረው የብድር ዕዳችን (ከአጠቃላይ የዓመት ገቢያችን 60 በመቶ ደርሷል) መጠንም ይኼንን እጥረት የሚጠናክር ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት በዚህ ዓይነት ጭንቀት ውስጥ መገኘት ደግሞ ለዓለም ባንክና ለዓለም የገንዘብ ድርጅት ‘’ዛሬማ አግኝተነዋል፣ እምቢ ሲለን የከረመውን ንብረቱን ሳያመልጠን እናሽጠው‘’ የሚሉበትን ዕድል ሰጥቷቸዋል፡፡ ቻይናም ከእነሱ ተገዳዳሪ ስለሆነች እሷም ከዚህ እሳቤ ጀርባ ብትሆን ብዙም አይገርምም፡፡

ኩባንያዎችን በከፊል የመሸጥ መከራከሪያ ነጥብ ላይ ብናተኩር ለተገልጋዩ ጥሩ አገልግሎት በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ ዋነኛና አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታው መጀመሪያ በመስኩ ተወዳዳሪነትን ማስፈን፣ ያንንም በአግባቡ የሚቆጣጠር ደርጅት ማቋቋም ነው፡፡ ተወዳዳሪነት ከሌለ ድርጅቶችን ከመንግሥት ወደ ግል ማዛወር፣ ከመንግሥት ሞኖፖል ወደ ግል ሞኖፖል ማዛዋወር ስለሆነ እንዲያውም ሕዝብን ሊጎዳ ይችላል፡፡ ምክንያቱም አዲሱ ባለሀብት የፈለገውን የዋጋ ተመን ከማውጣቱም በላይ፣ የራሱ ሀብት በመሆኑ ያገኘውን ትርፍ በፈለገው ጉዳይ ላይ ቢያጠፋ ሊናገረው የሚችል ኃይል አይኖርም፡፡ ከዚህ በላይ የቀረበውን ከመንግሥት ወደ ግል የማዘዋወርን አጠቃላይ ዓውደ ዕይታችንን እዚህ ላይ አቁመን፣ እስቲ ደግሞ ትኩረታችን በኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ እናድርግ፡፡

እንደ ቴሌ ያሉትን ድርጅቶች ብስለት፣ ብልኃትና ዕውቀት በተሞላበት መንገድ በከፊል መሸጥና ለግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ መክፈት ተገቢ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድን በከፊል ለመሸጥ ማሰብ ግን ምንም አይነት የኢኮኖሚ መከራከሪያ ነጥብ የሌለውና ኃላፊነት የጎደለው ከንቱ ሐሳብ ነው፡፡

በማንኛውም መሥፈርት የአየር መንገዱ ያለፉት 75 ዓመታት ጉዞ (በቅርቡ ከተከሰተው ብዝኃነትን ያላማከለ የቅጥር ሁኔታ በቀር) የኢከኖሚ ስኬትን አብርቶ የሚያሳይ ነው፡፡ የአየር መንገዱን የትርፍ ሁኔታ ላጤነው ለኢኮኖሚያዊ ጉዳይ ወይም ደግሞ አሠራሩን ለማሳለጥ ነው የምሸጠው የሚለው የመንግሥት መከራከሪያ ውኃ የማያነሳ ብቻ ሳይሆን መሠረትም የሌለው ነው፡፡. አካሄዱ ‘ከእነ ቴሌ ጋር የተገኘህ ሰሊጥ አብረህ ተወቀጥ’ ይመስላል፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት አየር መንገዱ ያስመዘገበው ከሰባት እስከ 13 በመቶ የሚደርስ የትርፍ ምጣኔ መጠን ዓለም ላይ አሉ የሚባሉ የአሜሪካ አየር መንገዶች እ.ኤ.አ. በ2018 ካስመዘገቡት የ4.9 በመቶ ትርፍ መጠን ከእጥፍ በላይ የሚበልጥ ነው፡፡ የአየር መንገዳችን ትርፍ አሜሪካ ውስጥ ካሉ ሰባት ምርጥና ትልልቅ የአየር መንገዶች የትርፍ መጠንም የበለጠ ነው፡፡ አነዚህ ትልልቅ የአሜሪካ አየር መንገዶች እ.ኤ.አ. በ2018 ያስመዘቡት የትርፍ መጠን ዘጠኝ በመቶ ብቻ ነበር፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ አየር መንገዳችን በአንድ መንገደኛ የሚያስገኘው የዶላር መጠንም የአውሮፓና የአሜሪካ አየር መንገዶች ከሚያገኙት በላይ ነው፡፡

