Thursday, July 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በመስቀለኛ መንገድ ላይ (የነፍስ አድን ዕርምጃ)

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በመስቀለኛ መንገድ ላይ (የነፍስ አድን ዕርምጃ)

ቀን:

የመጨረሻ ክፍል

በኤርሚያስ አመልጋ

ባለፈው ሳምንት የአገሪቱን የ15 ዓመታት የኢኮኖሚ ዕድገትና እግር ከወርች የያዙ ዝርዝር ችግሮችን ቅኝት፣ የኢኮኖሚ ልማት ስትራቴጂው ምን እንደሚመስልና ምን መደረግ እንዳለበት፣ በመንግሥት ባለቤትነት ሥር ስለሚገኙ ሀብቶች፣ አምስቱ ትልልቅ ድርጅቶች ምን ያህል እንደሚያወጡና ስለመሳሰሉ ጉዳዮች ትንታኔ መሰጠቱ ይታወሳል፡፡ ቀጣዩና የመጨረሻው ክፍል እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ኢትዮጵያ የመንግሥት ድርጅቶችን ፕራይቬታይዝ የማታደርግበት ምክንያት አላት?

ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብን የሚያካትት ጉዳይ ከመሆኑ አንፃር፣ በእርግጥም  የኢትዮጵያ የተከማቸ የመንግሥት ድርጅት ሀብትን መሸጥ የሚለውን ከላይ የቀረበ የመፍትሔ ሐሳብ የሚቃወሙ አማራጭ ሐሳቦች መኖራቸው አያስገርምም፡፡ ሰፋ አድርገን ስንመለከተው፣ እነዚህ ተቀናቃኝ አቋሞች ተከታዮቹን ፍሬ ጉዳዮች ይጠይቃሉ፡፡

1) በጥሩ አፈጻጸም ላይ የሚገኙ ውጤታማ የመንግሥት ተቋማትን ፕራይቬታይዝ የማድረግ ትክክለኛነት፣

 2) እንዲህ መሰል ግዙፍ ፕራይቬታይዜሽን ለልማታዊ መንግሥት ያላቸው ተገቢነት፣

 3) በአንዳንድ ቁልፍ ዘርፎች በሚካሄድ ፕራይቬታይዜሽን የተነሳ፣ አገራዊ አቅጣጫን ለመወሰንና ለመምራት የፖሊሲ ጉልበት ማጣት። እነዚህ ውኃ የማይቋጥሩ አባባሎችን፣ አንድ በአንድ እንመልከታቸው።

ውጤታማ ተቋማት ለምን ፕራይቬታይዝ ይደረጋሉ?

ለዚህ ቀላሉ መልስ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ጥሬ ገንዘብ የሚያስፈልጋት መሆኑ ነው፡፡ ከዚህ አንፃርም ለረዥም ጊዜ የተከማቸ ሀብት የያዙ ንብረቶችን፣ በአገሪቱ የኢኮኖሚ ታሪክ፣ ሽግግራዊ ለውጥ ማረጋገጥን ለመሰለ ታላቅ ዓላማ ፕራይቬታይዝ ማድረግ ፍፁም ትርጉም የሚሰጥ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር አምስቱ ትልልቆች፣ ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጡ ከመሆናቸው አኳያ ለፕራይቬታይዜሽን ግንባር ቀደም ዕጩ ያደርጋቸዋል፡፡ ለምሳሌ በእኛ ሥሌት መሠረት አምስቱ ትልልቅ ተቋማት ብቻ የታላቁ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ፣ ሁሉንም የኢትዮጵያ ሜጋ ፕሮጀክቶች ወጪ ሙሉ በሙሉ ይሸፍናሉ፡፡ ይህ ግድብ በራሳችን አቅም ሊገነባ የሚችል የሜጋ ፕሮጀክት ማለፊያ ምሳሌ ነው፡፡ ነገር ግን ከፋይናንስ አንፃር ትልቅ ተግዳሮቶች ገጥመውታል፡፡ አንደኛ የገንዘብ አቅርቦት በቀጥታ ያስፈልገዋል፣ ሁለተኛ የገንዘብ አቅም በውጭ ምንዛሪ ይፈልጋል፡፡ የመንግሥት ተቋማትን ፕራይቬታይዝ የማድረግ  አንዱ ፋይዳ፣ ከእነዚህ ሁለት መሠረታዊ ጉዳዮች አንፃር የሚታይ ነው፡፡ ከላይ ከተጠቀሰው በተጨማሪ፣ ውጤታማ ተቋማትን ፕራይቬታይዝ ማድረግ በአሉታዊነት መታየት የለበትም፡፡ ተቋማቱ ይበልጥ ውጤታማ የመሆን ዕድል እንዳላቸው በማሰብና ከጊዜ በኋላም፣ በመንግሥት እጅ ሆነው ከሚያመነጩት የበለጠ የታክስና የቅጥር ጠቀሜታዎችን እንደሚያስገኙ ከግምት ውስጥ በማስገባት፡፡ ወደ ግል ባለሀብት የተዛወረው ቢጂአይ የቢራ ፋብሪካ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ በውጭ ኢንቨስትመንትና አመራር አማካይነትም አሁን ፋብሪካው በአገሪቱ ከሚገኙ ትልልቅ ግብር ከፋዮችና ቀጣሪዎች አንዱ ሆኗል፡፡

መጠነ ሰፊ ፕራይቬታይዜሽን ከልማታዊ መንግሥት ጋር አይጣጣም ይሆን?

ሌሎች በርካታ ልማታዊ መንግሥታት ግዙፍ የመንግሥት ድርጅቶችን በባለቤትነት ይቆጣጠሩ የነበሩ ሲሆን፣ አሁንም ድረስ ይዘው የቀጠሉ መኖራቸው እርግጥ  ነው፡፡ በተለይም ለምሳሌ በቬትናምና ቻይና የእነዚህን መሰል መንግሥታት ፈጣን ዕድገት፣ የኢንዱስትሪ መስፋፋትና የድህነት ቅነሳ ስኬት የተከናወነውም እነዚህ የመንግሥት ተቋማት፣ በሰፊ የኢኮኖሚ ክፍሎች ውስጥ መንቀሳቀሳቸውን በቀጠሉበት  ሁኔታ ውስጥ ነበር፡፡ በሌላ በኩል ባለፉት 20 ዓመታት፣ በሁሉም ልማታዊ መንግሥት መር ኢኮኖሚዎች (ቻይናን ጨምሮ) የታየው አዝማሚያ ደግሞ፣ መጠነ ሰፊ የሆነ የፕራይቬታይዜሽን ሒደት መሆኑን ልብ ልንል ይገባል፡፡ በመላው ዓለም ፕራይቬታይዜሽንን የገፋፋው ኢኮኖሚያዊ ምክንያት፣ በተለይም ለኢትዮጵያ ይሠራል ለምን ቢሉ? ኢትዮጵያ ከእስያ ልማታዊ መንግሥታት በሁለት መሠረታዊ ባህርያት የምትለይ በመሆንዋ፡፡

አንደኛ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚው ውስጥ ማኑፋክቸሪንግና ኤክስፖርትን በመሳሰሉ ቁልፍ ዘርፎች ዕድገትን ወደፊት የሚያራምድ ግዙፍ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት የላትም፡፡ የምሥራቅ እስያ አገሮች ትላልቅ የመንግሥት ተቋማት ያላቸውም ጭምር፣ የኢኮኖሚውን ሰፊ ዕድገትና ኤክስፖርቱን ወደፊት ያስፈነጠረ፣ ሰፊ የኢንቨስትመንት ዕድሎች የፈጠረ፣ በግዙፍ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት የበላይነት የሚመራ ዘርፍ አላቸው፡፡ ሁለተኛውና ቁልጭ ብሎ የሚታየው ሌላው እውነት ኢትዮጵያ በከፍተኛ ቁጠባ ከሚታወቁት ከቻይናና ከቬትናም ጋር የሚስተካከል ቁጠባ ሊኖራት ቀርቶ፣ በአጠቃላይም ተዓምረኛ የኢኮኖሚ ግስጋሴ ካስመዘገቡት የምሥራቅ እስያ አገሮች መካከል ከአንዳቸውም የሚጠጋ የቁጠባ መጠን የሌላት መሆኗ ነው። የምሥራቅ እስያ የባንክ ሥርዓት፣ ከማያቋርጥ የአገር ውስጥ ምንጭ፣ ከፍተኛ የቁጠባ መጠን በመሰብሰብ፣ ለመንግሥታዊ ድርጅቶችና በፍጥነት ለሚስፋፋው ብድር ፈላጊ የግል ዘርፍ በቂ ፋይናንስ ማቅረብ ችሏል። ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ የቁጠባ መጠን የለም።

