Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትየመንግሥት የአጣዳፊ ጊዜ ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣንን እጀ ሰባራ ያደረገው ምንድነው?

የመንግሥት የአጣዳፊ ጊዜ ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣንን እጀ ሰባራ ያደረገው ምንድነው?

ቀን:

በገነት ዓለሙ

ለመላው ዓለም ምሳሌ የሚሆን ሕገ መንግሥትና ፌዴራሊዝም አለን በምትል (እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም ትልም በነበር) ኢትዮጵያ ውስጥ የብሔረሰብ ንቁርያዎች፣ መጤ እያሉ መበደልና መግፋት ሲተካተኩባትና ዋጋ ሲያስከፍሏት፣ በየጊዜውም ሲያስጠነቅቋት ቆይቶ ዓብይን ድንገት የወለደው፣ ዘግናኝ ግድያዎችን የታዩበትና በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ያፈናቀለ ቀውስ ተዘረገፈባት፡፡ ያው ቀውስ የሚያዛልቅ መፍትሔ ገና ባላገኘበት ወቅት የሶማሌ ክልል የአዲሱ የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት አደገኛ ፈተና፣ የሕገ መንግሥቱና የፌዴራሊዝማችን የማያልቅ ጉድ መገለጫ ሆኖ ቀርቧል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የማንኛውም ዓይነት መንግሥት ተግባር የሆነው የተራ፣ የሕግና የሥርዓት ዘልማድና ፀጥታ የማስከበርና የማቆም የማዕከላዊው መንግሥት አቅምና ግዴታ ዓይናችን እያየ ሲሰናከል ታዝበናል፡፡

ዘመናዊ አስተዳደር ፀጥታና ሕግ ማስከበር አልችል ሲል በየአገሩ እናያለን፡፡ እንዲህ ያሉ አገሮችም የቀውስና የዕልቂት ሥፍራዎች ሲሆኑ እናውቃለን፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ በጭካኔያዊ አስተዳደር አማካይነትም ቢሆን ፀጥታን ማግኘት ተመሥገን የሚያሰኝ ሲሆን፣ የጎረቤት አገር ምስክር ሆነን እናውቃለን፡፡ ተኩስና ዘርፎ በልነት በሰፈነባት (በዘጠናዎቹ) ሶማሊያ ውስጥ ‹‹የፍርድ ቤቶች ኅብረት›› እንኳን ተቀባይነት አግኝቶ የነበረ መሆኑ የዚህ ማስረጃ ነው፡፡

ዛሬ ሶማሊያ (ሶማሊያ የምትባለው አገር) ቢያንስ ቢያንስ ከባሰ አደጋ ለመትረፍ ከኢትዮጵያ ሕገ መንግሥታዊና ፌዴራላዊ ልምድ ጭምር ለመቅሰም እየተማረች፣ ልምድ ልውውጥ እየደረገች ነው በሚባልበት ወቅት ውስጥ ኢትዮጵያ በየቦታው በየትኛውም ክልል ውስጥ ጉዳዩ በቀረበበት፣ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ሶማሌ ክልል ውስጥ መንግሥታዊ ሥልጣኑን የሚያውሸለሽልና የሚያመክን እንቅፋትና አደጋ ሲጋረጥባት እያን ነው፡፡

የሶማሌ ክልል በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 47/1 ቋንቋ የፌዴራል መንግሥቱ አባል ነው፡፡ የኢትዮጵያ የግዛት ወሰንም አሁንም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 2 ቋንቋ ‹‹የፌዴራሉን አባሎች ወሰን የሚያጠቃልል›› ነው፡፡ ማንም ምንም ቢልም ሶማሌ የኢትዮጵያ የግዛት አካል ነው፡፡ ክልል አምስት ኢትዮጵያ ነው፡፡ የትም አገር ውስጥ ደግሞ ሌላው ቢቀር ፀጥታ፣ ሕግና ሥርዓት የማስከበር ሥልጣን የመንግሥት ነው፡፡ ኢትዮጵያም ውስጥ ይህ ሥልጣን የኢትዮጵያ መንግሥት ሥልጣን ነው፡፡