አንባቢያን ይህንን የትርፍ ሁኔታ ሲያዩ አየር መንገዱ ዕዳ በዝቶበት ይሆን ይሉ ይሆናል፡፡ በኦዲት የተመረመረው የአየር መንገዱ ዓመታዊ ሪፖርት እንደሚየሳየው ግን አየር መንገዱ የዕዳ ችግርም የለበትም፡፡ ለሕዝብ ይፋ የሆነው የአየር መንገዱ የወቅቱ ዓመታዊ ሪፖርት እንደሚያሳየው ዕዳው ወደ 64.5 ቢሊዮን ብር ገደማ ሲሆን፣ የንብረቱ ግምት ግን 83.2 ቢለዮን ብር በመሆኑ ንብረቱ ከዕዳው በእጅጉ የበለጠ ነው፡፡ አየር መንገዱ በዚህ ረገድ በጥሩ አቋም ላይ እንዳለ አመላካች ነው፡፡ ለዚህም ነው መንግሥት ለኢኮኖሚ ስሉጥነት ነው በከፊል የምሸጠው ሲል ሊገባኝ የማይችለው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከአንድ የምርምር ባልደረባዬ ጋር የዓለም የንግድ ድርጅትን ለመቀላቀል ተብሎ፣ አየር መንገዱ ለዓለም አቀፍ ውድድር ክፍት ቢሆን ውድድሩን ይችለዋል ወይ በማለት አጥንተን ነበር፡፡ የዚህ ጥናት ውጤትም ያሳየን አየር መንገዱ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳድሮ ለማሸነፍ ብርቱ አቅም እንዳለው ነው፡፡ ስለሆነም  አየር መንገዱን በከፊል የምሸጠው የተሳለጠና ተወዳዳሪ ለማድረግ ነው የሚለው የመንግሥት መከራከሪያ ነጥብ ውሸት ብቻ ሳይሆን ትርጉመ ቢስና ኃላፊነት የጎደለው ነው፡፡ በአየር መንገዱ የሥራ መስክ ችግር ያለበት ክፍል የአገር ውስጥና የቀጣናው የበረራ ትኬት ዋጋ በጣም ከፍ ያለ ስለሆነ፣ ለግል ተዋንያን በአግባቡ ቢከፈት ለሸማቹ በውድድር ምክንያት በአነስተኛ ዋጋ ጥሩ ግልጋሎት ሊመጣለት ይችላል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በከፊል እንዳይሸጥ ከኢኮኖሚያዊ የመከራከሪያ ነጥብ በተጨማሪ፣ ፖለቲካዊና ባህላዊ መከራከሪያ ነጥቦችንም ማንሳት ይቻላል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካውያንም የኩራት ምንጭ ነው፡፡ ብዙ ነገሮች ሳይሳኩልን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስኬት ያስመዘገብንበት ኩባንያ ነው፡፡ አየር መንገዱ ለአገራችንም ሆነ ለአፍሪካ ምሳሌያዊና ምልክታዊ ፋይዳውም ኃያል ነው፡፡ አየር መንገዱ በጥቁር አፍሪካውያን መንግሥት ንብረትነት ተይዞ፣ በጥቁር አፍሪካውያን እየተመራ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስኬት ያስመዘገበ ኩባንያ ነው፡፡ በመሆኑም ለኢትዮጵያም ሆነ ለመላው አፍሪካ ኩባንያዎች በተምሳሌነት የሚወሳ ድርጅት ነው፡፡ ብዙ አፍሪካውያን ድርጅቶችም ከዚህ ተምሳሌት ትምህርት ሊወስዱና አሠራሩን ሊቀዱት የሚገባ ድርጅት ነው፡፡ በደምሳሳው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አንደ ቤተ ክርስቲያኖቻችንና መስጊዶቻችን የጋራ ማኀበራዊ ካፒታል የሆነ ተቋማችን ነው፡፡ እንደ ተቋምም ለሉዓላዊነታችን የበኩሉን ሚና የተጫወተ ድርጅት ነው፡፡