ፕራይቬታይዜሽን (በተለይ የውጭ ባለሀብቶችን ታላሚ ያደረገ) ማኑፋክቸሪንግና ኤክስፖርትን ወደፊት ማራመድ የሚችል፣ ጠንካራ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ዘርፍ የመፍጠር ዕድል የሚሰጥ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ባንኮች ማደግና መስፋፋትም ለሚሻው የአገር ውስጥ የግል ዘርፍ፣ ብድር እንዲያቀርቡም ያስችላቸዋል፡፡ በተጨማሪም ኢትዮጵያን ለመሰለ አገር በምንም ሁኔታ ቢሆን በቁጠባ ረገድ በአንዴ ትልቅ ለውጥ ለማምጣት መጣደፍ አያስፈልግም፡፡ በተለይ ከአገሪቱ ዝቅተኛ ገቢ አንፃር በአጭሩ እንደ ኢትዮጵያ ያለች አገር፣ አገራዊ ቁጠባዋን እንደ ኢንቨስትመንት የገንዘብ ምንጭ አብዝታ መተማመን የለባትም፡፡ በተለይም ፕራይቬታይዜሽንን የመሰለ ቀላል መፍትሔ በእጅ እያለና ፍጆታን ማዳከም ሳያስፈልግ፣ ለአዲስ ኢንቨስትመንት ተጨማሪ የገንዘብ ምንጭ ማቅረብ እየቻለ፡፡

በፕራይቬታይዜሽን ለምን የፖሊሲ ጉልበት ማጣት ይፈጠራል?

ከመንግሥት ድርጅት ይዞታዎች ስፋት አንፃር፣ ጥቂት የመንግሥት ድርጅቶችን በመሸጥ ሳቢያ የሚፈጠር ተጨባጭና ትርጉም ያለው የፖሊሲ ጉልበት ማጣት  አይኖርም፡፡ በእርግጥ አንዳንድ ጥንቃቄ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ ለምሳሌ በመንግሥት ባለቤትነት የተያዘው ግዙፉ ባንክ (የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ) ፖሊሲ ተኮር ለሆኑ ጉዳዮች የማበደር አቅሙ ከፕራይቬታይዜሽን ጋር ሊከስም  ይችላል፡፡ በእንዲህ መሰሉ ሁኔታና የመንግሥት ባለቤትነት ሲያስፈልግ፣ በእጅ ላይ ያለ አማካይ መፍትሔ አለ፡፡ መንግሥት 51 በመቶ አብላጫ ድርሻ በመያዝ (በድርጅቶቹ  ውስጥ ያለውን አብላጫ የቦርድ መቀመጫ የመያዝና ስትራቴጂ የመቀየስ ተያያዥ መብቶች አቅም ጋር)፣ ቀሪውን 49 በመቶ ለግል የውጭና የአገር ውስጥ ባለሀብቶች መሸጥ ይችላል፡፡ ለማጠቃለል የጠነከረ የፕራይቬታይዜሽን መርሐ ግብር የማካሄድ ምክንያት ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችና የማዕድን ቁፋሮ ፈቃዶች ለባለሀብቶች  እየተሰጡ ያሉበት ተመሳሳይ ምክንያት መሆኑ ትርጉም ይሰጣል፡፡ የግል ባለሀብቶች ከፍተኛ መጠን ያለው ቀጥተኛ ገንዘብና የተለዩ ተግባራትን የሚመሩበትና የሚያስተዳድሩበት ዕውቀትና ክህሎትን  ያመጣሉ መንግሥት በታክስና በኤክስፖርት ገቢ አማካይነት ከሚያገኘው ቀላል የማይባሉ ትርፎች ይጠቀማል ሕዝብም በከፍተኛ ዓመታዊ የገቢ ምንጮች ሳቢያ፣ ይበልጥ እየሰፉ ከሚመጡ የመንግሥት አገልግሎቶች የመጠቀም ዕድል አለው፡፡

የፕራይቬታይዜሽን ሌሎች ፋይዳዎች

የፕራይቬታይዜሽን ጠቀሜታዎች ለዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ማስፈጸሚያ የሚያስፈልገውን የገንዘብ አቅርቦት ከማሟላት በእጅጉ ልቆ የሚሻገር ነው፡፡ ምንም እንኳን በራሱ ድንቅና አስደማሚ ስኬት ቢሆንም፡፡ የፕራይቬታይዜሽን ሌሎች ሁለት ትላልቅ ፋይዳዎች፣ ለዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ፣ የገንዘብ አቅርቦት ከማስገኘት ቢበልጥ እንጂ አይተናነስም፡፡ በመጀመሪያና በዋናነት ፕራይቬታይዜሽን በትክክል ከተተገበረ፣ ለዋጋ ንረት ፈውስ ይለግሳል፡፡ በኢትዮጵያ የዋጋ ንረት ከገንዘብ ችግር ጋር በእጅጉ ይቆራኛል፡፡ የመንግሥት ዘርፉ ሰፊ የገንዘብ ፍላጎት በባንክ ሥርዓቱ፣ ግዙፍ የብድር ዕድገት በመፍጠርና በብሔራዊ ባንክ ከፍተኛ መጠን ያለው ቀጥተኛ ብድር አማካይነት ሲስተናገድ ቆይቷል፡፡ የቀድሞዎቹ ልማዶች ከቀጠሉ፣ በመጪዎቹ ዓመታት ሁኔታው መባባሱ አይቀሬ ነው፡፡ ለምን ቢሉ? የወደፊት የገንዘብ ፍላጎቶች የሚገቱ አይመስሉም፡፡

ይህን መሰል ግዙፍ ብድሮች ከሦስት ምንጮች ሊገኙ ይችላሉ፡፡ ከብሔራዊ ባንክ፣ ከንግድ ባንክና ከውጭ መንግሥታት የመጀመሪያው (በዋናነት ገንዘብ ያትማል) በእጅጉ የዋጋ ግሽበት የሚያስከትል ሲሆን፣ ሁለተኛው ለግል ዘርፉ ይውል የነበረን የባንክ ብድሮች ያሟጥጣል፡፡ ሦስተኛው ደግሞ አደገኛ ለሆነ የውጭ ዕዳ ክምችት ይዳርጋል፡፡ በአጭሩ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ከሚያስፈልገው የገንዘብ መጠንና እያሻቀበ ያለውን የዕዳ ምጣኔ መቀነስ እንዲሁም መቀልበስም ጭምር  ከሚኖረው አስፈላጊነት አንፃር፣ መንግሥት ከብድር ውጪ የሆነ ገንዘብ ይፈልጋል፡፡ ፕራይቬታይዜሽን በእርግጥም መሰል የዋጋ ግሽበትና ዕዳ የማያስከትል የገንዘብ አቅም ይፈጥራል፡፡ ከዚህ አንፃር በአንዳንዶች እንደሚቀነቀነው ዝግ ያለ ወይም ይበልጥ የተረጋጋ ስትራቴጂ መከተል ሳይስፈልግ፣ ለክፉ ጊዜ የተቀመጠው መፍትሔ በርካታ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ግቦችን መድረስ እንዳለበት መገንዘብ ይቻላል፡፡