ካለፈው ቅዳሜ ማለትም ከሐምሌ 28 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ባለው ሳምንት ውስጥ ክልሉ ዝርዝሩ ተዘርግፎ ሊነገረን ባልቻለ ‹‹ሰብዓዊ ቀውስ›› ውስጥ መሆኑን እየሰማን ነው፡፡ የክልሉ ፖሊስ የፌዴራሉን መከላከያ ‹‹ቀጣው፣ ገረፈው . . . ›› ከሚል ምኞት ጀምሮ፣ ‹‹ሕገ መንግሥታዊ ያልሆነ ወረራ›› ያሉትን የተቃውሞ ሰዎች/ቡድኖች ድምፅ ሰምተናል፡፡ አንዳንዶችም የፌዴራሉ ሠራዊት በክልሉ ውስጥ ጣልቃ እንዳይገባ መቆጠብ አለበት፣ አስፈላጊ ከሆነም እንደ ሱዳን፣ ቱርክ፣ የመሳሰሉ አገሮች ወታደሮች የሰላም አስካበሪ ሆነው ሊጋበዙ ይችላሉ እስከማለት ድረስ ቀድሞ የእነሱ ብቻ ፀጋ በነበረው፣ ዛሬ ደግሞ (ዕድሜ ለእነሱ) ገና ባልለየለት የንግግር ነፃነት ሲበዛ ሲባልጉ ዓይተናል፣ ወዘተ፡፡

ይህ ሁሉ የሚሆነው አገር ምድር ሕዝብ ያለ ብሔረሰብ ልዩነት የተስፋ ብርሃን ያደረገው የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ለውጥ፣ የኦፊሴላዋ ፌዴራላዊት ዴሞክራሲዊት ኢትዮጵያ ይፋዊ መልክ ከመሆኑ በስተቀር፣ ከለውጥ ተጠናዋቾች ጋር ሥውርና  ግልጽ ትግልና ትንቅንቅ በሆነበት ጊዜ ነው፡፡ አሁን የምንገኘው ለውጡ የአደባባይ የአገር አቋም ሆኖ የወጣና ያን ያህልም የበላይነት ቢይዝም፣ ወደፊት ተራምዶ የፊት ለፊቱን በቅደም ተከተልና በዝርዝር ሰድሮ አውጥቶ የሕዝብን ተሳትፎና እንቅስቃሴ ከጀርባው አሠልፎ የአገሪቱ ዕድል ብሩህ በሚሆንበት ጊዜ ብቻ አይደለም፡፡ ለውጡ አደጋም አለበት፡፡ ለውጡን በቀጥታ የሚፃረሩ አሉ፡፡ ለውጡ የ‹‹ድሮ›› መንግሥት ራሱ ወይም ታማኞቹ ከሚያቀናብሯቸው መድረኮች አልፎ ወደ ነፃ የሕዝብ እንቅስቃሴ መሸጋገሩን የሚፈሩ ኢሕአዴጎችም አሉ፡፡ የለውጥ ምልዓቱን መከፋፈልና ማስመታት የሚፈልጉና የሚችሉም ፀረ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች፣ በቀለኞችና ከአፍንጫ ያልራቁ ብሔርተኞች አሉ፡፡