ለዚህም ነው አገዛዞቻችን እንኳ ቢለዋወጡም አየር መንገዳችን እንደ ድርጅት በሁሉም አገዛዞች የቀጠለ ተቋም የሆነው፡፡ ስለሆነም ይሀንን የመሰለ ኩባንያ ለሸያጭ ማቅረብ የታሪክ ቅርሳችንን፣ ተቋማችንንና ማኀበራዊ ካፒታላችን ለሽያጭ እንደ ማቅረብ ነው፡፡ ይህንን ጉዳይ በውል በማጤን ጠቅላይ ሚኒስትራችንና ኢሕአዴግ ድርጅቱን በከፊል የማዘዋወር ሐሳባቸውን ይለውጣሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ይህም ከታሪክ ተወቃሽነት ያድናቸዋል፡፡

በመጨረሻም የምዕራብ አገሮችና በተግባር የእነሱን ጥቅም አስከባሪ የሆኑት የዓለም ባንክና የዓለም የገንዘብ ድርጅት በዚህ ብቻ እንደማይቆሙ ላሰምርበት እፈልጋለሁ፡፡ ይህ የሽያጭ ነገር ካለቀ በኋላ የፋይናንሱን (ባንክና ኢንሸራንስ) ክፍለ ኢኮኖሚ ለእኛ ክፍት አድርጉት ማለታቸው አይቀሬ ነው፡፡ የፋይናንሱን ክፍለ ኢኮኖሚ በጥልቀት አጥንቼዋለሁ፡፡ ለውጭ ተወዳዳሪዎችም ክፍት እንዲሆን ፍላጐቴ ነው፡፡ ምክንያቱም ዝንተ ዓለም ድጋፍ እየተሰጠው ሊኖር አይችልምና፡፡ ሆኖም የፋይናንስ ክፍለ ኢኮኖሚውን በአግባቡ ሊቆጣጠርና ሊመራ የሚችል የተማረ ኃይል በብሔራዊ ባንክ ሳይቋቋም፣ ይህንን ማድረግ በባንኮችና በኢንሹራንስ ኩባንያዎች ላይ መዓት እንዲመጣ እንደ መጋበዝ ነው፡፡ በሌላ ጊዜና በሌላ ጽሑፍ ይህንን ጉዳይ በዝርዝር እመለስበታለሁ በማለት የዛሬ ጽሑፌን እዚህ ላይ አቆማለሁ፡፡ ከማቆሜ በፊት ግን የጠቅላይ ሚኒስትራችን ዋነኛ ደጋፊና ተደማሪ እንደሆንኩ እንዲታወቅልኝ እፈልጋለሁ (እንደ እውነቱ በሕይወቴ ጠቅላይ ሚኒስትሬ ያልኩት አሁን ነው)፡፡ ነገር ግን ዕውቁ ምሁራችን  ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ የዛሬ 100 ዓመት ገደማ እንዳለው፣ ‹‹መንግሥቱን የሚወድ ሰው ያ ቅዱስ ቅዱስ የሚለው አይደለም፣ ጥፋቱን የሚገልጽለት እንጂ፡፡››

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሰቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ፕሮፌሰር ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...