በሁለተኛነት ፕራይቬታይዜሽን በበርካታ ቁልፍ የኢኮኖሚው ዘርፎች ውስጥ፣ የተዛነፉ የግልና የመንግሥት ምጣኔዎችን ሚዛናዊ ያደርጋል፡፡ ለመንግሥት ዘርፉ ከውጫዊ ምንጮች የገንዘብ አቅርቦት በማፍሰስ፣ ፕራይቬታይዜሽን ለዓመታት ያሽቆለቆለውንና የደነዘዘውን የግል ዘርፍ የብድር ምጣኔ ሊለውጥ ይችላል፡፡ ይበልጥ በስፋት ስንመለከተው፣ መንግሥት ቁልፍ በሆኑ የኢኮኖሚ ዘርፎች ውስጥ ያለውን ይዞታ እየለቀቀ ሲመጣ፣ የግል ኢንቨስትመንትና የግል ማኑፋክቸሪንግ ለመሳሰሉት ምጣኔዎች ጤናማ  ሚዛንን  ይፈጥራል፡፡ ይኼ ይበልጥ አስፈላጊ የሚሆነው አንዳንድ ከመንግሥት ጋር ትስስር ያላቸው አዳዲስ ተቋማት በኢኮኖሚው ውስጥ በመከሰታቸው  ወይም በልማድ ከሚታወቁባቸው ተግባሮቻቸው ባሻገር በጣም በመስፋታቸው ነው፡፡ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ)፣ የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ባቡር ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ንግድ መርከብና ሎጂስቲክ ድርጅት፣ የኢትዮጵያ እህል ንግድ ድርጅት (በአንድ ወቅት የአገር ውስጥ የጥራጥሬ ንግድ ድርጅት የነበረ ቢሆንም ራሱን ወደ ግዙፍ ቡና ኤክስፖርተርነት ለውጧል)፣ በመጨረሻም አዲስ ሸቀጣ ሸቀጦችን የሚያከፋፍል  የመንግሥት ዘርፍ፡፡

ለማጠቃለል የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ የሚያንቀሳቅሱ አንድ ሳይሆን ሁለት ጠንካራ ሞተሮች (የግልም የመንግሥትም) መኖራቸው ተፈላጊ ነው፡፡ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የሚደገፉ ቁልፍ ዘርፎችን፣ የውጭ ኢንቨስትመንት፣ ዕውቀትና ክህሎት እንዲሁም ብቃት በመሳብ ፕራይቬታይዝ ማድረግ፣ ይኼንን ለማሳካትም ጉልህ ድርሻ ሊኖረው ይችላል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ቀውሱን እያሾረው ለሚገኘው፣ የአገሪቱ  የውጭ ክፍያ ጉድለትም ፕራይቬታይዜሽን ፈውስ ይሆናል፡፡ ፕራይቬታይዜሽን በእርግጥም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚን ከደዌው የሚፈውስ፣ የክፉ ጊዜ ተዓምር ሊሆን ይችላል፡፡

ፕራይቬታይዜሽን በነቢብና በገቢር

ፕራይቬታይዜሽን በመንግሥት ባለቤትነት ሥር የሚገኙ ድርጅቶች፣ ወደ ገበያ መሪ ኢኮኖሚ ተዋናይነት የሚለወጡበት የተለመደ ሒደት ሆኗል፡፡ ለኢንዱስትሪው፣ ለሠራተኞቹና ለደንበኞቹ በግልጽ የሚታዩ ፍሬዎችን በማስገኘት፡፡ እስከ 1970ዎቹና 80ዎቹ የቅርብ ዓመታት ድረስ፣ ኢኮኖሚያቸው ባደገ እንደ ዩናይትድ ኪንግደም ባሉ አገሮች እንኳ መንግሥት የከሰል ኢንዱስትሪ፣ የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ፣ የኤሌክትሪክ ማመንጪያ፣ የጋዝ አቅርቦት፣ የባቡር ትራንስፖርት፣ የወደብ፣ የባህርና  የከባድ መኪና ትራንስፖርትን ጨምሮ የኢኮኖሚውን ሰፊ ይዞታዎች በባለቤትነት በመያዝ ይቆጣጠር ነበር፡፡ መንግሥት ከቴሌኮም ኢንዱስትሪው በተጨማሪ  የአውሮፕላንና የመርከብ ግንባታ፣ ብዙውን የመኪና ማምረቻ፣ የኖርዝ ሲ ነዳጅና ሌሎችንም በባለቤትነት ይዞ ነበር፡፡ የእነዚህ ኢንዱስትሪዎች አጠቃላይ አፈጻጸም በዝቅተኛ ምርታማነት፣ በከፍተኛ ወጪ፣ በውድ ዋጋ፣ በመጥፎ የሠራተኛ አሠሪ ግንኙነቶች፣ ብቃት በጎደለው የሀብት አጠቃቀምና አጥጋቢ ባልሆነ የደንበኞች አገልግሎት ነበር የሚገለጸው፡፡ እነዚህን ችግሮች የፈጠረው የሠራተኛ ኃይሉ ባህሪ አይደለም፡፡ ለዚህ ተጠያቂው የመንግሥት የንብረት ባለቤትነት ያለው ተፈጥሮ ነው፡፡ ለምን ቢሉ? መንግሥት የኢንዱስትሪ ባለቤት ሲሆን ደካማ አፈጻጸም ወይም ውጤት ማስመዝገቡ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነውና፡፡

የገበያ ዲሲፕሊን አለመኖር፣ በመንግሥት ባለቤትነት የተያዙ ኢንዱስትሪዎች፣ ደካማ አፈጻጸም ያለ ተጠያቂነት እንዲያስመዝገቡ ይፈቅድላቸዋል፡፡ ቁልጭ ያለው እውነታ፣ በመንግሥት ባለቤትነት የተያዙ ኢንዱስትሪዎች ለመኖር  ስኬታማ መሆን  አያስፈልጋቸውም፡፡ ይኼን ደግሞ ሠራተኞቹ ሁሉ ያውቁታል፡፡ የአፈጻጸም ተጠያቂነት አለመኖር ትጋትን  የሚገድል  ሲሆን፣ የራስ ተነሳሽነትም ቦታ የለውም፡፡ በሌላ በኩል ተጠያቂነት፣ የግል ኢንዱስትሪውን ለፈጠራ፣ ምርታማነትን ለማሳደግና ብቃትን ለማሻሻል ያነቃቃል፡፡ ግራም ነፈሰ ቀኝ፣ የመንግሥትና የግል የኢንዱስትሪ ባለቤትነትን አስመልክቶ የሚደረገው ክርክር ያለቀለት ጉዳይ ነው፡፡ የግል የንብረት ባለቤትነት አሸንፏል፣  ምክንያቱም የሚሠራ መሆኑን አሳይቷል፡፡ የመንግሥት ንብረት ባለቤትነት ግን አይሠራም፡፡

ይህም ሆኖ ግን ትላልቅ ኢንዱስትሪዎችን ከመንግሥት ይዞታነት ወደ ግል ዘርፍ ለማዛወር የሚያስቡ መንግሥታት፣ ለብሔራዊ ጥቅም እንደ አሳሳቢ ጉዳይ የሚገለጹ በርካታ የተለዩ ሥጋቶችን ይጋፈጣሉ፡፡ የፕራይቬታይዜሽን ተቀናቃኞች ስለውጭ ኃይል ጣልቃ ገብነትና የውጭ ቁጥጥር፣ ስለገቢና መሠረታዊ አቅርቦቶች መጥፋት እንዲሁም ትርፋማ ያልሆኑ፣ ነገር ግን ለኅብረተሰቡ አስፈላጊ ስለሆኑ አገልግሎቶች መቀጠል  ሥጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡ ዝርዝሩ ማብቂያ የለውም፡፡ አብዛኞቹ የተነሱት ደግሞ፣ ኃላፊነት የሚሰማው መንግሥት የሚያሳስቡት ተገቢ ጉዳዮች  ናቸው፡፡ እነዚህን ሥጋቶች ለፕራይቬታይዜሽን እንደ እንቅፋት የሚያነሱ ወገኖች፣ ትልቁ ስህተታቸው የመንግሥት የንብረት ባለቤትነትን፣ ብቸኛው መፍትሔ  አድርገው ማሰባቸው ነው፡፡ መንግሥት የትኛውንም ኢንዱስትሪ በባለቤትነት ሳይቆጣጠር፣ ሙሉ በሙሉ ሊጠብቅና ሊከላከል ይችላል፡፡ በፕራይቬታይዜሽን የሕግ ማዕቀፍ ወይም ተራ የመንግሥት ሥልጣኖችን በመጠቀም ብቻ፡፡ ገቢ የታወቀ ምሳሌ ነው፡፡ አገር ሁሉ ተጠቃሚ እንዲሆን መንግሥት የግድ ስኬታማ የሆነ ኢንዱስትሪ በባለቤትነት  ሊኖረው አይገባም፡፡ ከትርፍ ላይ ግብር መሰብሰብ፣ የበለጠ  ውጤታማና ጠቃሚ ነው፡፡ በዚያ ላይ መንግሥት ኢንዱስትሪውን በባለቤትነት ሲይዘው፣ ትርፍ የሚባል ነገር ደብዛው ሊጠፋ ይችላል፡፡ አንድን የተወሰነ ኢንዱስትሪ በባለቤትነት መያዝ ተገቢ አይደለም ብሎ በትክክል የወሰነ መንግሥት፣ በምንም ዓይነት መንገድ እንደ ሕዝብ ጥቅም አስከባሪ ወገን፣ ኃላፊነቶቹን ዘንግቷል ማለት አይደለም፡፡ መንግሥት ነፃ ማኅበረሰቦች መሥራት የሚችሉበትን ሕግ የማውጣትና የማስፈጸም ኃላፊነት ነው ያለበት፡፡  የመንግሥት ትክክለኛው ሚናም ይኼ እንጂ የንብረት ባለቤትነት አይደለም፡፡