የለውጥ ኃይሎች በዚህ ውስብስብ ትግል ውስጥ ጥያቄዎችና ተወዝፈው ያደሩ የአገር ችግሮች፣ የአመፅ መንገድ ውስጥ ሳይገቡና ወንጀሎች የትግል ሽፋን ሳያገኙ የሚስተናገዱበትን መንገድ ለመዘርጋት ደፋ ቀና ሲሉ በዚህ መሀል እንደ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. እና ሶማሌ ክልል እንደ ገጠመው ያሉ ፈታኝ ችግሮች ድርብ አደጋ ይዘው ይመጣሉ፡፡ አደጋዎቹ ጥንድ ወይም ድርብርብ ፈተና ይዘው እንደመጡ መጀመርያ እንመልከት፡፡ ለምሳሌ የሰኔ 16 ቀን አደጋ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ጉዳት በማድረስ ብቻ የሚወሰን አልነበረም፡፡ ተፈለገም ተጠላም፣ አወቅነውም አላወቅነውም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ጉዳት ደረሰ ማለት፣ በዚያ ሥፍራ የነበረ ሥፍር ቁጥር ሌለው ሕዝብ በደም ፍላት ሰክሮ በአራቱም ማዕዘናት እንደ ቋያ የሚስፋፋ የመጨፋጨፍ ድብልቅልቅ አይከፍትም ነበር ወይ? ብለን የምንጠይቀው፣ አፋችንን ደም ደም እያለን ነው፡፡ ከዴሞክራሲ ጉዟችን ፈንታ በዚህ ሰቅጣጭ መጫፋጨፍ ውስጥ እንጠቀማለን የሚሉ ህሊና ቢሶች የሉም? የተቆጣ ሕዝብ ለማሰብ ጊዜ የለውምና ሮጦ ጥቃት የሚከፍተው በጠላው ላይ ይሆናል በሚል ‹‹ሥሌት›› ቁርሾ ለማወራረድ የፈለጉ ወፈፌዎች አሉ? የእርስ በርስ መጨፋጨፍ ሲፋፋም አገር መቀረጥ/ማስቆረጥ ይቀለናል ያሉ ሕመምተኞስ? ብዙ ደም በጎረፈበት ሰዓት ላይ በነፃ ዕርምጃና በጦር ፍርድ ቤት የሚቀጣ ‹‹ጊዜያዊ›› ወታደራዊ አገዛዝ እናውጃለን፡፡ ያን ጊዜ ሕዝብ ከሰማይ ወረዳችሁልን ብሎና እግር ስሞ፣ ማረኝም ብሎ ይቀበለናል ብለው የሚያደቡ ፈላጭ ቆራጮችና ዘራፊዎችስ የሉም? ይህ የችግሩ አንድ ነጠላ ገጽታ ነው፡፡ ችግሩን ድርብ ድርብርብ የሚደርገው የጉዳዩ ሌላ ገጽታ ችግሩን የምንከላከልበት፣ የምንጋፋበት፣ የምናስተናግድበት፣ የቆየና ይበልጥ እየተበላሸ እየባሰበትም የሄደ አሠራራችን ነው፡፡ እንደ ሶማሌ ክልል ውስጥ የደረሰን ሕገወጥነት ለመግታት የምንወስደው ዕርምጃ፣ የመንግሥትን የራሱን የሕግ አክባሪነትና አስከባሪነት የውኃ ልክ የሚያስገምትና የሚያሳፍር መሆኑ በጭራሽ አላቋረጠም፡፡

በሰኔ 16 ጉዳይ የሚደረገው የምርመራና የ‹‹ጊዜ ቀጠሮ›› ጉዳይ ዛሬም ከሚታወቅበት፣ ከተተበተበበትና ከተዘፈቀበት ችግር መንጥቆ የሚያወጣው የለውጥ ሒደቱ ራሱ ያፈራው ወይም ያደፋፈረው ዳኛ፣ ዓቃቤ ሕግ ወይም ፖሊስ ብቅ ሲል አላየንም፡፡

ሶማሌ ክልል ውስጥ ‹‹ሰብዓዊ ቀውስ›› ሲፈጠር እሱን ለመከላከልም ሆነ ኋላም የተፈጠረውን ቀውስ ለማረጋጋት መንግሥትን እጀ ሰባራ ያደረገው፣ የችግራችን ሌላው ገጽታ የሆነው የመንግሥት የሕግ የማስከበር የቆየ የጠና ገመናችን ነው፡፡ መንግሥት በሚያስተዳድረውና በሚገዛው አገር ሁሉ ደጋግሜ እንደገለጽኩት፣ ሕግና ሥርዓት ዘልማድና ፀጥታ የማስከበር ተራና መሠረታዊ ግዴታ ያለበት መሆኑ የማንኛውም መንግሥት ባህርይ ነው፡፡ ፅድቁ/ዴሞክራሲው ቀርቶ በቅጡ በኮነነኝ/በገዛኝ የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡ ኢትዮጵያም ውስጥ እንደ ሌላው አገርና መንግሥት ብቸኛው የታጠቀ ኃይል የመሆንና የአገር ሰላምና ደኅንነት የዘብ ጥበቃ ሥራ የመንግሥት ግዴታ ነው፡፡

በዚህ ረገድ አሁን ዛሬ ተመላልሶ የሚቀርበው ጥያቄ መንግሥት ሶማሌ ክልል ውስጥ ‹‹ጣልቃ ለመግባት›› ጊዜ የፈጀበት ለምንድነው? የሚለው ነው፡፡ ጥያቄውን በዚህ መልክ ያዋቀርኩት የሶማሌ ክልልን ችግር የፈጠረው ፖለቲካዊ ጉዳይ ዘንግቼ ወይም አቃልዬ አይደለም፡፡ ሰው በአገሩ፣ በመንግሥት አገር ሕግ የማስከበር ዕርምጃ እንዴት እንዲህ ቀርፋፋ ይሆናል? እንዴትስ ይህን ያህል ሰው እስኪያልቅና እስኪፈናቀል ድረስ ቀርፋፋ ይሆናል? የሚለው ጥያቄ ብቻ አይደለም አገሩን የሞላው፡፡ አገሩን ሁሉ ባይሞላውም አገሩን የሚያሳስበው ሌላም ጥያቄ አለ፡፡ በፌዴራል አገር ውስጥ፣ በኢትዮጵያ የግዛት ወሰን ውስጥ፣ የፌዴራል መንግሥቱ የመንግሥት ሥልጣን ‹‹በፈቃድ›› የሚመራ አስቀድሞ የክልሉን ፈቃድ ማግኘት ያለበት ሆኖ መነገሩ መብራራት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡

ጉዳዩን ማብራራት ይቻል እንደሆነ ለማየት መጀመርያ ‹‹ጣልቃ መግባት›› ስለሚባለው ነገር ትንሽ መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ ጣልቃ መግባት ማለትን ያመጣው አገር ከአሀዳዊ ወደ ፌዴራላዊ አስተዳደር በመሸጋገሯ መሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ፌዴራል በመሆኗ ወይም ሆነች በመባሉ የአገር ሉዓላዊነት በዚህ ምክንያት ብቻ ተከፋፈለ ማለት አለመሆኑ ግን ይታወቃል ብዬ እገምታሁ፡፡ ባለፉት 27 ዓመታት ብዙ ብዙ ነገር ቢባልም፣ ሉዓላዊነት የክልሎች የብሔር ብሔረሰቦች እየተባለ ቢደጋገሙም፣ ሕገ መንግሥቱ ቃሉን በሚያነሳበት ድንጋጌዎች ሁሉ ግን እንዲህ ያለ ነገር የለም (የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 8፣ 86፣ 87 እና 93 ይመለከታል)፡፡

በሰፊው በታወቀውና በተዘወተረው እሳቤ መሠረት ሉዓላዊነት ማለት የተወሰነና የታወቀ ሕዝብና መልክዓ ምድር ይዞ፣ የቆመ አገረ መንግሥት ሌላ አዛዥና አስገዳጅ ኃይል ሳይኖርበት በአገር ውስጥ አስተዳደሩም ሆነ በውጭ ግንኙነቱ ረገድ የመወሰን ሙሉ ብቃት ነው፡፡ ኢትዮጵያ አሃዳዊ መሆኗን ትታ፣ ፌዴራላዊ በመሆኗ ምክንያት ብቻ የዚህ ትርጉም አይነቃነቅም፡፡ ፌዴራል መንግሥት ማለት የመንግሥት ሥልጣን በማዕከላዊው መንግሥትና በዘጠኝ የክልል መንግሥታት መካከል የተከፋፈለበት ማለት ነው፡፡ እንዳንዱ ክልል በየክልሉ ዳር ድንበር ውስጥ የተወሰነ የመንግሥት ሥልጣን አለው፡፡