ተገቢ ተጨማሪ ማሻሻያዎች

አገራዊና ዓለም አቀፍ ቁጠባን ለማሰባሰብ፣ የፋይናንስ መሠረተ ልማትን መገንባት፣

 • የአክሲዮን ገበያ
 • የንግድ ተቋም ካፒታል
 • ፕራይቬት ኢኩቲ
 • የኢንቨስትመንት ባንኮች
 • የንግድ ባንክ የውጭ ባንኮችን መፍቀድና የብሔራዊ ባንክን የአቅም    ውስንነቶች  መፍታት
 • ብሔራዊ የኤሌክትሮኒክ ክፍያ ሥርዓት መፍጠር
 • የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪውን ማዘመን የውጭ የኢንሹራንስ ኩባንያዎችን መፍቀድ

የዳያስፖራና “ሌሎች” የውጭ ሐዋላዎችንና የኢንቨስትመንት ፍሰት ለማሰባሰብ የሚያግዙ ስትራቴጂዎችን  መቅረፅ፣

 • ከላይ በተዘረዘረው መሠረት፣ የውጭ ምንዛሪ ተመን አስተዳደር በገበያው እንዲመራ በማድረግ፣ የጥቁር ገበያ የውጭ ምንዛሪ ተመን ልዩነቶችን ማስወገድ
 • ቀጥተኛ የሞባይል/ኤሌክትሮኒክ የገንዘብ ዝውውርን ዕውን ማድረግ
 • የዳያስፖራ የኢንቨስትመንት መርሐ ግብርን መቅረፅ
 • የውጭ የፋይናንስ/በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ ኢንቨስተሮችን የተሻለ ለማነቃነቅ ስትራቴጂዎች መቅረፅ
 • የአክሲዮን ገበያ መመሥረት
 • ነፃ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር መክፈት
 • የኢንቨስትመንት ባንክ አገልግሎቶች መጀመር
 • ከልማት አጋሮች የተሻለ የገንዘብ ድጋፍ ለማሰባሰብ የሚያግዙ ስትራቴጂዎች መቅረጽ፣
 • የምንዛሪ ተመን ፖሊሲን በተመለከተ ከፍተኛ የቅድሚያ ትኩረት የተሰጠው  የፖሊሲ ለውጦች መተግበር፡፡ የኢትዮጵያ የአንጡራ ሀብት ልኬትና የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር በገበያው እንዲመራ ማድረግ፣ በመጠባበቂያ ገንዘብ መልክ፣ ብዙ ቢሊዮን ዶላሮች ከአይኤምኤፍና ከሌሎች የልማት አጋሮች ያስገኛል፡፡
 • የግል ዘርፍ የልማት ፖሊሲዎችና ፕሮግራሞችን ቅድምያ መስጠትና ማነሳሳት፣ ከፍተኛ መጠን ያለው ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ ሊያስገኝ ይችላል፡፡
 • ጉልህ የውጭ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት ለሚያግዙ ስትራቴጂዎች የቅድሚያ ትኩረት መስጠት፡፡

የኢትዮጵያ አሥሩ ቀዳሚ ከውጭ የገቡ ምርቶች

እ.ኤ.አ በ2017 የኢትዮጵያ የውጭ ምርት ግዢ 14.7 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን፣ ከ2013 ወዲህ በ34.1 በመቶ ጨምሯል፡፡ ከ2016 እስከ 2017 ግን በ10.5 በመቶ ወርዷል፡፡ ከዚህ በታች የቀረቡት የምርት ዘርፎች፣ ኢትዮጵያ በ2017 ከፈጸመችው የውጭ ምርት ግዢዎች፣ ከፍተኛውን የዶላር ዋጋ የሚወክል ነው፡፡ እያንዳንዱ የምርት ዘርፍ፣ ከአጠቃላይ የኢትዮጵያ የውጭ ንግድ ገቢዎች  አንፃር በመቶኛ ያለውም ድርሻ (በመቶ) ተጠቁሟል፡፡

 1. ኮምፒዩተሮችን ጨምሮ ማሽነሪዎች 2.7 ቢሊዮን ዶላር (ከአጠቃላይ የውጭ ምርቶች 18.1 በመቶ)
 2. ተሽከርካሪዎች፣ 1.4 ቢሊዮን ዶላር (9.6 በመቶ)
 3. የኤሌክትሪክ ማሽነሪ፣ መሣሪያዎች 1.3 ቢሊዮን ዶላር (8.8 በመቶ)
 4. ነዳጅን ጨምሮ የማዕድን ፊዩል 1.2 ቢሊዮን ዶላር (8.4 በመቶ)
 5. አይረን፣ ስቲል 799.3 ሚሊዮን ዶላር (5.4 በመቶ)
 6. የጥራጥሬ እህል 639.9 ሚሊዮን ዶላር (4.4 በመቶ)
 7. ፕላስቲክ፣ የፕላስቲክ ቁሳቁሶች 634.2 ሚሊዮን ዶላር (4.3 በመቶ)
 8. የአይረን ወይም ስቲል ቁሳቁሶች 569.5 ሚሊዮን ዶላር (3.9 በመቶ)
 9. የእንስሳ/አትክልት ስቦች፣ ዘይት፣ ሰም 539.9 ሚሊዮን ዶላር (3.7 በመቶ)
 10. የመድኃኒት ምርቶች 536.1 ሚሊዮን ዶላር (3.6 በመቶ)

የኢትዮጵያ አሥሩ ቀዳሚ ከውጭ የገቡ ምርቶች አገሪቱ ከሌሎች አገሮች ከምትሸምታቸው አጠቃላይ የምርት መጠን ውስጥ ከሁለት ሦስተኛ በላይ (70.3 በመቶ) ይወክላል፡፡

ማጠቃለያ

በድምር ከላይ በተገለጸው የፖሊሲዎችና የዕርምጃዎች ማዕቀፍ በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ከ50 ቢሊዮን ዶላር ያላነሰና ከዚያም የሚበልጥ የውጭ ምንዛሪ ገቢና ቁጠባን በዕውን ማሳካት ይቻላል። የፖሊሲዎቹና የዕርምጃዎቹ አስፈላጊነት ለውጭ ምንዛሪ ግኝት አስተማማኝ ዘዴ ከመሆናቸውም ሌላ፣ አገሪቱን ለፋይናንስ ቀውስ የዳረጉ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ልምሻዎችንና የመዛባት ምስቅልቅሎችን መልክ ለማስያዝ የሚያገለግሉ መሆናቸውም ነው። ይህ እውነት ሆኖ ሳለ፣ የፖሊሲ ማሻሻያዎቹ ማዕቀፍ ላይ ላዩ ሲታይ ከእስካሁኑ የፖሊሲዎች ነባር አቅጣጫ ወደ ሊበራል ያፈነገጠና ከልክ በላይ የተለጠጠ፣ የለውጥ ማዕቀፍ ሊመስል ቢችልም አይደለም። የፖሊሲ ማሻሻያዎችን አጣጥሞና አሰናስሎ የያዘው ማዕቀፍ ነባሩን የሚያሳድግ እንጂ፣ ከልማታዊ መንግሥት ሞዴል ወይም ከቢግ ፑሽ መሠረታዊ የንድፈ ሐሳብ ነባር ንጣፍና ማዕቀፍ ያፈነገጠ አይደለም። ማሻሻያ ሐሳቦቹ፣ በነባሩ የንድፈ ሐሳብ ውስጥ የመንግሥት ሚናና የገበያ ሥርዓት አቅሞች ሚና ወሰኖችን በተመለከተ በጊዜ ሒደት እየነጠሩ፣ በተግባራዊ ተሞክሮ እየጠሩ ከመጡት ዕድገቶች ጋር የተጣጣሙ ናቸው።