የየክልሉ የመንግሥት ሥልጣን ክልል በተባለው የአገር ክፍል ውስጥ ወይም በዚያ ክፍለ አገር ውስጥ የተወሰነ ነው ማለት፣ አንድ ክልል በሌላው ክልል ውስጥ ሥልጣን የለውም ማለት ጭምር ነው፡፡ የፌዴራል መንግሥቱ ሥልጣን ደግሞ በመላው የአገሪቱ ምድር ላይ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት በአንድ ክልል ውስጥ የክልልም የማዕከላዊ መንግሥትም ሥልጣን አለ፡፡ የክልል የመከላከያ፣ የክልል የገንዘብ፣ የክልል የጉምሩክ፣ ወዘተ ሥልጣን የማዕከላዊው መንግሥት ሥልጣን ነው፡፡ ማዕከላዊው መንግሥት እነዚህን ሥራዎች የሚሠራው ክልል ውስጥም ጭምር ስለሆነ ‹‹ጣልቃ መግባት›› የሚባለው ቃል አደናጋሪነት፣ አለዚያም አግባብነት ከዚህ አኳያ ሊገረዝ ይገባዋል፡፡ የማዕከላዊው መንግሥት የክልል ውስጥ ሥልጣንም ለማዕከላዊው መንግሥት በተከለለ፣ ለክልል ግን በተከለከለ ሥልጣን ላይ ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ በዚያው በተመሳሳይ የክልል የቆዳ ስፋት ውስጥ ጣምራ የዳኝነት፣ የሕግ ማስከበርና  የፖሊስ ሥራ ተግባራት አሉ፡፡

ከዚህም በላይ ደግሞ በተለይም የአገር ሉዓላዊነት (የጠቀስናቸው የሕገ መንግሥቱ አንቀጾች በአብዛኛው ሉዓላዊነትን ከአገር ህልውና ጋር ያስተባብሯቸዋል) የመንግሥትን የድንገተኛ ጊዜ፣ የአደጋ ጊዜ፣ የቀውጢ ጊዜ ሥልጣን የግድ ያደርጋል፡፡ የመንግሥት የድንገተኛና የአደጋ ጊዜ ሥልጣን የሚባለው ደግሞ በሕገ መንግሥት ውስጥ በቅጡም ባይሆን ተበታትነው የተደነገጉት ጦርነት የማወጅ፣ አስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ የመደንገግ የመሳሰሉት ናቸው፡፡ ከዚህ ጋር የሚያያዙ የጦርነት ጉዳይ፣ የአገርና የሕዝብ መከላከያ፣ የደኅንነትና የፖሊስ ኃይል አደረጃጀት (ሕገ መንግሥት አንቀጽ 52/7) በጠቅላላው የማዕከላዊው መንግሥት የሥልጣን ክልል ነው፡፡

እውነቱን ለመናገር ወግ ወጉ ባይቀርበትም ያን ያህል ‹‹ለዓለም ምሳሌ የሚሆን››፣ ‹‹እንከን የለሽ›› የሚባለውና ሚሊዮኖች ተሳትፈውበታል እየተባለ የሚነገርለት ሕገ መንግሥት ግን እንዲህ ላለ የክፉ ጊዜ የድንገተኛ ጊዜ ጉዳይ (Emergency Power) የሚገባውን ትኩረት የሰጠ በጭራሽ አይደለም፡፡ ከሚያስፈራሩና ከማያሳፍሩ ችግሮቻችን መካከል አንዱ ይኼው ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ሕገ መንግሥቱ ከወጣ ከዘጠኝ ዓመት በኋላ የወጣው ‹‹ፌዴራል መንግሥት በክልል ጣልቃ የሚገባበት ሥርዓት›› አዋጅ (ቁጥር 359/95) ሳይቀር ለራሱ ለወቅቱ ገዥ አስተዳዳር እንኳን ‹‹የሚመች›› አልነበረም፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የ23 ዓመታት ዘመነ መንግሥት ውስጥ ገዥው ፓርቲ ‹‹የተጠቀመው›› እንደፈለገ አድርጎ የሚያወጣው ሕጉ ሳይሆን፣ እንደፈለገ አድርጎ የሚተረጉመው ሕጉ ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ ማዕከላዊው መንግሥት ‹‹በክልል ጣልቃ የሚገባበት›› ሁኔታ በአዋጁ እንደተደነገገው ሲበዛ በጣም ቀፍዳጅ ነው፡፡