ኢትዮጵያ እንደ ማዕበል የተጋረጠባትን የኢኮኖሚ ቀውስ ተቋቁማ ለመሻገር፣ ይዋል ይደር ሳትል የተሻሉትና የተሻሻሉትን በማመዛዘን፣ የሚበጇትን የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በአፋጣኝ መርጣ መያዝና ሥራ ላይ ማዋል ይገባታል። ከመንግሥትና ከሌሎችም በሚቀርቡ አኃዛዊ የትንበያ ግምቶች፣ ኢኮኖሚው ከስድስት በመቶ እስከ ስምንት በመቶ ያህል የማይናቅ ዕድገት እንደሚያስመዘግብ እየሰማን፣ ባልተጨበጠ ተስፋ ተዘናግተን፣ ለማያዛልቅ የእፎይታ ስሜት ምርኮኛ ሆነናል። ወቅቱ ከታሪክ አንፃር የአገሪቱ ዕጣ ፈንታ የሚለይበት፣ የመነሳትና የመፈጥፈጥ አፋፍ ላይ በቋፍ የደረሰ ታሪካዊ ወቅት እንደመሆኑ በአርቆ አስተዋይነት፣ በፍጥነትና በብልኃት ዕርምጃ ከመውሰድ መዘናጋት ታሪካዊ ውድቀት ይሆናል። ውሎ አዳራችንን ሁሉ በሰጠነው የፖለቲካ ቀውስ፣ ላለፉት ሦስት ዓመታት እንደተጠመድነው፣ በዚያው ኢኮኖሚውን ለመዘንጋት መሞከር ከድጥ ወደ ማጥ የመግባት መዘዝ ራሳችን ባመጣነው ናዳ የመቀበር ዕዳ ይገጥመናል።

ቁጥሮቹ ይናገራሉ

ከትናንቱ ጉዞና ከዛሬው ሁኔታ ተከትለው የሚመጡ የነገ አማራጮችን፣ ከነውጤታቸውና ከነመዘዛቸው በቁጥር አስልቶ በሰንጠረዥ ማሰናዳት፣ የነጠሩ ንፅፅሮችን የሚያጎላና ዙሪያ ገባውንም የሚያስቃኝ የጠራ ምስል ለመጨበጥ ይረዳል። በመስቀለኛው መንገድ መንታ ጎዳናዎች፣ በሁለት የኢኮኖሚ ጉዞ አማራጮች መሀል ላይ ቆመን፣ በየትኛው በኩል የት እንደምንደርስና በየትኛውስ ምን እንደሚገጥመን ከወዲሁ  አማትረን ለመመልከት፣ መጪው ጊዜ ምን እንደሚመስል አሻግረን ለማየት፣ የማክሮ ኢኮኖሚ ቁልፍ መለኪያዎችን በየፈርጃቸው የሚዘረዝር የትንበያ ሠንጠረዥ ቀርቧል። የማክሮ ኢኮኖሚ ትንበያ፣ ሳይንስና ሥሌት የመሆኑ ያህል፣ ጥበብና ክህሎትም እንደሆነ እስካልዘነጋን ድረስ፣ “የሺሕ ቃላት ትንታኔን በአንድ ምስል የማስጨበጥ” ፋይዳ አለው። ተሰልቶ በሰንጠረዥ የቀረበው የትንበያ መረጃ፣ የወቅቱን ችግሮች ፈልፍሎ በሽታውን ከነገጽታዎቹ ለማየት፣ እንዲሁም የፖሊሲ መድኃኒቶቹን አጥርቶ በቅጡ ለመጨበጥ ያግዛሉ። የሥሌት ሠንጠረዡ መሠረታዊ መነሻዎች፣ በዚህ ጸሐፊ የተሰናዱ እንጂ የተቋም ወይም የቡድን አቋምን የሚወክሉ አይደሉም።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከአምስት ዓመታት በኋላ ምን መልክ እንደሚኖረው ለመረዳት፣ “ባለ ማሻሻያ” እና “ያለ ማሻሻያ” በሚሉ ሁለት የፖሊሲ አማራጮች ሥር፣ የኢኮኖሚው ቁልፍ መለኪያዎች በረድፍ ተዘርዝረዋል። ሁለቱን አማራጮች ለማነፃፀርም፣ በአገሪቱ ቁልፍ ኢኮኖሚ መሊያዎች ላይ የሚጠበቁ ለውጦች በቁጥር ሠፍረዋል። ሁለቱ የፖሊሲ አማራጮች የሚያስገኙልንና የሚያስከትሉብን የውጤት ልዩነት፣ በአኃዛዊ ሥሌት ወለል ብሎ ይታያል። የአገር ውስጥ የምርት ዕድገትን በጥቅል ስንመለከት፣ “ያለ ማሻሻያ” በተሰኘው የፖሊሲ አማራጭም እንኳ፣ አራት በመቶ ገደማ ዕድገት እንደሚመዘገብ ከትንበያው እንረዳለን። በእርግጥም ይህ የዕድገት ትንበያ አነሰ በዛ የሚባል ሳይሆን፣ በእስከ ዛሬ አመጣጥ ያለፖሊሲ ማሻሻያ ሊገኝ የሚችል ውጤት ነው ማለት ይቻላል። ይህ የዕድገት ትንበያ እውን እንዲሆን የሚጠበቀው ግን፣ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን በሚጨምርና ፍጆታን በሚቀንስ አንዳች ዘዴ፣ ጠንቀኛው የውጭ ምንዛሪ ቀውስ ቀስ በቀስ መልክ ይይዛል በሚል ተስፋ ላይ በመመርኮዝ እንደሆነ መረሳት የለበትም። በመላ ያልተገታ የውጭ ምንዛሪ ቀውስ፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ ድርቅና ሌሎች ጋሬጣዎች፣ አልያም ከአገር ውጭ የሚመጡ ችግሮች፣ የኢኮኖሚ ዕድገትን አሰናክለው ቁልቁል ከዜሮ በታች ሊያወርዱት ይችላሉ። ባለ በሌለ ኃይል እመርታ ማምጣት (ቢግ ፑሽ) የሚል የኢትዮጵያ ዘመቻ፣ በመጀመሪያዎቹ ዓመታት እንደገድ በአመቺ ሁኔታዎች ቢታጀብም፣ ኢኮኖሚው ወደፊትም ገድ ይቀናዋል ማለት ስላልሆነ፣ መሰናክሎች እንደሚገጥሙት አስቀድሞ መገመት ተገቢ ነው።

በተለይ በተለይ፣ የተተነበየውን ጥቅል ዕድገት አፍረጥርጦ ምንነቱን ከነምንጩ በትክክል መገንዘብ ያስፈልጋል። በመንግሥት ፊታውራሪነትና በብድር ኃይል፣ ለ15 ዓመታት እንደልብ በገፍ በተካሄደው ኢንቨስትመንት አማካይነት በኢኮኖሚ መዋቅር፣ በማምረቻ አቅምና በምርታማነት ላይ እየመጣ ያለው ለውጥ ወደፊትም ፍሬ የሚሰጥ አንድ የዕድገት ምንጭ ነው። የአገሪቱ ሕዝብ የዕድሜ ስብጥርም እንዳለፉት ዓመታት፣ የኢኮኖሚ ዕድገትን የሚያራምድ ቁልፍ ባለድርሻ ሆኖ ይቀጥላል። ሁሉንም መስክ የሚያዳርሱ እነዚህ የዕድገት ምንጮች በየትኛውም የፖሊሲ አማራጭ፣ ለኢኮኖሚው ኃይል ሰጪ ብርታት ይሆኑለታል። ታዲያ ያለማሻሻያ በነባሩ ፖሊሲ የመጓዝ አማራጭን ብንከተል እንኳ፣ መካከለኛ የኢኮኖሚ ዕድገት የሚመዘገብ ከሆነ፣ በዚህ ጽሑፍ የተገለፀው ያህል ተጋንኖና ገዝፎ፣ እንዴት እንደ አንገብጋቢ አደጋ ይቆጠራል የሚል ጥያቄ ይነሳ ይሆናል። እንዲያውም ፈር የለቀቀ ያለቅጥ የተጋነነ ሥጋት ሊሆንብን ይችላል። መጪዎቹን ዓመታት በአራት በመቶ ዕድገት መጓዝ የሚችል ኢኮኖሚ፣ ከቶ በጨረፍታ ቀውስ የጎበኘው ኢኮኖሚ መስሎ ባይታይም፣ አሁን ባለው ቅርፁና አወቃቀሩ ግን እንዲህ ዓይነቱ ዕድገት፣ ውድ ዋጋ የምንከፍልበት ከባድ ኪሳራ ጎትቶ ያመጣብናል፡፡ ወደ “መካከለኛ ገቢ አገሮች” ተርታ የመሸጋገር አገራዊ ህልማችንንም በአጭር ያስቀርብናል።  

በወጉ ያልጠና የውስጥ ለጋነቱንና ስስነቱን ሸፋፍኖ፣ ላይ ላዩን አሳምሮ ያጎፈረ ዕድገት፣ ወደፊት መገስገስና እመር ብሎ መሻገር ተስኖት፣ የዝቅተኛ ገቢ ወጥመድ ላይ ይጥለናል። ክፋቱ ደግሞ ወጥመዱ በተንሰራፋ መዋቅር መፈናፈኛ የማያገኙለት፣ በአጭር ጊዜ የማይገላገሉት፣ እንደዋዛ የማያመልጡት አጣብቂኝ መሆኑ ነው። የሚዘመርለት ጥቅል የኢኮኖሚ ዕድገት፣ አደገኛ የጉድ መዓት ከሥር ቀብሮ፣ የውስጡን የሚደብቅ የጎፈር ክዳን ነው። በጥቅል የተጠቀሰውን የኢኮኖሚ ዕድገት ዘርግተን፣ የተሸፈነውን ገላልጠን፣ የተከደነውን ከፋፍተን በየዘርፉ የሚጠበቀውን የዕድገት መጠን በዝርዝር ውስጡን ስንፈትሽ አደጋው ፈጥጦ ይታየናል። ያለማሻሻያ በነባሩ የፖሊሲ አማራጭ ከተጓዝን፣ በግብርና ዘርፍ እ.ኤ.አ በ2016 የተመዘገበው ስምንት በመቶ ዕድገት፣ በ2022 ቁልቁል ወደ 4.5 በመቶ እንደሚወርድ ይጠበቃል። 20 በመቶ ዕድገት በ2015 የተመዘገበበት የኢንዱስትሪ ዘርፍም፣ በ2022 ክፉኛ ተፍረክርኮ ወደ አምስት በመቶ ያሽቆለቁላል። የአገልግሎት ዘርፍ የ11 በመቶ ዕድገትም ተመናምኖ ወደ ሦስት በመቶ ይሟሽሻል። አደጋው ቁልጭ ብሎ የሚታይ ነው። የኢንዱስትሪና የአገልግሎት ዘርፎች የሚገጥማቸው ውድቀት ምንኛ ከባድ እንደሆነ በግልጽ እያዩ፣ ማምለጫ መላ ሳይዘይዱ መቀጠል፣ የሚንተከተክ እሳተ ጎመራ ላይ ተቀምጦ እስኪፈነዳ ድረስ እንደመጠበቅ ነው። በሚሊዮኖች እየገዘፈ ለምናየው የወጣት ጎርፍና እየበዛ ላለው የከተማ ነዋሪ፣ ብዙ የሥራ ዕድል በፍጥነት ሊፈጥሩ የሚገባቸው ዘርፎች እኮ እነዚሁ የኢንዱስትሪና የአገልግሎት ዘርፎች ናቸው።

ዋና የሥራ ዕድል ምንጭ የዕድገት መተማመኛ የመዋቅር ሽግግር አለኝታ እንዲሆኑ ተስፋ የተጣለባቸው የኢንዱስትሪና የአገልግሎት ዘርፎች፣ ለመፍረክረክ ክፉኛ ሲብረከሩ እናያለን። በአንድ በኩል የተንሰራፋ ሥራ አጥነት፣ የዋጋ ንረት፣ የምግብና የዕለት ኑሮ ሸቀጦች እጥረት በከተሞች ላይ እየከበደ በሌላ በኩልም፣ የኑሮ ተስፋ የማጣትና የመገለል ስሜት የሚያድርበት ወጣት እየበረከተ፣ ያለመፍትሔ የሚከማቸው ተደራራቢ ችግር፣ በቅርብ ዓመታት እንደታየው አገርን የሚያናጋ የቀውስና የሁከት ዋና ማጠንጠኛ ይሆናል። የፖለቲካ የአመራር ለውጥ ለመንግሥት የተወሰነ ፋታ የሚያስገኝለት ቢሆንም፣ ለእፎይታ የሚተርፍ ጊዜ ይሆንለታል ማለት አይደለም። የገጠሩን ነዋሪ ብናስርብ ድምፅ ሳያሰማ ማሳው ላይ እንዳሸለበ ሕይወቱ ታልፋለች። ከተሞችን ብናስርብ፣ አገሬው ይናወጣል፣ በአመፅና በቃጠሎ ያወድማል። ይህንን ደግሞ አይተነዋል፣ መራራነቱንም ቀምሰነዋል። ነገር ግን መራራው የመከራ ጊዜ በዚሁ ላይመለስ ያለፈልን፣ የባሰ ላያመጣብን የተገዘተ አይምሰላችሁ። ከጥፋት የሚያድን የአቅጣጫ ለውጥ በእውን ሳይመጣ እንዳይቀር ደግሞም ሳይሳለጥ እንዳይረፍድበት ካልተደረገ በቀር፣ ለከፋ አደጋ ይዳርገናል። አደጋውን ለመገንዘብ በርካታ አገሮች የተናወጡበት “የዓረብ ፀደይ” አመፅንና የቅርብ ጊዜውን የዮርዳኖስ ሁከት ማስተዋል በቂ ነው።

ኤክስፖርት፣ የውጭ ሐዋላ፣ የውጭ ኢንቨስትመንት፣ መጠባበቂያ የውጭ ምንዛሪና ሌሎች ቁልፍ መለኪያዎችንም ስንቃኝ በሁለቱ አማራጮች የምናገኘው ውጤትና የሚገጥመን መዘዝ፣ የመኖር አለመኖር ያህል ከመራራቁ የተነሳ ያስደነግጣል። በሥሌት ሰንጠረዡ ውስጥ ባይካተትም፣ የስኬትና የውድቀት፣ የመኖር አለመኖር አማራጭ ጎዳናዎችን ለይተን እንድናውቅ አፍ አውጥቶ የሚነግረን ሌላው መለኪያ፣ በመደበኛው የውጭ ምንዛሪ ተመንና በጥቁር ገበያ መካከል ያለው እላፊ የዋጋ ልዩነት ነው።  ከአምስት በመቶ እስከ አሥር በመቶ አካባቢ ሳይርቅ ለበርካታ ዓመታት የቆየው እላፊ የምንዛሪ ዋጋ ልዩነት ወደ 25 በመቶ 30 በመቶ አሻቅቦ፣ ፍላጎት ከአቅርቦት ይበልጥ መራራቁንና የውጭ ምንዛሪ እጥረት መባባሱን ያሳብቃል። ያለማሻሻያ የመቀጠል አማራጭን ከተከተልን የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ወደ ዜሮ ስለሚወርድ፣ የምንዛሪ ዋጋ ልዩነት ይባስኑ እየጋለበ፣ ጥቁር ገበያውም እየተጧጧፈ፣ ኢኮኖሚውን የሚያዛቡና የሚያናጉ የመዘዝ አጀቦቹን ያወርድብናል። የሸቀጦች የዋጋ ንረት፣ በአገር ደረጃ በጥቅል ሲታይ ከባድ ባይመስልም፣ በከተሞች ግን፣ የዋጋ ንረቱ ከጣሪያ በላይ እያሻቀበ፣ አብዛኛውን ወጣትና ደሃ የከተማ ነዋሪ ክፉኛ እያራቆተ ነው። በአጭሩ ከግራም ከቀኝም የሚያወላዳ አንዳች ጭላንጭል አይታይም።