በሕገ መንግሥት ውስጥ ተጻፈም አልተጻፈም፣ የተጻፈ ሕገ መንግሥት ኖረም አልኖረም እነዚህ ‹‹አገር ሲወረር መልካው ሲናጋ›› ተገቢውን ዕርምጃ የመውሰድ (ጦርነት የማወጅ የአገር ህልውናን የመከላከል) ሥልጣን የመንግሥትነት ተፈጥሯዊ ባህርያዊ ማለትም (Inherent) ሥልጣን ነው፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ደግሞ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በተለያዩ ድንጋጌዎች ተበታትኖ እንደተገለጸው የማዕከላዊ መንግሥትን ለክልሎች የሚያቋቁም ግዴታ አለ፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱ የኢትዮጵያን ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊካዊነትን በዋስትና ማረጋገጥ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ይህንን አፍ አውጥቶ እንዲህ ብሎ በእርግጥ አይናገረውም፡፡ ብዙዎቹ ድንጋጌዎች ግን ይህንን አስረግጠው ይደነግጋሉ፡፡

እነዚህን የሚወስኑትን ድንጋጌዎች እንመልከት፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 50(5) የክልል ምክር ቤት በክልሉ ሥልጣን ሥር በሆኑ ጉዳዮች የክልሉ የሕግ አውጪ አካል መሆኑን ይገልጽና፣ ‹‹ይህንን ሕገ መንግሥት መሠረት በማድረግ የክልሉን ሕገ መንግሥት ያዘጋጃል፣ የፀድቃል፣ ያሻሽላል›› ይላል፡፡ የፌዴራል መንግሥቱን ሥልጣን የሚወስነው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 51(1) ሕገ መንግሥቱን ይጠብቃል፣ ይከላከላል ይላል፡፡ የክልል ሥልጣን የሚደነግገው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 52(2) ክልሉ ራሱን በራሱ ማስተዳደርን ዓላማ ያደረገ ክልላዊ መስተዳድር ያዋቅራል፡፡ የሕግ በላይነት የሰፈነበት ዴሞክራሲዊ ሥርዓት ይገነባል፣ ይህን ሕገ መንግሥት ይጠብቃል፣ ይከላከላል በማለት ይደነግጋል፡፡ የፌዴራል ሕገ መንግሥት በአንቀጽ አንድ ይህ ሕገ መንግሥት ፌዴራላዊና ዴሞክራሲያዊ የመንግሥት አወቃቀር ይደነግጋል፣ በዚህ መሠረት የኢትዮጵያ መንግሥት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ በሚል ስም ይጠራል በማለት ብቻ አይወሰንም፡፡ በአንቀጽ 93(4)(ሐ) ደግሞ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ አዋጅ ሥር የሚያወጣቸው ድንጋጌዎችና የሚወስዷቸው ዕርምጃዎች ከሌሎች መካከል በሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ አንድ ‹‹… የተቀመጡትን መብቶች የሚገድቡ ሊሆኑ አይችሉም፤›› ይላል፡፡ የተጠቀሰው አንቀጽ አንድ ‹‹መብት›› ባይሆንም የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲዊ ሪፐብሊካዊነት የሚያናጋ ተግባር ክልልም፣ ማዕከላዊ መንግሥትም አይወስድም፡፡ የከፋ አስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ እንኳን ይህንን እንዲያናጋ አይፈቀድለትም፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የዚህ ሁሉ ጠባቂ ማዕከላዊ (ፌዴራላዊ) መንግሥት ነው ማለት ነው፡፡

ሌላው የማዕከላዊው መንግሥት ለክልሎች ያለው ግዴታ ክልሎችን ከወረራና ከውስጣዊ አመፅ መከላከል ነው፡፡ አገር መከላከልና ደኅንነት የፌዴራል ሥልጣን መሆኑን የማዕከላዊው መንግሥት የዚህ ግዴታው ማረጋገጫ ነው፡፡

እነዚህ የተጠቀሱት የመንግሥት የክፉ ቀን ጊዜ ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣኖች በሕገ መንግሥቱ ውስጥ በወጉና በዕውቀት ላይ የተመሠረቱ የምር ቦታ ባለማግኘታቸው፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ በዝርዝር ሕጉ ውስጥ ‹‹የተፍታቱበት›› ሁኔታ ስላጎሳቆላቸው፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የክፉ ጊዜ ሥልጣን ከተለመደና የቆየ ጣጣው ሳይወጣ ቀርቷል፡፡ የቆየውና የአገር ሰላም ሕመም ሆኖ ፀንቶ የኖረው ችግራችን የክፉና የአስቸኳይ ጊዜ የመንግሥት ሥልጣን የአገር ደኅንነትን ከሕዝብ ነፃነት ጋር ማግባባት ባለመቻሉ ነበር፡፡

የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥትና የሌላው ዝርዝር ሕግ እስካሁኑ ችግር ደግሞ መንግሥት በጠቅላላው ‹‹ሥራው በማይከለከል፣ የፈቀደው ሁሉ የሚሆን›› መሆኑ ነው፡፡ ያው ሕገ መንግሥት ራሱ ተፈጻሚ በሚሆንበት በዓብይ አህመድ አዲሱ የሥልጣን ዘመን ውስጥ የተፈጠረው ችግር ደግሞ ከዚህ ለየት ያለ ነው፡፡ ዓብይን እጀ ሰባራ ያደረገው፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሕገ መንግሥትዊ የአጣዳፊ/የክፉ ጊዜ ሥልጣን እጅና እግር የቀፈደደው ሕግና ፖለቲካ ተጋግዘውና ተባብረው ነው፡፡ ሕጉ የተመለከትነው ዓይነት ጉድለትና ጣጣ አለበት፡፡ ዝርዝር ሕግ የተባለውም የክልሉን ፈቃድ ጠይቁ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ስብሰባ ጥሩ፣ ወዘተ የሚል ነው፡፡ ከዚህ በላይ ደግሞ ዓብይ የሚኖርበት ፖለቲካ እንደ ሕጉ ማድረግን እንኳን የሚያግዝ አይደለም፡፡

ለምሳሌ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወረሰው በዚህ ውሽልሽልና ቡትቶ ሕግ ውስጥ ሆኖ፣ በሶማሌ/ክልል አምስት ላይ ካቢኔውን ይዞ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊያውጅ፣ እስከ 15 ቀን ባሉ ጊዜያትም ፓርላማውን ጠርቶ ሊያፀድቅ በቻለ ነበር፡፡ ትናንት የመጀመርያው የ2009 ዓ.ም. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ራሱ ለምን ተነሳ? ለምንስ አልተራዘመም? ብለው የተቆጡት፣ የ2010 ዓ.ም. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመነሳቱም ፓርላማ ውስጥ ሳይቀር (በድምፅ) ተቃውሟቸውን ያለብልኃት የገለጹት ኢሕአዴግ ውስጥ ያሉ የዓብይ ተቃዋሚዎች ግን፣ ዓብይ አስቸኳይ አዋጅ ለዚውያም ሶማሌ ክልል ላይ ብቻ ላውጅ ቢል ‹‹አያስተርፉትም›› ገና ከአሁኑ ወረራ፣ ዝባዝንኬ እያሉት ነው፡፡

የመከላከያ ሠራዊት ከስንት ቀናት በኋላ ገባ የተባለበት ሁኔታ ድብስብስ የሆነው፣ የለውጡ ተቃዋሚዎችም ሶማሌ ክልልን (Occupied Territory) እስከ ማለት ድረስ የሄዱት በዚህ ሁሉ ምክንያት ነው፡፡

እውነቱን ለመናገር ወይም እንደሚመስለኝ ዓብይ ራሱ ይህንን አግዞታል፣ ተባብሮታል፡፡ በዚህ ረገድ በግልጽ የሚታው የጠቅላይ ሚኒትራችን ችግር ከሚዲያ መራቁ ነው፡፡ ዛሬ ድረስ አምስተኛ ወሩ መጀመርያ ላይ ሆኖ ሚዲያ ጠይቆት አያውቅም፡፡ ከአሜሪካ መልስ ወዲህ በተለይም በክልሉ ጉዳይ ላይ ድምፁን አልሰማንም፡፡ ‹‹ሙያ በልብ ነው›› ያለ ይመስላል፡፡ ይህ ደግሞ ለለውጡም፣ ለእኛም ክፉ ነው፡፡ ‹የድበቅ ፖለቲካ ከእንግዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ አይሠራም፣ በመደበቅና እኛ ሸርበን እኛ አብስለን ኬክ ምናቀርብበት የዴሞክራሲ ሥርዓት የለም› ያለው እኮ እሱ ራሱ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...

አሳርና ተስፋ!

ከቱሉ ዲምቱ ወደ ቦሌ ጉዞ ልንጀምር ነው፡፡ ገና ከመንጋቱ...