ኢኮኖሚክስ ውስጥ የማናጣው አንዱ ቁምነገር፣ የቀድሞ ፖሊሲዎችና ውሳኔዎች ዛሬ ብቻ ሳይሆን ውሎ አድሮ የሚታይ፣ ዘንድሮ ብቻ ሳይሆን ለከርሞም የሚመጣ፣ የነገ ውጤት ወይም መዘዝ የሚፈጥሩ መሆናቸውን ነው። የቀድሞ ፖሊሲዎችና ኢንቨስትመንቶች ለበርካታ ዓመታት ከዚያም አልፈው ከአሥርና ከሃያ ዓመት በላይ የሚዘልቁ፣ በቀላሉ የማይነጥፉ ውጤቶችን ወይም በዋዛ የማይለቁ መዘዞችን ሊፈጥሩ ይችላሉ። ባለፉት 15 ዓመታት በስፋት የተካሄዱ ቁሳዊና ማኅበራዊ የመሠረተ ልማት ኢንቨስትመንቶች ለአገሪቱ የሚያስገኙላት ፍሬ ለመጪዎቹ ዓመታትም ይቀጥላል። ለመንገድ፣ ለኤሌክትሪክ ኃይል፣ ለጤናና ለትምህርት የዋለው ኢንቨስትመንትም ለተወሰኑ ዓመታት የሠራተኛና የካፒታል ምርታማነትን በማሻሻል የዕድገት ፍሬ ይሰጣል። ከግብርና ወደ አገልግሎትና ወደ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚያራምድ የመዋቅር ሽግሽግም፣ ለዘለቄታው ፋይዳ ያለው የምርታማነት ዕድገትን ያስገኛል። ከሁሉም በላይ ደግሞ፣ ለበርካታ ዓመታት ብዙ ኢንቨስትመንት የፈሰሰበት የግብርና ዘርፍ ምርታማነትን በማሳደግ የፍሬ በረከት መስጠቱን ይቀጥላል።  

የእስከ ዛሬ ፖሊሲዎች፣ ኢትዮጵያን ከድህነት ወጥመድ ለማውጣት፣ ጠፍሮ ከያዛት ገበያ አጥ የእርሻ ኢኮኖሚ በማላቀቅ ሻል ወዳለ ምርታማነት ለማነቃነቅ፣ የአነስተኛ ማሳ እርሻም ወደ ገበያ ቀመስ እርሻ ለማሻሻል፣ የአገልግሎት ዘርፍ ጎልቶ ወደሚታይበት የከተማ ኢኮኖሚ ለማራመድ ችለዋልና፣ ስኬታማ የመጀመሪያ ዕርምጃ ናቸው ማለት ይቻላል። “የመካከለኛ ገቢ አገር” የመሆን የሩቅ ህልምንና ረዥሙን የልማት ጉዞ፣ በአንድ ስንዝር የሚያስጠጋ፣ የመጀመሪያው አንድ ዕርምጃ ነው። ይሁን እንጂ፣ ብዙ የተደከመበት የአምራችና የኢንዱስትሪ ዘርፍ የረባ ውጤት ሳያስገኝ፣ ዕድገትና የምርታማነት ለውጥ ርቆት፣ ለመዋቅር ሽግግር ሳይበቃ መቅረቱ፣ ስትራቴጂዎችንና በፖሊሲዎን ፈትሾ መከለስ እንደሚያስፈልግ ያስገነዝባል። ለዘለቄታው የመዋቅር ሽግግርን የሚያሳልጥ ዋነኛ የዕድገት ሞተር ይሆናል የተባለው አምራች ዘርፍ ጨርሶ አልነሳ ብሏል። ወይ ብልሽቱን መጠገን አልያም ሌላ ሞተር ፈልገን ማስነሳት አለብን።

አገሮች በኢኮኖሚ ሲያድጉና ሲመነደጉ አለኝታ የሚሉት የተፈጥሮ ፀጋቸው፣ የመዋቅር ጥንቅራቸውና መወዳደሪያ የኢኮኖሚ አቅማቸው ይቀየራል። ከዚህ የለውጥ ሒደት ጎን ለጎን፣ የዕድገት ጉዞው ሳይቋረጥ እንዲራመድና ከአንድ የልማት እርካብ ከፍ ወዳለ እርካብ እየተሻገሩ እንዲጓዙ ከተፈለገ፣ የልማት ስትራቴጂና ፖሊሲዎቻቸውም አብሮ ማደግና መዳበር አለባቸው፡፡ ለሁሉም የልማት ደረጃዎች የሚሠራ አንድ የኢኮኖሚ ስትራቴጂ የትም የለም። በዕድገት ጉዞ ከሚቀየሩት የኢኮኖሚ አለኝታዎችና መልካም አማራጮች ጋር፣ በተገቢው መንገድ ስትራቴጂዎችና ፖሊሲዎችም እየተስተካከሉ መሻሻል አለባቸው። የኢኮኖሚ ስትራቴጂ ቆሞ ቀር ሳይሆን፣ አዳጊና መስተጋብራዊ ነው። የግብዓት አለኝታ አዝማሚያንና የመዋቅራዊ ለውጥን አስቀድሞ የማገናዘብ ብልሃትና የሥርዓት ማስተካከያ ዝግጁነት ያስፈልገዋል።

በኢትዮጵያ ዓውድ ይኼ ሁሉ ምን ማለት ነው?

የቢግ ፑሽ/ልማታዊ መንግሥት ስትራቴጂ በልማት ሒደት መጀመሪያ ላይ ሁሉም ኢኮኖሚዎች ያለፉበት ትክክለኛው ስትራቴጂ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የልማታዊ መንግሥት ስትራቴጂን በመተግበር በልማት ሒደቱ፣ የመጀመሪያውን ዕርምጃ ስኬታማ በሆነ መንገድ ወስዳለች፡፡ ኢኮኖሚውን ገፍቶ ማስነሳትን በማሳካት ረገድ  የመንግሥት ሚና እጅግ ወሳኝና አስፈላጊ ነው፡፡ አንዴ ገፍቶ ማስነሳቱ ዕውን ከተደረገ በኋላ የዕድገትና ልማት ለውጥ በፍጥነት ይገሰግሳል፡፡ ወደ መካከለኛ ገቢ ደረጃና ከዚያም ባሻገር የሚደረግ ቀጣይ ግስጋሴ፣ የዕድገት ዋነኛ ሞተሮችን መለወጥና ትክክለኛ  የአዲስ ኢኮኖሚ ተቋማት፣ ሥርዓቶችና መሠረተ ልማቶች ግንባታን ይጠይቃል፡፡ አሁን ያለነው እዚህ ላይ ነው፡፡

መንግሥት እጁን መሰብሰብና የገበያ ኃይሎች፣ የኢኮኖሚውን የሀብት ፍሰት  በመምራትና በመመደብ ረገድ የመሪነቱን ሚና እንዲወስዱ ዕድል መስጠት ይገባዋል፡፡ ኢኮኖሚው አንድ ጊዜ የተወሰነ የዕድገትና የእርስ በርስ ትስስር ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ፣ የትኛውም መንግሥት ይኼን የማድረግ አቅም የለውም፡፡ ተገቢ ማሻሻያዎቹ  የማይተገበሩ ከሆነ፣ በኢኮኖሚው ውስጥ የተፈጠሩት ማነቆዎች፣ መዛባቶችና መዛነፎች የማያፈናፍኑ ይሆናሉ፡፡ ኢኮኖሚው ከቀድሞ ግዙፍ ኢንቨስትመንቶች ፍሬ በሚገኝ ድጋፍ፣ ለተወሰነ ጊዜ ህልውናውን ሊያቆይ  ይችላል፡፡ አንዳች የዕድገት ከፍታን ግን አይቀዳጅም፡፡ የአሁኖቹ ዘመን ያለፈባቸው ፖሊሲዎች ሳይሻሻሉ መቀጠላቸው፣ ከቀድሞ ኢንቨስትመንቶች ኢምንት ፍሬዎች ጋር ተዳምረው ቀስ በቀስ ዕድገትን ይገቱታል፡፡

ተገቢ ማሻሻያዎች ኢኮኖሚው በዚህ ወቅት ከአንዱ የልማት እርካብ ወደ ቀጣዩ ከሚሻገርበት ዕድገትና ለውጥ የተለዩ ባህርያት ውስጥ በተጣጣመ መልኩ መተግበር አለባቸው፡፡ ይኼ ደግሞ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የመዋቅር ጥንቅርን ለያይተን መቃኘት ይጠይቃል፡፡ ማለትም የግብዓት አለኝታዎቹንና አንፃራዊ  አቅሞቹን፡፡ ኢኮኖሚው እያደገ፣ እየዳበረና ይበልጥ እየተሳሰረ ሲመጣ የልማት ስትራቴጂውም እንደዚያው ማደግና  መሻሻል ይገባዋል፡፡  አዳጊና መስተጋብራዊ  የኢኮኖሚ አስተሳሰብና ዕቅድ፣ ለሁሉም ኢኮኖሚዎች በእያንዳንዱ የዕድገት ደረጃ የሚፈለግ መሠረታዊ ጉዳይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የልማት ስትራቴጂዎችና ፖሊሲዎች፣ አገሪቱን እያጥለቀለቁ ከሚገኙት ሜጋ ፕሮጀክቶች ወደ ኋላ ቀርተዋል፡፡ የሚገነፍል  የሕዝብ ቁጥር ዕድገት፣ መጠነ ሰፊ  የሥነ ሕዝብ ለውጥና ፈጣን የከተማ መስፋፋት፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ኃይል ናቸው፡፡ እነዚህ ሜጋ ፕሮጀክቶች መልካም አጋጣሚም ሆነ  ክፉ ሥጋት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የኢትዮጵያ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ላይ ተማምኖ፣ በአምራች ዘርፉ ላይ የተመሠረተው የመዋቅር ሽግግር ስትራቴጂ በጠባብ አድማስ የታጠረ ነው፡፡ ያሉንን ሀብቶች ሁሉ፣ በአንድ እርግጠኛ ባልሆነና ችግሩ በግልጽ በሚታወቅ ቅርጫት ውስጥ ልናስቀምጥ አንችልም፡፡ በአምራች ዘርፉም ውስጥ እንኳን የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በሚጠባበቁ የኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ ሜቴክና የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን በመሳሰሉ ግዙፍ የመንግሥት ተቋማት፣ ብዙ ሀብት የሚፈጅ የአምራች ዘርፍን አሳካለሁ ማለትና አገር በቀል የአምራችና ኢንዱስትሪ አቅምን ዘንግቶ፣ ጀርባ የሚሰጥ አካሄድ ፈሩን የሳተ ነው፡፡

የኢንዱስትሪ ስትራቴጂያችንን ስንቀርፅ፣ የቴክኖሎጂ መሻሻሎች፣ ባህላዊ  የአምራች ዘርፍን እያስተጓጎሉ እንደሚገኙ መገንዘብ ይኖርብናል፡፡ አምራቹ ዘርፍ ይበልጥ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚና ብዙ ሀብት የሚፈጅ እየሆነ የመጣ ሲሆን፣ እሴት የሚጨምር  የሠራተኛ ኃይልና ሚናው እየሟሸሸ ነው፡፡ የዘርፉ ሠራተኞችን የመያዝ አቅም፣ በአነስተኛ ቀላል የአምራች ዘርፎችም ጭምር እየተመናመነ  ነው፡፡ ከ20 ዓመት በፊት በመቶ ሠራተኞች ይተዳደሩ የነበሩ ፋብሪካዎች፣ አሁን በአሥር ወይም ከዚያ ባነሱ ሠራተኞች እየተዳደሩ ይገኛሉ፡፡ በታዳጊም ሆነ ባደጉ አገሮች ዝቅተኛ ክህሎት ያላቸው ሠራተኞች ተፈላጊነት እየቀነሰ ሲሆን፣ ወደፊትም መቀነሱ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ እነዚህን የቴክኖሎጂ መሻሻሎችና የሚያስከትሏቸውን አንድምታዎች  መመልከትና በእነዚህ ተለዋዋጭ እውነታዎች አውድ ውስጥ ተገቢውን  መዋቅራዊ ሽግግር በተመለከተ እንደ አዲስ ማሰብ ያስፈልገናል፡፡ ወደ ኋላ ዞረን  የምንመለከተውና የምንማርበት ታሪክ የለንም፡፡ አዳዲስ እውነታዎችን እየተጋፈጥን ባለንበት ሁኔታ ውስጥ፣ የራሳችንን አዲስ ታሪክ መሥራት አለብን፡፡ ከሞላ ጎደል በሁሉም ታዳጊና ያደጉ አገሮች የታየው ቀደም ያለ የኢንዱስትሪ እንቅስቃሴዎችን የመቀነስ ወይም የማስወገድ (ማኑፋክቸሪንግ/አጠቃላይ አገራዊ ምርት ምጣኔ) የቅርብ ጊዜ ተመክሮ፣ በዓለም ኢኮኖሚ ውስጥ የተከሰተ የአዲሱ እውነታ አካል ነው፡፡ አሁን የአገልግሎት ዘርፉ፣ ከጥቂት (እስያ) አገሮች ኢኮኖሚ በቀር ከሞላ ጎደል በሁሉም አገሮች ኢኮኖሚዎች ውስጥ ትልቁ  ዘርፍ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በአገልግሎት ዘርፍ የሚመራ ኢኮኖሚ አትፈጥርም ተብሎ ተፈርዶባት ከሆነ፣ አሁን የተፈጠሩትን ዕድሎች አሟጦ ለመጠቀም መጣር ይኖርባት ይሆናል? በአምራች ዘርፉ የኢኮኖሚው የግብዓት አለኝታዎች ብዙ ሀብት ለሚፈጅ ኤክስፖርት ተኮር ማኑፋክቸሪንግ ገና ያልተዘጋጁ ቢሆንስ?  የኢትዮጵያ ሰፊ አገራዊ የፍጆታ ገበያ ለአምራች ዘርፍ ይበልጥ ተስማሚ ዕድል ይፈጥር ይሆናል? በገበያውና በመንግሥት እንዲሁም በግሉና በመንግሥት ዘርፍ መካከል ያለውን የሚዛናዊነት ዝንፈት  ለማረቅ የማሻሻያ ሥራ ይጠይቃል፡፡ አሁን ያለውን የዕዝ ፋይናንስ ፖሊሲ ለመለወጥ ያለመ የፋይናንስ ዘርፍ ማሻሻያና ገበያ መር አሠራር እንዲሁም ጠንካራና ጤናማ  የፋይናንስ ዘርፍ ግንባታ የግድ ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ የራሷን የኢኮኖሚ ታሪክ መፍጠር ይኖርባታል፡፡ ግድቦች፣ መንገዶችና ድልድዮች ለመገንባት የምትሰጠውን ትኩረት ያህል፣ የኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን መሠረተ ልማት ለመገንባት ትኩረት መስጠት ይገባታል፡፡ ለደሃ ገበሬዎች የምታደርገውን ዕገዛ ያህል፣ የወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ኢንቨስት ማድረግ ይኖርባታል፡፡ በዛሬው ፈጣንና ተለዋዋጭ ዓለም ውስጥ የኢኮኖሚ ስትራቴጂና ፖሊሲ፣ ጥልቅ ግንዛቤና አርቆ አሳቢነትን ይጠይቃል፡፡ በዚህ የጥናት ጽሑፍ ቀደም ብሎ የተቀነቀኑ የፖሊሲ ማሻሻያዎች ጥሩ መነሻ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected]. ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...